አቡጊዳ – አቶ አንዱዋለም ቶርቸር ተደረጉ -ፊታቸዉ ተላልጧል፣ አይናቸዉ አብጧል !

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት፣ አቶ አንዱዋለም አራጌ በእሥር ቤት ፣ ከእሥር ቤት ሃላፊዎች በተላከ ሌላ እስረኛ እጅ፣ ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

አቶ አንዱዋለም የተደበደቡት ከትላንትና ወዲያ እሮብ ቀን ሲሆን ፣ ጉዳዩን ለመከታተልና አቶ አንዱዋለም ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ፣ ዛሬ ጠዋት ወደ እሥር ቤት የሄዱት የአቶ አንዱዋለም ቤተሰቦችና የአቶ አድንዋለም ጠበቃ፣ አቶ አንዱዋለም እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ እንዳገኟቸዉ ይናገራሉ።

ብዙ ጊዜ አቶ አንዱዋለም በእሥር ቤት ቢሆኑም፣ ደስተኛ፣ የተረጋጉና መንፈሰ ጠንካራ ሰዉ እንደሆኑ የገለጹት ቤተሰቦቻቸው ፣ ዛሬ ግን እጅግ ተጎሳቁለዉ፣ እንዳገኟቸው፣ ፊታቸዉ በድብደባ እንደተላላጠና ፣ በቀኝ አይናቸው በኩል ትልቅ እብጠት እንደሚታይ ገልጸዋል። አቶ አንዱዋለም ቤተሰባቸዉንና ጠበቃቸዉ ባገኙበት ጊዜ ፣መንፈሳቸዉ ተሰብሮ ያለቀሱ ሲሆን ከዚህ በፊት አይተዉ በማያዉቁበት ሁኔታ ከፍተኛ የራስ ሕመም እንደያዛቸው ለማወቅ ችለናል። ይሄን ያህል ዘግናኝ ድብደባና ቶርቸር የደረሰባቸው አቶ አንዱዋለም፣ ምንም አይነት ሕክምና አላገኙም። «እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ» ሲሉም ያላቸዉን ፍርሃት ገልጸዋል።

አቶ አንዱዋለም ሶስተኛ ዞን በተባለዉ ፣ እሥራ አራት ሰዎች በሚገኙበት መስኮት በሌለው ክፍል፣ ከአቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ኦልባና ሌሊሳና ዶር ጥላሁን ፋንታሁን ጋር ታስረዉ ባለቤት፣ ከአንድ ወር በፊት ኢብሳ አስፋዉ የሚባል ወንጀለኛ እንደተቀላቀላቸው የደረሰን ዜና ያትታል።

ኢብሳ አስፋዉ በነፍስ ግድያ ለአሥራ ስድስት አመታት የታሰረ ፣ የሚተላለፍ በሽታ ያለበት፣ የሚሳደብ፣ የሚደባደብ፣ ነገር የሚፈልግ ፣ በእሥር ቤቱ የሚጠላ ፣ የሌሎች ታሳሪዎች ምግብ የሚነጥቅ፣ ከእሥር ቤት አስተዳዳሪዎች ጋር የቅርብ ወዳጅኘት ያለዉ፣ በሃላፊዎች ቢሮም በብዛት የሚሄድ እንደሆነ ምንጮቻችን ይገልጻሉ።

ኢብሳ አስፋዉ ፣ ከአራት ቀናት በፊት አቶ አንዱዋለምን መስደብ ይጀምራል። አቶ አንዱዋለም ከሁለት ሳምንታት በፊት በፍርድ ቤት የሚያቀርቡትም መከራከሪያ ነጥቦች የጻፉበትን ወረቀት ወስዶ ይጥላል። ከሶስት ቀናት በፊት ሌላ ሁለተኛ እሥረኛ ከሌላ ክፍል ይመጣል። ከአቶ አንዱዋለም ጋር የሚናገገሩት ሚስጥር እንዳለ በመግለጽ በቦታዉ የነበሩ አቶ በቀለ እና ዶር ጥላሁን፣ ለጊዜዉ ከክፍሉ እንዲወጡ ያዟቸዋል። አቶ በቀለ እና ዶር ጥላሁን አንወጣም ይላሉ። ያን ጊዜ ኢብሳ ቀጥታ ወደ አቶ አንዱዋለም ሄዶ፣ በቡጢ መደብደብ ይጀምራል። አቶ አንዱዋለም ሕሊናቸዉን ስተው ይዘረራሉ። አቶ በቀለ ፣ ኢብሳን ወደ ጎን ለማድረግ ሲሞክሩ፣ ዶር ጥላሁን የእሥር ቤት ጠባቂዎችን ይጠራሉ። ጠባቂዎቹ ይመጣሉ።

ከዚይ በኋላ ኢብሳን ወደ እሥር ቤት አስተዳዳሪዉ እንደተወሰደ በዚያም 2300 ብር እንደተከፈለዉ ምንምጮቻችን ይጠቁማሉ።

የአቶ አንዱዋለም ጠበቃ ለእሥር ቤት ሃላፊዎች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች፣ ሃላፊዎቹ እስረኞችን በፈለጉበት ቦታ የመመደብ ስልጣን እንዳላቸው ፣ ለኢብሳ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድበት ፣ የአቶ አንዱዋለምን ወረቀት ከኢብሳ እንደሚቀበሉ፣. አቶ አንደዋለም ከፈለጉ መስከስ እንደሚችሉ በመግለጽ፣ በአቶ አንዱዋለም ላይ ለደረሰዉ ኢሰብዓዊ የጭካኔ ተግባር ደንታ እንደሌላቸው አሳዉቀዋል።

ኢብሳ ይህን ድርጊት የፈጸመዉ፣ ታዞ እንደሆነ የገለጹት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡን፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ድርጊቱ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እንደደረሰው፣ በሶቬት ሕብረት ጉላክ እሥር ቤቶች እንደነበረዉ፣ አቶ አንዱዋለምን በስነልቦ በመንፈስ፣ በስሜትና በአካል ለመሰባባር እና ለማዋረድ፣ የአይምሮ በሽተኛ ሆነዉ አቶ አንዱዋለምን ከጨዋታ ዉጭ ለማድረግ፣ ሆን ተብሎ የተፈጸመ አሳፋሪ ፣ ኢሰብዓዊና ኢፍትሃዊ ድርጊት እንደሆነ ያናገራሉ።

በጉዳዩ ላይ የፓርቲዉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምን አይነት እርምጃ መዉሰድ እንዳለበት ለመነጋገር አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያደርግ የገለጹት ዶር ነጋሶ፣ በአገር ዉስጥ እና ከአገር ዉጭ የሚኖር ሰላምና ዴሞክርሲ ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ ይሄን አሳዛኝ ክስተት እንዲያወገዝ፣ ለአለም አቀፍ ማህበርሰብ፣ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ለሚመለከታቸው ኃይላት ሁሉ እንዲያሳዉቅ፣ አቶ አንዱዋለም አስቸኳይ ሕክምን እንዲያገኑ ከፍተኛ ግፊት እንዲደረግ፣ ይህ አይነቱን ጸረ-ሰላም፣ ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ፍትህ የሽብር ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዳይኖር ለማድረግ፣ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቅርበዋል።