አቡጊዳ – የ«አቶ መለስ ማጀራት መቺ» አቶ ናትናዔል ወደ ታሰሩበት ተወሰደ !

ከአምስት ቀናት በፊት በቃሊት እሥር ቤት ሃላፊዎች ቤት ትእዛዝ፣ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዱዋለም አራጌ ላይ፣ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ የፈጸመዉ ኢብሳ አስፋዉ የተባለ ግለሰብ፣ ሶስት መቶ እስረኞች በሚገኙበት የቃሊት እሥር ቤት ዞን እንደተሸጋገረ ፣ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያመለክታል።

ከነዚህ ሶስት መቶ ሰዎች መካከል፣ መሰረት በሌለዉ የሽብር ተግባር የተከሰሰዉ፣ ሌላዉ የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባል፣ አቶ ናትናኤል መኮንን የሚገኝ ሲሆን፣ ደብዳቢዉ በአቶ ናትናኤል ላይ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል ፍርሃት እንዳላቸው የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት የደረሰን ዜና አክሎ ያትታል።

አቶ መለስ ዜናዊ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ፣ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመታረቅና ለመስማማት ፍላግት እንዳለባዉ በገለጹበት አፋቸው፣ የአንድነት ፓርቲን ጨምሮ በመድረክ አመራር አባላት ላይ ጠረቤዛ እየደበደቡ ዛቻ መሰንዘራቸው ይታወሳል።

በአቶ አንዱዋለም ላይ የደረሰዉ፣ በአቶ ናትናዔልና ሌሎች ላይ ሊደርስ የሚችለው አሳዛኝ የድብደባና የቶርቸር ድርጊቶች፣ ምን ያህል በኢትዮጵያ፣ ለስብእና ደንታ የሌላቸው ፣ ጨካኝ ግለሰቦች እየገዟት እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በአቶ አንዱዋለም ላይ ድብደባ የፈጸመዉንና ዛሬ ወደ አቶ ናትናኤል የተላከዉን ግለሰብ፣ « በአቶ መለስ የተላከ፣ የአቶ መለስ ማጀራት መቺ» ብለዉታል።