ወይ ቫለንታይን… ወይ የፍቅር ቀን…!? በፍቅር ለይኩን፡፡

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአገራችን የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲሁም የመዝናኛ ስፍራዎች ‹‹የቫለንታይን ቀን›› ወይም በሀገሪኛው አገላለፅ ‹‹የፍቅረኞች ቀንን›› በተመለከተ እለቱን በሚያዘክሩ የተለያዩ ዝግጅቶችና የሙዚቃ ድግሶችን በማዘጋጀት ፍቅረኞች እለቱን በደስታና በሐሴት እንዲያከብሩት ሽር ጉድ የሚሉበትን ሁኔታ እየታዘብን ነው፡፡ ይህ እለትም ለአበባ ሻጮች፣ ለስጦታ ዕቃ መሸጫ ሱቆችና መዝናኛ ስፍራዎች ሞቅ ያለ ገቢ የሚያገኙበት የሞቀና የደራ የገበያ እለትም እየሆነ እንደመጣ ልብ ይሏል፡፡

በእለቱ ኮረዶችና ጉብሎች እንደ ዘመነ ኮሚኒስቱ ሥረዓት በቀይ አልባሳት የሚደምቁበት ቀን ነው፣ በእጆቻቸውም ላይ ለፍቅራችን ታማኝ በመሆን እስከ ሞት ድርስም እንኳን መስዋዕት ቢያስከፍለን ወደኋላ አንልም ሲሉ የቃል ኪዳናቸው ምልክት ይሆን ዘንድ የቀይ አበባ እንቡጥ በመለዋወጥ ቀኑ በቀይ አበባ፣ በቀይ አልባሳት፣ ካፌዎችና መዝናኛ ስፍራዎችም በቀይ ምንጣፍና በቀይ አልባሳት ያሸበርቃሉ፤ ይደምቃሉ፡፡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ለስለስ ያሉ የፍቅር ዜማዎች ሌላው የእለቱ ማድመቂያዎች መሆናቸው ጭምርም ሳይረሳ፡፡

በሀገራችንም ያሉ የኤፍ ኤም ሬዲዮኖቻችን እለቱን ለማዘከር ቀኑን በፍቅር ዜማዎችና በፍቅር ጭውውቶች ለማድመቅ ሲጥሩ መዋላቸውን ታዝበናል፡፡ ፋታ የሌለው ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የበርካታ አድማጮች የእንኳን አደረሳችሁ የስልክ መልእክቶቻቸውም አጀብ የሚያሰኝ ሆኖ ነው የዋለው፣ ለዚሁ ለቫለንታይን ቀን መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡

በዚህ ሁኔታ ሞቅ ደመቅ ባለ ሁኔታ እየተከበረና የብዙዎችንም ቀልብ በመሳብ ላይ የሚገኘው የቫለንታይን ቀን በተለይ ለአዲስ አበባ ወጣቶች ቀኑ መቼ በደረሰ በሚል በናፍቆት እንዲጠበቅ እያደረገው እንደሆነ ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡ ከባህላችን እያፈነገጥን ነው፡፡ ይህ የእኛ ባህልና ወግ አይደለም፣ ከማንነታችን እየራቅን፣ ከራሳችን ጋር እየተጣላን ነው የሚሉ ወገኞች ይህንን ከዓመት ወደ ዓመት ዝናውና ድምቀቱ እየጨመረ የመጣውን የቫለንታይን ቀን በማውገዝ ቢናገሩም ቢፅፉም እምብዛም ሰሚ ጆሮ አስተዋይ ልብ ያገኙ አይመስልም፡፡ ምን አለ መኮረጅ፣ መከተል ካለብን የምዕራባውያኑን የስራ ፍቅር፣ ለጊዜ የሚሰጡትን ዋጋና መረዳዳታቸውን መውረስ ብንችል እንዴት ባማረብን ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ክርክሩ አሸናፊም ተሸናፊም ሳይኖረው የዘለቀበትን እውነት ነው እያስተዋልን ያለነው፡፡

ሌሎች ደግሞ በቅንነት መንፈስ ሆነው የፍቅር ቀንን ማክበር ካለብን በራሳችን ባህል፣ በአገራችን ወግና ስርዓት፣ በሀገራዊ ስሜትና ኩራት፣ በእውነተኛ ፍቅር፣ በመተሳሰብና በመረዳዳት ብናከብረውስ፣ እስከ መቼ የውጭ ናፋቂ እንደሆንን እንዘልቃለን፣ መቼ ነው ለራሳችንና በእጃችን ላለው ነገር ክብር የሚኖረን በማለት እንደውም አልታወቀንም እንጂ አስቸኳይ መፍትኄ በሚሻ በምዕራባውያን የመንፈስ ቅኝ ግዛት ውስጥ የሚማቅቅ ትውልድ ነው እያፈራ ነው ያለነው አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት ሲሉ ፍርሃታቸውን የሚገልጹ ሰዎችም እየተበራከቱ ነው፡፡
የዚህ ጹሁፍ ዋና ጭብጥ ስለ ‹‹ቫለንታይን ቀን/የፍቅረኞች ቀን›› የግራ ቀኙን ክርክር በመዳኘት የተቃውሞና ድጋፍ ድምፅ ለመስጠት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የእኛ ባልሆነ፣ ትርጉሙ በቅጡ ባልገባን፣ በተውሶ ባህል፣ ከጨዋነት፣ ከሀገራችን ባህልና ወግ እንዲያም ሲል ለመንፈሳዊ ሕይወት በማይጠቅም ረብ በሌለው በየዘመኑ ንፋሳት መወሰድ እንደሌለብን ለክርስቲያን ወገኖቻቻችን ማስተላለፍ የምፈልገው ቁም ነገር አለ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-

እንግዲያውስ ወንድሞች ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ፣ በቃላችንም ቢሆን በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ፡፡ … ወንድሞች ሆይ፣ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ስርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፡፡ ፩ተሰ ፪፣፲፭ ፤ ፫፣ ፮፡፡
በማለት ክርስቲኖች ለወንጌል እንቅፋት ከሚሆን ከመንፈሳዊ አባቶቻቸው ከተቀበሉት መልካም ባህል፣ መንፈሳዊ ስርዓትና ወግ ውጭ እንዳይሆኑ በማስጠንቀቅ ያስተላለፈው መልእክት ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖች በተለይም ደግሞ ለወጣቱ ትውልድ ብዙም ስሜት የሚኮረኩርና አድማጭ ጆሮ ያገኘ እንዳልሆነ እየታዘብን ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ መሰልጠን ነው፣ ማወቅ ነው እየተባልን ነው፡፡ ድንቄም ማወቅ! ድንቄም መሰልጠን! የሚል ድምፅ ተሰማኝ ልበል፣ ወይስ ጆሮዬ ነው…!?

እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከዚያም ሲያልፍ እንደ ክርስቲያን ትውልዳችን እየነጎደበት ላለው የጥፋት መንገድ፣ እየሳተና እያሳተ ከራሱና ከማንነቱ ከጠፋበት ጉዞው ይገታ ዘንድ፣ ትውልዱ ሀገሩን የሚወድ፣ የራሱ የሆነውን መልካም ነገር ሁሉ የሚያከብር፣ ለወገኑ ፍቅርና ክብር ያለው ይሆን ዘንድ ቤተክርስቲያንም፣ ሆነ እኛ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ትውልዳችንን እንደርስለትና እንታደገው ዘንድ የተጣለብንን ትልቅ መንፈሳዊ ኃላፊነት እንዴት እየተወጣን እንደሆነ ወደ ኋላ ዞር ብለን መፈተሸ ያለብን ጊዜ ላይ እንደምንገኝ መግለፅ እወዳለሁ፡፡
በዘመናችን በትውልዳችን ላይ እያየነው ያለው ዝብርቅርቅ፣ ቅጥ ያጣ የምዕራባውያን ባህል ጥገኝነት፣ የመንፈስ ቅኝ ግዛትና ከገባበት የማንነት ቀውስ (Identity Crisis) ውስጥ ይወጣ ዘንድ ከጸሎታችን ባሻገር የተግባር ምላሻችንን ይጠብቃል፡፡ በቃላችንና በኑሮአችን መልካምና የፍቅር መገለጫ የሆነውን የአኗኗራችንን የሕይወት ምስክርነት ትውልዱ ከእኛ ከክርስቲያኖችና ከአገልጋዮች ዘንድ ማየትን ይሻል፡፡ የምንሰብከውን የክርስቶስ ኢየሱስን ቅዱስ ወንጌል መኖር ካልቻልን የሚሰሙንና የምናፈራቸውም የእኛኑ ፈለግ የሚከተሉ የሕይወት መካን፣ ፍሬ አልባ የሆኑ የቃል ሰዎች ናቸው የሚሆኑት፡፡

እኔ እንደማስበው እያንዳንዱ ቀን ‹‹የእግዚአብሔር የፍቅር ስጦታ ቀን›› እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እያንዳንዱ በእድሜያችን ላይ የሚጨመር ቀንም ፍፁምና ልዩ ወደ ሆነው የእግዚአብሔር ፍቅር በንስሓና በመመለስ፡- ምሕረትን፣ እውነትንና ፍቅርን ወደሚገኝበት ወደ አምላካችን የጸጋ ዙፋን ስር በእምነት የምንቀርብበት ከብዙዎች ተለይቶ የተሰጠን ዳግመኛና ልዩ እድል እንደሆነ ጭምርም፡፡ የዛሬዋን አዲስ ቀን ለማየት እየናፈቁ ያን እድል ያላገኙ ብዙዎች አሉና ሰለዛሬዋ አዲስ ቀን፣ በእድሜያችንም ላይ ስለተጨመረልን ስለዚህች ቀንም አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል፡፡ የፍቅርን ቀን አስመልክቶም መቼም ቀኖች ሁሉ የፍቅር ቢሆኑልን የሁላችንም ጸሎትና ምኞት እንደሆነ አስባለሁ፡፡

ግና ዛሬ ዛሬ በከተማችን ‹‹የቫለንታይን ቀን›› በሚል ስያሜ እያየነው ያለው የፍቅርኛ ተብዬዎች ቀን ግን በስልጣኔ ስም የተላከብን ትውልዱን ለሌላ ርኩሰት ለሌላ ጥፋት ድግስ የሚጋብዝ የርኩሰት ቀንን በስምምነት ህጋዊ የሚያደርግ ወደ መሆን እያሸጋገረን ነው፡፡ የየቀኑ ኃጢአትና ርኩሰት እንዳይበቃ ቀን ተለይቶለትና ተወስኖለት በዳንኪራ፣ በመዳራትና በዝሙት ፍትወት መቃጠል አፍላ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ወደ ጥፋት መንገድ የሚነጉዱበት፣ የእኛ ባልሆነ ባህልና ማንነት ብዙዎች ሰልጥነናል፣ አውቀናል በሚል ባዶ ኩራት በራሳቸው ለራሳቸው የጥፋትን ነጋሪትን የሚጎስሙበት እለታቸው መሆኑን ስንታዘብ በእጅጉ ልባችን ያዝናል፣ እንደ ክርስቲያንም መንፈሳችን ይታወክብናል፡፡

በቫለታይን ቀን በፍቅር ስም በከተማችን የታዘብኩት እውነት ቢኖር ጭል ጭል በሚል የሻማ ብርሃን በየመዝናኛው የታደሙ ወጣት ተባዕትና እንስቶች ተስፋና ብርሃን ወደ ማይታይበት ድቅድቅ የጨለማ ሕይወት ሲጣደፉና በፍቅር ስም የአፍላ ወጣቶቻችንን አሳዝኝ የጥፋት ጉዞ ዘግናኝ ትእይንት ያየሁበት፣ ፍቅር ከተራ ቋቋነት በእጅጉ ወርዶ፣ ከእውነትና ከንፅህና አደባባይ ተሸሮ በፋንታው ራስ ወዳድነትና የማሰመሰል ሕይወት የተንሰራፋበትን፣ ነውር ክብር የሆነበትን የከተማችንን የምሽቱን ሽር ጉድ በመታዘብ ፍቅር ይሄ ነው እንዴ… የቫለንታይን ቀንስ ለእኛ ምናችን ነው… ፍቅርን ማክበር፣ ፍቅርን መዘከር ካለብንስ በእንዲህ ሁናቴ ነው እንዴ!? ትውልዳችንስ ወደየት አቅጣጫ ነው እየሄደ ያለው በማለት እጅግ በዳመነ ስሜት ራሴን ለመጠየቅ ተገደድኩ፡፡

ፍቅር ክብር፣ ፍቅር ነፃነት፣ ፍቅር ንፅህና፣ ፍቅር የሕይወት ብርሃን ነው… ፍቅር ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ ፍቅር የተለየ ቀን፣ ፍቅር ክብር፣ ፍቅር ማስታወሻ ይገባዋል ካልንም በፍቅር ቀን ሊሰበክ የሚገባው እውነት፣ ንፅህና እንጂ የጥፋት ርኩሰት ሊሆን ባልተገባው ነበር፡፡ በእለቱ ያየነውና የታዘብነው ሁሉ ልብን በሐዘን የሚያደማ ነው፡፡ ሀገሩ በረጅም ዘመን ታሪኳ ካለፈችበትና ካለችበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስና ውጥንቅጥ የተነሳ በብዙ ተስፋ መቁረጥና የሕይወት ምስቅልቅል ውስጥ ላለ ትውልድ አንገቱን ካቀረቀረበት ቀና የሚያደርገው፣ በምድሪቱ ላይ ከነገሰው ክፋትና የሞራል ውድቀት የተነሳ ነፍሱ ከተቀረቀረችበት ምድራዊ ሲዖል ጎትቶ የሚያወጣውና የተስፋ ብርሃን ጭላንጭል የሚያሳየው የመጽናናት የሕይወት ቃል እንጂ ‹‹በቡሀ ላይ ቆረቆር›› እንዲሉ አበው ሌላ ሸክም ሌላ ቀንበር በመጫን የትውልዱን ጥፋት የሚያፋጥን እንዲህ ዓይነቱ የጥፋት ድግስ ባልሆነ ነበር፡፡

የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን ተለይም ደግሞ የኤፍ ኤም ሬዲዮኖቻችን ቀኑን ሙሉ ስለ ቫለንታይን ቀን በማውራት መዋላቸውንና ማምሸታቸው በእውነቱ የሚያስተዛዝብ ነው፣ ምነዋ ስለ ስራ ባህላችን፣ መኮረጅ ስለሚገባን የምዕራባውያኑ መልካም ባህላቸውና ባህርያቸው፣ ከምናቡ ዓለም የእውነተኛ ፍቅር ማሳያ ከሆኑት ሮሚዎና ጁሌት ይልቅ የሀገራችንን የፍቅር ጀግኖች የሚስተዋውቁበት መድረክ ቢኖራቸው ብዬ ተመኘሁ፤ ሀገርንና ትውልድን በመለወጥ ረገድ ሰፊውን ድርሻ መጫወት የሚገባቸው መገናኛ ብዙኃኖቻችን እንዲህ በማያገባን ጉዳይ በግድ እየጎተቱ ታዳሚዎች ባያደርጉን ምን ነበረበት!? አደራችሁን ኤፍ ኤሞቻችን ወቀሳውን የሚጠቅም ነገር የላችሁም ወይም አልሰራችሁም በሚል መንፈስ የተሰነዘረ አድርጋችሁ እንዳትወሰዱብኝ፡፡
‹‹ረጅም ዕድሜ ለፍቅር!›› ነው ያለው ያ በፍቅረኛው ምክንያት ከሚወዳት ሀገሩ እንግሊዝና ከንግስናው መንበር የተሰደደው ኩሩው ልዑል፤ ለነገሩ ፍቅር ዘላለማዊ ነው… ሁሌም አዲስና ህያው፣ የማይሰለች የልብ ሐሴትና ሲሳይ… የሕይወት እርካታ… የህልውናችን መሰረት ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከላቸው መልእክቱ እንደተናገረው፡- ‹‹ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፣ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፣ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፣ እውቀትም ቢሆን ይሻራል… እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፣ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው፡፡›› በማለት ፍቅርን ዘመን የማይሽረው፣ ዘመናትን እንኳን የሚስረጅ ዘላለማዊ መሆኑን አስረግጦ ነግሮናል፡፡

በዚህ ፍቅር ውስጥ ላለን ሁሉ ሰላም ጽድቅ ነው! በዚህ መንፈስ… በንጹህ ኅሊና፣ ከእውነተኛ ልብ በመነጨ ፍቅር ቀኑን አሰበውም ሆነ አክብረው ያለፉትን ሰዎች የፍቅር አምላክ ያስባቸው ለማለት እወዳለሁ፣ ሁሉም ቀናቶቻችን፣ ዘመናችን ሁሉ የፍቅር ይሁንልን! ፍቅርን በሚመስል ሽንገላ ከእውነተኛው የፍቅር ንጽህና ጎዳና የወጡትንም ወደ ሕይወት መንገድ የድንግል ማርያም ልጅ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመልስልን!

ወዳጆች ሆይ፣ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ፣ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፣ እርስ በርሳችን እንዋደድ፡፡ ፍቅር የሌለው ሰው እግዚአብሔርንም አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና፡፡ ፩ ዮሐ ፬፣ ፰፡፡

ፍቅርን ያብዛልን ቸሩ አባታችን!