የፖለቲካን ፍርድ አንቀበልም! (ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽ)

የፖለቲካን ፍርድ አንቀበልም! ( ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽ )

በኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ በዛሬው እለት ማለትም ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2007 እኢአ (August 3, 2015) የሰው ልጅ ሊሸከመው ቀርቶ ለመስማትም የሚሰቀጥጥ የታሪክ ጠባሳ የሆነ ብይን በወያኔ አገዛዝ የሚታዘዘው ፍርድ ቤት አስተላልፏል። ምንም ወንጀል ባልሰሩት ንፁሀን ኮሚቴዎቻችን ላይ አሳፋሪና አስደንጋጭ የረጅም ጊዜ እስራት ተበይኗል።
ኮሚቴዎቻችን በአሸባሪነት በውሸት ተወንጅለው ላለፉት ሶስት አመታት በእሰር ሲሰቃዩ የኖሩት ሳይበቃ ለ 22 ዓመት እንዲታሰሩ የተሰጠው ብይን ትግሉን የሚያስቆም ሳይሆን ይበልጥ እንዲቀጣጠል የሚያደርገው መሆኑን ዘረኛው የወያኔ መንግስት ሊያውቀው ይገባል።
አሸባሪነትን ከለላ በማድረግ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያወናብደውና የሚዘርፈው የወያኔ መንግስት በወኪሎቻችን ላይ የወሰደው ከባድ ፍርድ መቀጣጫ እንዲሆን ቢታሰብም መላው የኢትዮጵያ ሙስሊም ህብረተሰብ ይበልጥ እንዲታገል የሚቀሰቅሰው ትልቅ ሀይል መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው።


ሰላም ወዳድ ወገኖቻችን ፍትኅ ከትግል በኋላ የሚገኝ ምንዳ መሆኑን ሳንዘነጋ በእንድነት ለተነሳንበት የተቀደሰ ዓላማ ተግተን መስራት እንዳለብን የወያኔ እኩይ ተግባር ያስገነዝበናል። በአገራችን በተለያዩ ዓመታት በርካታ አምባገነን ነገስታት ተስተውለዋል። ሁሉም ግን በተጣመረ የህዝብ ትግል ተንደዋል። የወያኔም እጣ ፋንታው ከዚህ የተለየ አይሆንም። ከዚህ የወያኔ ግፍ አገዛዝ የምንላቀቀው ተግተን ስርዓቱን ስንታገል ብቻ ነው። ሰላማዊ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል።


የህዝብ ብሶት የፈጠረው ድምፃችን ይሰማ የተሰኘው ንቅናቄ ዛሬ የተፈረደባቸውን 18 መሪዎቻችንን አፍርቶልናል። የታሰሩለት የተሰቃዩለት መስዋዕትነት የከፈሉለት እንቅስቃሴ በኛ በወንድሞቻቸው የተባበረ ክንድ እስከ መጨረሻው እንደሚቀጥል ልናበስራቸው እንፈልጋለን። ኢንሻ አላህ!

ትግላችን እስከ ድል ድረስ በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ፍትሕ ለሁሉም ወገኖቻችን!!
አሏሁ አክበር!!!

ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን
ዋሽንግተን ዲሲ