በዋሽንግተን ዲሲ የቤተክርስቲያን የአንድነት ጥሪ በተሳካና በደመቀ ሁኔታ መካሄዱን የሚያሳይ በፎቶ የተደገፈ ዘገባ (ተጨማሪ መረጃ ተካቷል)

በተለያዩ የሐይማኖት ተቋማትና የሲቪክ ድርጅቶች ተሳታፊነት በዛሬው ዕለት ዋሽንትግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያለቸው ኢትዮጵያዊያን ዘር፣ሐይማኖት፣ጾታና ዕድሜ ሳይለዩ በነቂስ በመገኘት ታላቅና ደማቅ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዝግጅት አድርገዋል። የዝግጅቱ ዋና ትኩረት በሊቢያ በሰማዕትነት ያለፉትን ኢትዮጵያውያን ለመዘከርና እንዱሁም በተለያዩ አገሮች ውስጥ በግፍ ለተገዱትን ወገኖች ጸሎተ ፍትሃት ለማድረግ ነው።  በዝግጅቱ ላይ የሕጋዊው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ የእየሩሳሌምና አውስትራሊያ ሊቀጳጳስ የሆኑት አቡነ መቃሪዮስ ተገኝተው ቃል ምዕዳን ሰጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የዘመናችን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አንጋፋው ሊቅ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ እጅግ ወቅታዊ የሆነ ቀስቃሽና አነቃቂ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፈርስት ሂጅራ በመባል የሚታወቀው የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ማህበር ተወካይ አይሲስ የሚባለው ሽብርተኛ ድርጅት እስልምናን የማይወክልና ስራውም ከእስልምና የወጣ መሆኑንን ጠቁመው በኢትዮጵያዊያን ላይ ሊቢያ ውስጥ በደረሰው ግድያ በኢትዮጵያዊነታቸው ማዘናቸውንና መቆጨታቸውን ልብ በሚነካ ሁኔታ ገልጸዋል። አይሲስን ለመቃወም የሚያስፈልገው ሃይማኖተኝነት ሳይሆን ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው ብለዋል። ከዚህም አያይዘው የአይሲስ ስራ ከአውሬም የከፋ መሆኑ ጠቁመው ጅብ ሌላ ጅብን እንዲሁም አንበሳ ሌላ አንበሳን አይበላም አይሲስ ግን ከነዚህ አራዊት በከፋ ሁኔታ ሰውን ያርዳል ብለዋል።በመጨረሻም ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በአንድነት መቆም እንዳለብን ማሳሰቢያ ሰጠተዋል።እንዲሁም ዝግጅቱን አስመልክተው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባም ያስተላለፉት መልዕክትም ተነቧል።

ይህ ታሪካዊ ዝግጅት ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ሥራውን በማስተባበርና በመምራት እንዲሁም አስፈላጊውን ነገር በሙሉ በማሟላት የዋሽንግተን ዲሲ ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጋለች። በዚህም መሠረት የቤተክርስቲያኒቷ አስተዳዳሪ ሊቀ ማዕምራን ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሣዬ የግንባር ሥጋ በመሆን ከፍተኛ ርብርቦሽ በማድረጋቸው “ትወልደ ጻድቃን ይትባረኩ” እንደሚለው ልጆቻቸውን እግዚያብሔር ይባርክላቸው እንላለን።በዚህ ታሪካዊ ዝግጅት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገላቸው የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አካባቢ ቤተክርስቲያኖች ቁጥራቸው በርካታ ቢሆንም በስፍራው ላይ የተገኙት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው። አንዳንዶቹ ላለመሳተፋቸው የሰጡት ምክንያት ጥሪ “በስማችንና በአድራሻችን” አልተላከልንም ወዘተ.. የመሳሰሉ ተልካሻና ውሃ የማቋጥሩ ሰበቦችን ቢደረድሩም፣ አብዛኛው የዝግጅቱ ተሳታፊዎች ግን እውነተኛው ምክንያታቸው አንዱ እግራቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ ሌላው እግራቸው ደግሞ ወያኔ ውስጥ በመገኘቱ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

እነዚህ ባለሁለት ባሕርይ ካህናት ለማኛውም አገራዊ ጉዳይ በተለይም ወያኔን በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ የሚሰጡት ምክንያት ዙሪያው ጥምጥም የሆነ “ፖለቲካ ውስጥ አንገባም፣ቤተክርስቲያን እራሷን አዋርዳ ለዓለም ገዥዎች ሰልፍ አትወጣም፣ እኛ ጸሎት ብቻ ነው የምናደርገው ወዘተ..” እያሉ ምዕመናንን በማዘናጋት ከወያኔዎች ጋር በተለያየ ጥቅሞች ተቆራኝው የሕዝብን መከራ በማራዘም ላይ ይገኛሉ። ወገኖቻችን የስራና የኑሮ ሁኔታዎች ስለጨለሙባቸው ከአገራቸው በመሰደድ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው መልካም ቀን ይመጣልን ይሆናል ብለው በማለም በበረሃ ውስጥ ለአይሲሲ አራጆች የተዳረጉት በወያኔዎች ምክንያት እንደሆነ እየተወቀ፣ እነዚሁ ሆዳም ካህናት ሁኔታዎችን አለባብሰው ለማለፍና ወያኔን ከተጠያቂነት ለማዳን የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

እጅግ የሚያሳዝነው ዐቢይ ጉዳይ ደግሞ እነዚህ መምህራንና ካህናት ወንጌል እንደሚያስተምረን እውነቱን እውነት፣ ሀሰቱንም ሀሰት ማለት የተሳናቸው ለሁለት ጌቶች ያደሩ አጭበርባሪዎች የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ቤተክርስቲያንን ያሽመደመዱና አቅመ ቢስ ያደረጉ በመሆናቸው በነሱ ላይ የመረረ ተቃውሞ የሚያሰሙ ምዕመናን ሁልቆ መሳፍርት ናቸው። በቅርቡ በሊቢያ ውስጥ የተሰዉ ወገኖቻቸን ማተባቸውን አንበጥስም ብለው አንገታቸውን ለሰይፍና ጭንቅላታቸውን ለጥይት ሲሰጡ ያስተማሪን ታላቁ ቁም ነገር አስመስሎና ቀላምዶ ከመኖር እውነተኛውን ነገር ጨብጦ ይህንን አላፊ ጠፊ ዓለም በክብር ማለፍን ነው። ሆኖም ዛሬ በየቤተክርስቲያናቱ ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ጥቅመኛ ካህናት ምንያህል የዘቀጡና የተዋረዱ መሆናቸውን ከሥታቸው ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንም። ሆኖም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በረዥም ዓመት ታሪኳ እንደአሁኑ ዓይነት የፈተና ጊዜዎችን ተቋቁማ በማለፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ስትሸጋገር ኖራለች። ወደፊትም ትኖራለች።እውነት ምንም ብትቀጭጭም ብትደበዝዝም ጨርሳ ስለማትጠፋ ከሕዝብ ወገን የሆኑ እውነተኛ ካህናትን እንደነ አቡነ መቃሪዮስ፣ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ፣ ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሣዬ፣ መምህር ሳሙኤልና ሌሎችንም እግዚያብሔር ስለሰጠን ነገን በእምነትና በተስፋ እንድንጠብቅ አስችሎናል። የእነዚህን አባቶቻችንን ቁጥር ያብዛልን።

በዝግጅቱ ላይ የተነሱ ፍቶግራፎችን ይመልከቱ።

p18 p12 p10 p9 p1 p4 p3 p6 p8