ባህላችን ቀስ በቀስ እንዳይጠፋ ሠጋሁ በአሸናፊ ቀለሙ
በጨዋታ መካከል አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝን በቅድሚያ ማንሳት ፈለግኩ፡፡ እንደ ጓደኛዬ፡ አንድ ጉርጥ ነበረች በመጀመሪያ በሞቀ ውሃ ውስጥ ሰዎች ጨመሯት ውሃው ስላቃጠላት በፍጥነት ከውሃው ዘላ ወጣች፡፡ ቀጥሎ ቀዝቃዛ ውሃ ላይ ቢጨምሯት እንደ ቀድሞው ዘላ አልወጣችም፡፡ ቀስ በቀስ ውሃውን እያሞቁት ቢሄዱም ልትወጣ አልፈለገችም፡፡ ከቆይታዎች በኃላ ግን ሳታውቀው ሙቀቱ እየጨመረ ሄዶ ተጐድታ ኖሮ ሞተች፡፡ አየህ አለኝ ጓደኛዬ፡ እኛነታችንን የምናጣው ቀስ በቀስ እንጂ በአንድ ጊዜ አይደለም፡፡ መጠጥትን ፡ ስካርን የምንጠላ ሰዎች የጓደኞቻችንን የመጀመሪያ ጊዜያት ግብዣዎች በፍፁም አንቀበልም፡፡ የሞቀው ውሃ ላይ እንደተጨመረችዋ ጉርጥ፡፡ ነገር ግን ጓደኞቻችን በሻይ ቡና ያለማምዱናል ፣ ከዛ ለስላሳም ቢሆን ይዘህ እንጫዎት በጊዜ ገብተህ ምን ትሠራለህ ይሉናል፡፡ ልብ በሉ ቀስ በቀስ ውሃውን እያሞቁብን ነው፡፡ ከዛ በቃ አንድ እስቲ ሞክር ምንም አይልህም ይሉናል፡፡ እኛም የመጠጡን ሽታ ሁለመናውን እየለመድን ስለመጣን አንዴ መሞከር ብቻ ከዛ በኃላ ጋባዥ የማንፈልግ እንሆናለን፡፡ እንደ ጉርጧ ቀልጦ መቅረት ማለት ይሄ አይደል፡፡
ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት የጐንደር ካርኒቫል ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሪፖርተር (http://www.ethiopianreporter.com) በጽሑፋቸው ስለ በዓሉ አከባበር ገልፀውልናል፡፡ ከጓደኞቼም ሆነ ከተለያዩ ድኀረ ገጾች የተዘበራረቁ ሃሳቦች ተሰጥተዋል እየተሰጡም ነው፡፡ እኔም ሃሳቤን ለመሠንዘር ብዕሬን አንስቻለሁ፡፡ በሚቀጥለው እሮብ የጥምቀት ባዕል የሚከበር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን መንፈሳዊ አከባበሩ ከ ፈንጠዝያው ጋር እንዳይምታታብን ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ይቅርታ ይህ ጽሑፍ የዘገየ ይመስለኛል፤ ጥቂት ቀናት ቢቻል ደግሞ ሳምንታት ሊቀድም ይገባው ነበር፡፡ “… ከሃይማኖታዊና ባህላዊ አከባበሩ በተጓዳኝ በየመንገዱ ፈንጠዝያውን ሊያስተናግድ የሚችል ባህላዊ መጠጥና ባህላዊ ምግብ የሚኖርበት…” ከኢትዮጵያን ሪፖርተር የተወሰደ፡፡ ይህንን ባነበብኩና ባሰብኩ ጊዜ ከበዓሉ አከባበር በስተጀርባ አላዋቂነት ወይም እያወቁ ትልቅ የታሪክ ክፍተትን የሚፈጥሩ ሰዎች ያሉ ይመስለኛል፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ተጎጂዋ ቤተ/ያን ናት፡፡ ያሰብኳቸውን ጉዳዮች በሁለት ከፍዮ ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡
1) እንደ መርሃ ግብሩ መሠረት መጠጥ፣ ጭፈራ የተለያዩ ነገሮች ሊካተቱ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ባህሉን ከመንፈሳዊ ይዘቱ ወደ ዓላማዊ ይዘትነት እንዳይሸጋገር ከፍተኛ ሥጋት አለኝ፡፡ እዚህ ጋ ዳንኪራ፣ እዛ ጋ ልብን የሚመስጥ ዜማና መንፈሳዊ አገልግሎት፡፡ ሁለቱ ባንድነት የሚሄዱ ስላልሆኑ እንደ ክርስቲያንነቴ ካሁኑ ቢቀር ደስተኛ ነኝ፡፡ ለምን ክርስቲያን ሲባል ለዘብተኛ እንደምንሆን አይገባኝም፡፡ ምናለበት እንደዚህ ቢደረግ፣ እኔን እስካልነካኝ ድረስ ግድ የለኝም የምንል ብዙዎቻችን ነን፡፡ ይህ የኔ ኃላፊነት የእኔ አይደለም የምንለውንም ቤቱ ይቁጠረው፡፡
ነገር ግን የቱሪዚም ባለስልጣናትና ሌሎች የመንግስት አካላት የበዓሉን አከባበር እንዳሉት የሚያካሂዱት ከሆነ ከቤተክህነት፣ ከሰባኪያን፣ ከመዘምራን፣ ከሌላው የኦርቶዶክስ አማኝ ምን ይጠበቃል???????????? ይህ ጥያቄ መመለስ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ ወደ መጣሁበት ልመለስና፡ በአንድ ጊዜ መከበር ካለበት አንዳንድ ነገሮችን አስቀድመን በጥንቃቄ ልናያቸው ይገባናል፡፡ ባህላዊ ዘፈን፣ ውዝዋዜ የእኛነታችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡም ቢሆን እነዚህን ነገር አይጠላም (ሁሉም በስርዓት ከሆነ ክፋት የለውም)፡፡ የማሲንቆ ፣ የአዝማሪዎች አገር ተብላ ለምትጠራዋ ጐንደርም ትልቅ መገለጫዋ ነው፡፡ ለምን ዓለማዊውንና መንፈሳዊ አገልግሎት ለያይተን አናከብራቸውም ታድያ፡፡ ጥር 10፣ 11 እና 12 እንደ ቀደመው ጊዜ የጥምቀት በዓልን ብቻ ለምን አናከብርም፡፡ የተለያዩ መንፈሳዊ እይታዎችንና አገልግሎቶችን መጨመር የሚቻል ሲሆን ምናልባትም የሸክላና የእንጨት የእደ ጥበብ ውጤቶች የሚታዩበትና የሚገበዩበት ትዕይንት በነዚህ ቀናት ሊከናወኑ የሚችሉበት መንገድ ማመቻቸት ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ቀናት ውጭ (የጥምቀትን መንፈሳዊ አከባበር በማይነካ መልኩ) ማለትም አስቀድመን ጥር 8 እና 9 ወይም በስተመጨረሻ ጥር 13 እና 14 ኢትዮጵያ በጐንደር ካርኒቫል የሚለውን ለምን አናከብርም፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በመርሃ ግብሩ ዝግጅት ላይ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ በካርኒቫሉ የብሔር ብሔረሰቦችን አለባበስ፣ እስከስታ ውዝዋዜ ባጠቃላይ ሌሎች ባህሎችን ማንፀባረቅ ይቻላል፡፡
2) ሁለተኛው ሥጋቴ፡ የጉርጧ እንዳይከሰትብን ነው፡፡ ለዘላለም የቆየውንና ሁላችንም በየጊዜው የምንናፍቀውን ትውፈታችንን ቀስ በቀስ እንዳይገድለው ፈራሁ፡፡ የእኛ ትውልድ መንፈሳዊነት እንደ ኃላ ቀርነት እያየ በመጣበት ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች በፍጥነት ማንነትን ሙሉ በሙሉ የሚያጠፉ ናቸው፡፡ እንደ መፍትሔ፡ ሁላችንንም ምናለበትንና ለዘብተኝነት አቁመን መንፈሳዊ የሆኑ በዓሎቻችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል፡፡ ጥምቀት ለእኛ እንደሚያስደስተንንና ትልቅ መንፈሳዊ አስተምህሮ (አምላክ በመጥምቁ ዩሐንስ የተጠመቀበትን ፣ አንድነቱን እና ሦስትነቱን የገለጠበትን ቀን እናስታውሳለን) ያለው በመሆኑ ልጅ ልጆቻችን የዚህ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠብቅብናል፡፡ የኢትዮጵያ ቤ/ያን ብዙ ፈተናዎች በየጊዜያቱ ቢገጥማት ለማለፍ ችላለች፡፡ ትውፊትን ከመንፈሳዊነት ጋር አካሂዳ በመቀጠሏ ይመስለኛል እምነታችንን ከሌሉቹ በተሻለ ሁኔታ የጠበቅነው፡፡ እንደ አውሮፓውያንና እንደ ሌሎቹ ከሆነማ መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እያሉ ትውሉዱን ከቤ/ያን አራቁት፡፡ የገና በዓል ባሁኑ ጊዜ ባጠቃላይ ዓለማት ፤ መንፈሳዊ በዓልነቱ ቀርቶ የሥጦታ እና የህፃናት በዓል ሆኗል፡፡ የየግላችንን የልደት በዓል በምናከብርበት ጊዜ እኛ የተወለድንበትን ቀን እንደምናስብና እንደምናከብር፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምንኛ ማክበር ይገባን ይሆን? አለበለዚያ ክርስቲያን ነን ማለት የሥም ብቻ ይሆንብናል፡፡ ቀስ በቀስ ማንነትን የማጣት ችግር ኢትዮጵያን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃት ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ነው አንዳንዶቹ እኛ (ምድራችን) የቅኝ ግዛት ሰለባ ባትሆንም ህሊናችን ከመገዛት አልፎ በአውሮጳና በአሜሪካ ውስጥ ነው ያለው ሲሉ የሚደመጡት፡፡ የሚገርም ህዝብ ሱሪ ከአሜሪካ ተላከልኝ ብሎ በጓደኞቹ የሚያክት…. ስንቱ ተዘርዝሮ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ በፌስ ቡክ (Face book) የማየው በጣም ይከነክነኛል ስለ የገና አባት (Christmas Father) እና ሁለችንም ለኢትዮጵያዊም ቢሆን የፈረንጆቹን ገና ነው እንኳን አደረሳችሁ የምንለው፡፡ የሌላውን ባህል ማወቅ ምንም ክፋት የለውም በአንድ ጠባብ ዓለም ስለምንኖር፡፡ ነገር ግን የራሳችን ስላለን የእኛ እንዳንለቅ፡፡
በመጨረሻ መልዕክቴ እኛ ለማደግ፣ ለመበልጸግ፣ እንደ “ነጮቹ” (ይቅርታ መልክም ማየት ስለጀመርን ነው) መልበስ፣ መጠጣት፣ ማውራት፣ ባጠቃላይ እንደ እነርሱ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ እኛ እንደ እኛ ሆነን ማደግ እንችላለን፡፡ የእኛን እድገት የገታው፤ የበዓል አከባበራችን ሳይሆን አስተሳሰባችን ነው፡፡ አበሻ ማለት በሌለው የሚኮራ የሚኮፈስ ምቀኛ ህዝብ ነው (እኔን ጨምሮ)፡፡ ሰውን በመናቅ ደግሞ አንደኛዎቹ ሳንሆን አንቀርም፡፡ ባክህ እሱ ተወው፡ ዝም ብሎ፣ እሱ ቀጥቃጭ አይደል፣ የእንትን ቤተሰብ አይደል እንላለን፡፡ ብረታ ብረትን የሚቀጠቅጡትን ባንንቅ ኖሮ ለዘመናት ያክል በበሬ የምናርስ ይመስላችሁ ነበር፡፡ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እኮ ቀስ በቀስ እያደጉ የሚመጡ ናቸው፡፡ ለአነስተኛ እደ ጥበቦች አድናቆትን ካልሰጠን መቼም አንለወጥም፡፡ “ነጮቹ” ከዚህ አንጻር በጣም ይቀድሙናል፤ የትኛውንም ሥራ ያከብራሉ፡፡ መኮረጅ ካለብን እንደዚህ ዓይነቱን ነበር፡፡ አበዛሁ መሰለኝ እንዳትሰለቹኝ እዚህ ላይ ላብቃ፡፡
ማንነታችንን ቀስ በቀስ እንዳናጣ እንንቃ!! ለብርሃነ ልደቱ በሠላም ያደረሰን ለብርሃነ ጥምቀቱም በሠላም ያድርሰን፡፡ አሜን፡፡
“ባሕር አየችው ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደ ኃላው ተመለሰ ተራሮች እንደ በግ አውራ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፡፡” መዝ 113፡3