አማራው የህወሓት ቼ ጉቬራ
ተመስገን ደሳለኝ
ፍትሕ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)
አማራው የህወሓት ቼ ጉቬራ
ፋኖ ተሠማራ… ፋኖ ተሠማራ…
እንደ ሆቺሚኒ… እንደ ቼ ጉቬራ…
በዱር በገደሉ ታሪክ ልትሰራ
ዛሬ ፋኖ ወደ ዱርም፣ ወደ ገደልም አይሰማራም፡፡ አለመሰማራት ብቻ አይደለም፡-
‹‹ፋኖ፣ ፋኖ፣… ኧረ ፋኖ… ጥራኝ ጫካው፣ ጥራኝ ዱሩ
ለአንተም ይሻልሀል ብቻ ከማደሩ
ፋኖ፣ ፋኖ፣ ኧረ ፋኖ፣ ፋኖ… የሚል ዘፈንም አይዘፍንም፡፡ የቱንም ያህል መብትህ ቢገፈፍም፣ ድምፅ ቢጭበረበርም አንተም አታንጎራጉረው፡፡ ሌላው ቀርቶ እነዚህ መብቶች ቅንጦት ናቸው ብለን ብናልፋቸው እንኳ ቢርበህ እና ቢጠማህም ‹‹ፋኖ፣ ፋኖ፣ አረ ፋኖ…›› ብለህ አትዘፍንም፡፡
ለዚህም ነው ከእስር ይልቅ በረሀብና በጥማት ለመሞት የሚመርጥ ህዝብ ከኢትዮጵያ በቀር የትም የለ የሚል አባባል እየሰማህ ያለህው፡፡ የትም… መቼም በዛሬ ጊዜ ‹‹ነጋዴ ሙዚቀኞቻች››ን ‹‹ፋኖ፣ አር ፋኖ…››ን ይዘፍኑልኛል ብለህ እንደማጠብቅ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እነሱ ባይሆን ልማታዊ ዘፈኖችን ይዝፈኑልህ፡፡ ያውም ‹‹የኮፒ ራይት መብት›› እያሉ እያላዘኑብህ፡፡ አየህ! ለእነሱ የመብቶች ሁሉ ቁንጮ መብት፣ የኮፒ ራይት መብት ነው፡፡ ለዚህም ነው ከኮፒ ራይታቸው ውጭ ወደብ መጣ፣ ወደብ ሄደ፤ ኑሮ ተወደደ፣ነዳጅ ጨመረ፤ ምርጫ ተጭበረበረ፣ ኮሮጆ ተሰረቀ፤ ፍትህ ተዛባ፣ሙስና ተስፋፋ፤ አምባገነንነት ነገሰ፣ ጨመንጃ የበላይ ሆነ…ጉዳያቸው ያልሆነው፡፡ ብቻ ያንቡሌ፣ ከስከሲና፣ ወላይታ ጊዜ ነው፣ አለምዬ ሶራ ሶራ፣ ኪያዳ፣ ኢቦንጎ፣ወሃለ ባይ…. እያሉ የጎሳ ፖለቲካውን ከኢህአዴግ ንድፈ ሀሳብ መፀሀፍና መፅሄቶች ገልብጠው፤ ወደ ግጥም አስቀይረው፣ ዜማ ገዝትው (አንዳንዴም መንትፈው) ይዘፍኑልሀል፡፡ ዘፍነው ብቻ አያበቁም፤ በእጅም በእግር ብለው ከተዘፈነላቸው ክልሎች ልክ እንደ ቡሄ ሽልጦ መሬትን የሚያህል ነገር ተሸልመው ‹‹አመት አውደ አመት… ድገምና አመት›› ይሉልሀል፡፡ ያውም ለከፋፋይ ስራቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህማ ብሶባቸዋል፡፡ ስለሀገር አንድነት፣ ስለአንድ ህዝብ፣ ስለኢትዮጵያዊኒት…እንኳን ሊዘፍኑ፣ አያስቡትም፡፡ ድንገት አጀንዳው ቢነሳ እመነኝ ‹‹ጎመን በጤና›› ወይም ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ…›› ሲሉ ትሰማቸዋለህ፡፡ እስቲ እንደው ‹‹አንድ ሀገር፣ አንድ ህዝብና አንድ ባንዲራ›› ማለት በየት ሀገር ነው ገዥውን ፓርቲ እንደመቃወም ተቆጥሮ የሚያሸማቅቀው? ብቻ ይቅር፤ ሁሉን ቢያወሩት…
የሆነ ሆኖ የዛሬው አጀንዳችን ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይን (ሕወሓትን) ከመሰረቱት አስራ አንድ ሰዎች ውስጥ አንዱ በእናቱም በአባቱም አማራ ስለመሆኑ መዘከር በመሆኑ ወደዛው እንለፍ፡፡
በመጀመሪያ ለመግባባት ይረዳን ዘንድ ቼ ጉቬራ ማነው? የሚለውን እናስቀድም፡፡ ደህና! ይህ ሰው እ.ኤ.አ በ1928ዓ.ም ሮዛሪዮ በምትባል አንዲት የአርጀንቲና ከተማ ተወለደ፡፡ ወላጆቹ ያወጡለት ሙሉ መጠሪያ ስሙ አርነስቶ ጉቬራ (Ernesto Guevara) ይሰኛል፡፡ ጉቬራም እድሜው ለትምህርት ደረሰ እናም ተማራ፤ ተመራመር፡፡ በህክምናም ከቦነስ አይረስ ዩንቨርስቲ ዲግሪውን አገኘ፡፡
ዶ/ር አርነስቶ ጉቬራ በህክምናው አለም ለመሰማራት ወደጓቲሟላ ሄደ፡፡ በጓቲማላም በአንድ ሆስፒታል ተቀጥሮ እስከ 1954 እ.አ.አ አገለገለ፡፡ ሆኖም በ1954 ሶሻሊስቱ የጓቲማላው ፕሬዘዳንት ጃኮቦ አርቤንዝ (Jacobo Arbenz) በአሜሪካ አቀነባባሪነት በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣኑ ሲባረር፣ ገና ከተማሪነቱ ጀምሮ የሶሻሊዝም አቀንቃኝ የሆነው ጉቬራ በቀጥታ ወደሜክሲኮ ተሰደደ፡፡ ነገር ግን በሜክሲኮ ከሚገኙ ሆስፒታሎች በአንዱም ስራ ይቀጠር ዘንድ አላመለከተም፡፡ ይልቁንም ከጥቂት ኩባውያን አብዮተኞች ጋር ጓደኝነት መሰረተ፡፡ ከእነዚህ ኩባውያን አብዮተኞች የአንደኛው ስም ፊደል ካስትሮ ይሰኛል፡፡
ጉቬራ እና ካስትሮ የነፍስ ትስስር ፈጠሩ፡፡ እናም ከሁለት አመት በኋላ (በ1956እ.አ.አ) ሁለቱ አብዮተኞች ሌሎች ስምንት ሴት እና ወንድ ወጣት አብዮተኞችን አስከትለው፣ ለታላቅ አብዮት፣ ለታላቅ ነውጥ ኩባ ገቡ፡፡
ኩባ ከገቡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የጄነራል ፉሌንሶ ባቲስታ (Fulgencio Batista) መንግስት ላይ መፈንቅለ መንግስት አደረጉ፡፡ ሆኖም ከሸፈባቸው፡፡ ይህ መፈንቅለ መንስት ሙከራም የJuly 26 Movement በመባል ይታወቃል፡፡
የፍንቀላውን መክሸፍ ተከትሎ እነካስትሮ አስራ ስድስት ሆነው፣ አስራ ሁለት አሮጌ ጠመንጃዎችን በማንገብ ወደበረሀ ገቡ-ሳይራ ማስትራ በረሀ፡፡
ምሽጋቸውን ሳይራ ማአስትራ (Sierra Maestra) ተራራ ላይ አድርገው ከባቲስታ መንግስት ጋር መፋለማቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ ወቅትም ኩባውያን አብዮተኞች ከባእድ ሀገር መጥቶ ለማያውቀው ህዝብ ደሙን የሚያፈሰውንና አጥንቱን የሚከሰክሰውን አርጄንቲናዊ አብዮተኛ በራሳቸው ቋንቋ ‹‹ቼ›› ሲሉ የበረሀ ስም አወጡለት፡፡ ትርጓሜውም ‹‹የእኛ›› ማለት እንደሆነ ነገሩት፡፡
ትግላቸውም ጋመ፡፡ የመንግስት ወታደሮችም በደፈጣ ተዊጊዎቹ በእነቼ ከባድ ጉዳት ይደርስባቸው ጀመረ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ከተሞችንም ነፃ ማውጣት ቻሉ፡፡ እናም ነፃ በሚያወጧቸው ከተሞች ለገበሬው መሬት እያከፋፈሉ ወደሀቫና ገሰገሱ፡፡ በድል ላይ ድል እያገኙም በጃንዋሪ 9 ቀን 1959እ.አ.አ ሀቫና ከተማን ተቆጣጠሩ፡፡ አዲስ የሶሻሊስት መንግስትም መሰረቱ፡፡
ፊደል ካስትሮ የኩባ ፕሬዘዳንት ሲባል፤ አለም አቀፍ አብዮተኛው ቼ ጉቬራም የእንዱስትሪ ሚንስትር ሆኖ ተሾመ፡፡ ከ1961-65 እ.አ.አ ድረስ ኩባን ካገለገለ በኋላ አፕሪል 15 ቀን 1965 በራሱ ፍላጎት ስልጣን ለቀቀ-ቼ፡፡ ስልጣን ከለቀቀ በኋላም በቀጥታ ወደቦሊቪያ ሄዶ የቦሊቪያ አብዮተኞችን ተቀላቀለ፡፡ ነገር ግን በ1967 እ.አ.አ. በቦሊቪያ መንግስት ወታደሮች ተማርኮ በዛው አመት ኦክቶበር 9 ቀን ተገደለ፡፡ ቼ ጉቬራ ማለት ይሄ ነው፡፡ ፋኖ ተሰማራ
እንደ ቼጉቬራ… ታሪክ ልትሰራ
ማለትም ይሀው ነው፤ ሌላ አይደለም፡፡ ቼ ጉቬራ፣ ቼ ጉቬራ፣ ቼ ጉቬራ፣ ቼ ጉቬራ…ቼ ጉቬራ፣ ሀገሩ ቬትናምን ከአሜሪካ ነፃ ካወጣው አጐት ሆ ቼሚኒ ጋር ስሙና ስራው ለኢትዮጵያውያን አብዮተኞችም አርአያ ሆነ፡፡ እናም በ1966ቱ ታለቁ የኢትዮጵያ አብዮት ዋዜማና ማግስት፣ ያ ትውልድ
ፋኖ ተሠማራ ፋኖ ተሠማራ
እንደ ሆ ቺሚኒ እንደ ቼ ጉቬራ
እያለ በመዘመርም ድፍን የሀበሻን ምድር አጥለቀለቀው፡፡ ተራሮች እና ኮረብቶችም ‹‹…እንደ ቼ ጉቬራ…›› በሚል ህብረ ዝማሬ ተንቀጠቀጡ፡፡ ተራራውን ያንቀጠቀጠ ትውልድ፡፡ የዚህ ትውልድ አካል የሆኑት የትግራይ ልጆችም ለትግራይ ነፃነት በረሀ ገቡ፡፡ እናም ህወሓት የሚባል ድርጅት መስርተው ተራራውን አንቀጠቀጡ፡፡ ከእነዚህ መስሯች እና መሪ ተራራ አንቀጥቃጮች ወይም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የትግራይ ተወላጅ አይደለም፡፡ የአማራ ተወላጅ ነው፡፡ ሆኖም እስከዛሬ ድረስ አንዳቸውም የህወሓት አመራሮች ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ ብለው አያውቁም፡፡ ህወሓትን ከመሰረቱት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አማራ የሆነ አንድ ሰው አለበት መባሉ በፍፁም በታሪካቸው እንዲካተት አይፈልጉም፡፡ እናም ይህን ያልተሰማ ዜና ለመስማት በጥፍራችው ቁሙ፡፡
በእርግጥም ከነገ በስቲያ በሚከበረው የህወሓት ምስረታ 37ኛ አመት ላይ ታሪኩ ስለማይነገርለት፤ እንዲሁም ያለፉት 36ት አመታዊ የድርጅቱ በአል ሲከበር ሽራፊ ታሪኩ ተነግሮለት ስለማይታወቀው አማራው ቼ ጉቬራ ልነግራችሁ ነው፡፡ መቼም ይህ ዜና የትግራይ ህዝብን ሲያስደስት፣ የታሪክ ‹‹ፎቢያ›› ላለባቸው የህወሓት ሰዎች ‹‹ኳክብት ይርገፉ፣ ፀሀይ ትጨልም፣ ጨረቃ አትድመቅ…›› ቢሆንም መነገር አለበትና እናገራለሁ፡፡
በኦርቶዶክስ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ አንድ ታላቅ በአለ ነግስ አለ፡፡ በየዓመቱ በህዳር 21ቀን የሚከበረው የአክሱም ማርያም፡፡ ታቦተ ጽዮን እንዳለ በሚነገርባት በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ከአራቱም አቅጣጫ፣ የመጡ የእምነቱ ተከታዮች ይሠባሠባሉ፡፡ ያን ጊዜም አክሱም ሞልታ ትፈሳለች፤ በሰው ጎርፍ ትጥለቀለቃለች፡፡
…እለቱ ህዳር 21 ቀን ነው፡፡ አመቱ 1967 ዓ.ም፡፡ ‹‹በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሠ ያለው የአማራ ጭቆናን እና ቅኝ አገዛዝን ከዚህ በላይ መሸከም አንችልም›› ያሉ ወጣቶች ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ (ማ-ገ-ብ-ት-) በሚል መጠሪያ ስም የመሰረቱት ድርጅታቸውን የፖለቲካ ፕሮግራም፣ በዚሁ እለት ታቦት ለማንገስ ለተሰባሰበው ምዕመናን በተኑት፡፡ ይህ ከሆነ ከከሶስት ወር በኋላ ማግበቶች፣ የደርግ መንግስትን ለመፋለም አስራ አንድ ሆነው በረሀ ገቡ፡፡ ከሺሬ ከተማ በስተምዕራብ በ80 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ ወደሚገኘው ደደቢት በረሃ፡፡
የተወለደው በ1929 ነው፡፡ ቼ ጉቬራ በተወለደ በአመቱ፡፡ ይህ ሰው ልክ እንደ ቼ ጉቬራ ከኢትዮጵያ ከተሞች በአንዱ የገጠር ከተማ ተወለደ፡፡ ከመሀል አዲስ አበባ 774 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጎንደር ክፍለ ሀገር፡፡ በእርግጥ የትውልድ ከተማው ከጎንደር ከተማም 118 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች-ድብ በሐር፡፡
በደባርቅ ወረዳ የምትገኘው ድብ በሐር ከተማ ከአምስት ሺ በላይ ሰዎች እንደሚኖሩባት ይነገራል፡፡ በፍራፍሬ፣ ጫት እና ዋንዛ እንጨት ምርቷም ትታወቃለች፤ ድብ በሐር፡፡ ለከተማው አንድ ለእናቱ ከሆነው ድብ በሐር አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስተቀር ምንም አይነት ትምህርት ቤት የለም፡፡ ይህች የገጠር ከተማ በአመት ሁለቴ ትደምቃለች፡፡ በአብዛኛው ነዋሪዎቿ ዘንድ በሚከበረው የድብ በሐር ጊዮርጊስ ደብር ንግስ እለት፡፡
የድብ በሐር ከተማ በርካታ ሰዎች በደርግ የግፍ አገዛዝ ከተወረወሩበት ሊማሊሞ ገደል ስር ትገኛለች፡፡ በህወሓት ታሪክ ውስጥም ጉልህ ስፍራ ሊይዝ የሚገባውን፤ ነገር ግን አመድ አፋሽ የሆነ አንድ ሰው አፍርታለች፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ቀን የተወለደውን-አብተው ታከለን፡፡
ስለአብተው የልጅነት ታሪክ የተፃፈ ነገር ባለመኖሩ ብዙ ማለት አይቻልም፡፡ ለነገሩ እንኳን የልጅነት ታሪኩ ቀርቶ የመሰረተው፣ የታገለለት፣ የሞተለት፣ የቆሰለለት፣ የወጣለት፣ የወረደለት… ድርጅትም ታሪኩን አልዘከረለትም፡፡
የሆነ ሆኖ አብተው ከደብ በሐር በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው የሽሬ ከተማ ሄደ፡፡ ኑሮውን በዛው አደረገ፡፡ የሽሬ ከተማ ግምጃ ቤት ሀላፊ የሆኑትን የባላባራስ አፅባሀ ልጅ ወ/ሮ አለም አፅበሀንም አግብቶ ሶስት ጉልቻ መሰረተ፡፡ ባለንባራስ አፅበሀ የሌላኛው የህወሓት መስራች ስሁል አየለ (ገሠሠ) አጎት ናቸው፡፡ ይሄ ሁኔታም አብተው እና ስሁል እንዲቀራረቡ መንገዱን ከፈተላቸው፡፡ እናም ከእለታት አንድ ቀን የትግራይ ህዝብን ከአማራ ጭቆና ለማላቀቅ እና ነፃይቱን ትግራይ ለመፍጠር ድርጅት መመስረቱ አስፈላጊ እንደሆነ ተወያዩ፤ አብተው ምንም እንኳ አማራ ቢሆንም፤ ‹‹የተጨቆነ ካለማ…›› ሲል ለመታገል ወሰነ፡፡ እናም ከሌሎች 10 የትግራይ ልጆች ጋር በመሆን ወደ ደደቢት በረሃ አመራ፡፡ አስራአንድ ሆነው ስድስት አሮጌ መሳሪያ ታጥቀው፡፡ ቼ ጉቬራም ከእሰራአምስት ኩባውያን እና ከአስራሁለት አሮጌ መሳሪያ ጋር አይደል እንዴ ሲይራ ማስተራ በረሀ የገባው፡፡ እናም በደደቢት በርሀ ህወሓትን መሰረተ፡፡ በእርግጥ አብተው ቼ ጉቬራ የሚሆነው ከህወሓት የምስረታ ታሪክ ስንነሳ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በህወሓት ታሪክ አፃፃፍ ህግ መሰረት አብተው አማራ የሚባል የሌላ ሀገር ሰው ሆኖ ስለምናገኘው ነው፡፡ ልክ ቼ ጉቬራ የአርጀንቲና ሰው ሆኖ ለኩባውያን ታግሎ፣ ለቦሊቭያውያን እንደሞተው ማለት ነው፡፡
ከህወሓት የፈጠራ ታሪክ ከወጣን ግን የአብተው በደደቢት መገኘት አስገራሚ አይሆንም፡፡ ቼ ጉቬራም አያሰኘውም፡፡ ምክንያቱም አስራ አንዱም በደም የተሳሰሩ ኢትዮጵያውያን ናቸውና፡፡ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ… ለአብተው ታከለም ሆነ፤ ለአስገደ ወ/ስላሴ አሊያም ለስዩም መስፍን የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ የአብተው ቼ ጉቬራነት ለህወሓት ብቻ ነው፡፡ እንዴት ብሎ? የሚጠይቅ ካለ መልሱ ግልፅ ነው፤ የትግራይ ህዝብ ህወሓት በሚለው ታሪክ አይስማማም የሚል፡፡
ህወሓት የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዓመት ታሪክ ነው ይልሃል፡፡ ነገር ግን ከህወሓት ውጭ ያለ የትግራይ ተወላጅን ብትጠይቅ ፍርጥም ብሎ ‹‹ሀገሬ ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ አመት ታሪክ አላት›› ይልሃል፡፡ ህወሓት በረሀ የገባው ትግራይ ለብቻዋ ነፃ አገር ነች እንጂ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም በሚል ነው፡፡ አሁንም ከህወሓት አመራር ውጪ ያለውን የትግራይ ተወላጅ ስለዚህ ሁኔታ ብትጠይቀው ጤንነትህን ይጠራጠረዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበርም አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ደማቸውን ያፈሰሱ እልፍ አላፍት የትግራይ ሰዎችንም ታሪክ ይነግርሃል፡፡ ከዚህም አኳያ ነው አብተው ለትግራይ ህዝብ ወንድም፤ ለህወሓት ግን ከባእድ ሀገር የመጣ ቼ ጉቬራ የሚሆነው፡፡
እነዚህ አስራ አንድ የመጀመሪያው በረሃ የገቡ ታጋዮች በስም ስንዘረዝራቸው ስሁል አየለ (ገሰሰ)፣ አረጋዊ በርሀ፣ ስዩም መስፍን (አምባዬ)፣ ግደይ ዘርአፅዮን (ፋንታሁን)፣ አጋዚ ገሰሰ (ዘርኡ)፣ አስፋሐ ሐጎስ (ሙሉ)፣ ፀሀዬ ካሕሳይ (አረፈአይኔ)፣ ምስጋና ቡርሀ (ካሕሳይ)፣ ቀለበት ታዬ (ንጉሴ)፣ አስገደ ወ/ስላሴ ( ወ/ሚካኤል) እና አብተው ታከለ (ሚካኤል) ይባላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ መስራቾች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእነሡ አንዱ የትግራይ ተወላጅ አይደለም፡፡ አማራ ነው፡፡ አብተው ታከለ ይባላል፤ ደደቢት በረሃ እብረውት የገቡ ጓደኞቹ ደግሞ ‹‹ሚካኤል›› ሲሉ ሰየሙት፡፡ አርንስቶ ጉቬራን ኩባውያን ‹‹ቼ-የእኛ›› ሲሉ እንደሰየሙት ሁሉ፣ የህወሓት መስራቾቹም አብተውን ከዋነኞቹ የመላዕክት አለቃ በአንዱ ስም ሰየሙት-ሚካኤል፡፡
የሆነ ሆኖ ህወሓት የአብተውን መስዋትነት ብቻ አይደለም የካደው፤ በርካታ የኢትዮጵያን ታሪክም እንጂ፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴን ታሪክም ከአፍሪካ ህብረት ድርጅት መስራች ታሪክ መፋቅም አንዱ የኢህአዴግ የታሪክ ግጭት ነው፡፡ ለምሳሌ ህወሓት ታሪክን ለመካድ ችግር እንደሌለበት ለመረዳት ሩቅ ሳንሄድ ጥር 27 ቀን 2004ዓ.ም በአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያ ትግርኛ ፕሮግራም ላይ የቀድሞ ሁለቱ የህወሓት ሊቀመንበሮች አረጋዊ በርሄ እና አቦይ ስብሓት ነጋ የተከራከሩትን ክርክር ሸርፈን እንየው፡፡ የክርክሩ መነሻ በቀድሞ የህወሓት የስለላ ሀላፊ የተፃፈው ‹‹ፍኖተ ገድል›› መጽሐፍ ሲሆን፤ መጽሐፉ የአክሱም ታሪክ የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው ማለቱ ነው ለውይይት ያቀረበው፡፡ መጀመሪያ አረጋዊ በርሄ የአክሱም ታሪክ የትግራይ ብቻ ሳይሆን፣ ከላይ ከቀይ ባህር ጀምሮ ድፍን ኢትዮጵያን አካሎ እስከ ሱዳንም የሚደርስ እንደሆነ አብራራ፡፡ አቦይ ስብሓት ግን ይህንን ማብራሪያ አምርረው ተቃወሙ፡፡ ተቃውሞአቸውንም በትግርኛ እንዲህ ሲሉ ገለፁ
‹‹ነቲ ፅሁፍ ግን ከም ባግራውንድ ካብ ትግራይ ወፃኢ ካብ ኤርትራ ወፃኢ ንኻልእ ከምዘልአልካየ፤ ንጋምቤላ፣ ንኻልዕ ዝሐውስ አይኮንን አክሱም፡፡ ትግራይ እውን ሙሉእ ትግራይ ዝሐውስ አይመስለንን፡፡ ተምብየን አካል ናይ አክሱማይት ኢምፓየር ዶ ነይሩ ዝብል ሕቶ አለኒ፡፡ ኢቨን ዓጋመ ነይሩ ዶ? አብ ሓደ አጋጣሚ ፐርፕለስ ኦፎ ዘ ኤርትርያን ሲ ዘብል ናይ ዓጋመ ስይም ዝብል አብኡ ሪኤ፤ ስያሞ አበይ እዩ እንተበልኩ ዓጋመ እዩ ኢሎምዎ በቲ ናይ ቀደም አፀዋውዓ ንሱዋን ፓርት ኦፎ አክሱማይት ከምዘይነበረ እየ ተረዲአ፡፡›› (ይህ ፅሁፍ እንደ መነሻ ሲወሰድ አንተም እንዳነሳከው ከትግራይና ከኤርትራ ውጭ ጋምቤላና ሌላም የሚያጠቃልል አይደለም አክሱም፡፡ ወደ ትግራይም ስንመጣ አሁን ያለውን ትግራይ በሙሉ የሚጨምር አይመስለኝም ተምቤን የአክሱማይት ኢምፓየር አካል ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ አጋሜስ ነበር ወይ? በአንድ አጋጣሚ ፐርፕለስ ኦፍ ኤርትራ መጽሐፍ ላይ የአጋሜ ስያሞ የሚል አየሁ፡፡ ስያሞ ማለት ደግሞ አጋሜ ነው ብለውታል፡፡ እናም አጋሜ የአክሱም አካል እንዳልሆነ ተገነዘብኩኝ)
መቼም ይህ የጤና አይመስለኝም፡፡ እንግዲህ የአክሱም ታሪክን ከመላው ኢትዮጵያ ከመንጠቅም አልፈው፤ መላው የትግራይ ህዝብንም አይወክልም ማለት ምን ማለት ይሆን?
በአቦይ ስብሃት የታሪክ ትረካ መሰረት አክሱም የኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ከትግራይም ተንቤን እና አጋሜ አውራጃ የአክሱም ታሪክ አይመለከታቸውም፡፡ ግዙፉ የአክሱም ኢምፓየርም በህወሓት ጊዜ ጠቦ፣ ጠቦ፣ ጠቦ…ከአንድ ቀበሌ የማይበልጥ ሆነ፡፡
በዚህ ስሌት ነው አብተው ታከለም ከህወሓት መስራቾች ታሪክ ዝርዝር ውስጥ የተደለዘው ወይም መስዕዋትነቱ የተነጠቀው፡፡ በእጅጉ የሚያስገርመው ትግራይ በቆመው የሰማዕታት ሀውልት ላይ የአስሩ መስራቾች ስም እና ፎቶ አለ፡፡ የአብተው ታከለ ግን ስሙ አለ፣ ፎቶው የለም፡፡ ይህ ሰው ፎቶ የለውም እንዳይባል ደርግ ከወደቀ በኋላም በህይወት ነበረ፡፡ እስከ 2000ዓ.ም በጎንደር ደባርቅ፣ ደብ በሐር ከተማ ከባለቤቱ ጋር ይኖር ነበር፡፡ የአራት ልጆችም አባት ነው፡፡ ህይወቱ ያለፈው በአንጀት ድርቀት ተሰቃይቶ ነው፡፡ በ1999ዓ.ም መታከሚያ ገንዘብ አጥቶ ወደ መቀሌ ሄደ፣ በመቀሌም አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እና ጉዳዩን የሰሙ የመቀሌ ነዋሪዎች ገንዘብ አዋጥተው ከመቀሌ ሆስፒታል ዶ/ር ኬዳኔ ጋር ተባብረው አሳከሙት፡፡ ለሁለት ወር ያህልም አቶ አስገደ ቤቴ ካረፈ በኋላ ወደ ትውልድ መንደሩ ጎንደር ድብ በሐር ተመለሰ፡፡ እዛም የሚንከባከበው አጥቶ ህይወቱ አለፈ፡፡ ያ የህወሓት ቼ ጉቬራ፡፡ የሰራው ታሪክ የሌላ ብሄር ተወላጅ በመሆኑ ብቻ ተቀበሮ እንዲቀር የተፈረደበት- ቼጉቬራ፡፡
በእርግጥ ህወሓት የአብተው ታከለን ታሪክና አማራነት ስለምን መደበቅ አስፈለገው? የሚለው ጥያቄ ዛሬ ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ ትውልድም የሚነሳ ይመስለኛል፡፡ ከህወሓት መስራቾች ውስጥ የተወሰኑት መጽሐፍ ፅፈዋል፡፡ ለምሳሌ አረጋዊ በርሄም ሆነ ግደይ ዘራፅዮን በመጽሐፋቸውም ሆነ ቃለ ምልልስ በሚሰጡበት ጊዜ ስለአብተው አማራነት ነግረውን አያውቁም፡፡ የብአዴን መስራቾችም ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሱ አልተሰሙም፡፡ ስለማያውቁ ነው እንዳይባል ያውቃሉ፡፡ ምናልባት ህወሓት የጠላውን መጥላት፣ ህወሓት የወደደውን መውደድ የሚለው ያልተፃፈው የህወሓት ህግ አስሮአቸው ሊሆን ይችላል፡፡