“የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላትንም ፍቱልን! (አፈንዲ ሙተቂ)
“የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላትንም ፍቱልን! (አፈንዲ ሙተቂ) – ===
የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች በመፈታታቸው ደስ ብሎናል፤ ፍርድ ቤቱን ለዚህ ጥሩ ስራው እናመሰግነዋለን፡፡ ሆኖም “የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት ያለ ጥፋታቸው ጥፋተኞች መባላቸው እስከ አሁን ድረስ እያሳዘነን ነው፤ በርካቶችም እያለቀሱ ነው፤ የኮሚቴው አባላት ህዝብም ሆነ መንግሥት ባደነቀው ሰላማዊ ሂደት የተመረጡ የህዝብ ወኪሎች መሆናቸው እየታወቀ ያለጥፋታቸው ያንን ሁሉ ዓመት እንዲታሰሩ መወሰኑ በእውነትም ያስለቅሳል፡፡ ምንድነው ጥፋታቸው ቢባል ማንም በትክክል ሊመልስ አይችልም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጨዋታ ውስጥ የገባው በራሱ ተነሳሽነት አይደለም፡፡ ከጅምሩ ስንናገር እንደነበረው ከይሲ የሆኑ አማካሪዎች በሰጡት ምክር ተገፍቶ ነው ወደዚያ የሄደው፡፡ ለዚህ ግንባር ቀደም ሆነው የሚጠቀሱት ደግሞ ሞሳድ-ቀመስ የጂኦ-ፖለቲካ ትንተና የሚሰብኩት ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤልሪክ፣ በአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ ከኔ በላይ ላሳር የሚሉት የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ጉዳዮች ተጠሪ የነበሩትና በኋላም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምሳሳደር ሆነው ያገለገሉት ዶናልድ ያማሞቶ ናቸው፡፡ ሁለቱ ፕሮፌሰሮች ሲያቀርቧቸው የነበሩት መርዘኛ ትንተናዎች በግለሰብ ደረጃ የተደረቱ በመሆናቸው የግለሰብ እይታ ነው ብሎ ማለባበስ ይቻላል፡፡ የአምባሳደር ያማሞቶን አቋም ግን በጭራሽ ለማለባበስ የሚቻል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አምባሳደሩ በመንግሥት ተወካይነታቸው የላኳቸውን መልእክቶች በዊኪሊክስ በኩል አግኝተናልና!!
አምባሳደር ያማሞቶ ወደ አሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከላኳቸው ቴሌግራሞች መካከል ሶስት ያህሉ “የወሃቢዝም ስጋት በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ነበራቸው፡፡ አምባሳደሩ “ወሃቢያ” ብለው የጠሩት አካል በኢትዮጵያ ውስጥ ድሩን እንዴት እንዳስፋፋ ከዘረዘሩልን በኋላ የዋሀቢያን መስፋፋት ለመቀልበስ የወጠኑትን ፕሮጀክት በግልጽ ነግረውናል!! ፕሮጀክቱንም ወደ ተግባር በመቀየር በአሜሪካ ኤምባሲና በሌሎች ተቋማት በኩል ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ የመጅሊሱ ም/ፕሬዚዳንት የነበሩት ሼኽ ኤልያስ ሬድማን ለኤምባሲው የጻፉት ምስጋናና ድንፋታ የተሞላበት ደብዳቤም በፌስቡክ ላይ ተበትኖ አይተነዋል፤ በሆነው ነገር ሁሉ እጅጉ አዝነናልም (ሼኹ “ወሀቢያን ለማጥፋት እንፈልጋለን” እያሉ የተጀነኑበትን ደብዳቤ ያስታውሱ)፡፡
አሜሪካ በሌላው የዐረብና የሙስሊም ሀገራት ስትጫወት የነበረውን ጨዋታ ነው ወደኛ ሀገር ለማምጣት የሞከረችው፡፡ ዓላማዋ “ሱፊያ” ለምትለው ቡድን የተቆረቆረች በመምሰል ሙስሊሞችን በሁለት ጎራ ከከፈለች በኋላ እርስ በራሳቸው እንዲጨራረሱና እንዲተላለቁ መቀስቀስ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙሃኑ ህዝብ ስለነቃባት በኢትዮጵያ ውስጥ የፈለገችውን ነገር ማሳካት አልቻለችም፡፡ የተነሳው አዋራ ግን ቀላል አይደለም፤ የኛን ወኪሎች ያለጥፋታቸው ያሳሰረብን ይኸው ከይሲ ዓላማ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ነገር ሲገባበት (ገብቶበታል አላልኩም) በቂ መረጃና ጥናት አልሰራበትም፤ መጅሊሱ የህዝብ ድጋፍ ያለው መስሎት ሃላፊነቱን ለርሱ አሸክሞታል፤ ነገር ግን መጅሊሱ አጀንዳውን ወደ ህዝቡ ጆሮ ማድረስ እንኳ አልቻለበትም፤ በዚያ ላይ የተጠቀመው ስትራቴጂ ህዝቡን የሚያጋጭ መሆኑ ቢነገረውም እርሱ ግን በእልህ ሄዶበት የትም ሊደርስ አልቻለም፤
የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዳዩን አሳሳቢነት ዘግይቶም ቢሆን ተረድቶታል፤ በውጤቱም መጅሊሱ የጀመረው ዘመቻ እንዲቆም ተደርጓል፤ በዚህ ረገድ ላደረገው መሻሻል ትልቅ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ህዝቡ የወከላቸው የሃይማኖት አባቶችና ሰባኪያን አሁን በእስር ላይ በመሆናቸው የህዝቡ ልብ አሁንም እንዳለቀሰ ነው፡፡ በተለይም በአሜሪካና በጽዮናዊን አቀነባባሪነትና በመንግሥት አላዋቂነት የተተገበረው ይህ በደል ለብዙ ክፍለዘመናት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ሲካሄድበት በነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊም ላይ የተፈጸመ መሆኑ በታሪክ መድረክ በምሬት መዘከሩ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ የኢፌዴሪ መንግሥት ያኔ የተሰራውን አሳዛኝ ስህተት ሙሉ በሙሉ በማስተካከል የጎደፈ ስሙን ማደስ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ቀዳሚው እርምጃ ደግሞ የብዙሃኑ ወኪሎች የሆኑትን ኢማሞች፣ ሼኾችና ኡስታዞች ከእስር መልቀቅ ይሆናል፡፡
ወኪሎቻችን የሚለቀቁበትን ሁኔታ እኛ አናውቀውም፤ የኛ ፍላጎት ከእስር ቤት ወጥተው ከሚወዷቸው ቤተሰቦችና ከመስጂድ ጀመዓ ጋር እንዲቀላቀሉ ማስቻል ነው፤ ቢፈልጉ ይቅርታ ይጠይቁ፤ ቢፈልጉ በሽምግልና ይጨርሱት፤ ቢፈልጉ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቅርባችሁ እንዲለቀቁ አድርጉልን፤ የኛ ፍላጎት መለቀቃቸው ብቻ ነው፤
—-
በተረፈ እነዚህን ነገሮች መጨመር እፈልጋለሁ
1. በዚህ ጉዳይ ላይ እየደጋገምኩ የምጽፈው ነገሩን ከስረ መሰረቱ ስለማውቀው ነው፤ ፌስቡክ በሚባለው ድር ላይ “የመጅሊሱ አካሄድ ህጋዊ አይደለም” በማለት መጻፍ ከጀመሩት ቀዳሚ ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ፤ በዚህም ብዙ ከፍለንበታል፤ ጥያቄያችን መጅሊሱ ሊተገብረው የተነሳውን ህገ-ወጥ እርምጃ መቀልበስ ነው፤ “ይህንን አመለካከት ትተህ ይህኛውን ብቻ ተቀበል” የሚለው የመጅሊሱ አካሄድ ኢ-ህገ መንግሥታዊ ነው፤ ይህንን እርምጃ ከመቀልበስ የዘለለ ዓላማ አልነበረንም፤ ዛሬም ዓላማችን ይኸው ነው፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማያቸው የፌስቡክ ጽሑፎች ጥያቄአችን “ወያኔን መገልበጥ” የመሰላቸው ሰዎች እንዳሉ እየታዘብኩ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች የምትጽፉ ሰዎች ራሳችሁን ቻሉ፤ ፍላጎታችሁን ከህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄና ከኮሚቴው ጋር ለማያያዝ አትሞክሩ (እንትና ደግሞ እንደለመድከው “ወያኔን ተለማመጥክ፤ ጉቦ ተቀብለህ ነው” ጂንኒ ጀቡቲ በል፡፡ አንተን ብሎ ለኛ አሳቢ! አንተን ብሎ ጀግና ተዋጊ!! እንዳንተ የውሸት ስም እየተጠቀሙ ከአውሮጳና አሜሪካ የሚተኩሱትን አታልል፤ እኔ እዚሁ ሀገሬ ላይ ቁጭ ብዬ ነው በራሴ ስም የምጽፈው)፡፡ እኛ ጥያቄያችንን ያቀረብነው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ነው፤ ዛሬም ቢሆን መንገዳችን ይኸው ነው፤ ከዚህ ውጪ ሌላ መንገድ አንሻም፡፡
2. ያንን ህገ-ወጥ እርምጃ የጀመረው መጅሊስ አሁን የለም፤ በምትኩ ሌላ ቡድን ወደ ስልጣን መጥቷል፤ የመጅሊሱ ምርጫ የህዝቡን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ እንዲካሄድ መጠየቃችን እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ወቅት አንገብጋቢው ፍላጎታችን ወኪሎቻችን እንዲፈቱልን መወትወት ነው፡፡ እነርሱን ወደ እስር ቤት ሸኝተን የሰላም እንቅልፍ መተኛቱ ከባድ ነው፡፡
3. የአሜሪካ መንግሥት ጨዋታውን በመወጠኑ ሂደት የነበረውን ሚና ከላይ በመጠኑ ገልጫለሁ፡፡ ታዲያ ይህቺው አሜሪካ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቆርቋሪ ሆና የኢትዮጵያን መንግሥት ስትከስ በጣም እስቃለሁ፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ እምነት ነጻነት ኮሚሺን የተባለው ተቋም የኢትዮጵያ መንግሥት የሙስሊሞችን መብት አያከብርም የሚል መግለጫ ለሁለት ጊዜ ያህል አውጥቷል፡፡ ድንቄም ተቆርቋሪ!
4. ምዕራባዊያን ይህንን መጥፎ ፕሮጀክት የደገሱልን እንድንባላላቸው ፈልገው ነው፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ የተባላ አንድም ፍጡር የለም፤ ኮሚቴው ከህዝቡ የተሰጠውን አደራ ቀልብሶ ወደ ሌላ አቅጣጫ አልወሰደውም፤ ለዚህም ሁላችንም ምስክሮች ነን፤ ኮሚቴው በስሜት ተነድቶ የፀረ-ህዝቦች መጠቀሚያ ባለመሆኑ ምስጋናችን ከልብ ነው፤
5. በመጨረሻም እኔ አፈንዲ ሙተቂ፤ በእስልምና ውስጥ የሻፊዒ መዝሐብ ተከታይ እና የአሽዐሪ የስነ-መለኮት (አቂዳ) ርዕዮት አማኝ ነኝ፤ ነገም እንዲሁ ነኝ፤ ተነገ ወዲያም ኢንሻ አላህ እንዲህ ነኝ፤ (“አሽዐሪ” ሲባል ሳዳት ከማል የሚባለው ጥራዝ ነጠቅ ወጠጤና ጀሌዎቹ እንደሚቀባጥሩት አዲስ ዓይነት የአቂዳ መንገድ አይደለም፤ አሽዐሪ የአል-አዝሐር ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምረው እና አብዛኛው የዓለም ሙስሊም የሚያምንበት ርዕዮት ነው፤ 70 % የሚሆነው የዓለም ሙስሊም በዚሁ መንገድ ነው የሚያምነው፤ ምንነቱን ባጭሩ ለማወቅ የሚፈልግ ሰው “አብደኡ ቢስሚላሂ ወርራሕማኒ-የቢ-ርረሒሚ ዳኢሙል ኢሕሳኒ” የሚለውን ዝነኛ ነሺዳ ያስታውስ፤ ሁሉንም እዚያ ውስጥ ያገኘዋል፤
ቢሆንም እኛ እንደ “ሳዳት” ወፍራም የፔትሮ-ዶላር ደመወዝ እየተከፈለን በአቂዳ ስም የጽዮናዊያንን ጨዋታ አንጫወትም)፡፡
ታዲያ እኔ እንዲህ ብሆንም የሰለፊ መዝሐብ ተከታይ ከሆነው ወዳጄ አሕመዲን ጀበል ጋር አልተጋጨንም፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ አሕመዲን “አሕባሽና የአላህ ባህሪያት” የሚለውን መጽሐፉን ሲጽፍ ከኔ መጽሐፍ በብዙ ተጠቅሞበታል (“በኡባህ አብዱሰላም ሰዒድ” የተጻፈው መጽሐፍ የሚለው የኔን መጽሐፍ ነው)፡፡
መጅሊሱን በጋራ የተቃወምነው የአንድ መዝሀብ ተከታዮች ብቻ ሳንሆን የብዙ መዝሐቦች ተከታዮች ነን፡፡ ኮሚቴውንም የወከለው ብዙሃኑ ህዝብ ነው፤ ስለዚህ ለብዙሃኑ አክብሮት ሲባል ኮሚቴውን መልቀቁ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
