ኢትዬጲያዊያን ሙስሊሞች አሁን በሃገራችን ያለንበት ተጨባጭ ይህን ይመስላል :: (አቡ ዳውድ ኡስማን )
ኢትዬጲያዊያን ሙስሊሞች አሁን በሃገራችን ያለንበት ተጨባጭ ይህን ይመስላል
አቡ ዳውድ ኡስማን
ወደፊት ለመጓዝ አሁን ያለንበትን ተጨባጨ መመዘን ተገቢ ነው፡፡ የተጋረጠብንን ችግሮችም ለመጋፈጥ እና ችግሩን ጥሶ ለማለፍ ያሉትን ችግሮች ማወቁም ተገቢ ነው፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ 3 ቀላል ጥያቄዎችን ለመንግስት አቅርቧል፡፡
ይህም ጥያቄዎች መጅሊስ በህዝበ ሙስሊሙ በሚመረጡ አመራሮች ይተኩ፣ አወልያ በህዝብ በሚመረጡ ቦርድ ይመራ እና የአህባሽ አስተሳሰብ በግዳጅ በሙስሊሙ ላይ መጫን ይቁም የሚል ነበር፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙም ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ የሚልም አራተኛ ጥያቄ ተጨመሯል፡፡ ሙስሊሙ የጠየቀው ጥያቄ እና የተሰጠው ምላሽ ግን ፍፁም ለየቅል ናቸው፡፡ እንዴት የሚለውን ከታች በተዘረዘሩት ተጨባጮች እንመለከተዋለን፡
የኢትዬጲያ ሙስሊሞች በአሁን ሰዓት የምንገኝበት ተጨባጭ እንደሚከተለው ነው
ይህን ለማስተካከል ባለመቻላችን አላህ ፊት ምን ይሆን ምላሻችን???
1. በሃገሪቱ ብቸኛ የሙስሊሞች ወካይ አካል የኢትዬጲያ እስልምና ጉዳዬች ጠ/ምክር ቤት ወይም መጅሊስ በትክክለኛ ሙስሊሞች መመራት ካቆመ አስርት አመታትን አስቆጠረ፡፡
2. የሙስሊሙ መሪ ይመረጥ ሲባል ለመንግስት ባላቸው ታማኝነት በቀበሌ ግለሰቦች እንዲመረጡ ተደረጓል
3. መንግስት በቀበሌ አስመርጦ ለመጅሊሱ መሪነት እራሱ የሾማቸው ግለሰቦችም የመንግስት አጥፊ ተልኮ አናስፈፅምም ሲሉት እነሱን በመፈንቅለ ስልጣን በማንሳት ፅንፈኛ እና አክራሪ የሆኑ የአህባሽ ተከታይ አመራር አድረጎ በሙስሊሙ ተቋም ላይ ተሾመ
4. በኢትዬጲያ ብቸኛው ሁሉን አቀፍ ተቋም የሆነው አወልያ በመንግስት አስገዳጅነት ከሙስሊሙ ተነጥቆ ለህገ ወጡ መጅሊስ እንዲሰጥ ተደረገ
5. ተቋሙ በህዝብ በተመረጡ የቦርድ አባላት ይመራ የሚለውን ጥያቄ በመፈንቅለ ስልጣን የተወገዱት አመራሮች በከፊል ለመመለስ የሞከሩ ቢሆንም አዲሱ አህባሽ መራሹ የመጅሊስ አመራረች ቦሩን አፍርሰው ሙሉ በሙሉ በፅንፈኛ አህባሾች እንዲዋቀር እሰሩ ነው፡፡
6. አወልያ ለመጀመሪያ ጊዜ አህባሾች በአስተዳዳሪነት እንዲረከቡት ተደርጓል፡፡ በአስተዳዳሪነት የነበሩትን ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ ባመድረግ አህባሽ ግለሰቦች ቦታውን ተረክበውታል፡፡ ፅንፈኛው ሃጂ ኢዘዲን የተባለው የአህባሽ መሪም አጠቃላይ አወልያን ወደ አህባሽ መናሃሪያነት ለመቀየር የበላይ ተቆጣጣሪ ሆኖ ተሹሟል፡፡
7. በአወልያ ሲረዱ እና ሲማሩ የነበሩ የቲሞች እንዲባረሩ እንዲሁም የቁርዓን ሂፍዝ ትምህርትም እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ከጀናዛ እጥበት እና ከንፁህ ውሃ በስተቀር ማንኛውም አይነት የነፃ አገልግሎት የአወልያ ተቋም ለሚስኪን የቲሞችም ቢሆን እንዳይሰጥ ተደርጓል፡፡
8. ከአወልያ ቀጥሎ የነበረው የወልዲያው ግዙፉ ተቋም በአህባሾች ስር እንዲወድቅ ተደርጎ በርካታ የቲሞችን እንዳልተንከባከበ አሁን የቲም ሆኖ የህልውናወ ጉዳይ አጠያያቂ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ተደርገዋል፡፡
9. በመላው ሃገሪቱ የነበሩ የተለያዩ ኢስላማዊ ድርጅቶች እና ማህበራት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡
10. .መንግስት እኔ ትክክለኛውን ኢስላም አውቅላቹሃለው በማለት አህባሽ የተባለውን አንጃ መቀበል አለባችሁ በሚል የግደጅ ዘመቻ ሲደረግ ቆይቷል አሁንም በአዱስ መልኩ ዘመቻውን ለመክፈት በከፍተኛ ደረጃ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡
11. አህባሽ የተባለው ፅንፈኛ አፈንጋጭ አስተሳሰብ ቀድሞ የነበረ ቢሆንም በግዳጅ የሙስሊሙን አቂዳ እንዲበርዝ ሽርክ እና ቢድአን እንዲያስፋፋ በመንግስት ድጋፍ እየተደረገለት ነው
12. አባቶቻችን ብዙ ደማቸውን አፍስሰው በመስዋትነት የገነቡትን መስጂዶቻችንን በመንግስት አስገዳጅነት ከሙስሊሙ በመንጠቅ ለአህባሽ መራሹ መጅሊስ አሳልፎ እየተሰጠ ነው፡፡የመስጂዱን የስልጣን ጉዳይ ሳይሆን መስጂዱን ከተረከቡት ቡሃላ ብልሹ የሆነውን አቂዳቸውን እና የጥመት አስተምህሯቸውን በመስጂዳችን በነፃነት ማስተማር ጀምረዋል፡፡ ደሴ ከተማ ለዚህ መስክር ናት
13. በመስጂዶቻችን ለረጅም አመታት በኢማምነት ሲመሩን የነበሩትን ኡለሞቻችንን እና መሻይኮቻችን በኩፍር እና በቢድአ በተጨማለቁ የአህባሽ እምነት አራማጅ ግለሰቦች በመንግስት እንዲተኩ ተደረገ፡፡ እየተደረገም ነው፡፡
14. በአህባሽ እና በቢድአ አራማጆች ተከትለን አንሰግድም በሚል ሁለተኛ ጀምአ ለመስገድ ሲሞከር በመንግስት ሁለተኛ ጀምአ መስገድ ሃራም ተደርጎ ሙስሊሞች ሲታሰሩ ቆይተዋል፡፡ እየታሰሩም ነው፡፡
15. .በመስጂዶቻችን የዳዕዋ እና ኢስላማዊ ትምህርቶችን እንዳንማማር እየተከለከለ ይገኛል፡፡ በአዲሱ የአህባሽ መራሹ ባወጣው ህገ ደንብ መሰረት ከመጅሊሱ ፈቃድ ውጪ ዳዕዋ ማድረግም፣በመስጂድ መመሪያ አውጥተዋል፡:
16. ዳኢዎች እስልምናን ለማስተማር ከፈለጉ ከአህበሽ መራሹ መጅሊስ መታወቂያ ካላወጡ በየትኛውም መስጂድም ሆነ ቦታ ማስተማር አይችሉም ተብሎ መመሪያ ወጥቷል፡፡
17. ማንኛውም ኢስላማዊ ትምህርት በመፅሃፍም ሆነ በኦዲዬቪዋል ለማሳተም ከተፈለገ የአህባሻዊ መጅሊሶችን ፈቃድ እና ይሁንታ ማግኘት አለበት ተብሎ መመሪያ ወጥቷል፡፡
18. የመስጂድ ኻዲሞች፣ኢማሞች እና ሙዓዚኖች የአህባሽን አስተምህሮ የማይከተሉ ከሆነ ከስረቸው እንዲፈናቀሉ እና በነሱ ቦታም የአህባሽን አቂዳ የሚከተሉ፣በአደባባይ ወሃቢያ ብለው የሚያስቡትን ሙስሊም በግልፅ በየመሳጀዱ የሚቃወሙ እና የሚያስተምሩ ሰዎች እንዲተኩ ወስነዋል፡፡
19. ሁሉም ኢስላማዊ የህትመት ውጤቶች የሆኑ ጋዜጦች እና መፅሄቶች በሃገራችን ኢትዬጲያ ለሙስሊሙ እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡
20. በመላው ሃገሪቱ ታላላቅ ቂርአት ቦታዎች እና ዛውያዎች በመንግስት እንዲዘጉ እና እንዲፈርሱ ተደርገዋል፡፡
21. በሺዎች የሚቆጠሩ ደረሶች ከሚቀሩባቸው የቂርአት ቦታዎች ኡስታዛቸውን ለአልሸባብ ወጣት እየመለመልክ ነው በሚል እንዲታሰሩ ተደርጎ ደረሶቹንም እንዱበተኑ እና ወደ ሃገራቸው እንዲሄዱ በታጣቂዎች ተደርጓል
22. .በሃገሪቱ የሚገኙ ኢስላማዊ መድረሳዎች እንዲታሸጉ ተደረገ
23. ህፃናት በልጅነታቸው ቁርአን የሚቀሩ ከሆነ ሲያድጉ አክራሪነት ስለሚጠናወታቸው ከ 18 አመት በታች ቁርአን እንዳይቀሩ የሚል ሃሳብ በዶ/ር ሽፈራው በተባለው የኢስላም ጠላት በሆነ ግለሰብ ቀርቦ በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ባሉ አንዳንድ ከተሞች ተግባራዊ ሲደርግ ቆይቷል
24. በየመስጂዱ የነበሩ ኢስላማዊ ቤተ መፅሃፍቶች እንዲታሸጉ አልያም በውስጣቸው ያሉ የተውሂድ ኪታቦች እንዲሁም በስም በሚታወቁ ታላላቅ ኡለሞች የተፃፉ መፅሃፍቶችን የዋሃቢያ ናቸው በሚል እንዲቃጠሉ እና እንዲወገዱ ተደረጓል
25. ፂም ማሳደግ እና ሱሪ ማሳጠር የነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሱና መሆኑ እየታወቀ የአክራሪዎች እና የአሸባሪዎች ነው በሚል እየታሰርን፣ እየተደበደብን እና እየተሰቃየን እንገኛለን
26. ሙስሊም ተማሪዎች አላህ (ሱ.ወ) ግዴታ ያደረገባቸውን የግዴታ ሰላት በጀምአ እንዳይሰግዱ ተከለከሉ፡፡
27. ሙስሊም ሴት እህቶቻችን በት/ቤቶች እና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሂጃባቸውን ካላወለቁ መማር እንደማይችሉ ተነገራቸው፡፡ በየቦታው ሂጃባቸውን በመጠበቃቸው ብቻ እያመናጨቁዋቸው፣ሂጃባቸውን እየገፈፉ አንቺ የአረብ አመንዛሪ እየተባሉ እየተሰደቡ እና እየተዋረዱ ይገኛሉ
28. በመስጂድ ውስጥም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች ቂርአት ተሰብስቦ መቅራት በተለያዩ ቦታዎች ተከልክሏል፡፡ በአካል ብቻ ሳይሆን ኢስላማዊ ትምህርት በሚሞሪ ካርድ እየቀዱ ተሰብስቦ ማዳመጥም እንደወንጀል ተቆጥሮ በርካታ ሙስሊሞች መታሰራቸው የሚታወቅ ነው፡፡
29. በመላው ሃገሪቱ ለኢስላም ብዙ ሲለፉ እና ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ኡለሞች፣ ኡስታዞች እና ወንድሞች በየእስር ቤቱ በአሸባሪ የሚል ታፔላ ተለጥፎላቸው ወህኒ ወረዱ፡፡ ከቤታቸው ጎትተን ወኪል ሁኑን ያልናቸው ኡስታዞቻችን ከ 7 አመት እስከ 22 አመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡
30. .በመስጂዶቻችን ወታደሮች ከነጫማቸው በመግባት መስጂዳችንን በማርከስ በሙስሊሞች ደም አጨቀዩት
31. .ኢስላማዊ የሰደቃ እና የዳዕዋ ዝግጅቶች ሙስሊሙ እንዳያካሂድ በመንግስት እንዲታገዱ ተደረገ:: ኢስላማዊ ኮንፍረንሶች በደህንነቶች ትዕዛዝ እስካሁን ድረስ ደስ ሲላቸው እከለከሉ ይገኛሉ፡፡
32. ኢስላማዊ ትምህርቶችን መስጫ ፓምፍሌቶችን ማሰራራጨትም ሆነ መበተን ሽብር ነው በሚል ተከለከለ
33. በመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ስራውን የፈለገ ስራውን ይስራ ያልፈለገ ደግሞ ስራውን ይልቀቅ በሚል ሰላት እንዲያቆሙ አልያም ማታ ቤታቸው ሲገቡ ሰብስበው እንዲሰግዱ፣
ኢስላማዊ መገለጫዎችን ፂም ማሳደግ እና አለባበሳቸውንም ኢስላማዊ ማድረግ ክልክል በጥብቅ ተከለከሉ
34. ከወለድ ነፃ የሆነ የባንክ ስርአት ፍቃድ አግኝቶ እንቅስቃሴ ከጀመረ ቡሃላ መልሶ እንዲታገድ እና እንዲፈርስ ተደረገ
35. በመላው ሃገሪቱ ያሉ እስር ቤቶች ቢፈተሹ በሙስሊሞች ተሞልተው ይገኛሉ፡፤ ሁሉም በሽብር ወንጀል በሚል ተከሰው ይገኛሉ፡፡
36. ይህን ሁሉ በደል እና ግፍ ለምን ይፈፀማል ብሎ የጠየቀውን ንፁሃን ሙስሊም አክራሪ፣አሸባሪ፣ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚንቀሳቀሱ፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ በማለት ታፔላ በመለጠፍ ከፊሉ በጥይት ተደብድቦ ሲገደል፣ ከፈሉ በዱላ ድብደባ ሂወቱን አጥቷል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ለእስራት እና ለአካል ድብደባ እና ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩም በየእስር ቤቱ እንዲማቅቁ ተደርገዋል፡፡
37. በርካታ ኡለሞች፣ዱዓቶች እንዲሁም ለሙስሊሙ ብዙ ሲካድሙ የነበሩ ሙስሊሞች መንግስት ሲያሳድዳቸው የሚወዷት ሃገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡
38. ሴት እህቶች ባሎቻቸው በግፍ ታስረውባቸው ልጆቻቸውን በመከራ ለማሳደግ ተገደዋል፡፡ የእለት ተዕለት ስራቸው በየማረሚያ ቤቱ ስንቅ በማመላለስ፣በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ሙስሊም በመሆናቸወ ብቻ አጸያፊ ስድቦችን እና ትንኮሳዎችን እያስተናገዱ መራራ የሆነውን ሂወት ለመጋፈጥ ተገደዋል፡፡
39. ህፃናት ያለአባት የቲም ሆነው እንዲያድጉ፣በልጅነታቸው መማር ሲገባቸው ሰው ቤት ተቀጥረው ኑሯቸውን ለመምራት የተገደዱበት ተጨባጭ ተፈጥሯል፡፡ እነዚህን ሁሉ ለመርዳት እና ለማግዝ ሙስሊሙ ጥቂትን እንጂ አላስታወሳቸውም፡፡
40. ባጠቃላይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከማህበራዊ፣ከኢኮኖሚያዊ እና ከሃይማኖታዊ መብቶቹ ተገሎ በሃገረ ባዕድ ሆኖ እንዲኖር እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት በኢትዬጲያውያን ሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ከሚገኘው በደል እና ግፍ በጥቂቱ ሲሆን ይህ ሁላ በደል እና ግፍ ሲፈጸም ጀግኖች መስዋትት በመክፈል ይህን በደል ለማስቆም ሲንቀሳቀሱ እኛ ግን በደሉን ተላምደን ዜና ከማንበብ ውጪ የፈጠርነው አንዳችም ነገር የለም፡፡
አባቶቸችን ከአፄዎቹ ስርአት ጋር በመጋፈጥ ብዙ መስዋትነት ከፍለው፣ አንገታቸው እየታረደ፣እጅ እና እግራቸው እተቆረጠ፣እጃቸው ተቆርጦ እንደክራቫት አንገታቸው ላይ እየተንጠለጠለላቸው እስልምናችንን አንለውጥም ብለው ታሪክ ሰርተው ለዚህ ትውልድ ኢስላምን አስረክበው አልፈዋል፡፡
በኛ ዘመን ደግሞ ዳግማዊ አፄዎች እስልምናችንን በበካይ አስተሳሰብ ለመበረዝ ሲንቀሳቀሱ ከንፈር ከመምጠት ፣ በባዶ ከሞፈክር ውጪ አንዳችም ነገር ለማድረግ አልተቻለም፡፡ እስልምና በሂወት እያለን ይህ ሁላ ሲደፈር ማየት ምነኛ ሞት ነው ፡፡ ቀደምት ሰሃቦች ይህን ጉድ ቢያዩ ምን ይሉ ነበር?????
ይህ ሁሉ ግፍ እና በደል ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡ ነገም እስካሁን ከነበሩት ግፎች የበለጠ ትልቅ የመከራ ድግስ እየተደገሰልን ነው፡፡ ከዚህ ፈተና ወደ አላህ በመቃረብ ካልሆነ በስተቀር ልንወጣውም አይቻለንም፡፡ ከዲን ርቀን ነስር መቼም አይታሰብም፡፡ አላህን እያመፅን፣ሱናን እየተቃረንን፣ስሜታችንን እየተከተልን አላህ ነስርም አይሰጠንም፡፡
አሁን ያለንበት ተጨባጭ ይህን ይመስላል፡፡ ነገ አላህ ፊት ዲንህ በተደፈረ ጊዜ ምን አደረክ ስንባል ምላሻችን ምን ይሆን
አላህ በወንጀላችን አይፈትንን፡፡ በሃይማኖታችን ላይም የማንችለውን ፈተና አያሸክመን፡ በጠላቶቻችንም ላይ ድልም እንድንቀናጅ ሁልጊዜም እርዳታው አይለየን!!!
አሚን!!
አሚን!!
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
