ህዝባዊ አመጽ ከቱኒስ ወደ ካይሮ እና ሰንዓ፤ አዲስ አበባስ?
በቱኒዚያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ እንደ ሰደድ እሳት ወደ አካባቢው አገሮች እየተዛመተ ነው። ወላፈኑ አልጄሪያ፣ ሞሮኮና ሊባኖስን አዳርሶ አልባኒያ ደርሷል። አሁን የእሳቱ ሰደድ ግብጽና የመን ውስጥ በመንቦግቦግ ላይ ይገኛል።
ሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ናቸው። የአምባነኖች ጡንቻ መፈርጠም፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም ህዝቡን ከትግል እንዲሸሽ አላደረገውም። እንደ ቱኒዚያው መሃመድ ቦዛዚ እንደየመንዋ ታዋኮል ኮርማን ያሉ “እስካሁን በነበርንበት ሥርዓት ከምንቀጥል ህይወታችን ማጣት ይቀለናል” የሚሉ ወጣቶች ተበራክተዋል።
የአንባገነነት መንሰራፋት፤ “በመተካካት” ስም ስርወ-መንግሥት የማቋቋም ህልም፤ የፍትህ እጦት፤ የውሸት ምርጫዎች መብዛት፤ የሰብዓዊ መብቶች መረገጥ፤ የሥራ አጥነት መበራከት፤ የፓሊስ፣ ጦር ሠራዊትና እና “የጆሮ ጠቢዎች” መብዛት፤ የኑሮ መወደድ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም ከቱኒዚያም ሆነ ከግብጽ ይልቅ የኢትዮጵያው አምባገነን መለያ ባህርያት ናቸው።
ለውጥ እንደ ወረርሽን የመሰራጨት ኃይል አለው። በአንዱ አገር የተነሳው ተቃውሞ ወደ ጎረቤት ለመዛመት ጊዜ አይፈጅበትም። እናም ቱኒዝያ የተጫረው እሳት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሰሜን አፍሪካንና የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮችን መንካቱ በጭራሽ የማይቀር ነገር ነው። በእነዚህ አገሮች ሁሉ የሥርዓት ለውጥ ከመጣ አዲስ ጂኦ-ፓለቲካ ይፈጠራል።
ይህ የሰደድ እሳት አዲስ አበባ ሊደርስ ይችላል። ከላይ እንደተገለፀው ኢትዮጵያ ከሰሜን አፍሪካና መካከለኛ ምሥራቅ የምትጋራቸው በርካታ ባህርያት አሉ። በኢትዮጵያውያን እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ በግብጽም በየመንም ከበደረሰው በብዙ እጥፍ ይበልጣል፤ እኛ ዘንድ ያለው ችጋርም እነሱ ዘንድ ካለው ጊዜዓዊ ረሃብ ጋር የሚወዳደር አይደለም። አገራችን በአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ሥር በመሆኗ ህዝባዊ እምቢታን ካረገዘች ቆይቷል። ቅራኔዎች ለመፈንዳት ሰበብ መጠበቅ ከጀመሩ ውሎ አድሯል። ስለሆነም ዛሬ ካይሮና ሰነዓ እያየነው ያለው ህዝባዊ ትዕይንት ነገ አዲስ አበባ ውስጥ ልናየው እንችላለን።
ይህ መልካም ዜና ቢሆንም ሥጋትም አለብን። እኛ ኢትዮጵያውያን ወያኔ የተከለብን ተጨማሪ በሽታ ስላለብን ጥንቃቄዓችን የላቀ መሆን ይኖርበታል። ወያኔ በዘር ያደራጀው ጦር ከህዝብ ጋር ይወግናል ብሎ መጠበቅ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ወያኔ የተከለብን ዘረኝነት እኛንም ጠልፎ እንዳይጥለን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ እንዲነሳ ይጠይቃል። እኛም ለመብቶቻችን መቆም ግዴታችን ነው ይላል። የነፃነትና የዲሞክራሲ ወገንተኛ የሆን ፓርቲዎች ሁሉ እየተፈጠረ ያለውን ሁኔታ በንቃት እንድንከታተል፤ ተመሳሳይ ሁኔታ በአገራችን ቢከሰት መከተል ስለሚኖርብን ስልቶች እንድንወያይና፤ በጋራም በግንባር ቀደምትነት እንድንቆም ያሳስባል። የወያኔ ዘረኛ አወቃቀር የትግላችንን አቅጣጫ እንዳያስት ሁላችንም በኃላፊነት እንንቀሳቀስ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!