ትግል በጥበብ የተሞላ መንገድ ነው! ከስሜታዊነት እንቆጠብ!!! (የሱፍ ጌታቸው/FB)
ከተመክሮ ሁሉ ጥንቃቄን የሚፈልግ ተመክሮ የትግል ተመክሮ ነው፡፡በቂ ዝግጅት ማጣት አንድም ንዝህላልነት፣ አንድም አቅለ-ቢስ መሆን ነው ከማለት በስተቀር ምን ትርጓሜ ይኖረዋል? ራስን ለክፍፍል ማጋለጥ፣ የራስን ችግር ራስ አለመፍታት፣ የተፎካካሪን ስልትና ስትራቴጂ አለማስላት፣ የህዝብንና የሀገርን ፍላጐት አለማስቀደም፣ የመንገዶችን ኮረኮንችና ሊሾነት አለመለየት አባዜዎች ሁሌ እንደተፈታተኑን አሉ፡፡
ጠንካራነትን ብቻ ሳይሆን ደካማነትንም መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡ ደካማ ከሆንክ በማታሸንፈው ጦርነት ውስጥ ለክብርህ ብለህ አትዋጋ፡፡ ይልቁንም ማፈግፈግን እወቅ፡፡ ማፈግፈግ ጊዜ መግዛት ነው፡፡ ማገገሚያ ነው፡፡ ቁስልህን ማከሚያና ባላንጣህን ማዳከሚያ ነው፡፡ ቁልፉ ነገር ማፈግፈግን የኅይል ማፍሪያ መሳሪያ ማድረጉ ነው!
ጉዞን በረዥሙ ማቀድ ሌላው የብልህነት ስልት ነው፡፡ “ዛሬ ካልተሳካ ሞቼ እገኛለሁ” ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው! አጓጉል ፍዘትም ስስ ብልት መስጠት ነው፡፡
ፖለቲካ ማመዛዘንን፣ ጊዜ-መግዛትንና ፍጥነትን መሰረት የሚያደርግ “ሸቃባ ሚዛን” ነው ይባላል፡፡ ይሄን ልብ ማለት ግድ ነው፡፡ “ታሪክ ባሸናፊዎች የሚፃፍ ተረት ነው!” የሚባለውንም አለመርሳት ነው፡፡ ሁሉም መስዋእትነት ይጠይቃል፡፡ መስዋእትነት እንደ ዴሞክራሲ ሁሉ ገጠመኝ አይደለም፡፡ ቀድመው መሰረትና እሳቤ የሚያበጁለት ነው፡፡“አንተኛም ካላችሁ እንገንድሰው = መኝታ እንደሆነ ቀርቷል ካንድ ሰው!” እያልን የምናላዝንበትም ከቶ አይደለም፡፡ ሂደት ነው፡፡ መቀጠል አለበት፡፡ዝምታ እንኳ መስዋእትነት የሚጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡
ትግል በጥበብ የተሞላ መንገድ ነው! ካልበሰሉ በድፍረት ብቻ የሚወጡት የወጣት ስሜታዊነት ዘመቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እንደ ፋሽን በወረት የሚያሸበርቁበት የገና ዛፍም አይደለም፡፡ ከጀመሩ በኋላ “ፉርሽ ባትሉኝ!” የሚባልበት ጨዋታም አይደለም! “ሰይ ብል ባንከረባብት” እያሉ ያሹትን የሚያጭዱበት ቁማርም መሆን የለበትም! “አርፋ ስጠኝ”፣ “አቫንስ ስጠኝ” እያሉ የሚጠባበቁበት አይደለም፡፡ ትግል መሰረቱ የፖለቲካ ክህሎት ነው፡፡ ያልተነገረ ያልተሰማ ነገር የለም፡፡ ከአንጃ እስከ ዋና መስመር፣ ከቀኝና ግራ መንገደኛ እስከ አምስተኛ-ረድፈኛ፣ ከውጪ ወራሪ እስከ ውስጥ ቦርቧሪ፣ ከአናርኪስት እስከ ዘውድ-ናፋቂ፣ ከገንጣይ-አስገንጣይ እስከ በታኝ-ከፋፋይ፣ ከጠባብ እስከ ትምክህተኛ፣ ከአኢወማ እስከ ሊግ፣ ከአንጋፋው ፎረም እስከ ብላቴናው ፎረም…” ስርዝ የኔ ድልዝ ያንተ፣ እመጫት የሷ፣ ሆያ-ሆዬ የሰፊው ህዝብ ስንባባል በኖርንበት አገር ትግል “ሁለት አንድ ዐይናዎች ተጋብተው ሁለት ዐይን ያለው ልጅ ወለዱ፡፡ ምነው ቢሉ፣ አንዱን ከእናቱ አንዱን ከአባቱ!” ብለው የሚገላገሉት አይደለም!? “
ዋና የማይችል ባህር አይግባ፤ ትግል የማይችል ልፊያ አይውደድ” የሚባለው ተወዶ አይደለም፡፡ እሙናዊውን ዓለም እናጢን!
ሁሌ ልጅ አንሁን- ልብ-እንግዛ!
