የአወሊያ የእርዳታና የልማት ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ በህልውናው ዙሪያ ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ!
ከነሐሴ 12/2007 ጀምሮ በአስገዳጁ ሁኔታ ምክንያት ህልውናው ማክተሙን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል!
አርብ ነሐሴ 22/2007
የአወሊያ የእርዳታና የልማት ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ በህልውናው ዙሪያ ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ!
ነሐሴ 12/2007 በራሃ ሆቴል በዶክተር ሐሰን ሰዒድ ሰብሳቢነት የተካሄደው ይኸው ስብሰባ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዬች ጠቅላይ ምክር ቤት በ21/11/2007 የተፃፈውን ስድስት የእግድ ደብዳቤ ተከትሎ የተጠራ ሲሆን መጅሊሱ በእግድ ደብዳቤው የስራ ቦርዱ ስራ እንዲያቆም፣ የልማት ድርጅቱ ለእለታዊ ስራ ማስኬጃ ማንኛውንም ወጪ እንዳያደርግ፣ የመምህራን ቅጥርና እድገት እንዲቆም፣የልማት ድርጅቱ ለማህበረሰቡ የሚሰጠው የነፃ አገልግሎት እንዲቆም እና ስራ አስኪያጁ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የታዘዘበትን ሁኔታ ለመነጋገር ነበር፡፡
በበጎ አድራጎት ደርጅቶችና ማህበራት ኤጅንሲ በፀደቀው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 14 ቁጥር 6 መሰረት ቦርዱን የማፍረስ ስልጣን የተሰጠው ይኸው የስራ አመራር ቦርድ ጠቅላላ ጉዳዔ መሆኑን በግልፅ ያስቀመጠ ቢሆንም የህገ ወጡ የመጅሊስ አመራር ግን ደንቡን በመጣስ ነው የእግድ ደብዳቤውን የፃፈው፡፡ የአወሊያ የእርዳታና የልማት ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ በህገ ወጡ መጅሊስ የተላለፈበት ህገ ወጥ እግድ ተገቢ እንዳልሆነ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን ኤጀንሲውም ህገ-ወጡ መጅሊስ የወሰዳቸው እርምጃዎች ህግን ያልተከተሉ መሆናቸውን ለስራ አመራሩ ቦርድ በመግለፅ ለመጅሊስ ደብዳቤ ፅፏል፡፡
የመጅሊስ እግድ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ በሚመለሱበት ወቅት ሁከት ለማስነሳትና ሰላም በማደፍረስ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስተጓጎል ያለመ በመሆኑ የስራ አመራሩ በዚህ ተጠያቂ እንደማይሆን በስብሰባው ላይ አፅንዖት በመስጠት ያሳሰበ ሲሆን መሰል የመጅሊስ ትንኮሳዎች ውጤታቸው የከፋና እንደሚሆንና እነሱም ህዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት አመቺ የስራ ከባቢ ባለመኖሩ ስራቸውን ለመቀጠል እጅግ አስቸጋሪ የሆነባቸው መሆኑን የቦርድ አባላቱ ገልጸዋል፡፡
ይህንን አስገዳጅ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የአወሊያ የእርዳታና የልማት ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ ከነሐሴ 12/2007 ጀምሮ ህልውናው ማክተሙን በሙሉ ድምፅ ያጸደቀ ሲሆን የስብሰባውን ቃለ-ጉዳዔ በሸኚ ደብዳቤ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የልማት ማህበራት ኤጀንሲ በፅሁፍ እንዲደርሳቸው በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት በግልባጭ አሳውቋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎች ሲኖሩ የምናሳውቅ ይሆናል!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!

