ለሁለቱ ሲኖዶሶች የእርቅ እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ከሙሉ ሰው

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ከተወጋገዙ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ለመታረቅ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ስንሰማ እጅግ ደስ ብሎን በጉጉት እየጠበቅነው ነው ነገር ግን አንዳድ እንቅፋቶች ይኖራሉ ብለን ስለምናምን እነዚህን ጉዳዮች ለውይይት ልንቃርባቸው ወደድን።
እንደሚታወቀው ሁለቱም ሲኖዶሶች በተወጋገዙበት ቃለ ውግዘት ውስጥ የኢትዮጵያው ሲኖዶስ በጻፈው ላይ መልክአ ሥእል እና ታምረ ማርያም አያነቡም የሚል ውግዘት እንዳለበት ተመልክተናል። ነገር ግን በአሜሪካው ሲኖዶስ ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ታምረ ማርያም ከቅዳሴ በፊት እንደሚያነቡ ሰምተናል።

ይሁን እንጂ የታምረ ማርያም ነገር በዚህ እርቅ መፍትሔ ካልተሰጠበት የሰው ስም ማጥፊያ፤ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ትውልድ ሲያወጋግዝ ሊኖር ይችልላና አብሮ ቢታሰብበት ለትውልድ የሚሆን መፍትሔ ያመጣል ብለን እናምናለን።

መጽሐፉን ለግምገማ ይመች ዘንድ በውስጡ ያለውን ይዘት ጥቂት ለማቅረብ ሞክረናል።

ታምረ ማርያም የሚባለው መጽሐፍ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን[በ1530 ዓ.ም.] ተጽፎ በየገዳሙ እንደተላከና ደቂቀ እስጢፋኖስ እንደተቃወሙት በዚህም ምክንያት በእሳት ተቃጥለው እንደሞቱ የታወቀ ታሪክ ነው።

ይህ ከጊዜ በሁዋላ ሰርጎ የገባ መጽሐፍ እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ቀሳውስትን፤ ዲያቆናትን ምእመናንን እየከፋፈለ የሚገኝ አንዳዶችንም ያስደበደበ ከዚያም አልፎ ደም ሲያፋስስ የኖረ መጽሐፍ ነው።

በመቅድሙ መጀመርያ ላይ ም 1 ቁ 35 ላይ “በእሑድ ሰንበት የማርያምን ታምር ለመስማት የማይሄድ ክርስቲያን ቢኖር አባ ገብርኤል እና አባ ሚካኤል በሚባሉ ጳጳሳት ተወግዟል” ይላል ስለዚህ ክርስቲያን ነኝ ያለ ሁሉ ከውግዘቱ ለመዳን እሑድ ተገኝቶ ታምረ ማርያም መስማት ግዴታው ነው።
ምእመኑ ታምረ ማርያም ሲባል እንዲሁ በደፈናው ለመስማት እና ለመሳለም ይጣደፋል እንጂ ደም ሲያፋስስ የኖረ መሆኑን በውስጡም ያለውን ይዘት አስተውሎት አያውቅም። ነገር ግን የማርያምን ስም ስለሚጠራ ብቻ ከፍተኛውን ቦታ ይዞ የኖረ መጽሐፍ ነው።
ዛሬም ከቅዳሴ በኋላ በቀሳውስቱ የሚነበብ ሲሆን አንዳድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት የተረዱ ካህናት ግን እየተሸማቀቁ ሲያነቡት ይታያሉ። አብዛኛዎቹ ቀሳውስት በታምረ ማርያም ማንበብ ደስተኛ አይደሉም ነገር ግን ሕዝብ የለመደው ስለሆነ ሕዝቡን ላለማስቆጣት ስለሚጠነቀቁ በግእዝ ሸፋፍነውት ያልፋሉ።

ለመሆኑ ታምረ ማርያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው ግጭት ምንድን ነው?

ከዚህ ቀጥለን በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ አንዳድ ሐሳቦችን በማቅረብ ለፍርድ አቅርበነዋል።
”በእንተ እግዝእትነ ማርያም ተገብረ ኩሉ ዓለም በእንተ እግዝእትነ ማርያም ተፈጥሩ አዳም ወሄዋን” ትርጉም “ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ፤ አዳም እና ሄዋንም ስለ እመቤታችን ተፈጠሩ” የዘወትር መቅድም ም 1 ቁ 7
ይህ አባባል መጽሐፍ ቅዱስን ፈጽሞ የሚቃረን ነው። ፍጥረት የተፈጠረው እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው። ሰማይና ምድር በሙሉ እንኳ የእግዚብሔርን ክብር እንደሚገልጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ”ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” መዝሙር 18 ቁ 1። ሰማይና ምድር ለሰው ልጆች ሁሉ የተፈጠሩ የእግዚአብሔር የክብሩ መግለጫ ናቸው እንጂ ለእመቤታችን ተፈጠሩ የሚለው የተጋነነ ውሸት ነው የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም ጥንታውያን አባቶችም ትምህርት አይደለም።
አዳም እና ሄዋን ለማርያም ተፈጠሩ ማለትስ ምን ማለት ነው? ያን ያህል ዘመን በሲኦል ሲማቅቁ የኖሩት ለማርያም ተብሎ ነውን? ነገሩ ግልጽ አይደለም። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታችን እናት በመሆኗ ክብር ይገባታል። ከዚህ ውጭ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በምንወዳት በድንግል ማርያም ስም ማጣመም ተገቢ አይደለም።

”ወቅድመ ሥእላ ስግዱ ዘኢሰገደ ላቲ ይደምሰስ እምቅዋሙ ወኢይት አወቅ ዝክረ ስሙ” ትርጉም፥ “በሥእሏ ፊት ስገዱ ለሥእሏ ያልሰገደ ከቆመበት ቦታ ይጥፋ ስም አጠራሩም አይታወቅ” የዘውትር መቅድም ም 1 ቁ 35።
ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ካመነ ስሙ በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጻፍ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ሉቃ ም 10 ቁ 20። በዘዳ ም 4 ቁ 15-19 ላይ ”እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ፤ እንዳትረክሱ፥ ተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥ በምድር ላይ ያለውን የእንስሳን ሁሉ ምሳሌ፥ በሰማይም በታች የሚበረውን የወፍን ሁሉ ምሳሌ፥ በምድርም ላይ የሚሽከረከረውን ሁሉ ምሳሌ፥ ከምድርም በታች በውኃ ውስጥ የሚኖረውን የዓሣን ሁሉ ምሳሌ እንዳታደርጉ፥ ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ ሁሉ በታች ላሉት አሕዛብ ሁሉ የሰጣቸውን ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንና የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባየህ ጊዜ፥ ሰግደህላቸው አምልከሃቸውም እንዳትስት ተጠንቀቅ” ይላል። ታዲያ ለሥእል መስገድን ምን አመጣው?

በተለይም ”የወንድ ወይም የሴት ምስል” የሚለውን ቃል ማስተዋልና መጠንቀቅ ተገቢ ነው ለማርያም ስእል ግን መስገድ የተፈቀደበትን ስፍራ አናገኝም። አጼ ዘርዓ ያዕቆብ የእግዚአብሔርን ቃል ከመተላለፉም በላይ “ከቆመበት ይጥፋ ስም አጠራሩ አይታወቅ” የሚሉትን የእርግማን ቃላት ያለቦታቸው አስቀምጧቸዋል ሥእል ትምህርት ሰጪ ታሪክን የሚገልጥ ሊሆን ይገባል እንጂ ስግደት ጸሎት አምልኮ ሊቀርብለት እና ሰውን ለማጥፋት መራገሚያ ሊሆን አይገባም።

መልክአ ስእል የሚባለው ድርሰት ሁልጊዜ በየጠዋቱ የሚጸለይ ሲሆን የሚናገረው ስለ ስእል ቁንጅና ፤ ለሥእል ስግደት እንደሚገባ የሚናገር ነው ሁልጊዜ ካህናቱ ከኪዳን በፊት የሚጸልዩት የጸሎት ክፍል ነው። በዚህ መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚል አለ።

“ዘኢሰገደ ለስእልኪ አሥሪጾ ምማኤ በሥጋሁ ወበነፍሱ ኢይርከብ ትንሣኤ” ትርጉም፦ “እራሱን ዝቅ አደሮጎ ለሥእልሽ ያልሰገደ ቢኖር በነፍሱ እና በሥጋው ትንሣኤ አያገኝም” ይህ ድርሰት አባ ስጢፋኖስን ለመራገም የተደረሰ ሲሆን በሐግሪቱ ላይም ሥጋዊ እና ማሕበራዊ ውድቀት ሊያመጣ የሚችል ስለሆነ ባስቸኳይ ሊቆም ይገባል ። ጸልዩልን ብሎ የሚማጸንን ሕዝብ ለሥእል ካልስገደ ተብሎ በሥጋው[በኑሮው] እና በነፍሱ ትንሣኤ አያግኝም ተብሎ ለዚያውም ጠዋት ጠዋት ሊረገም አይገባውም።

“ወዘኢተክህሎ ነሢአ ቍርባነ ሰሚኦ ይሑር ውስተ ቤቱ ወይከውኖ ከመ ቁርባን ለእመ ሰማዐ በአሚን” ትርጉም፦ “ሥጋውን ደሙን መቀበል ያልቻለ ታምሯን ሰምቶ ይሂድ ሥጋውና ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል” መቅድም ም 1ቁ 45

ይህ ደግሞ ጌታ ሥጋዬን ያልበላ ደሜንም ያልጠጣ የዘለዓለም ሕይወት የለውም ብሎ ያስተማረውን ትምህርት ፈጽሞ ያላገናዘበ ነው ። ሥጋውን ደሙንም ምንም ዓይነት ታምር ሊወክለው አይችልም። ብዙ ሰዎች ብዙ ታምር ሰምተዋል አይተዋልም ነገር ግን በክርስቶስ ማመን እንዲሁም ሥጋውን ደሙን መቀበል ስላልቻሉ ወደ ሕይወት አልመጡም። በጣም የሚያሳፍር አባባል ነው። ዛሬ ታምር በመስማት የሚንከራተተው ሕዝባችን ከዚህ እርግማን ጋር ተያይዞ የመጣበት ይሆንን?

ዋናው የጠብ ምንጭ በታምረ ማርያም ውስጥ

“ኦ ኃጥአን አኃውየ እለ ከማየ እምይእዜሰ ኢንሕሥስ ከዊነ አግብርተ እግዚአብሔር ለፈጽሞ ሕግጋት አሠርቱ ወሰደስቱ እስመ ውእቱ መጠወነ ኪያሃ እግዝእተ ኪዳን ጊዜ ቀትር አመ ሀሎ ዲበ ዕፀ መስቀል እንዘ ይብል ነያ እምክሙ ወእግዝእትክሙ ወበእንተዝ እብለክሙ ንቅድም ወንትባደር ከዊነ አግብርት ለማርያም እምነ ወእግዝእትነ”
ትርጉም “እንደ እኔ ያላችሁ ኃጥአን ወንድሞቼ ሆይ እንግዲህ አሠርቱ ትእዛዛትን እና ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን በመጠበቅ የእግዚአብሔር ባሪያ ለመሆን ማሰብ የለብንም እርሱ በቀትር ጊዜ በመስቀል ላይ ሆኖ እመቤታችንን እናት አድርጎ ሰጥቶናልና፤ ይልቁንስ የእመቤታችን እና የእናታችን የማርያም ባሪያ ለመሆን እንሽቀዳደም” ይላል። ታምረ ማርያም ምዕራፍ 12፡52-53።
እንግዲህ ይህ አባባል በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ተጽፎ ወደየገዳማቱ በተላከ ጊዜ ከፍተኛ ውዝግብ አስነሥቶ አባ እስጢፋኖስ እና ደቀ መዛሙርቱ እንዲገደሉ ምክንያት የሆነው እና እስከ ዛሬ ድረስ መፍትሔ ያላገኘ እንቆቅልሽ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብትወዱኝ ትዛዜን ጠብቁ ብሎ አስተምሯል። ስድስቱ ቃላተ ወንጌል የሚባሉት በ ማቴ 25 ቁ 35-44 ላይ ይገኛሉ። ታዲያ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ምን አይነት መጻሕፍትን ቢያነብ ነው የእግዚአብሔርን ትእዛዛት መጠበቅ አያስፈልገንም ያለው? ይህን መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያናችን ሰይጣን አስርጎ ያስገባው የጠላት ተንኮል እንጂ ልናነበው እና ልንሳለመው የሚገባ መጽሐፍ አይደለም አሁንም ከቤተ ክርስቲያናችን ተጠርጎ መውጣት ያለበት ቆሻሻ ነው። ጥንታውያን የወንጌል አርበኞች ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ይህንን ጉድ ቢያዩ እንዴት ያዝኑ? ወንጌሉን ከማንበብ ይልቅ ሕዝቡ በዚህ መጽሐፍ ተሸፍኖ ሕይወት ያለበትን የወንጌል ቃል እንዳይሰማ ተደርጓል። ወንድሞቻችንንም እያጣንበት ያለ መጽሐፍ ነው።

የኢትዮጵያው ሲኖዶስ አባላት ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ታምረ ማርያምን አይቀበሉም አያምኑበትም፤ ሕዝቡን በመፍራት ብቻ ተሸክመውት ይኖራሉ። ነገር ግን እውነቱን እያወቁ ጠላቴ የሚሉአቸውን ማጥቂያ እና የፖለቲካ መሳሪያ ማድረጋቸው አልቀረም። የማሕበረ ቅዱሳንም የመጀመሪያዎቹ አመራሮች ታምረ ማርያምን እንደማያምኑበት ብዙ ጊዜ ባደረግናቸው ውይይቶች ተገንዝበናል። የማህበሩ ተራ አባላት ግን ይህን አይረዱም። የማህበሩ መሪዎች ይህ መጽሐፍ በ እናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም የገባ የሲይጣን ስራ መሆኑን ልባቸው እያወቀው ጠላቴ የሚሏቸውን የቤተ ልርስቲያኒቱን ውድ ልጆች ለማጥቃት ሲሉ የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ማድረጋቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው። ለማንኛውም ሕዝባችንን ማሳወቅ የምንፈልገው ሁለቱ በማያምኑበት ነገር የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆኖ ኃጢአት እንዳይሠራ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቀኖና የተቀበለቻቸው መጻሕፍት ሰማኒያ አንድ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ታምረ ማርያም እና መልክአ ሥእል አይገኙበትም። አንድ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እምነቱ መፈተሽ ያለበት በሰማኒያ አሐዱ መጻሕፍት መሆን ሲኖርበት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝነው ባልተጣሩ እና እርስ በርሳቸው በማይስማሙ የደብተራ ድርሰቶች የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጥቃት ሊፈጸምባቸው አይገባም።

ስለዚህ የኢትዮጵያው ሲኖዶስ እርሱ በማያምንበት እና ከሰማኒያ አሐዱ መጻሕፍት ውጭ በሆኑ መጻሕፍት አማካኝነት ስም አጥፍቷልና ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዚህ መጽሐፍ መፍትሔ በመስጠት ወደ ፊት ሊፈጠር የሚችለውን የመከፋፈል አደጋ ከወዲሁ ማስወገድ አለባት። የእርቅ ኮሚቴው እውነተኛ እርቅ ማምጣት ከፈለገ ይህን ጉዳይም ቢመለከተው መልካም ነው፤ የሁለት ግለሰቦች መስማማት ብቻ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ችግር ሊፈታው አይችልም የሚል ሥጋት አለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
ከሙሉ ሰው