የአገር ቤት ጋዜጠኞች ምን ጻፉ? (ከጥር 9 -15፣ 2003)

የፀረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነር  የ18ሺ ብር አይፎን ሞባይል ገዙ

አቶ አዲሱ መንግሥቱ ይባላሉ፡፡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮምሽነር ናቸው፡፡ የኢህአዴግ አባልም ናቸው፡፡ ሰሞኑን ተገምግመው ወደ ዕጩ አባልነት ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡የሰሯቸው ኀጥያቶች በሪፖርተር ጋዜጣ ተዘርዝረው ነበር፡፡ መጀመርያ በኮሚሽኑ በጀት ባለ 10 ሺሕ ብር የሞባይል ቀፎ ገዙ፤ ትንሽ ከተጠቀሙበት በኋላ “መልኩ ደስ አይልም” ብለው በተመሳሳይ ወጪ ሌላ ሞባይል አስገዝተዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ባለ18 ሺሕ ብር አይፎን ሞባይል በማስገዛት የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ላልተፈለገ ዓላማ አውለዋል›› ይላል የሪፖርተር ዘገባ፡፡

የእንግዳ መቀበያ ሶፋ በ30 ሺሕ ብር ከማስገዛታቸውም በተጨማሪ፣ በቅርቡ የ35 ሺሕ ብር ሶፋ በድጋሚ ማዘዛቸው ተነግሯል፡፡ አቶ አዲሱ ሁለት የመንግሥት ቤት በመያዝ ባንዱ እየኖሩ አንዱን እያከራዩ መሆናቸውን ተዘግቧል፡፡

ለድርጅቱም ሆነ ለመንግሥት ሥራ ደንታ የለቸውም ተብለው መገምገማቸውንና ፣ ለግምገማ ሲፈለጉም በየጊዜው እንደሚሸሹ፣ የሚጨነቁትም ለሥራቸው ሳይሆን ለክብራቸው መሆኑን በግምገማ ተወስቷል፡፡

በመጨረሻ አቶ አዲሱ ከአመራርነት ወደ ዕጩ አባልነት እንዲወርዱ፣ በትርፍ የያዙትን የመንግሥት ቤት ባስቸኳይ እንዲመልሱ፣  በትርፍ የያዙዋቸውን ሞባይሎች እንዲመልሱና የሦስት ዓመታት የድርጅት የአባልነት ክፍያ ከፍለው እንዲያጠናቅቁ በሙሉ ድምፅ ተወስኖባቸዋል፡፡ አቶ አዲሱ በበኩላቸው “እውነቱን ወደ ፊት እግዚአብሔር እንደሚያወጣው” ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

—-

የዋጋ ተመኑ ቀልዶች

አቶ ኪዳኔ መካሻ የተባሉ የሕግ ባለሙያና የሰንደቅ ጋዜጣ አምደኛ በዋጋ ተመኑ ዙርያ የተነገሩ ቀልዶችን አሰባስበው ባሳለፍነው ሳምንት አስነብበዋል፡፡ አንዱን እንሆ፡፡

ቅዳሜ ምሽት አንድ ቡና ቤት ቁጭ ብለን ያላበው ቢራችንን በ7 ብር ከ10 ሳንቲም እየጠጣን ነበር፡፡ አንዱ ድንገት ከመቀመጫው ላይ ተነሳና ሞቅታ በያዘው አንደበት እንዲህ ሲል ሰምተን በጣም አሳቀን፤               “ስሙ..ኢህአዴግ አገሪቷን ከተቆጣጠረ በ20ኛ ዓመቱ ታህሳስ 20 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ ገባ፡፡” አለና ድምጹን ሞረድ አድርጎ “ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ መንግሥት ጥቂት ራስ ወዳድ ነጋዴዎች ሲቆጣጠሩት የነበረውን የአዲስ አበባ ገበያ የዋጋ ገበያ ተመን በማውጣት ተቆጣጥሮታል፡፡ ታህሳስ 20 ሺህ ዘጠኝ ሞቶ ….” ቤቱ በሳቅና በሁካታ ተሞላ፡፡

—-

ታምራት ደስታ የመኪና አደጋ በማድረስ ሀትሪክ ሰራ

“ሮያል” መጽሔት ባሳለፍነው ሳምንት እንደዘገበው ድምጻዊ ታምራት ደስታ ላንድ ክሩዘር መኪናውን ሀያት ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው ቀለበት መንገድ ጋር አላትሞ በራሱም ፣ በመኪናውም ፣ በቀለበት መንገዱም ላይ መጠነኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከዚህ ቀደም ቦሌ አካባቢ አደጋ አድርሶ መኪናውን ባለችበት ትቷት የውጭ በረራ ማድረጉንና ሲመለስ ተገቢውን ቅጣት እንደተቀጣ ያስታወሰው መጽሔቱ ከዓመታት በፊትም ድምጻዊው ከደንበል ህንጻ  ጋር በምሽት መጋጨቱን የሚዘነጋ አይደለም ሲል ዘገባውን ቋጭቷል፡፡ “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የሚለውን ተወዳጅ ዜማ ለድምጻዊው መጋበዝ ክፋት ይኖረው ይኾን?

—-

ከቡናና ከዳያስፖራ የቱ ይበልጣል?

ባሳለፍነው ሳምንት መንግስት “ከዳያስፖራዎች” ጋር ውይይት እንዳደረገ የአገር ቤት ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ “አዲስ አድማስ” በቅዳሜ እትሙ እንዳመለከተው ዳያስፖራዎች “የፍትህ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው” አስነብቧል፡፡ “ጤና፣ ትምህርት፣ ሆቴል፣ መንገድ ብዙ ተሰርቷል፤ ዳኝነት ግን የለም” ሲሉ ዲያስፖራዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የትራንስፎርሜሽኑ ጎማዎች ናቸው፤ “አሁን ባለው ሁኔታ አራቱም ጎማዎች አይሰሩም” ሲሉ መንግሥትን ተችተዋል፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው “የትራንስፎርሜሽኑ ባቡር በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አይደለም እንጂ ጎማው ይሰራል፡፡” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢ በበኩላቸው “ከቡና ዳያስፖራ ይሻላል” የሚለውን ከተወያዮች የተነሳውን አባባል ጠቅሰው በዚህ ዓመት ከቡና የተገኘው ገቢ ወደ 6 መቶ ሚልዮን ዶላር ሲሆን ከዳያስፖራ የተገኘው ግን 1.8 ቢልዮን ዶላር እንደሆነ አምነዋል፡፡

—–

ሦስት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከሕግ በላይ እንዳልሆኑ ተረጋገጠ

በኢትዮጵያ የፍትሕ ታሪክ ልዩ የተባለለት የፍርድ ቤት ዘገባ “ሪፖርተር” ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ ሦስት የጉምሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ ሀላፊዎች የፍርድ ቤት ትእዛዝን ስላላከበሩ ወደ ወህኒ ቤት እንዲወርዱ ተፈርዶባቸዋል፡፡

የጉምሩም ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ተወልደ ብስራት፣ የእስረኞችና የሰነዶች ክትትል ሐላፊ አቶ ኃይላይ ገብረመድህን እንዲሁም የወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ አቶ ገላን ሰቦቃ “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ፍርድ ቤት እንዲፈቱ የወሰነላቸውን ግለሰቦች በገዛ ፈቃዳቸው ሆን ብለውና አስበውበት እስረኞችን ከስድስት እስከ አሥር ወራት ድረስ አስረው አቆይተዋል፡፡” በዚህ ምክንያትም ሦስቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የፍርድ ቤት ትእዛዝን ባለማክበራቸው በተራቸው ለሁለት ወራት ወህኒ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸዋል፡፡

ከውሳኔው በፊት አቶ ተወልደ ብስራት የፍርድ ማቅለያ ሲጠየቁ “ጥፋተኛ አይደለሁም፤ አስተያየት ማቅረብ አልፈልግም” ብለው ፍርድ ቤቱን ተቆጥተዋል፡፡ ይህን ንግግራቸውን ተከትሎም ዳኛው “አሁንም ለሕግ አልገዛም ባይነታችሁ አልበረደም፤ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣናትም ሆኑ ሁሉም ሠራተኞች ከሕግ በላይ አለመሆናችሁ ማወቅ አለባችሁ” በማለት አስገንዝበዋቸዋል፡፡

ብርቱካን ሚደቅሳና የዚህ ሳምንት ጋዜጦች

ዘወትር ረቡዕ የሚታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ “የብርቱካን ዝምታ” በሚል ሰፊ ፊቸር ያስነበበ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ “አውራምባ ታይምስ” በቅዳሜ እትሙ “የብርቱካን እንቆቅልሽ” የሚል ርእስ በፊት ገጹ አስነብቧል፡፡“አውራምባ ታይምስ” እንደ ጃዋር መሀመድ፣ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያምን እና አቶ ግርማ ካሳን  የመሰሉ ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኞችን በማነጋገር ባስነበበው ፊቸር “ብርቱካን ላልተወሰነ ጊዜ /ምናልባትም ለሁለትና ሦስተ ዓመታት ከፖለቲካ ትርቃለች” ሲል ጽፏል፡፡

ብርቱካን ላይ ያጠነጠነውን ይህንን ሀተታ የጻፈው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እንደሚለው “ብርቱካን በቅርቡ በፖለቲካ ሕይወቷ ዙርያ ለሕዝብ ይፋ መግለጫ እንደምትሰጥ” አረጋግጣለታለች፡፡ “ፓርቲዋ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ አዲስ ሊቀመንበር እንዲመርጥ ጠይቃለች” የሚል ዜና እንደደረሰውና ይህንኑ እንድታረጋግጥለት ይኸው ጋዜጠኛ ጠይቋት ጭንቅላቷን በመነቅነቅ የዜናውን እውነታነት አረጋግጣለታለች፡፡

ቦክሰኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ

አውራምባ ታይምስ አንዳፍታ በተሰኘ አምዱ “ታዋቂ” ሰዎችን እየጋበዘ የማሳጣት ስራ በመስራት አንባቢዎቹን ያዝናናል፡፡ በዚህ ሳምንት የመኢብን ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ መሳፍንት ሽፈራውን ተረኛ አድርጓቸው ነበር፡፡

መኢብን ፓርቲ “ገዢው ፓርቲ ጠፍጥፎ ሰርቷቸዋል” ከሚባሉ “ተቃዋሚ” ፓርቲዎች አንዱ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ፓርቲውን የሚመሩት የቀድሞው ቦክሰኛ/ በሞስኮ ኦሎምፒክ ተሳትፈዋል/  የአሁኑ ተቃዋሚ አቶ መሳፍንት ሽፈራው ናቸው፡፡ ስማቸውን ከመስፍን ወደ መሳፍንት ለምን እንደቀየሩ ተጠይቀው እንዲህ አሉ –

‹‹ስሜ መስፍን ነበር፡፡ በዚህ ስም ተቸገርኩ፤ አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ መስፍን ሽፈራው የሚባል ነጋዴ አለ፡፡ መልኩም ከእኔ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ፣‹በቫት አለመክፈል ይፈለጋል› እያሉ በቴሌቪዥን ገለጹ፡፡ ፖሊሶች እኔ እየመሰልኳቸው ቤቴ ድረስ እየመጡ…፡፡ ፖሊሶችን ፈርቼ ሳይሆን ‘የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሆኖ የመንግስት ቫት አይከፍልም’ የሚል ወሬ ሲመጣ ለምርጫ 2002 ስሜን ከመስፍን ወደ መሳፍንት ቀየርኩት፡፡”

የኢህአዴግ ተለጣፊ ፓርቲ ተደርገው መታየታቸው ቅር ያሰኛቸው እንደሆነ በጋዜጣው የተጠየቁት አቶ መሳፍንት/ የድሮው መስፍን/ እንዲህ አሉ፡-

“የኢህአዴግ አባል መሆን ወንጀል አይደለም፡፡ ግን ኢህአዴግ ምን አጥቶ ነው እኛን የሚያቋቁመን? ምንም ያደረግንለት ነገር የለም፡፡…እኛ የምንፈራው ሕዝብን ነው፤ በውጭ አገር ሆኖ በተስፋ ለሚኖር ሳንድዊቹን የሚግጥ ወኔ ቢስ የፈለገውን ቢል ምንም አይደንቀንም፡፡”

አውራምባ፡-ከምርጫው በኃላ ግን ድምጻችሁ ጠፍቷል፤ የምትሰሩት ለምርጫ ብቻ ነው?

አቶ መሳፍንት፡- …ከማንም ፓርቲ በላይ በፌደራሊዝም ጉባኤ ላይ ሐሳባችንን ገልጸናል፡፡ ከዚህ በተረፈ የመንግስት ስልጣን ስላልያዝን ሌሎች ስራዎችን መስራት አንችልም፡፡

አውራምባ፡- ሕገ መንግሥቱ ስንት አንቀፆች አሉት?

አቶ መሳፍንት፡- ሕገ መንግስቱን ስንት አንቀፆች እንዳሉት የማጥናት ግዴታ የለብኝም፡፡

አውራምባ፡- ሚያዝያ 27 የሚከበረው ለምንድነው?

አቶ መሳፍንት፡- እኔ ቀን አላከብርም፤ ቀን ማከበሩንም በራሱ እተቻለሁ

አውራምባ፡- ቀኑን አያክብሩ ግን በአገራችን ቀኑ ለምን እንደሚከበር ይንገሩን

አቶ መሳፍንት፡- አልኩህ እኮ! የሰው ልጅ እንጂ ቀን ሊከበር አይገባውም፡፡ በአላትን ማብዛት ትክክል አይደለም ብዩ አስባለሁ፡፡

በዲላ ሴተኛ አዳሪዎች በማኅበር ለመደራጀት ወሰኑ

/ኢዜአ/ በዲላ ከተማ የሚሰሩ ሴተኛ አዳሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የሚደርስባቸውን ጥቃት በጋራ ለመከላከል ወሰኑ፡፡ የደቡብ ክልል ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ለሁለት ቀናት በዲላ ከተማ ባዘጋጁት አውደ ጥናት ላይ የተሳተፉ የቡና ቤት ሴተኛ አዳሪዎች እንዳመለከቱት በደንበኞቻቸውና አሰሪዎቻቸው ሰብአዊ መብታቸውን የሚጋፉባቸው ችግሮች ያጋጥማቸዋል፡፡

በቡና ቤቶች ኮንዶም በነፃ ይታደላል ቢባልም አሰሪዎቻቸው እስከ አንድ ብር እንደሚጠይቋቸውና አንዳንዴም ኮንዶም እያለ አልቋል በማለት ችግር እንዲመፈጥሩባቸው ገልጸዋል፡፡ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመከላከል “ህብረት” በሚል መጠሪያ ማኅበር ለማቋቋም መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡

“ላይፍ” መጽሔት “አዲስ ዘመን” ጋዜጣን ጠቅሶ የዘገበው

የአገር ቤት ምርቃት

አረሱት መተማን ዘቅዝቀው እንደቦይ

አረሱት አርማጮን ዘቅዝቀው እንደቦይ

አረሱት ቋራን ዘቅዝቀው እንደቦይ

አባትየው ቢሞት ልጅየው የለም ወይ

የ “ፍትሕ” ጋዜጣ ጸሐፊ ለጎንደር ካርኒቫል ጎንደር ከተማ በሄድኩበት ወቅት አዝማሪ ቤት ሰማሁት ብሎ የጻፈው

“በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ለቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ተበረከተ”

ሰንደቅ ጋዜጣ

“እግር ኳስ በጣም እወድ ነበር”

አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ -ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሮያል መፅሄት

____

“ባን ኪ ሙን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ”

አውራምባ ታይምስ

____

“የ12 ቀን ህፃን ልጃቸውን ተስማምተው የጣሉት ወላጆች በእስር ተቀጡ”

ሰንደቅ ጋዜጣ

_____

“መንግሥት ከልቡ ለሕዝብ የሚጨነቅ ከሆነ ለምን በምግብ ላይ የጣለውን ቫት አያነሳም?”

አቶ አስራት ጣንሴ፤ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ ለአውራምባ

_____

“ባለፈው እትማችሁ አውቶብስ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ሙከራ አድርጓል የተባለ ሰው መከሰሱን፤ሌላ ጊዜ ደግሞ የሰማንያ ዓመት አዛውንት ከውሻ ጋር ወሲብ መፈጸማቸውን የሚገልጹ ወሬዎች ጋዜጣችሁ ላይ አንብቤ በእጅጉ ተገርሚያለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ወሬዎች በጣም ጣፋጭ ስለሆኑ ተከታትላችሁ እንድታወጡልን አስተያየቴን እሰጣለሁ፡፡”

እመቤት ስጦታው የተባለች አንባቢ ለሰንደቅ ጋዜጣ የላከችው መልእክት

_____

“የሰብአዊ መብትን ከሚጥሱ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ሆነች”

መሰናዘርያ ጋዜጣ

_____

“ሎሚ ቢወደድ ቃላት ወረወርኩ”

የአውራምባ ታይምስ የዚህ ሳምንት ሽሙጥ አምድ ርእስ

_____

“ኤርትራ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ልትከፍት ነው”

ፍትሕ ጋዜጣ

_____

የሳምንቱ ድንቅ አባባል

‹‹ትግሉን ዳር ሳላደርስ አላገባም››

የገዢው ፓርቲ ተለጣፊ እንደሆነ የሚነገርለት የመኢብን ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው አውራምባ ታይምስ ‹‹ለምን ትዳር እንዳልመሰረቱ›› ላቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ