የአዲስ አበባ መስተዳደር ‹‹ህዳር 18/2008 አልፏል›› በሚል የሰማያዊ ፓርቲን ደብዳቤ እንዳልተቀበለው ታወቀ

የአዲስ አበባ መስተዳደር ‹‹ህዳር 18/2008 አልፏል›› በሚል የሰማያዊ ፓርቲን ደብዳቤ እንዳልተቀበለው ታወቀ

ሰማያዊ ፓርቲ ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ በመብራት ኃይል አዳራሽ ህዳር 18/2008 ዓ.ም ስብሰባ እንደሚያደርግ ለአዲስ አበባ መስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የላከው ደብዳቤ ‹‹ቀኑ አልፎበታል›› በሚል እንዲቀመጥ መደረጉን ዛሬ ህዳር 6/2008 ዓ.ም ሁኔታውን ለመከታተል ወደ መስተዳደሩ የሄዱት የፓርቲው አባላት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የዕውቅና ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ፅ/ቤት 5 ጊዜ አቅርቦ የሚቀበለው በማጣቱ ህዳር 1/2008 ዓ.ም በሪኮመንዴ መላኩ ይታወቃል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ደብዳቤውን ለአስተዳደሩ በሪኮመንዴ ከላከ በኋላ ‹‹ደብዳቤዎችን አይተን የምንወስነው የህግ አማካሪዎች ካዩት በኋላ ነው›› በተባለው መሰረት የህግ አማካሪ የተባሉት ሰው አይተው ለአስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊው ቢሰጧቸውም ኃላፊው ‹‹ስብሰባ ለማድረግ የተጠቀሰው ቀን (ህዳር 18/2008 ዓ.ም) ስላለፈ ይቀመጥ›› ብለው መወሰናቸውን ሰራተኞቹ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አስተዳደር ፅ/ቤት ለሄዱት የሰማያዊ አባላት ገልፀውላቸዋል፡፡ አባላቱ ‹‹ህዳር 18/2008 ዓ.ም ገና ነው፡፡ ቀኑ አላለፈም፡፡›› በማለታቸውም ሰራተኞቹ የፅ/ቤት ኃላፊው እንደገና እንዲያዩት እንደሚያደርጉ ለአባላቱ ገልፀዋል፡፡

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር