ከሳሽ ሲከሰስ – ካለፈው የቀጠለ – ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ ቢኖር
ከሳሽ ሲከሰስ – ካለፈው የቀጠለ
(ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ ቢኖር ነበር እኛ ኢትዮጵያን ሙስሞች እንዲህ ብለን እንከስ እንበር!)
7ኛ. ተከሳሽ የኢ.ፌዲ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
የሽብር ቡድኑ የስልጠናና የምልመላ ክፍል በመሆን ሰርቷል፡፡ የህዝብን ሃብትና ጊዜ ለእኩይ ዓላማው በመጠቀም የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማስፈፀም በሙሉ ልቡ ተንቀሳቅሷል፡፡ 10ኛ ተከሳሽን (መጅሊስን) እንደ ኃይማኖታዊ ሽፋን በመጠቀም አክራሪ ስልጠናዎችን አዘጋጅቷል፤ አካሂዷል፡፡
“ህገ-መንግስት ማስተማር” በሚል ስም በኃይማኖታዊ ጉዳዮች በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የሚያምኑባቸውን ጉዳዮች በአዲሱ አክራሪ አስተሳሰብ መተካት እንዳለባቸው በ2003 ሐምሌ ወር በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ከ10ኛ ተከሳሽ የኢ/እ/ጉ/ጉባኤ (መጅሊስ) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የአህባሽ ስልጠና ላይ የ1ኛ ተከሳሽን (የመንግስትን) አቋም አንፀባርቋል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአክራሪ አስተሳሰቡን ማስፋፋትና በሙስሊሙ ኃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገባ ቀጥተኛ ትዕዛዝና መመሪያ መስጠት የዕለት ከዕለት ተግባሩ በማድረግ ህገ-መንግስታዊ ጥሰት ፈፅሟል፡፡
የሽብር ቡድኑ ለመፈፀም ላቀደውና ለፈፀመው የሽብር ድርጊት የአስተሳሰብ መደላድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ስለሆነም የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈፀም ስልጠና በመስጠት ወንጀል በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(1)(2) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡ 8ኛ. ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የሽብር ቡድኑ ለሚፈፅማቸው ህገ-ወጥ ድርጊቶች የህግ ሽፋን በመስጠት ተንቀሳቅሷል፡፡ በስሩ በሚገኘው የፌዴራል ዓቃቢ ህግ በኩል ከ11ኛ ተከሳስ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ) ጋር በመተባበር የሽብር ቡድኑ የሚፈፅማቸውን የህገ-መንግስት ጥሰቶችና የሽብርተኝነት ተግባራት የሚቃወሙና ለህዝብ የሚያጋልጡ የነፃነት ታጋዮችን፣ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ሰዎችን በሀሰት ውንጀላ በመክሰስ እና የሀሰት የምስክርና ሰነድ በማዘጋጀት ወንጀል ፈፅመዋል፡፡
በተለይም የህዝበ-ሙስሊሙን ህጋዊ ወኮሎች የሽብር ቡድኑ በፈፀመው በሽብር ወንጀል በመክሰስ ለሽብርተኝነት ከለላና ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የህዝበ-ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ የዓለም ማህበረሰብን ባስደመመ ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የመሩና ያስተባበሩ የህዝብ ልጆችን ያለምንም ሀፍረት ወይም ርህራሄ ለእስርና እንግልት ዳርገዋል፤ የንፁሃንን ቤተሰብ አባወራ አልባ አድርገዋል፡፡ ህፃናቶቻቸውን ያለ አባት እንክብካቤ እንዲያድኑ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሽብር ቡድኑ የዜጎች ዋስትና የሆነውን የፍትህ ስርዓት ለጊዜያዊና ለርካሽ የፖለቲካ ጥቅም እንዲያውል ተባብሯል፡፡ በዚህም የሚ/መ/ቤቱ የህዝብን ደህንት አደጋ ላይ በመጣል የፍትህ ስርዓቱን ለጥቂት የሽብር ቡድኑ አባላት ፖለቲካዊ ጥቅም በማዋሉ እና ለሽብር ድርጊት ከለላና ሽፋን በመስጠቱ በሽብር ድርጊት ተባባሪነት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(2) እና 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡ 9ኛ. ተከሳሽ የኢ.ፌዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሽብር ቡድ በረጅም ጊዜ እቅዱ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማኮሰስ በሚያደርገው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴርን ሲጠቀም የሚስቴር መስሪያ ቤቱ ለሽብር እቅዱ ስኬት በፈቃደኝነት ተባብሯል፡፡ ተከሳሹ የእምነት ነፃነትን የሚቃረን የተማሪዎች ደንብ በማርቀቅ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን በማያደናቅፍ ሁኔታ የሚተገብሯቸውን ኃይማኖታዊ ስርዓቶች ለማገድ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም የእስልምናም ይሁን የክርስትና እምነት ተከታዮችን ከኃይማኖተኝነት በማራቅ ለሽብር ቡድኑ አጎብዳጅ ትውልድ የመፍጠር የረጅም ጊዜ የጎድንዮሽ ዓላማ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ሆን ብሎ የሽብር ቡድኑ ተባባሪ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ሽብርተኝነትን በመርዳት ወንጀል የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡ 10ኛ. ተከሳሽ የኢ/እ/ጉ/ጉባኤ (መጅሊስ) የሽብር ቡድኑ ኃይማኖታዊ ሽፋን ሰጭ ተቋም በመሆን ከ1992 ጀምሮ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግና የሽብርተኝነት ድርጊትን ሲረዱና ሲተባበር ቆይቷል፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ስልጣን የተቆናጠጡ አባላቶቹ ህገ-ወጥ ምርቻ በማድረግ ህዝበ-ሙስሊሙ ባስሰጣቸው ውክልና ያለፈቃዱ ሲመሩት ቆይተዋል፡፡ ተቋሙ የ1ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት አንድ ቢሮ በመሆን የመንግስት ባለስልጣናት በተለይም 13ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በቀጥታ የሚያዙት በኃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ዓላማ የሚራመድበት ተቋም እንዲሆን ፈቅዷል፡፡ የህዝብን አደራ ወደ ጎን በመተው የመጅሊሱ አመራሮች በከፍተኛ ምዝበራ በመዘፈቅ ከሐጅና ዑምራ ጉዞ የሚገኘውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለግል ጥቅማቸውና አክራሪ አስተሳሰባቸውን ለማስፋፋት ተጠቅመዋል፡፡ በተጨማሪም በምዝበራ የተገኘውን ገንዘብም ለ6ኛ ተከሳሽ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት በማካፈል የህዝብን ንብረት ህገ-ወጥ ዓላማን ለማስፈፀም አውለዋል፡፡ ያስመጣውን አህባሽ የተሰኘ አስተሳሰብ በኃይል በመጫን የእምነት ነፃነትን ተቃርነዋል፡፡ ተቋሙ ከ7ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመሆን የግዳጅ ስልጠናዎችን አዘጋጅቷል፡፡ በ8ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ስር ከሚገኙ የፍትህ ቢሮዎች ጋር በመተባበር በግዳጅ ስልጠናዎች ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑና ከአክራሪ አስተሳሰባቸው ውጭ የሆኑ የመስጅድ ኢማሞችን አባርረዋል፤ በምትካቸውም ምዕመናኑ የማፈልጓቸውን ኢማሞች ሾመዋል፤ በህዝብ በተመረጡ የመስጅድ ኮሚቴዎች የሚተዳደሩ መስጅዶችን ከ6ኛ ተከሳሽ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ጋር በመተባበር ከህዝብ በኃይል ነጥቀዋል፡፡ “መንግስት የሾማቸውን ኢማሞች ተከትለን አንሰግድም” በማለት ስግደታቸውን ለብቻቸው የከወኑ ምዕመናን ለእስርና እንግልት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆነዋልል፡ በአጠቃላይ ተቋሙ የሽብር ቡድኑ (ህውኃት/ኢህአዴግ) በህዝበ-ሙስሊሙ ላይ የፈፀማቸውን የሽብር እንቅስቃሲዎች ኃይማኖታዊ ቡራኬ የሰጡ በመሆኑ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡ 11ኛ. ተከሳሽ የፌ/ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ) የሽብር ቡድኑ ቶርቸር እና ማውጣጫ (Inquisition) ክፍል ሆኖ አገልግሏል፡፡ ዜጎች ያልፈፀሙትን ወንጀል እንዲናዘዙ የአዕምሮ፣ የስነ-ልቦና የአካል ቶርቸር በማካሄድ የሀሰት ሰነድና ማስረጃ በማቀነባበር ከ8ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሀሰት ክስ በመመስረት ንፁሃንን ወንጅሏል፡፡ ያልተፈፀመ ወንጀልን በማውጣጣት ሂደትም እጅግ ኢ-ሰብአዊ የምርመራ መንገዶችን በመጠቀም በከሳሾች ላይ ከፍተኛ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የክፍሉ አባላት የሽብር ቡድኑ የሚፈፅማቸውን የሽብር ድርጊቶች ለመደበቅና ከለላ ለመስጠት ሆን ብለው ንፁሃን ላይ አሰቃቂ ድብደባና የማሰቃያ መንገዶችን በመጠቀም ሽብር የተፈፀመው በእነኝህ ንፁሃን መሆኑን ለማስመሠል ከሞራል ህግጋትም ሆነ ከህገ-መንግስት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የተቃረኑ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈፅመዋል፡፡ ተቋሙ በሀሰት በሚወንጅላቸው ንፁሃን ላይም የሀሰት ምስክሮችን በማዘጋጀት፣ በማባባል፣ አሊያም በማስፈራራት የሽብር ድርጊቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረጉ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(1)(ሀ)፣5(2) እና 10(1)(2) የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል ተከሷል፡፡ …ክፍል አምስት ይቀጥላል…