ወገኔን ታዘብኩት… ትዝብቴ ለሚሰደዱ! (ሶሎሞን አ.)
ኢትዮጵያዊ ተዋዶ፣ ተዋልዶና ተዛምዶ ኖሯል ለዘላለምም ይኖራል!
እንዳትሰደድ የሚለውን የወዳጅ ዘመድ ምክር ችላ ብለህ ብትሰደድ ከሁሉ በላይ ሕውሓትን አስደስተህ አንተም ይብዛም ይነስም ችግር ውስጥ ለመባዘን ተዘጋጅ። ከዲያስፖራው ወገን ጋዜጠኛ ወይ ባለጠጋ ካልሆንክ ስለተሰደድክ እምቢልታ አይነፋልህም፣ ነጋሪት አይጎሰምልህም። በስደትህ ምክንያት ስለአገርህ የዲሞክራሲና የነፃነት ዝቅጠት አይነገርም፣ አይወራም ወይም አይፃፍም። እንደዘበት በአንድ ውድቅት ሻንጣህን አንጠልጥለህ ትወጣለህ። ባንተ መሰደድ ምክንያት ስለተደሰተው መንግስትህ፣ ስለተዳከመው ትግል፣ ስለፈረሰው ትዳርህ፣ ስለተበተነው ንግድህ፣ ስለተቋረጠው እቁብህ፣ ስላልተከፈለው እድርህ፣ ስለተጓጎለው ማህበርህ በቅርብ ከምታውቃቸው ሰዎች ውጪ ማንም አያውቅልህም ያንተን መከራ ማንም አያግዝህም። አንድ ኢትዮጵያዊ ተሰደደ አልተሰደደ ምን ለውጥ ሊያመጣ አይነት የዲያስፖራ ፖለቲካ አፉን ከፍቶ ይጠብቅኃል።
ወዴትኛውም የምድር አቅጣጫ ብትሰደድ፤ ባገር ልጅ የተቋቋሙ እጅግ ብዙ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችን ታገኛለህ፣ ካገር ከወገን ተለይቶ ብዙ በመኖር ምክንያት ብዙ ነገር የዘነጉ አንተም የዘነጋኃቸውን ጨምሮ። ካገር ከወገን ተለይቶ ብዙ በመኖር ኢትዮጵያዊ ወዛቸውን ያሟጠጡ በርካታ ወገኖችህን ታገኛለህ። በወያኔ እጅ መርዘም ምክንያት በነፃነት ምድር ላይ ነፃ ያልወጡ በርካታ ወገኖችህን ትቀላቀላለህ። በፖለቲካ ምክንያት ተሰደድኩ ግን ደግሞ ፖለቲካ አያገባኝም የሚሉ እጅግ ብዙ ሰርቶ አደር ቢጤዎችህን ትተዋወቃለህ። በቋንቋህ የሚናገር፣ በባሕልህ የሚያስብ፣ እንጀራ በበርበሬ አዘውትሮ የሚመገብ ትንሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግመህ መኖር ትጀምራለህ። እንዲህም ሆኖ ግን በጥቂት አገር ወዳድ ወገኖችህ ሞቅ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በዲያስፖራው ውስጥ መኖሩን ትመለከታለህ። ይህ የዲያስፖራው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያለ አገርቤት አይደምቅም እስከምትል ድረስ አብሮ ሲሞቅና ሲከስም ለማየት ተዘጋጅ። ምንም እንኳን መምረጥም መመረጥም የሚችላው ሕዝብ አገር ቤት ቢኖርም በኢትዮጵያ ውስጥ አንጻራዊ ለውጥ ለማምጣት ለሚታገሉ ማናቸውም የፖለቲካ ድርጅቶች የዲያስፖራው ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ይህንንም ለመረዳት የሚከተሉትን ጥቂት እውነታዎች በአንድ አቅጣጫ የነበረውን እንቅስቃሴ ብቻ እየጠቀስኩ ላስታውስህ።
በምርጫ 97 ወቅት ለምርጫው የተለየ ገፅታን ያላበሱት ሁለት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ሕብረት እና ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲዎች ነበሩ። የ97 ምርጫ ሊደርስ ወራቶች ሲቀሩት ከተመሰረተው ከቅንጅት በፊት ከፍተኛ ድጋፍ የነበረው ሕብረቱ የተመሰረተው በዲያስፖራው ሆድ ውስጥ ነበር። ነገር ግን ከምርጫው ቡኃላ በተነሳው ወደ ፓርላማ የመግባትና አለመግባት ውዝግብ ምክንያት ሕብረቱ በተነፈገው የዲያስፖራ ድጋፍ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲገባ ተገዶ ነበር።
የቅንጅቱ የአገር ውስጥ እንቅስቃሴ በጉልህ ፍሬ ማፍራት የጀመረው ምርጫ 97 ሁለት ወራት የሚጠጋ ጊዜ ሲቀሩት ዶ/ር ብርሃኑ ወደ አሜሪካ አቅንተው ስለቅንጅቱ አጠቃላይ ገለፃ አድርገው ባሰባሰቡት ድጋፍ ነበር። በዚህም በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ባገር ውስጥ ያለውን ሚና ትገነዘባለህ።
ቅንጅት ሲሰነጣጠቅ የክፍፍሉ መንስዔ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ቅንጅት አለምዓቀፍ መሆኑን ካልረሳህ ዲያስፖራው ለአገርቤት ፖለቲካ ያለውን ወሳኝነት ትገነዘባለህ።
ምንም እንኳን የመያድ ሕግ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተረቆ በስራ ላይ ቢውልም እነዚህን ከመንግስት ቁጥጥር ነፃ የሆኑ ድርጅቶችን በመምራትና አብሮ በመስራት አገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከታተል የዲያስፖራው ድርሻ ከፍተኛ ነበር።
ከሚያዚያ 30 1997 ወዲህ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገህ አገራዊ ስሜትህን ድምፅህን አሰምተህ እንደማታውቅ ግልፅ ነው። ስትሰደድ ከሚገጥሙህ ጥቂት ጥሩ ነገሮች ውስጥ አንዱ የሰልፍ ናፍቆትህን እዚህ ለመወጣት መቻልህ ነው። አገርቤት የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ሲታሰሩ፣ ገዜጠኞች ሲታሰሩ፣ መሬታችን ሲቸበቸብ፣ የተለያዩ የህብረተሰቡ አካላት በመንግስት በደል ሲደርስባቸው የታፈነውን የአገር ውስጥ ጩኅት የሚያሰሙት በውጭው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም በውጭ መንግስታት ፊት የዲሞክራሲን ጭምብል አጥልቆ ለአመታት ሲሞካሽ የነበረውን የመለስ መንግስት ማንነቱ እንዲገለፅ የተሳካም ያልተሳካም ተቃውሞ በማሰማት ዲያስፖራው አገሪቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ጥሯል።
ስለዚህ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የዲያስፖራው ሚና የማይናቅ ቢሆንም አሁን የሚጠብቅህ የዲያስፖራው የማይጨበጥ ችግር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እያሰለቸ ይገኛል። ይህንንም ስለተሰደድክ እንደልብ ከምታገኛቸው የመገናኛ አውታሮች ትገነዘባለህ። ባገርቤት ኢቲቪና ጥቂት የሬድዮ ጣቢያዎች በሕውሓት ተይዘው ያሻቸውን እንደፈለጉ ይናገራሉ ስለሆነም ህፃናትና ወጣቶች ውሸትን፣ ዘለፋንና ስድብን እየተማሩ እውነትን ሳይሰሙ እያደጉ ይገኛሉ። ወደዚህ ከመጣህ ነገሩ ለየት ይልና ለሶስት የተከፈለ ቡድን ያጋጥምኃል። የምታውቀውን አይነት ዘለፋና ስድብ ካማረህ የመጀመሪያውን ቡድን ኢቲቪንና ኢቲቪን የመሰሉ ጥቂት ድረ-ገጾችን ፈልገህ መክፈት ትችላለህ፣ ከዚህ በጣም በትንሹ ለየት ያለ ስድብ ከፈለክ ሁለተኛውን ቡድን ማለትም የተወሰኑ የፖለቲካ ሃይሎች የሚያሥተደድሯቸውን ድረ-ገጾችን ከፍተህ መዳሰስ ይጠበቅብኃል። ሶስተኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን የሚያከብሩ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ያላቸው ሲሆኑ በተለያየ ቋንቋ የሚፅፉ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ስለምታውቃቸው ላይገርምህ ይችላል ሁለተኞቹ ግን ከተቃዋሚ ወገን ሆነውና ያደረ ስማቸውን ይዘው የሚንገታገቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሆኑ የተፈጠሩበትን ነገር አለም ዘንግተው የተሳካለት የመሰላቸውን ቢጤያቸውን ሲሰድቡ፣ የገዛ ጓደኞቻቸውንና ሻል ያሉ ፖለቲከኞችሕን ሲዘልፉ፣ ከግለሰብና ከነጋዴ ጋር ሲነታረኩ፣ ኢሳትንና በሥነምግባር የሚመሩ ድረ-ገጾችን ሲያብጠለጥሉ ታነባለህ።
ኢሳት ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ገጸ-በረከት ነው። ዲሞክራሲና መልካም አስተደደር በሰፈነበት አገር ላይ እንደኢሳት አይነት የሚዲያ ተቋማት እንደአራተኛ የመንግስት ተቋም ተቆጥረው አገልግሎት ሲሰጡ ይታያል። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ነፃ ተቋማት ባልተፈጠሩባት አገር ደግሞ ኢሳትን የመሰሉ ተቋማት እንደሁለተኛ መንግስት ያገለግላሉ። የመንግስት ተቋማት የሚባሉት ማለትም ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ ሲሆኑ ሁሉም ከአራት ኪሎ በሚከፋፈልባት ኢትዮጵያ ላይ ኢሳት የሕዝብን ጩኸት ለማሰማት ብቸኛው አማራጭ ነው ድርጅቱም እያደረገ ያለው ይሕንኑ ነው። ሙያዊ ስነምግባራቸውን በጠበቁ በጥቂት ብርቱ ጋዜጠኞች አማካኝነት የሕዝብ ብሶት ወደሕዝብ እንዲደርስ ማድረግ፣ ለማንም ሳይወግኑ ግን አገርን የሚያጠፉትን ማጋለጥ፣ የተበላሸውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲስተካከል ለማገዝ የመንግስትን የተሳሳተ መንገድ መተቸት(መንግስት ብቻ አጥፊና አልሚ በመሖኑ ምክንያት)፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቅ፣ ብሄራዊ እርቅ እንዲኖር መሻት፣ አንድነትን መስበክ ፣ ስለአገሪቱ ያለውን እውነታ መዘገብ ከኢሳት እስካሁን ያየነው ሂደት ነው።
በበኩሌ በጣት የሚቆጠሩት ኢሳቶች የሚሰሩትን አይቼ ተገርሜአለሁ። የገዘፉ ውሸቶችን ለመዋሸት ብዙ አቅም እንደሚጠይቅ ለማወቅ ከፈለግህ ኢቲቪን ከኢሳት ማወዳደር ብቻ ይጠበቅብሃል። ከኢቲቪ በገዘፈ ሕንፃ፣ በገዘፈ በጀት፣ በበርካታ የሰው ሃይል በየቀኑ ውሸትን ትሰማለህ። ኢሳት ግን ኢምንት ሆነው እኛን እልፎችን ከቤታችን ተቀምጠን ያለምንም ልፋትና ብርበራ ስለአገራችን እውነተኛና በቂ መረጃ እንዲኖረን ያደረገ የሚዲያ ተቋም ነው። እየተዋረደ ያለውን የኢትዮጵያዊነት ስብእና ለመጠገን ድርጅቱ የሚያደርገውን ጥረት፣ እየጠፋች ያለችውን አገር ለመታደግ የሚያደርገውን ትግል፣ በየስርቻው በኃፍረት ማቅ ለብሰው ያጎነበሱትን ወገኖች ቀና እንዲሉ የሚያደርገው ትጋት፣ ኢትዮጵያ የወላድ መካን አለመሆኗን ልጆቿን ከያሉበት እያወጣ ለማስተዋወቅ የሚሄድበትን መንገድ ለተመለከተ ቅን ሰው ኢሳትን ለጥፋት የተቋቋመ ድርጅት ለማለት መድፈሩ ያስገርምኃል። ኢሳት ነፃና ገለልተኛ ነው፣ ይህ ማለት ደግሞ ኢሳት የሚደግፈው የፖለቲካ ድርጅት የለም ማለት ነው እንጂ የተበላሸን አገራዊ ችግር አይተችም ማለት አይመስለኝም፣ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በኢሳት አይቀርቡም ማለት አይመስለኝም። ኢትዮጵያዊነትን ማጉላት፣ አንድነትን መስበክ፣ ነፃነትን መሻትና ማኃላፊነትን ለመወጣት ጥረት ማድረግ ከኢሳት የምታያቸው እሴቶች ናቸው።
በሚገርም ሁኔታ ይሕንን በጥቂት ኢትዮጵያዊነት በሚሰማቸው ወገኖችህ የተመሰረተ አንድ ምርጥ ስጦታ ከራዲዮ ሚሊ ኮሊንስ የሚያመሳስሉ ሰዎች ብቅ ብለውልኃል። እስቲ ስለዚህ ራዲዮ ጣቢያ ላስታውስህና ስለኢሳት ከነገርኩህ ጋር እያዛመድክ ተዝናና። ሚሊ ኮሊንስ የሩዋንዳ ሬድዮ ጣቢያ ነው፤ ሚሊ ኮሊንስ ሲተረጉሙት የሺህ ትራሮች ምድር ማለት ነው አሉ። በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ወቅት ሁቱዎች በቱትሲና በለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ ላደረሱት ጭፍጨፋ ሚሊ ኮሊንስ የተባለው ሬድዮ ያሰራጨው መርዘኛ ቅስቀሳ ባጠቃላይ ካለቀው ሕዝብ 10%ቱን ወይም ወደ 45 ሺ ለሚጠጋው ሞት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። አቶ መለስ በምርጫ 2002 ከመደረጉ ከሶስት ወራቶች በፊት የአሜሪካ ሬድዮ ጣቢያን በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ወቅት አሰቃቂው ጭፍጨፋ እንዲቀጣጠል ምክንያት ከሆነው ከሚሊ ኮሊንስ ሬድዮ ጋር አመሳስለውት ነበር። በወቅቱ የቪኦኤን የአዘጋገብ ስልት ኮንነው ሊሸብቡት እየተዘጋጁ መሆናቸውን መለስ አስታውቀው ነበር።
ታዲያ ይሕን ንፅፅር ምን ትለዋለህ? “ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል” ነበር የሚሉት አሮጊቷ የልጅነት ጎረቤቴ? ሴት ስለሆኑ በወንድ መተረት ይወዱ ነበር። ወሬ መጠረቅ ይችሉበታል፤ ያውም በተረትና ምሳሌ እያዋዙ፣ በታሪክ እያስደገፉ። ያኔ አንድ ትልቅ ቤት ውስጥ ለብቻቸው ይኖሩ ነበር። ዘወትር የሚቀመጡባት አንድ የጠፍር ወንበር ነበረቻቸው። ሲቀመጡ ቤቱንም ውጭውንም ለመቆጣጠር እንዲመቻቸው አድርገው አይን የሆነ ቦታ ላይ ነው። ወሬ እንዲያመልጣቸው ስለማይፈልጉ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በዚች በርጩማ ላይ ተቀምጠው ወደ ውጭ እያዩ ይውላሉ። አላፊ አግዳሚውን ሲታዘቡ። ድምፃቸው ስለሚያምርና ከሩቅ ስለሚሰማ የሚሰሩ ሰዎችን ሲያርሙ፣ የሚጫወቱ ልጆችን ሲቆጡ፣ በሚልከሰከሱ እንሣትን ሲዝናኑ፣ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም ዛሃርምስኬ ሲሉ ይውሉ ነበር።
አሮጊቷ ከሁለት አስርት አመታት በፊት ነበር ይህን አይነት ያአኗኗር ስልት ይከተሉ የነበረው ነገር ግን ይህ የኑሮ ሂደት ተቀይሯል ብለህ ካሰብክ መሳሳትህን እነግርሃለሁ። ልክ ካገርህ ስትወጣ የሚቀበልህ ዲያስፖራ ከጥቂቶቹ በስተቀር ያሮጊቷን በርጩማ በተሽከርካሪ ወንበር ቀይሮ፣ ከፊቱ ኮምፒውተሩን ገርግዶ፣ ማይኩን ከጆሮው ደንቅሮ የጥቂቶችን የስራ ውጤት ሲያመክን፣ ጥሩ የሰራን ሲቆጣ፣ በቀልድና በቧልት ሲዝናና፣ የወሬ ሱሱን ከፌስ ቡክ ወደ ፓልቶክ ወደ ስካይፒ ካንዱ ወዳንዱ እየዘለለ ሲዘላብድና ሲያናሽር ታያለህ ። በተደላደለ ሶፋ ላይ ተቀምጦ የርቀት መቆጣጠሪያውን ከጁ ላይ አጣብቆ ከቻናል ወደቻናል እየዘለለ አገር ወገኑን የረሳ፣ ስልክ ከጆሮው ሳያወርድ ለምግብና ለፅዳት እንኳ ጊዜ ያጠረው፣ አገር አገር የሚሉትን ጥቂቶችን ሲያነቅፍ ስታይ ኢትዮጵያዊው ወገንህ ካገር ወጥቶ ሳይቀየር መገልገያ እቃው ብቻ እንደተቀየረ ትታዘባለህ።
አንዳንድ ፍረጃዎችና ክሶች ከምን ተነስተው እንደሚደመጡ ባይገባህም ስራ ማጣት ወይም ልምድ እንዲመስሉህ ትገደዳለህ። በመሰረቱ የኢትዮጵያን ታሪክ በቁንጽል መዘርዘርና ቁንፅል ታሪኳንም የፖለቲካው ግንድ ለማድረግ መድከም የራድዮኑን ግብር መድገም ነው። አሉባልታን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማጠንጠኛ አስመስሎ ማቅረብ ራዲዮ ሚለ ኮሊንስን መሆን ነው። ታሪክን በመርዝ እየለወሱ ማቅረብና ፖለቲካውን ወደ ዘር ፖለቲካ እንዲዞር መርዳት ምን ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም ስለሆነም እንዲህ የሚያደርጉትን ግለሰቦችና ድርጅቶች ከራዲዮ ሚሊ ኮሊንስ ጋር ማነፃፀር ያባት ነው።
ነገር ግን ኢሳትና ተሰዳቢዎቹ ድረ-ገጾች እርስ በርሱ የተከባበረ ኢትዮጵያዊን ለመፍጠር እንጂ የዘር ፖለቲካን ሲያራግቡ አልታዩም። ከምን ተነስተው ለመሳደብ እንደደፈሩ ግርም ይልሃል። የሚገርምህ ደግሞ ካለማወቅ ነው እንዳትል አብዛኞቹ ተምረዋል። መማር ማወቅ ነው፣ እውቀት አይንን ይከፍታል፣ ለህሊና ብርሃን ይሆናል። እውቀት ለእውነት አሳልፎ ይሰጣል። እውነትን በተከፈተ አይን ማየት ደግሞ ለነፃነት እንጂ ለማላከክ አይተጋም። እውነቱን ማየት ካቃታቸው ውሸትን፣ ስድብንና ፍረጃን ግን ማስወገድ ነበረባቸው። አንዳንዴ በምድራዊ እውቀት ጨቅላነት ምክንያት ሰው እምነቱን ወይም አምላኩን እንደማጣቀሻ ሊጠቀም ይችላል። ሃይማኖትና ሳይንስ ጠላቶች አይደሉም። ምድር ሁለቱንም ተጠቅማባቸዋለች፣ ሁለቱንም ትፈልጋቸዋለች። ኢሳት የሕዝባችንን መከራ አይተው በተነሱ በጥቂቶች እርዳታ እየተደገፈ ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ እየተጋ ያለ የቴለቪዥን ተቋም ነው።
ዞምቢዎቹ እንደ ራዲዮ ሚሊ ኮሊንስ!
በስድብ ባላምንም ክፉ ሰው እንዳለ ግን እውነት ነው። ኢትዮጵያን የዞምቢ ምድር ያደረጓት ክፉ ሰዎች እንዳሉም ግልፅ ነው። ክፉ ሰው ለተሸከማት ጠባብ ሆድ እልፎችን ይበድላል፣ እፍኝ ለማትሞላ እድሜው ሚሊዮኖችን ያጎሳቁላል፣ ወንዝ ለማይሻገር እውቅናው ሕዝቦችን ይዘልፋል፣ የተሰጠውን ፀጋ ለጥፋት ያውለዋል፣ ለሰይጣን ያልታሰበ ክፋት ያስባል። በንደዚህ አይነት ሰዎች ምክንያት ለመነገር የሚከብዱ ታሪኮች ተፈፅመዋል፤ ንፁሓን ተጨፍጭፈዋል፣ ሕዝቦች ተሰደዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ሕፃናት ታርደዋል፣ መንደሮች ጋይተዋል፣ ተራሮች በሰው ልጅ ሬሳ ተሞልተዋል፣ ወንዞች በሰው ልጅ ደም ቀልተዋል።
ይህንን የመከራ ምድር የሚፈጥሩትን ክፉ ሰዎች ያዩ አባቶቻችን አምላክን “በእለተ አርብ ግን በከንቱ ውለሃል”ይሉታል። ይሕን ያሉበት ምክንያት እለተ አርብ አምላክ ለሰው ልጅ ሲል ስለተሰቀለ አይደለም ወይም የስራ መጨረሻም ሆኖ አይደለም ወይም ከሌሎቹ ቀኖች አርብ የተለየ ሆኖም አይደለም። ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረት የፈጠረ አምላክ በዕለተ አርብ በፍጥረታት ሁሉ የሰለጠነውን ሰውን ስለፈጠረ ነበር። በዚህ እለት እግዜሩ ሁሉን ውብ አድርጎ ፈጥሮ የፍጥረት መጨረሻ ላይ ለእረፍት እየተዘጋጀ ሰውን ፈጠረ። ይሕን በክፋትና በተንኮል የተሞላ ፍጡር ፈጠርክብን ሲሉ ነው በከንቱ ውለኃል ብለው አምላካችንን የደፈሩት። በደፈናው ሰውን ፈጠርክብን ይበሉ እንጂ ሁሉንም ሰው ማለታቸው አይመስለኝም። ክፉውን፣ ተንኮለኛውን፣ ዘረኛውን፣ ጎሰኛውንና ሰው በሰላም እንዳይኖር የሚያደርገውን ለማለት ነበር።
ታዲያ ይህን አባባልና ኢትዮጵያችንን ካሰብክ አንዳንድ ነገሮችን ራስህን መጠየቅህ አይቀርም። እንዲህ እያልክ፤ ቋንቋን እያንሻፈፉ በመተርጎም ሕዝብን ከሕዝብ ሊያቀያይሙ የሚሞክሩት የተወለዱ እለት ይሆን አምላክ የተወቀሰው? የሃሜት ማስታወሻቸውን እንደደገኛ ድርሰት ደጉሰው የተንኮል እንክርዳዳቸውን በየዋሓን ላይ የሚዘሩት የተፈጠሩ እለት ይሆን አምላክ በከንቱ የዋለው? በብሔሮች ላይ የመጨቆንን፣ የመሸነፍን፣ የውርደትን የፈጠራ ታሪክ ለፖለቲካ ትርፍ ሲሉ የሚተርኩና ይህንኑ ውሸታቸውን በሥነጽሁፍ እያስዋቡ ማቅረብና ለቂም በቀል ማነሳሳትን የእለት ግብራቸው አድርገው የሚያሴሩት የተዘሩ እለት ይሆን ፈጣሪ የተሳሳተው? እያልክ መቀጠልህ አይቀርም። እንዲህም ብለህ የዚህን አይነት ሰዎች ወዴት እንዳሉ ለማወቅ ትጋት ወይም ምርምር አያስፈልግህም። ጣትህንም ወደነሱ ብትጠቁም ማንም ተሳሳትክ አይልህም።
ለማንኛውም እንደማያዋጣ እየታወቀ ቅዱሱን ማርከስ ይዋል ይደር እንጂ ከፀፀት አያድንም። እንደዚህ አይነት ስሌቶችን ትተን የምንታገለውን ክፉ ባለጋራ በጋራ ብንገጥመው ለሁላችንም መልካም ይሆናል። ከሁሉ በላይ በድኅነት ለሚማቅቀው ወገናችን(የተሻለ ይኖራል የሚባለው አብዛኛው የአዲስ አባባ ሕዝብ ለብቻው እያወራ ይሄዳል አሉ፤ ገበሬው ደግሞ ራሱን እያጠፋልህ ይገኛል)፣ በየአገሩ ለሚደፈሩት እናትና እቶቻችን (ሸዋዬ ሞላ በሳት ተለብልባ የወገን ያለህ እያለች 3 ወራትን በቁስል እየተንገበገበች ኖራ የደረሰላት ባእድ ነበር)፣ በየበረኃውና በየባሕሩ ለሚያልቀው ኢትዮጵያዊ(በየመንገዱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆዳቸው እየተቀደደ ይበረበራል፣ ጉበት ኩላሊታቸው ይዘረፋል)፣ መጠጊያ አጥተው ለሚሸጡት ሕፃናት (የሚቀምሱት ያጡ የሰፈርሕ ሕጻናት በምግብ እየተታለሉ ይደፈራሉ ያውም በግብረሰዶማውያን)፣ የሚደርስላቸው አጥተው በየእስር ቤቱ ለሚንገላቱ ወገኖች(ወንድሟንና እናቷን ለማብላት በአረብ አገር የምትንከራተትን አንዲት ኢትዮጵያዊትን ቆንጆ በግፍ የገደለ ሳይጠየቅ ይባስ ብሎ አስከሬኗን እንኳን የሚቀበል መንግስት ሲጠፋ)፣ ከርስት ከጉልታቸው በጉልበት ለሚፈናቀሉትና ለውጭ ባለኃብት ለሚሰጠው መሬታችን (….) ስንል አንዋሽ። የዘር ማጥፋቱን፣ ከሱማሊያና ከኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነት እያልን ብንቀጥል የበደል ጥግ መድረስ ይቸግረናል። ይህን ግፍ አስቀምጠን መሰዳደብን ምን አመጣው? እስካሁን ይህ ተፈፅሞብናል ካሁን ቡኃላስ ምን እስኪመጣ ነው የማንተባበረው? በሬድዮ ሚሊ ኮሊንስ ስንከራከር ወገናችንስ የሚደርስበት ከዚያ ያነስ ይሆን?
ካልሆነም ጡረታ መውጣትና ለተስፋዎቻችን መንገዱን መልቀቅ እንዲህ ብሎ ከመዝፈን ያድናል።
ይብላኝ ለወገኔ፣
እኔስ ደርሷል ቀኔ፣
አገሬን ገድያት፣
ሳያምርብኝ ልሞት፣
እንዳፈርኩ በስደት፣
በምድሬ ሳልዘራ ሳላፈራ ራሴን፣
ባውድማው ሳልወቃ ሳልሰበስብ ሰብሌን፣
ቀና ሳልል ሞትኩኝ፣
እንደተዋረድኩኝ፣
ፕሮፌሰር ዶክተር ደራሲ መምህር አንቱታው ትምርቱ ከፀፀት ከቁጭት ከሞት ላያድነኝ።
ለዚህ ተፅእኖ ፈጣሪ ዲያስፖራ ልቡና ይስጥልን እያልክ መፀለይ አትርሳ!የሚከተለውንም ሊንክ ተጫን!
http://ethsat.com/Main/esat_recurring_monthly_donation.html
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ሶሎሞን አ.
[email protected]