ትግላችንን የበለጠ ተደራጅተን እንቀጥላለን! ድምፃችን ይሰማ
ድምፃችን ይሰማ #Ethiopia #EthioMuslims #EthioMuslimsPeacefulStruggle
ትግላችንን የበለጠ ተደራጅተን እንቀጥላለን!
ነገ ሐሙስ ሐምሌ 30/2007 የመጀመሪያውን የግንዛቤ ማዳበሪያ እና ለተጠናከረ የትግል ሂደት ግብዓት የሚሆን ውይይት እናደርጋለን!
ረቡእ ሐምሌ 29/2007
አምባገነኑ የኢትዮጵያ መንግስት ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ያለው ንቀት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ቁልጭ አድርጎ በሚያሳይ ሁኔታ በገዛ ሕዝቡ ላይ እየፈጸመ ያለውን ኢ-ሕገ መንግስታዊ በደል አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙም በትግሉ እንደሚቀጥል ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ሲያሳይ ቆይቷል፡፡ የወኪሎቻችን የግፍ ፍርድ ተጨማሪ የትግል ተነሳሽነት ምንጫችን ሆኖ መቀጠሉ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ወቅቱን እየጠበቀ ከእርከን እርከን ሲሸጋገር የቆየው ትግላችን የወደፊት ጉዞውን በበለጠ መደራጀት ላይ የመሠረተ ይሆናል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙም ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የሚያወጣቸውን ወቅታዊ መርሃ ግብሮች ሁልጊዜ ሳይጠብቅ ለትግሉ የወጡ አቅጣጫዎችን እና የእንቅስቃሴውን መርሆች መሰረት ባደረገ መልኩ ትግሉን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ለትግበራ የሚወጡ መርሃ ግብሮች እና አፈጻጸማቸውም በተለያዩ ግለሰቦችና ስብስቦች ተነሳሽነትና ፈጠራ የሚታገዝ ይሆናል፡፡ ይህም ዘርፈ ብዙ እና ጫና ፈጣሪ፣ እንዲሁም ወደሌላ ቦታ በቀላሉ ሊዛመቱ የሚችሉና መንግስትም ሊቆጣጠራቸው የሚያስቸግሩ እንቅስቃሴዎችን ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ከዚህ በፊት እንደጠቀስነው ህዝብ ውስጥ ያለ የተለያየ ችሎታና አቅም አለ፡፡ በዲናዊ እውቀት፣ በትምህርት፣ በገንዘብ፣ መረጃ በማግኘት፣ መረጃ በማዳረስ፣ ሃሳብ በማፍለቅ፣ በማደራጀትና በመሳሰሉት ትልቅ ኃይል አለው፡፡ በመሆኑም ይህንን እምቅ ሐይል ይበልጥ ወደተግባር የሚቀየርበትን መንገድ መከተል ይኖርብናል፡፡ ህዝባዊ መሰረት ያለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የተጠናከረ ህዝባዊ መዋቅር ያስፈልገዋል፡፡ በመሆኑም ለመደራጀት አመቺ የሆነ ዘርፍ በመምረጥ (በመኖሪያ ሰፈር፣ በስራ ቦታ፣ በሙያ ወዘተ) ውስን የአባላት ቁጥር ያለው አደረጃጀት እንፈጥራለን፡፡ አስቀድሞ የተደራጁ ስብስቦች ስራ ላይ ባሉባቸው ቦታዎች እንደአዲስ ከማቋቋም ይልቅ የበፊቱን የማጠናከር እና የማነቃቃት ስራ ብቻ ይሰራል፡፡ በዚህ መልኩ የምንፈጥረው ህዝባዊ ስብስብ ጊዜያዊ ብቻ ሳይሆን ዘለቄታዊ ስራን ለመስራት የሚያስችል መሰረት እንደመሆኑ መጠን ነገ ሐሙስ ሐምሌ 30 የመጀመሪያውን የግንዛቤ ማዳበሪያ እና በቀጣይ ለተጠናከረ የትግል ሂደት ግብዓት የሚሆን ውይይት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ውይይቱን የምናካሂደው ከ5 ሰዎች ባልበለጠ ስብስብ ሲሆን ለዚህም የምናውቃቸውን እና የምናምናቸውን ሰዎች ብቻ በመምረጥ እንንቀሳቀሳለን፡፡ ለውይይቱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ከመንግስት ደህንነቶች፣ ከውስጥ ሰላዮች፤ ከስልክ ጠለፋና ከአህባሽና መጅሊስ አቀንቃኞች በተሰወረ መልኩ ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በነገው እለት የሚደረገው ውይይት የሚከተሉትን ነጥቦች መዳሰስ ይኖርበታል፡- • አሁን ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል? • የአባላቱ ችሎታና አቅም ምንድን ነው? • አባላቱ ለትግሉ ሊያበረክቱ የሚችሉት የትግል ስልት ምንድን ነው? • ይህ የትግል ስልት በስራ ዝርዝር ሲገለፅ ምን ውጤት እንዲያመጣ ታስቧል? • ይህንን ስራ ለመስራት ምን ምን ያስፈልጋል? • የታሰበው ስራ በቡድኑ አባላት ብቻ የሚፈፅም ነው ወይስ ከፍ ያለ አደረጃጀት ይጠይቃል? ማሳሰቢያ • አስፈላጊው የደህንነት ጥንቃቄ ይደረግ፤ • ከመንግስት ደህንነቶች፣ ከውስጥ ሰላዮች፤ ከስልክ ጠለፋ እና ከአህባሽና መጅሊስ አቀንቃኞች እንጠንቀቅ፤ • ስለስራው ሃሳብ ስራው ሳይሰራ ለሌላ ሰው ከማስታወቅ ፈፅሞ እንቆጠብ፤ የውይይቱን ውጤት በነገው እለት በኢንቦክስ መላክ አንርሳ! የወኪሎቻችን ፍርድ ተጨማሪ የትግል ተነሳሽነት ምንጫችን ሆኖ ይቀጥላል!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ! አላሁ አክበር!
