በእግዚያብሔር ህግ ላይ ድርድር የለም!
በእግዚያብሔር ህግ ላይ ድርድር የለም
“………..እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ ……..” የይሁዳ መልዕክት 1፡12
ሰሞኑን ከእምነቱ ተከታዮች እውቅናና ውክልና ውጭ ለወያኔ ባደሩ “አስታራቂ” ተብየዎች አማካይነት በሚስጢር ፊኒክስ ውስጥ በህጋዊው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ሲኖዶስና በህገውጡ የአባ ገብረመድህን “ሲኖዶስ” መካካል ሲካሄድ የነበረው ውይይት ለወያኔ በሚያመች ሁኔታ መደምደሙን ከስፍራው የሚናኙ ወሬዎች ያመለክታሉ። ከሁሉም በላይ የእግዚያብሔር ህግ እንደ ዓለማዊ ህግ በፖለቲካ ድርድርና ሰጥቶ መቀበል እንዲሁም “በእከከኝ ልከክልህ” የሚለወጥና የሚሻር ነገር እንዳልሆነ እየታወቀና “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” የሚለውን የወንጌል ቃል ደፍጥጠው በቤተክርስቲያኒቷ ታሪክ እንደ አርዮስ ክህደት የሚቆጠር ከፍተኛ ክህደትና ደባ ፈጽመዋል። የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ህግንና ቀኖና ጥሰው በነፍጥ አንጋቾች መንበረ ፓትርያርኩ ላይ የተቆናጠጡት አባ ገብረመድህን ወርደው ንስሃ ይግቡ፣ ትክክለኛው ፓትርያርክ ወደ መንበራቸው ይመለሱ በማለት ፋንታ የተጭበረበር የፖለቲካ ውሳኔ ማሳለፋቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤተክርስቲናኒቷን አማኞች እንደሚያበሳጭ ይታወቃል።
በአገራችን የተጣላ ሰው ለማስታረቅ እንደምሳሌ ሲነገር የኖረ ብሂልን እዚህ ላይ ማቅረብ ይጠቅማል። ይኽውም አንደ ሰው ሌላው ሰው በድሎት፣ ጎድቶት፣ ገንዘቡን ቀምቶት ከኖረ በኋላ በዳይ ለመታረቅ ቢፈልግ በመጀመሪያ ማድረግ ያለበት የቀማውን ገንዘብ መመለስ፤ ከዚያም ይቅርታ መጠየቅ በመጨረሻም መካስ ናቸው። አባ ገብረመድህን የቀሙትን መንበረ ፓትርያርክነት ሳይመልሱ ምን አይነት እርቅ ነው ሊደረግ የሚችለው? አታራቂዎችስህ ይህ ተራ ጸብ አለመሆኑን እያወቁና የእግዚያብሔር ህግ መጣሱን እየተመለከቱ አለማዊና ፖለቲካዊ መርዛቸውን ለምንድን ነው በየኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ላይ ለመርጨት የሚፈልጉት? በእግዚያብሔር ህግ ላይ ድርድር የለም። ወንጌሉ የሚያስተምረን “ እውነቱን እውነት በሉ፤ ሀሰቱንም ሀሰት በሉ” ነው። እርቅና ሰላም የቤተክርስቲያናችን የማዕዘን እራስ ናቸው። እርቅና ሰለም ግን እውነቱን ይዞ፣ ፈሪሃ እግዚያብሔርን ተመልክቶ እንጅ መካሄድ ያለበት በስልጣን ላይ ያለውን ለማስደሰት የሚደረግ ግን ቤተክርስቲያኒቷን በእጅጉ የሚጎዳና የህዝበ ክርስቲያኑን እምነት የሚያቀጭጭና የሚያጨልም ነው። በቅርቡ በዚህ ርዕስ ላይተጨማሪ ዘገባ ይቀርባል።