ጥርስ ያወለቀ ጥርሱ ይውለቅ የምትሉ ኦሪታዊያን ሆይ ስሙ!!! ከአሮን

አሁን ሰሞኑን በህዝቦች መካከል እየደመቀ የመጣው የመተባበር እና አብሮ የመስራት መልካም ፍላጎት ጥቂቶችን እያሸበረ ነው።መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹስ በብሄሮች መካከል የገነቡት የጠብ ግድግዳ ሲናድ አይተው ብዙ ቢጮኹ የቆሙበት መሠረታቸው ቀስ በቀስ እየተናደ በመሆኑ ተሸበርን ቢሉ እውነት ስላላቸው አይገርምም።የሚገርመው ግን “መለስ ዜናዊ የገነባው የጭቆና መረብ መበጣጠስ አለበት ብለን” ተነስተናል ብለው ሲያበቁ እየደመቀ የመጣውን የትግል አንድነት ጥሪ አልቀበል ማለት ብቻ ሳይሆን መተባበሩ እንደማያዋጣ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚጮኹ ቡድኖችን መስማት ነው።አንዳንዶቹም “ከእንዲህ ዓይነቱ ትብብር መለስ ዜናዊ የዘረጋው ሥርዓት ይሻለናል” ሲሉም ተደምጠዋል።ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው እንዲሉ በነጻነት ትግል ሥም የህዝቦችን ነጻነት ለማደናቀፍ የቆሙ የጨው ሃውልቶችን ለመለየት ግዜው አሁን ደርሷል።

በጄኔራል ከማል ገልቾ የሚመራው ኦነግ የወሰደውን አገር የማዳን እርምጃ ጥቂት ቂመኞች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጥላሸት ሊቀቡ ሲዳክሩ በትዝብት እየተመለከትናቸው ነው።እነዚህ ቂመኛ ኃይሎች ነጻነታችን የሚሉት የድሮ ዘመን ሰዎች ፈጽመዋል የሚሉትን እነርሱ ዛሬ በዚህ ትውልድ ላይ ለመድገም የሚቀዳጁትን መብት ነው።እንዲያ ያለውን መብት አገኛለሁ ብሎ ማሰብ እኔ አንዳንድ ግዜ ክንፍ አውጥቼ በሰማይ ስበር የማየውን ህልም ይምሰላል።እነ ጄኔራል ከማል ገልቾ ለሁላችንም የምትሆን አገር እንፈጠር ሲሉ ይሄን የመሰለ ወርቅ ሃሳብ ማጣጣል መለስ ዜናዊ በአገሪቷ ላይ እያደረሰ ካለው በደል በምንም መልኩ ተለይቶ አሚታይ ነገር አይደለም።

ከጄኔራል ከማል ገልቾ በተቃራኒው የቆሙ ቡድኖች ከታሪክ እሰርኝነት ራሳቸውን ማስፈታት አቅቷቸዋል።ምክንያቱ ግልጽ ነው።ቂም እና የበቀል ፍላጎት።ፍትህን መቶ ዓመት ወደ ኋላ ሂዶ ራሱን የታሪክ እሰረኛ ካደረገ ኃይል እጅ ማግኘት የሚቻል ነገር አይደለም።እንዲህ በደልን እየቆጠረ ያን በደል መልሶ ለመድገም ከሚመኝ ቡድን እጅ ሠላም ይገኛል ብሎ ማሰብም ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ የሚለውን ተረት ያስታውሰናል።በትላንትናው ክፉ ታሪክ ላይ ቆሞ በደልን ብቻ ከሚያመነዥክ ቡድን እጅም ዴሞክራሲያዊ ሥራዓትን ማግኘት ፍጹም የሚቻል ነገር አይደለም።ለዚህ እነመለስ ዜናዊ ህያው ምስክሮች ናቸው።

ነጻነት የሰፈነባትና ሁሉም ዜጎች ተከባብረው የሚኖሩባት አገር ለመፍጠር አለመተባበር የመለስ ዜናዊን ምኞት ማስፈጸም ነው ብል ስህተት አይሆንም።ነጻነትና እኩልነት እንዲሰፍን፤ፍትህ እንዲነግስ፤እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ አልተባበርም የሚል ድምጽ የሚሰማው ከባእዱ ከመለስ ዜናዊ ካልሆነ በቀር ለነጻነት ቆሜአለሁ ከሚል ወገን ይመጣል ብለን ለማመን በብዙ እንቸገራለን።ሆኖም ግን እንዲህ ያሉ ድምጾችን ከዶ/ር በያን አሶባ እየሰማን ነው።እንዲህ ዓይነቱን ድምጽ ከዳውድ ኢብሳ እየሰማን ነው።እንዲህ ዓይነቱን ድምጽ ከጅዋር መሃመድ እየሰማን ነው።ይሄ በጣም የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍርም ነው።

የእነ መለስ ዜናዊን ክፉ ድምጽ ማስተጋባት አሳፋሪ እና ነውር ተግባር ነው።መለስና ቡድኑ ህዝቦች በአንድነት ጸንተው እንዳይቆሙ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።ወደ ፊት ከማየት ይልቅ ወደ ኋላ ብቻ እየተመለከትን ባለፈ ታሪክ ላይ እየተነታረክን ግዜያችንን በከንቱ እንድናጠፋ የመለስ ዜናዊ ምኞት ነው።እስከ ዛሬ እንዲህ ውሉ በማይታወቅ ንትርክ ውስጥ በመቆየቱ የተወልድንባት አገር ለውረድት በቃች እንጂ እንድትከበር አልሆነችም።አሁንም እንደገና ሰበዝ እየመዘዛችሁ ለጋራ አገር አብረን አንቆምም ማለት የበለጠ አገሪቷንና ህዝቧን ያዋርዳል እንጂ አያስከብረንም።ዛሬ የረሳናቸውንና ማስታወስም የማንፈልጋቸውን በደሎች እየመዘዛችሁ አያቶቻሁ እንዲህ ነበሩ እያላችሁ አታላዝኑብን።እኔ የዚህ ዘመን ትውልድ ነኝ።ያን ግዜ ለተፈጠረው በደል ዛሬ የምጠይቀው ትውልድም የለም።አሁን ህዝባችን ባለበት መከራ ውስጥ የመለስ ዜናዊን ድምጽ መልሳቸው አታስተጋቡ።ይሄ ነውር ነው።

ዛሬ መለስ ዜናዊ በህዝቦች ላይ ከሚያደረሰው በደል ይልቅ ትላንትናና ከትላንት ወዲያ አጼዎቹ በፈጸሟቸው ስህተቶች ላይ አተኩረው በቂም በቀል ስሜት ተውጠው ከሌሎች ጋር አብሬ አልሰራም ማለት ባንድም በሌላም መንገድ የፋሽስቱን መለስ ዜናዊን ህልም እውን ከማድረግ ተለይቶ አይታይም።አገራችን በክፉ ዘረኞችና ዘራፊዎች እጅ ተይዛ ባለችበት በዚህ ክፉ ዘመን ብሄርን እየቆጠሩ በጠባብ ጎሰኛ ስሜት ታጥሮ ከሌሎች ጎን አብሬ አልቆምም ማለት ለተገፋው እና የመከራን ጽዋ ለሚጎነጨው ህዝብ እፎይታን አያስገኝም።ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር በዓይናችን የምናየው በጆሮአችንም የምንሰማው ህያው ዘረኛና ዘራፊ ቡድን አለ።ዛሬ ዜጎችን እትብታቸው ከተቀበረበት መሬት እያፈናቀለ መሬት አልባ የሚያደርግ ሃይል በኢትዮጵያ አለ።ዛሬ ዜጎችን በችጋር እየወቀረ የድሆችን አንጡራ ሃብት እየዘረፈ በባእድ አገራት ባንኮች የሚደብቅ በክፉ አፍቅሮተ ንዋይ የተለከፈ ቡድን በአገራችን አለ።ዛሬ በዚያች አገር መልካም ዜጋ እንዳይበቅል በሰብቅና በሥለላ ላይ ተመሥርቶ የአገሪቷን እሴቶች ሁሉ የሚያዋርድ ብርቱ ጠላት አለ።

በአጠቃላይ ህዝብ የማያውቀው፤እርሱም ህዝቡን የማያውቅ ሌላ ባእድ ጠላት በህዝባችን ላይ ነግሶ ሳለ የወደፊቱን ትቶ የኋላውን በደል አጉልቶ ማሳየት የሚጠቅመው እነ መለስ ዜናዊን ነው እንጂ ለእኛ ደቂቃን ጠብ የሚል ነገር አይኖረውም።ዛሬ በደል ሞልቶ ተርፎናል።ዛሬ በወግኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን በደል ዓይናችሁ እያየ፤ ጆሯችሁም እየሰማ ሌላ በደል ፍለጋ ከመቶ ዓመት በላይ ወደ ኋላ ሂዳችሁ እርባና ቢስ በሆነ ንትርክ ውስጥ ዜጎችን የምትጠምዱትን ቡድኖች ባየን ግዜ በዚያች አገር ውስጥ ነጻነት በመጥፋቱ የምትጠቀሙት አንዳች ነገር ይኖር ይሆን ብለን ለመጠየቅም ተገደናል።

ዛሬ ዜጎች መለስ ዜናዊ በተባለ ጨካኝ እጅ ተይዘው የመከራ ጽዋን ሲጎነጩ፤ የመከራ እንጀራንም ሲበሉ እያያችሁና እየሰማችሁ ያለፈንና ትውልዱ የማያውቀውን በደል ፍለጋ መቶ ዓመት ወደ ኋላ ሂዳችሁ የምትኳትኑ ሆይ ያለፈው በደል ዛሬ ከሚደርስብን አይበልጥም።የዛሬውን በደል ካስቆማችሁ በኋላ የድሮውን ለማውራት ብዙ ግዜ ይኖራችኋል።ወርቃማ ግዜያችሁን እርባና ቢስ በሆነ ንትርክ አታጥፉ።እኛንም አታስልቹን።አሁን ያለን ግዜ ወርቃችን ነው።እባካችሁ ዓይናችሁን ክፈቱና ዛሬ ቆመንለታል የምትሉት ህዝብ ያለበትን መከራ እዩ።ርሃቡን ተራቡለት።ጥሙንም ተጠሙለት።ስደቱን ተሰደዱለት።

የዛሬውን ህያው ጠላት ከራሱ ላይ አሽቀንጥራችሁ ለመጣል ትጉ እንጂ አያቶችህ እንዲህ ሆነው ነበር እያላችሁ ግዜያችሁን በከንቱ አታባክኑ።የአያቶቻችን በደሎች ለዛሬ ነጻነታችን የሚያግዙት ምንም ነገር የለም።በድሮ ዘመን የተፈጸመ በደልን ማውራት ለዛሬ ክብራችንና ነጻነታችን የሚያግዘን ቢሆን ኑሮ ከጥቂቶች በቀር ብዙዎቻችን ብዙ በደል ባወራን ነበር።ነገር ግን ያ አይጠቅምም።ስለሆነም ወገኖቻችን ሆይ !! ስሙ !! በእውነት ነጻነት እና ክብር ትፈልጉ እንደሆን ከታሪክ እሰርኝነት ተፈቱና ከእውነተኛ ነጻነት ታጋዮች ጎን ቁሙ።እውነተኛ ነጻነት ፈላጊ ያለፈውን በደል እየቆጠረ እና እያጋነነ የመጪውን ትውልድ እድል ፈንታ አያጨልምም።

አንዳንዶቹ የትላንትናውን በደል የሚቆጥሩት በነገው ትውልድ ላይ ያንኑ በደል ለመድገም ፍላጎት እንዳላቸው ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል ህያው ምስክር እየሆነባቸው ነው።እነዚህ ኃይሎች “ጥርስ ያወለቀ ጥርሱ ይውለቅ” ከሚለው ከኦሪት ህግ መላቀቅ የተሳናቸው ብቻ ሳይሆኑ ወደ ኋላ ማየትን አልተውም ያለችውን የሎጥን ሚስት ይመስላሉ።ወደ ኋላ ማየትን አልተውም ያለችው የሎጥ ሚስት የጨው ሃውልት ሁኖ ከመቅረት በቀር ያተረፈችው ክብር የለም።”ጥርስ ያወለቀ ጥርሱ ይውለቅ” የሚለው የድሮ ዘመን ህግም አሁን ተሽሯል።

እየደመቀ የመጣውን የመተባበር ጥሪ አልቀበልም አልተባበርምም ማለት እነመለስ ዜናዊ ለዘረጉት ክፉ ዘረኛ መረብ ድርና ማግ ሆኖ ከማገልገል በቀር የትላንትናውን በደል አይሽረውም።የትላንትናውን በደል የሚሽረው ተፈጽሟል ብላችሁ የምታስቡትን በደል ላለመድገም ለራሳችሁ ቃል ስትገቡና ነጻነትንና እኩልነትን ለተነፈጉ ሁሉ መሟገት ስትጀምሩ ብቻ ነው።ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥም የሰው ልጆች ሁሉ በእኩልነትና በነጻነት መኖር ሲጀምሩ ያን ግዜ የቀድሞው ቁስላችን ይፈወሳል።ድምጻችንን ከፍ አድርገን ለኢትዮጵያዊያኖች በሙሉ ነጻነትና እኩልነት ይሁን ብለን በጮኽን ግዜ የጠቡ ግድግዳ ይፈርሳል፤ ቁስሉም ፈጽሞ ይፈወሳል፤ ነጻነትም ይሰፍናል።

ከበቀል ስሜትና ከጥላቻ ነጻነት፤ፍትህ፤እኩልነትና ሠላም ፈጽሞ ሊገኙ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም።ለዚህ እነመለስ ዜናዊ ህያው ምስክሮች ናቸው።ከበቀለኝነትና ከጥላቻ ስሜት አልላቀቅ ስላሉ በአገሪቷና በህዝቧ ላይ እያደርሱ ያሉትን ውርደት ማየት በቂ ነው።ወደፊትም ቢሆን ነጻነቱን የሚመኝ መጀመሪያ ከበቀለኝነት ስሜት መውጣት ይጠበቅበታል።ነጻነት ሌላውን ከማግለልና መልሶ ሌላ ጨቋኝ ለመሆን ፍላጎት ከማሳየት አይገኝም።ነፃነት እርባና ቢስ በሆነ ታሪክ ውስጥ ታጥሮ በመመኘትም አይመጣም።የሌላውን ነጻነት ገፍፎ ነጻነትን መቀዳጀትም አይቻልም።በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ነጻነቴን ተነፍጌአለሁ ክብሬም ተነክቷል የሚል ሁሉ ይውጣና ከወገኖቹ ፊት ይቁም።ልዩነትን ሳይሆን ትብብርንና መከባበርን ያውጅ።ያለፈውን ትውልድ ህጸጽ ሳይሆን ለመጻኢው ትውልድ ሠላም ፍቅርና አንድነት እንዲሆን ያስተምር።

አሮን ነኝ
ሁላችሁም ሠላም ይብዛላችሁ !!!