የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ኢሳትን እያዳመጠች ልጃቸው ኒዮሊበራሎችን እየተከተለች የቤታቸው ንትርክ ጦፏል::

[ክቡር ሚኒስትሩ እሑድ ቀን ከቤታቸው ሊወጡ ሲሉ ልጃቸው አገኘቻቸው]
Source – Reporter Amharic
– ወዴት እየሄድክ ነው ዳዲ?
– ዘመድ ልጠይቅ፡፡
– ምን ዓይነት ልብስ ነው የለበስከው?
– ያው ዊኬንድ ስለሆነ ቱታ ነዋ ያደረኩት፡፡
– እኔ የጠየቅኩህ ቀለሙን ነው?
– ቀለሙማ እንደምታይው አረንጓዴ ነው፡፡
– እሱ ነዋ ችግሩ፡፡
– ይኼ ቀለምማ ችግር የለውም፡፡
– በጣም አለው እንጂ፡፡
– አረንጓዴ ለምን እንደምለብስ ታውቂያለሽ?
– ለምንድን ነው የምትለብሰው?
– አገሪቷ እየለመለመችና እያደገች ስለሆነ እሱን ላመላክት ነዋ፡፡
– እየለመለመች?
– አዎና፡፡
– ድርቅ ገብቷል እየተባለ ሲወራ አልነበር እንዴ?
– እ…
– ለማንኛውም ዛሬ የሚለበሰው አረንጓዴ ሳይሆን ቀይ ነው፡፡
– ለምን ተብሎ?
– ቫላንታይንስ ዴይ ነዋ፡፡
– ምንድን ነው ደግሞ እሱ?
– የፍቅረኛሞች ቀን፡፡
– መንግሥት የሚያከብረው ቀን ነው?
– ኧረ በመላ ዓለም የሚከበር ነው፡፡
– የኒዮሊብራሎች በዓል ነው አትይኝም ታዲያ?
– እኔ እሱን አላውቅም፡፡
– ለመሆኑ ቀኑ ምንድን ነው?
– ፍቅረኛሞች ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ቀን ነው፡፡
– ምን ማለት ነው?
– በቃ አንዳቸው ለአንዳቸው ፍቅራቸውን በዚህ ቀን ይገልጻሉዋ፡፡
– በሌሎቹ ቀኖች ጥላቻቸውን ነው የሚገልጹት ማለት ነው?
– እንደ እሱ ማለቴ አይደለም ዳዲ፡፡
– ለነገሩ ተይው በዚህ በተወደደ ፍቅር በዓመት አንዴ እንኳን ሰው መዋደዱ ቀላል አይደለም፡፡
– ለማንኛውም ዳዲ ዛሬ አንተም ማሚን እራት መጋበዝ አለብህ፡፡
– ቤት ምግብ የለም እንዴ?
– ነገርኩህ እኮ ዛሬ የፍቅረኛሞች ቀን ነው አልኩህ፡፡
– ለእኔና ለእናትሽ ሁሉም ቀን የፍቅረኛሞች ቀን ነው፡፡
– ለማንኛውም እኔ የቤቱን ዕቃ ቀለም ልቀይረው ነው፡፡
– የቱን ዕቃ?
– መጋረጃውን፣ ሶፋውን፣ ብቻ ሁሉንም ነገር፡፡
– ምን ዓይነት ቀለም ልታደርጊው?
– ቀይ ነዋ፡፡
– እንግዲህ እንደፈለግሽ፡፡
– እኮ ዳዲ አንተም ቱታህን ቀይረዋ፡፡
– ምን ላድርግ?
– ቀይ ቱታ፡፡
– ለነገሩ ከቀይ ቀለም ጋር ችግር የለብኝም፡፡
– ስለዚህ ትቀይረዋለህ?
– አንቺን ካስደሰተሽ እቀይረዋለሁ፡፡
– ታንኪው ዳዲ፡፡
– የማልቀይረው ሌላ ዓይነት ቀለም ቢሆን ነበር፡፡
– ምን ዓይነት ቀለም?
– ሰማያዊ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ሆነው ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ነው]
– ለምንድን ነው አንተ ዜና ላይ የማትቀርበው?
– ምን ሠራሁ ብዬ?
– ምንም እየሠራህ አይደለም እንዴ?
– የዕለት ተዕለት ሥራዬን ነዋ እየሠራሁ ያለሁት፡፡
– እኮ እሱም ቢሆን ለምን በዜና አይቀርብም?
– ዜና እኮ አዲስ ነገር መሆን አለበት፡፡
– ከመቼ ጀምሮ?
– ሁሌም ቢሆን እንደዚህ ነው፡፡
– ዛሬ ስከታተል አልነበር እንዴ ዜና?
– እና ምን አየሽ?
– ይኸው የአንተ ጓደኛ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ጐበኙ ተብሎ አይደል እንዴ ዜና የተሠራላቸው?
– እ…
– ለዛውም መክፈቻ ዜና ነው፡፡
– ምን ችግር አለው ታዲያ?
– ጣቢያው እኮ የሕዝብ ነው፡፡
– ማን አይደለም አለ?
– አትመጻደቁ እባካችሁ?
– እንዴት ማለት?
– ጣቢያው ከዚህ በፊት የደርግ ፕሮፓጋንዳ መንፊያ ነበር ትላላችሁ፡፡
– እና አልነበረም?
– አሁንስ ምንድን ነው?
– የሕዝብ ድምፅ የሚሰማበት ጣቢያ ነዋ፡፡
– ኧረ ሰው እንዳይሰማህ?
– ቢሰማስ ምን ያመጣል?
– ይኼ ነገራችሁ እኮ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው፡፡
– እንዴት?
– ሰው እንደማትሰሙ አውቆ በግድ እንድትሰሙ ያደርጋችኋላ፡፡
– ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
– ያልኩት በደንብ ስለገባህ ማብራራት አያስፈልገኝም፡፡
– ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ገጥመሻል ማለት ነው?
– በእናትህ እነዚህን ልማታዊ ቃላት ከመደርደር የሕዝቡን ድምፅ በሚገባ ብታዳምጡ መልካም ይመስለኛል፡፡
– የሕዝቡን ድምፅ አታዳምጡም እያልሽኝ ነው?
– ብታዳምጡማ ይኼ ሁሉ ባልተፈጠረ፡፡
– የተቃዋሚዎቹን ጣቢያ ማዳመጥ ጀመርሽ እንዴ?
– ሰውዬ እውነቱን ለምን ትሸሻለህ?
– ለመሆኑ እውነቱ ምንድን ነው?
– አሁን ጥሩ ጥያቄ አነሳህ፡፡
– እኮ ንገሪኛ?
– ሕዝቡን ካዳመጥክ እውነቱን ታገኛለህ፡፡
– ሕዝቡንማ እያዳመጥነው ነው፡፡
– እያላመጥነው ነው ያልከኝ?
– የለም የለም፤ እያዳመጥነው ነው፡፡
– ብታዳምጡትማ ይኼ ሁሉ ባልመጣ፡፡
– ይኼ ሁላ ምን?
– ብጥብጥ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን ወሬ አለ?
– ወሬ መቼ ይጠፋል ክቡር ሚኒስትር?
– ለነገሩ የሚሠራ ሰው ነው ያጣነው፡፡
– የሚሠራም አይጠፋም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለማንኛውም ወሬውን ንገረኝ እስቲ?
– ነጋዴዎች ደስተኞች አይደሉም፡፡
– ደግሞ ለምን?
– በዚህ በኤልሲ ጉዳይ ነዋ፡፡
– ይኸው አንበሸበሽናቸው አይደል እንዴ?
– አይ ብሔራዊ ባንክ አዲስ መመርያ አውጥቷል እኮ፡፡
– የምን መመርያ?
– በአንድ ጊዜ በተለያዩ ባንኮች ኤልሲ መክፈት አይቻልም የሚል መመርያ ወጥቷል፡፡
– ለምን?
– ፍትሐዊ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ክፍፍል እንዲኖር ነዋ፡፡
– ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሳይኖር ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል?
– ጥሩ ነጥብ ነው ያነሱት፡፡
– እና አሁን ባንዴ ከአንድ ባንክ የምንጠይቀውን የውጭ ምንዛሪ ይሰጡናል?
– ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ይጠይቃሉ እንዴ?
– ማለቴ ነጋዴዎች የሚጠይቁትን ይሰጧቸዋል?
– እሱን የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡
– ለመሆኑ እኛን ለማጥፋት ነው እንዴ ቆርጠው የተነሱት?
– እኛን ሲሉ አልገባኝም፡፡
– ማለቴ ነጋዴዎችን ሊያጠፉ ማለቴ ነው፡፡
– እንደዛ እንኳን አይመስለኝም፡፡
– አለቀልን በለኛ፡፡
– እርስዎ ነጋዴ ሆነዋል እንዴ?
– ማለቴ አለቀላቸው ልልህ ፈልጌ ነው፡፡
– አይ ራስዎትን እያስገቡ ሲያወሩ ግራ ገብቶኝ ነው፡፡
– ያው ነጋዴዎች እኮ የእኛው አካል ናቸው ብዬ ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ነጋዴ ጋ ደወሉ]
– ከየት ተገኙ ክቡር ሚኒስትር?
– ምንድን ነው የምሰማው እባክህ?
– ምን ሰምተው ነው?
– የኤልሲውን ጉዳይ፡፡
– ቆየ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ታዲያ ምንድን ነው የምናደርገው?
– መላ መቼ ይጠፋል ብለው ነው?
– ምንድን ነው መላው?
– በቃ 17 ኩባንያዎች መሥርቶ በየባንኩ ወረፋ ማስያዝ ነዋ፡፡
– የምን ወረፋ?
– የዶላር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወዲያው ሚስታቸው ጋ ደወሉ]
– እስቲ የምታምኛቸው ስንት ዘመዶች አሉሽ?
– ምን እያልከኝ ነው?
– የጠየኩሽን ለምን አትመልሺም?
– ምን ሊያደርጉልህ?
– በስማቸው ድርጅት ለመክፈት፡፡
– ሁለት እህቶች አሉኝ፡፡
– ሌላስ?
– አገር ቤት ደግሞ ሁለት የአክስቶቼ ልጆች አሉ፡፡
– በቃ በአስቸኳይ ይምጡ፡፡
– ለምን?
– በስማቸው ድርጅት እንከፍታለን፡፡
– ያለን ድርጅት አይበቃንም?
– እነዚህኞቹን ድርጅቶች ለሠልፍ ነው የምንፈልጋቸው?
– ለሠልፍ?
– አዎን፡፡
– ተጣላህ እንዴ ሰውዬ?
– የምን ጥል ነው?
– ሰላማዊ ሠልፍ ተከልክሏል ብዬ ነዋ፡፡
– አልገባሽም እባክሽ፡፡
– ለነገሩ ሰላማዊ ያልሆነው ሠልፍ የበዛው ሰላማዊው ስለከተለከለ ይመስለኛል፡፡
– እስቲ ፖለቲካውን ትተሽ በአስቸኳይ በዘመዶችሽ ስም አራቱ ድርጅቶች ይከፈቱ፡፡
– ምን ያደርጉልናል?
– ወረፋ ይይዛሉ፡፡
– የምን ወረፋ?
– የዶላር ወረፋ!
[አንድ ዳያስፖራ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]
– ክቡር ሚኒስትር አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
– የምን ሐሳብ?
– አንድ ተቋም የመክፈት፡፡
– የምን ተቋም?
– የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፡፡
– በአገሪቷ ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ችግር የለም፡፡
– ክቡር ሚኒስትር የእርስዎን ድፍረት እኮ አንበሳ ራሱ የሚቀናበት ይመስለኛል፡፡
– ምን እያልከኝ ነው?
– አገሪቱ በሰብዓዊ መብት ችግር የተንበሸበሸች አይደለች እንዴ?
– ምን ይላል ይኼ?
– ብቻ ይተውት፡፡
– ለማንኛውም ችግሩ ቢኖርም በውጭ ገንዘብ እዚህ ላይ መሥራት አይቻልም፡፡
– እኔ እኮ የምልዎት ሌላ ነገር ነው፡፡
– በቃ ጨርሻለሁ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር…
– ጢጢጢ…
[ዳያስፖራው መልሶ ደወለ]
– ክቡር ሚኒስትር…
– አንተ ሰውዬ ለምን አተወኝም?
– እኔ የምልዎት ሌላ ነው፡፡
– ምንድን ነው የምትለኝ?
– ማቋቋም የምፈልገው ተቋም ለውሾች የሰብዓዊ መብት የሚሟገት ነው፡፡
– ለውሾች?
– አዎን ለውሾች፤ ውሾች አሉን አይደል እንዴ?
– ያውም ብዙ ውሾች ነዋ፡፡
– ተቋሙ መጠለያ ለሌላቸው ውሾች፣ ጐዳና ለወጡ ውሾች፣ አሳዳጊ ለሌላቸው ውሾች መብት የሚሟገት ነው፡፡
– ሥራ ፈተሃል ልበል?
– ትልቅ ሥራ ይዤ ነው እንጂ የመጣሁት፡፡
– እንዴት?
– ክቡር ሚኒስትር ይኼ ጠቀም ያለ ዶላር የምናገኝበት ሥራ ነው፡፡
– ዶላር?
– አዎና ክቡር ሚኒስትር፣ ጠቀም ያለ ፈንድ እናገኝበታለን፡፡
– በቃ የተቋሙ የበላይ ጠባቂ እሆናለዋ፡፡
– ለዛ አይደል እንዴ አደዋወሌ?
– ወይ ኒዮሊብራሎች እኛ ለሰው ዶላር አጥተናል እነሱ ለውሻ ይሰጣሉ?
– ዶላር በሽበሽ ነው አልኩዎት እኮ፡፡
– ዶላር ካለውማ እንኳን የውሻ መብት ተሟጋች የሌላም መክፈት ትችላለህ፡፡
– የሌላ የምን?
– የዝንብ!