መጀመሪያም ባዶ ቃል ነበር! ቃሉም የጠ/ሚሩ ነበር…
ከአዜብ ጌታቸው
ጠ/ሚሩ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ለራሳቸው ጋዜጠኞች የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ሳታደምጡ የቀራችሁ አይመስለኝም። መቼም በጠ/ሚርነት ተቀምጠዋልና እንኳን መገለጫቸው ግልምጫቸውም ዜና ሊሆን (News Worthy) ግድ ነውና እኛም ግድ ሆኖብን መስማታችን አልቀረም።
ልብ ብላችሁ እንደሆነ ጠ/ሚሩ በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሁሌም አንድ ሻጥ የሚያደርጓት አዲስ ነገር አትጠፋም። የአሁኗ አዲስ ነገር ደግሞ “መተካካት” የምትለዋ ቃል ነች። ቃሏ ሳትሆን አዲስ ፤ ቃሏ የምትወክለው ሃሳብ ነው። ይህን በተመለከተ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ።
ምንም እንኳ ጥያቄዎቹም መልሶቹም ከአንድ አይምሮ የፈለቁ የአንድ ብዕር ፍሬዎች መሆናቸውን ከልምድ የምናውቀውን ወገኖች መሸወድ ባይችሉም፤ ስብጥርጥር ያለው አቀራረባቸውና፤ በተቻለ መጠን ደግሞ ሁሉን ለመነካካት መሞከራቸው በተለይ የወያኔን ባህሪ ለማያውቅ ሰው በጣም አሳማኝ ይመስላሉ።
የጠ/ሚሩ ጋዜጣዊ መግለጫ በዋናነት ያተኮረው (ያስፈለገበትም) ሃገሪቷን ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ እንደሚያስመነጥቃት በመስበክ የወያኔ ካድሬዎች ላለፉት 2 ወራት በትጋት የተንቀሳቀሱበት የአምስት አመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብርን በተመለክተ ማብራሪያ ለመስጠት ይመስለኛል።
ከአምስት አመት በኋላ ወይም በአምስት አመታት ውስጥ እመርታዊ እድገትን ግቡ ያደረገው ይህ መርሃ ግብር ተፈጻሚ ሊሆን መቻሉን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ በርካታ ግቦችን የያዘ ነው የሚሉ ብዝዎች ናቸው ።
መርሃ ግብሩ በአምስት አመት ውስጥ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በእጥፍ ማሳደግን በዋና መርህነት ይዟል። ይህ የተሰላውም በአመት 15% የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ከተደረሰበት እምነት በመነሳት ነው። እምነቱ የተንደረደረውም ባለፉት አመታት 11% እድገት ተገኘ ከሚለው ጭብጥ ላይ ነው።ጭብጡ ደግሞ የኢኮኖሚ ሙያተኞች “cooked” የሆነ እንጂ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመረኮዘ አይደለም እያሉት ነው።
ይህ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብር እውን እንዲሆን የግብርናው ምርትና የኢንዱስትሪው እድገት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር እንዳለበትም ታሳቢ ሆኗል ተብሏል። ከዚሁም ጋር ተያይዞ በርካታ የመሰረት ልማት ግቦች ተነድፈዋል። ከብዙ በጥቂቱ የ2000 ኪ.ሜትር የኤሌትሪክ ባቡር ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስፋፋት፤ መንገዶች፤ የኮንስትራክሽን ስራዎች፤ የስፖርት አካዳሚዎች፤ ኢንቨስትመንቶችን ፤ ትራንስፖርት አገልግሎቶች፤ የኢንተርኔት አገልግሎቶች …..ምኑ ቅጡ !
በደምላላው መርሃ ግብሩ አዲስ አበባችንን ከአምስት አመት በኋላ አፍሪካዊቷ ቤጅንግ ለማድረግ ያቀደ ይመስላል። እንደ ልባችሁ ሳይሆን እንደ እቅዳችሁ ያድርግልን ከማለት ሌላ ምን ይባላል።
ጠሚሩ ከ20 አመት በፊት ስልጣን እንደተቆናጠጡ ሰሞን የ10 ዓመት እቅድዎ ምንድነው? ተብለው ሲጠየቁ “ሕዝባችን በቀን 3 ግዜ እንዲበላ ማድረግ ነው” የሚል ቃል መግባታቸውን የሚያስታውስና ዛሬ ከ 20 አመት በኋላ እንኳ 9 ሚሊዮን ህዝብ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ መሆኑን የሚያስተውል ዜጋ፤ ዛሬ በጠ/ሚሩ ቅመራ አምሮ፤ በካድሬዎች ፉከራ ዳብሮ የቀረበውን የ5 አመት የእድገት መርሃ ግብር ዲስኩር የሚያደምጠው “ መጀመሪያም ባዶ ቃል ነበር!“ ቃሉም የጠ/ሚር
ነበር….” በሚል ስሜት ውስጥ ሆኖ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው።የትናት ልምዳችንም የሚያሳየን ጠ/ሚሩን(ወያኔን) አምኖ ለነገ ተስፋ መሰነቅ እንደማይገባ ነው።
ስለዚሁ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብር እየተሰጡ ካሉ አስተያየቶች አብዛኞቹ፤ መርሃ ግብሩ ትልቅ ትኩረት ያረገው ፖለቲካዊ ተቀባይነትን ለማትረፍ በመሆኑ ያለልክ መንዛዛትና አቅምን ያለማጤን ይታይበታል የሚለውንና ወያኔ ደግሞ የዛሬን ስልጣኑን ማቆያ እንጂ እቅዱ ሊፈጸም ስለመቻል አለመቻሉ ብዙም የሚጨነቅ አይደለም የሚሉትን ጭብጦች በጥምረት የሚስማሙባቸው ይመስላሉ።
ድመቲቷን “ዛሬ ምን ያህል ወተት ታለበ ? ቢሏት “እኔ ምን አገባኝ ሺህ ቢታለብ ለኔ ያው በገሌ ነው” አለች ይባላል። በበርሜልም ታለበ፤ በማሰሮ ለሷ እዛቺው ገሏ ላይ ፈሰስ አድርገው ከሚሰጥዋት በስተቀር ምንም ጠብ እንደማይልላት ስትገልጽ ነው። ዛሬም ድረስ ከችግርና ከርሃብ ያልወጣው የኢትዮጵያ ሕዝብም፤ አንዳንዴ ተስፈንጣሪ አንዳንዴ ተወርዋሪ የሚሆነውን የአቶ መለስን የኢኮኖሚ እድገት የሚሰማበት ጆሮ ሊኖረው አይችልም። ብልኋ ድመት ሺህ ቢታለብ ለኔ ያው
በገሌ እንዳለቺው ሕዝባችንም ለኔ ያው ርሃቤ የሚል ይመስላል ….!
የአቶ መለስ ጋዜጣዊ መግለጫ የቃላት ጨዋታ ስለሚበዛበት ብዙም አይጥመኝም ።አንድ ና አንድ ሲደመር ስንት ይሆናል ለሚል ቀጥተኛ ጥያቄ፤ ሁለት ብለው ከመመለስ ይልቅ፤ 3 ወይም 4 ሊሆን የማይችልበትን ረዥም ዲስኩር እያሰሙ ከጭብጡ ሲሸሹ ማድመጥ ይሰለቸኛል። አሁን አሁንማ ጥያቄ ሲቀበሉና ማስታወሻ ሲይዙ ሁሉ ሳቄ ይቀድማል። ራሳቸው የሰጡትን ጥያቄ መልሰው ሲቀበሉ ማየት የሚያሰቅ አይደለም ትላላችሁ?… ሰጥቶ መቀበል ወይስ አቀብሎ መቀበል
እንበለው?
በነገራችን ላይ ይህ ለጋዜጠኞች ጥያቄ የማደሉን ነገር እውነተኝነት የሚያረጋግጥ አንድ አጋጣሚ በአሁን ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መከሰቱን ስንቶቻችሁ ልብ እንዳላችሁ አላውቀም።
እንዲህ ነበር የሆነው፦ ጋዜጠኛው የግብርናና የኢንዱስትሪውን መርሃ ግብር አስመልክቶ የተሰጠውን ጥያቄ በደንብ አላጠናውም መሰለኝ አገለባብጦ ነበር የጠየቀው፦
ጋዜጠኛው ጥያቄውን ያቀረበው “ በአምስት አመት መርሃ ግብሩ ውስጥ የግብርናው ምርት አድጎ የአገሪቷን ኢኮኖሚ መሪነት ከኢንዲስቱሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ይረከባል ማለታችሁን በተመለከተ፦ ብዙዎች በምን ታምር ነው በአምስት አመት ውስጥ ይህ ሊሆን የሚችለው የሚል ጥያቄ ያነሳሉ ፤፡ ስለዚህ ምን የሚሉት አለ?” በማለት ነበር።
ጥያቄውን ከታች ባለው አድራሻ ሄደው 10ኛው ደቂቃ ላይ ሊያደምጡ ይችላሉ
ግብርና- መር የሚለውን የወያኔ ካድሬዎች እድገት ለፋፊ ዲስኩር፤ መክፈቻ ቃል ለሚያስታውስ፦ ጋዜጠኛው ጥያቄውን ያቀረበው የግብርናውን ቦታ በኢንዱስቱሪው አሳስቶ እንደሆነ አይጠፋውም።
መጠየቅ የነበረበት “ በአምስት አመት መርሃ ግብሩ ውስጥ የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ አድጎ የአገሪቷን ኢኮኖሚ መሪነት ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ይረከባል ማለታችሁን በተመለከተ፦ በምን ታምር ነው በአምስት አመት ውስጥ ይህ ሊሆን የሚችለው ሲሉ ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ ፤፡ ስለዚህ ምን የሚሉት አለ።” በሚል ነበር። ነገር ግን ጋዜጠኛው ደንግጦም ይሁን ጭብጡ ሳይገባው ቀርቶ፤ አሳስቶ አቅርቦታል።
ይሁንና ጠ/ሚሩ በተለምዶ የተሳሳተ ጥያቄ ሲቀርብላቸው እንደሚያደርጉት “እዚህ ጋ ሊመጣ የሚገባው ጥያቀ ቢኖር …..” በሚል የተሳሳተውን ጥያቄ ሳያርሙ፤ በዘዴና በማያሳጣ መልክ፡ በመልሳቸው ውስጥ ጥያቄውን አካተው አልፈዋል። ይህ የሚያሳየው ጋዜጠኛው ቢያሳስትም እሳቸው ያወጡትን ጥያቄ ሊረሱት አይችሉምና ምን ለማለት እንደፈለገ አውቀው መመለሳቸውን ነው። ጥያቄው የቀረበው ከነጻ ጋዜጣ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፡ ጠ/ሚሩ ቢያንስ ቢያንስ አይናቸውን እያጉረጠረጡ
ምን ለማለት ፈልገህ ነው? በማለት በጠየቁ ነበር። አልያም በእንዴት ያለ የቃላት ቃሪያ ጥፊ የጋዜጠኛውን ሞራል ባነፈሩት ነበር። ነገር ግን የራስ ገመና ሆነና በለሆሳስ ታለፈ። ጋዜጠኛው ግን ግምገማ ላይ እሱን አያርገኝ…..ልማት አደናቃፊ ነዋ!..!
የሆነው ሆኖ እድገት የሚጠላ የለምና አሁንም እንደ አፋችሁ እንጂ እንደ ልባችሁ አይሁን እያልን፤ ተወንጫፊው የኤሌትሪክ ባቡር ከመቀለ- ሸገር ሲወረወር፤ ለማየት ያብቃን እንላለን።(ደርግ ለዘመናት ባካሄደው ጦርነት የተጎዳው መቀለ በመሆኑ ክልሉን በልማት ለመካስ ሲባል የሃዲዱም መነሻ ከዛ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ነው።)
ሌላው ጥያቄ ፦ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጨርሰው የሚወጡት ምሩቃን የሥራ ዕድል አለማግኘት በጣም እየተባባሰ ነው፤ የአምስት አመቱ መርሃ ግብር ይህን ችግር ለመቅረፍ የያዘው እቅድ አለ ወይ? የሚል ነበር።ለዚህም የሰጡት ምላሽ፡ አለ ወይም የለም የሚል ሳይሆን፤ ዙሪያ ጥምጥም ሄደው ነው። ጠ/ሚ ሲመልሱ “እኛ ችግሩን ለመቅረፍ ያሰብነው፤ ተማሪዎች ሃገሪቷ እጥረት ባለባት የሙያ ዘርፍ እንዲሰለጥኑ በማድረግ ነው። ለምሳሌ ከፍተኛ የሆነ የኢንጅነሮች እጥረት አለብን፤ በተቃራኒው በሶሻል ሳይንስ (ማህበራዊ ሳይንስ) ደግሞ የስራ እጥረት አለ፡፤ ስለዚህ እቅዳችን የተፈጥሮ ሳይንስ ላይ ትኩረት በማድረግ ስልጠናውን 40% ያህል ለመጨመር ነው። ብለዋል። ይህም ጥሩ እቅድ ነው። ይህን ማድረጋችሁ (መርሃ ግብሩ) የተማሪውን ሊማር የሚፈልገውን ትምህርት የመማር መብት አይጫንም ወይ? የሚል ጥያቄ ማስከተል ተገቢ ይሆን ነበር…(ምናልባት ጥያቄ አውጭው መልስ ላይ ሆኖ ረስቶት ይሆናል!)
በነገራችን ላይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንወያይ ለመሆኑ ኢንጅነሮች ጥብስ የሆኑት ኮንስትራክሽኑ ተስፋፍቶ ነው ማለት ነው? ብዬ ብጠይቀውም ያልጠበቅኩት መልሱ መራር ሳቅ አስቆኛል።
እንዲህ ነበር ወዳጄ ያለኝ” ኢንጅነሮቹ ጥብስ የሆኑት የኢህአዴግን የአባልነት ፎርም አንሞላም በማለታቸው በሥራ አጥነት በችግር እየተጠበሱ ስለሆነ ነው”
የአምስት አመቱን የእድገት መርሃ ግብር በተመለከተ እዚሁ ላይ ላብቃና ወደ ፖለቲካው ላምራ። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ጠ/ሚ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ አዲስ ይዘውልን የመጡት መተካካት የምትለዋን ቃል ነው።
የቀረበው ጥያቄ “ የዲሞክራሲያዊውን ሂደት ለማጎልበት በምርጫ ብቻ ሳይሆን በመተካካት የስልጣን ለውጥ የሚደረግበት አካሄድም እየታሰበ መሆኑን ገልጻችኋል። መተካካት ማለት ምን ማለት ነው? ይህ በቀጣይ 5 ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል? (ጥያቄውን ቃል በቃል አይደለም)፡፤ ጠ/ሚ በሰጡት መልስ፦ ምንም እንኳ ምርጫው በዲሞክራሲያዊ መንገድ እስከተካሄደ ድረስ የአንድ ፓርቲ ደጋግሞ ማሸነፍና ሥልጣን መያዝ ችግር ባይኖረውም። በኢሃዴግ እምነት ግን አንድ ፓርቲ ለረዥም አመታት ስልጣን የመያዙን ሂደት “በመተካካት” የስልጣን ሽግግር መለወጡ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል ብለዋል። ይህም ማለት አውራው ፓርቲ በራሱ
ፈቃደኝነት በመድብለ ፓርቲ ውስጥ ካሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ እንዲተካውና ስልጣን እንዲይዝ የሚያድርገበት ሂደት ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ይህን በተመለከተ ጠ/ሚሩ ተቃዋሚዎችን በሹመትና በስልጣን ለማባበል የወረወሩት እንጂ ፡ የየትኛውም አገር ፖለቲካ ልምድ እንደሚያሳየው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለተቀናቃኙ ፓርቲ ትከሻ መስፋት የሚሰጠው ወይም የሚያደርገው እርዳታ ሊኖር አይችልም የሚሉ ብዙ ናቸው። የጠነከረውን ተቃዋሚ አስሮና አፍርሶ ደካማ ለማጠናከር ቃል መግባትም ቀልድ ነው ! የሚሉም አጋጥመውኛል።ከሁሉ በላይ በአብዛኛው ሕዝብ አይምሮ የተጸነሰው ጥያቄ አቶ መለስ መተካካት በሚሏት ቃል ሊጫወቱ የፈለጉት ቁማር ምንድነው? የሚለው ነው…ሊተኩስ የፈለጉት ማንን ይሆን….?
ሌላው በአንድ ጋዜጠኛ በቀረበ ጥያቄ ውስጥ “የአውራ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት” የሚል መጠሪያ ሰምቻለሁ(dominat party) ጋዜጠኛው ኢሃዴግ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉ በሃገሪቱ “የአውራ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት” መኖሩን ያሳያል በማለት ነበር ጥያቄውን የጀመረው። ይህ ቃል “የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሰፈነበት” ወይም “አምባገነን” የሚለው ቃል የሚሰጠውን አሉታዊ ትርጉም ለመሸሽ ወይም ለማለዘብ ብቅ ያደረጉት ይመስላል።
በኔ በኩል ይህን ቃል ወያኔ 96.6% ድል አገኘሁ ከማለቱ በፊት ሲጠቀምበት አልሰማሁም። የሆነው ሆኖ ቃሉ በራሱ እራሱን የሚቃረን ይመስላል። አውራ ብሎ ዲሞክራሲ ምን ማለት ይሆን? የዲሞክራሲያዊ ሥርአት ትልቁ መመዘኛው ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል አይን ማየቱ መሆኑ እየታወቀ አንዱን አውራ ሌላውን ጭፍራ ብሎ ፈርጆ፦ የበላይና የበታች አካሎችን ፈጥሮ ሲያበቃ፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርአት ነኝ ማለት ይቻላል ወይ? ለኔ አልገባኝም የምታውቁ ብታስረዱኝ
ውለታ እመልሳለሁ።
በሌላ በኩል ካኮረፉት ጋር ሁሉ ለመደራደር ዝግጁ ነን የሚለው ሰላም ወዳድነን አይነት መግለጫቸው “ህገ መንግስቱንና” የኢሃዴግን ህጋዊ መንግስትነት ከተቀበሉ ብቻ በሚል ቅደመ ሁኔታ መታጠሩ የተለመደው የቃላት ጨዋታ ሆኖብኛል። የዛሬውን ጽሁፌን የምቋጨው ኢህ አ ዴግ ተቃዋሚውን ሁሉ አባሮ በምክር ቤት ብቻውን መቅረቱ የዲሞክራሲውን ሂደት አጨልሞታል የሚሉ አሉ ስለዚህ እርስዎ ምን ይላሉ ለሚለው ጥያቄ የሰጡትን አስገራሚ መልስ በመቃኘት ነው።
ጠ/ሚ እንደተለመደው ለዚህም ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ መልስ ፍልጋ ወደ አሜሪካ መብረር ነበረባቸው። አሜሪካ ውስጥ አሉ ጠ/ሚሩ “አሜሪካ ውስጥ የፋሽሽት ፓርቲ አለ ። ነገር ግን ይህ ፓርቲ በህዝብ ተቀባይነት ስለሌለው በአሜሪካ የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ምን ችግር ሊፈጥር አልቻለም። ይህ የፋሽሽት ፓርቲ በሕዝብ ውስጥ ተቀባይነቱ ከጨመረ ግን የዲሞክራሲው ሂደት ችግር ይገጥመዋል። እኛም አገር የሆነው ይህ ነው። ሰላም ጠል የሆኑትን ፓርቲዎች ሕዝቡ
ተፍቷቸዋል፡፡ይህ መሆኑ ደግሞ የዲሞክራሲውን ሂደት ደህንነት ዋስትና የሚሰጥና የሚያጠናክር እንጂ የሚያዳክም አይሆናም” ብለዋል።
ይህ የጠ/ሚሩ ምሳሌዊ አገላለጽ ከእውነት የራቀ ብቻም ሳይሆን ብዙዎችን ጉድ ያሰኘ ሆኖል። እውን ዛሬ በወያኔ ዕስር ቤት የምትገኘው ጀግናዋ እንስት ብርትኳን ሚዲቅሳ ትመራው የነበረው ፓርቲ ከአሜሪካው ፋሽሽት ፓርቲ ጋር በንፅፅር የሚቀርብ ነውን? እውን ብርትኳን ሚደቅሳ ወይስ መለስ ዜናዊ በሕዝብ ተወዳጅ? የሚለውን ጥያቄ በወያኔ ግዞት ላይ ላሉ ህሊኖች ሁሉ እያቀረብኩ በዚሁ የዛሬውን ጽሁፌን እቋጫለሁ።
ሰላም ለኢትዮጵያ ይሁን!
አዜብ ጌታቸው [email protected]