አንዳንድ ፣ አሸባሪ ፣ ልማት እና ወዘተ፣ የቃላት ትርጉም ( ሄኖክ የሺጥላ )
አንዳንድ ፣ አሸባሪ ፣ ልማት እና ወዘተ፣ የቃላት ትርጉም ( ሄኖክ የሺጥላ )
አንድ ወዳጄ <አንዳንድ> የሚለው ቃል ትርጉም ምን ማለት እንደሆነ ልታስረዳኝ ትችላለህ ወይ ብሎ የቃላት እውቀቴን ተፈታተነው ። በመጀመሪያ በፈረንጅኛው a small amount or number of people or things የሚለው ሊሆን ይችል ይሆን አልኩ ? ሲገባኝ ግን <አንዳንድ> በ ( contextual meaning ) አገባብ ትርጉሙ ላይ መሰረት ያደረገ የቃላት ትርጉም ከሆነ ደሞ ሊለይ እንደሚችል ስለማውቅ ፣ አንዳድን ማለት አንዳንድ ጊዜ ብዙ ማለት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደሞ ጥቂት ማለት ነው አልኩት ሳስረዳውም የሚከተለውን ምሳሌ ጠቀስኩ ።
አንዳንድ የሚለውን ቃል የሰማኸው በ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራዲዮ ከሆነ ፣ አንዳንድ ማለት እጅግ በጣም ብዙ ፣ ሊቆጠር የማይችል ፣ ህልቆ-መሳፍርት ፣ የትየ-ለሌ ፣ ወይም ( negative infinitive ) ወይም እንጦሮጦስ ማለት ሊሆን ይችላል ። ይህንን አንዳንድ የሰማኸው ሌላ ሀገር ከሆነ ትርጉም ( insignificant ) ( ይህን-ታህል ) ወይም ጥቂት ወይም ከቁጥር የማይገባ ማለት ነው ። ስለዚህ የቃላት ትርጉም ከቃሉ ምንነት ተነስተን ብቻ ትርጉም የምንሰጠው ነገር እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል ።
ለምሳሌ አሸባሪ ( terrorist ) የሚለውን ቃል ኢትዮጵያ ውስጥ ከሆነ የሰማኸ ፣ ትርጉሙ ጋዜጠኛ ፣ ጠሐፊ ፣ የመንግስትን አሰራር ተጠያፊ ። ሀይማኖተኛ እና ህገ መንግስቱን አክብሮ የሚኖር ሕዝብ ፣ ህገ መንግስቱን ረግጦ በሚኖር መንግስት የሚወጣለት ስም ማለት ሲሆን በሌሎች ሀገሮች ግን አሸባሪ ማለት ከጥሬ ትርጉሙ ሌላ የአገባብ ትርጉም የለውም ።
ለምሳሌ ልማት የሚለውን ቃል ብንወስድ ። ይህ ቃል በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ተነግሮለት ግን ያን ያህል አድማጭ ያላገኘ ቃል ነው ። ምክንያቱ ደሞ < ልማት > የሚለው ቃል በሀገራችን ኢትዮጵያ ሲተረጎም የሚከተለውን ቀለም ስለሚይዝ ነው
ልማት ማለት ፣ ህወሓት ሲሰርቅ ሌላው ቆሞ የሚያይበት የኑሮ መስመር ነው ።
ልማት ማለት ፣ ያንድ ጎሳ አባላት ሀገሪቷን ሲመዘበሩ ሌሎች ዝም ይሉ ዘንድ የተነገራቸው ማግባቢያ ቃል ነው ።
ስለዚህ አንድ ኢትዮጵያዊ ልማት ላይ ነን እንስራበት ካለህ ፣ በ 11 ፐርሰንት አድጌ ፣ ምንም የምበላው የሌለበት ሀገር ሕዝብ አባል ነኝ ማለቱ ነው ። ታስጨርሰኛለህ እኔ ፖለቲካ አልፈልግም ማለቱ ነው ። ልማት ላይ ነን ማለት አጭር ትርጉሙ ፣ ፍርሃት ላይ ነን ፣ ዝምታ ላይ ነን ማለት ነው ። ስለዚህ ወዳጄ ቃል እንደ አገባቡ ነው የሚፈታው ።