አቶ መለስ ዜናዊ እና የኤርትራ ፖለቲካቸው – ግርማ ካሳ
የጦርነት ነጋሪት እየሰማን ነዉ። ገዢዉን ፓርቲ የሚደግፉ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘዉ የትግራይ ተወላጆች ማህበር አባላት፣ እንደ አይጋ ፎረም ያሉ ድህረ ገጾች፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በኤርትራ ላይ ጦርነት እንዲከፍት ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ነዉ።
እነዚህ ወገኖች ከኤርትራ ጋር ጦርነት ቢከፈት በቀላሉ አስመራ መግባት የሚቻል ሳይመስላቸው አይቀርም። ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ ። የኤርትራ ጦር ተዳክሟል። ወታደሮቹ መዋጋት አይፈልጉም። በተባበሩት መንግስታት እቀባ ስለተደረገባትም ኤርትራ በቂ መሳሪያ ላይገባላት ይችላል። በአቶ ኢሳያስ ላይም ሕዝቡ ያለዉ ጥላቻ በጣም ስር የሰደደ ነዉ። በመሆኑም በቀላሉ የኢትዮጵያ ጦር ፣ በኤርትራ ሕዝብ ድጋፍ አስመራ ያለዉን መንግስት ሊያስወገድ ይችላል።
ከታሰበዉና ከተጠበቀዉ ዉጭም፣ የኤርትራ ጦር ጥንካሬ አሳይቶ፣ ጦርነቱም ረዝሞ፣ እንደ ባድመዉ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች፣ ከሰባ ሺሆች በላይ ወንድሞቻችን የሚያልቁበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
ለሁሉም የሚያዋጣዉ፣ የተሻለዉ አማራጭ፣ ወደ ጦርነት ከመጀመሪያዉኑ አለመሄድ ነዉ። ጦርነት አይጠቅምም። ችግርን በጦርነት መፍታት ለነአሜሪካም አልበጀም።
ለዚህም ነዉ አቶ መለስ ዜናዊ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ለፓርላማ በቅርቡ የሰጡትን ምላሽ በአዎንታዊነት የምቀበለዉ። ችግሮችን በሰላምና በውይይት መፍታት እንደሚጠቅም ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት። «ከኤርትራ መንግስት ጋር ቢሆን የመጀመሪያ ምርጫችን ጉዳዩን በሰላም መፍታት ነዉ። ሁለተኛዉ ምርጫችን በሰላም መፍታት ነዉ። ሶስተኛዉ ምርጫችን በሰላም መፍታት ነዉ» ሲሉ ለሰላም አለኝ ብለዉ የሚያስቡትን ቁርጠኝነት ይፋ አድርገዋል።
ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በየትኛዉ ቦታ፣ በማንኛዉም ጊዜ ፣ በማንም አደራዳሪነት፣ አደራዳሪ ካላስፈለገም ያለ ማንም አደራዳሪ፣ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ የገለጹት አቶ መለስ፣ በተለይም በአይጋ ፎረም አዝማችነት እየተቀጣጠለ ያለዉን የጦርነትና የጀብደኝነት መንፈስ ላይ ቀዝቃዛ ዉሃ ከልሰዉበታል።
ብዙዎቻችን ፣ ምን አልባት ሁለት የተለያዩ መንግስታት ስላሉ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን የተለያዩ አገሮች አድርገን ልንወስድ እንችላለን። ነገር ግን እዉነትና ታሪክ የሚያሳያን የኤርትራ ሕዝብ ወንድማችን እንደሆነ ነዉ። «የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ የኤርትራን ሕዝብ እንደ ወንድሙ አይቶ የሚያስተናገድ ነዉ። አሁን ብዙ ስደተኞች ነዉ እየመጡ ያሉት ከኤርትራ። ስደተኛዉ ሲመጣ ባእድ አገር ዉስጥ እንደገባ ሆኖ አይሰማዉም። የኢትዮጵያ ሕዝብም የሆነ ባእድ እንደመጣ አድርጎ አይደለም የሚያየዉ » ሲሉ አቶ መለስ በጥሩ ሁኔታ ከመረብ ባሻገርና ከመረብ ወዲህ ያለዉ ሕዝብ አንድ ሕዝብ እንደሆነ አስረድተዋል።
ብዙዎች አቶ መለስ ዜናዊ በእናታቸው የአዲ ቋላ (ኤርትራ) ሴት እንደነበሩ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት አቶ መለስ ዜናዊ ለኤርትራ ፍቅር እንዳላቸው ተደርገዉ ይታማሉ።
እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለኤርትራ ፍቅር አለኝ። ትዉልዴ አዲስ አበባ ነዉ። «ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሌላ የት ከተማ መኖር ትመርጣለህ» ብባል ድሬደዋ፣ አዋሳ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር ምርጫዬ አይሆኑም። ምርጫዬ አስመራ ነዉ የሚሆነዉ ። የኤርትራን ሕዝብ ከትግራይ ህዝብ፣ ከጎንደር ህዝብ ከጎጃሜው፣ ከወለጋዉ ለይቼ አላየዉም።
ለዚህም ነዉ ሳልፈራ አቶ መለስ ዜናዊ ለኤርትራዉያን መቆርቆራቸው «ጠቃሚ ነዉ፤ መልካም ነዉ። ኢትዮጵያዊ ተግባርም ነዉ» የምለዉ። የተባረሩ የኤርትራ ስደተኞች እንዲመለሱ መደረጉ፣ በስደት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የኤርትራ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቋማት እንደሌላዉ ኢትዮጵያዊ እንዲማሩ መወሰኑ አስደስቶኛል። የሚገነባ ነዉ። የሚያንጽ ነዉ። የሚያቀራርብ ነዉ። በዚህ አቶ መለስ ዜናዊ ሊወቀሱ የሚገባ አይመስለኝም።
በርግጥ ከኤርትራ ጋር ያለዉን ችግር እነ አይጋ ፎረም እንደሚሉት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ያስፈልጋል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ልንቀጥል አንችልም። ነገር ግን በጦርነት ሳይሆን በሰላምና በዉይይት ችግሩን በአስቸኳይ መፍታት ለሁሉም የሚበጅ ነዉ።
ሌላዉ ለማንሳት የምፈልገዉ ነጥብ ቢኖር፣ አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ካደረጉት ንግግር በሌሎች ተቃዋሚዎች ላይ ያንጸባረቁትን የንቀትና የጥላቻ አስተያየት ነዉ። =
አቶ መለስ ዜናዊ ከኤርትር ጋር ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ፣ ያላቸዉን ልዩነቶች ለመፍታት፣ ሲወስኑ ከአንድነት ለዲሞክራሲን ለፍትህ ፓርቲ እንዲሁም መድረክ ጋር በምንም መልኩ፣ የስነ ምግባር ኮድ የሚባለዉን ሰነድ ካልፈረሙ በቀር፣ ለመነጋገር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነዉ የገለጹት።
እንግዲህ አስቡት ስለኤርትራ በተናገሩበት፣ ስለ ሰላም ባወሩት አፍ ነዉ ይህን የሚሉት። ይሄ ምን ማለት ነዉ ? የሰላምና የእርቅ እጅ ለአንዱ ተዘርግቶ ለሌላዉ የሚከለከልበት ምክንያቱ ምንድን ነዉ ?
በአፋር ለተፈጠረዉ ችግር፣ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ አቶ ኢሳያስን ተጠያቂ አድርጓል። እንደዚያም ሆኖ ግን አቶ መለስ የኤርትራን መንግስት ሽብርተኛ መንግስት አላሉት። «አተራማሽ» ነዉ ያሉት።
እንግዲህ አተራማሽ ባሉት ቡድን ላይ የኃይል እርምጃ እንደማይወስዱ ፣ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት እንደሚሞክሩ በአንድ በኩል እየተነናገሩ፣ በሌላ በኩል የአገሪቷን ሕገ መንግስት አክብረዉ፣ በሰላም የሚንቀሳቀሱ እንደ አቶ አንዱዋለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ ያሉ የመድረክ አመራር አባላትን፣ እንደ አቶ እስክንድር ነጋ፣ ዉብሸት ታዬ ያሉ አንጋፋ ጋዜጠኞችን «ሽብርተኞች ናቸዉ። ኢሳያስ አፈወርቂ ይረዳሉ…» ብለዉ የኃይል እርምጃ መዉሰዳቸው፣ ወህኒ እንዲወርዱ ማዘዛቸው የሚያስተዛዝብ ነዉ።
አቶ መለስ ለሰላም ቆሜያለሁ የሚሉ ከሆነ፣ ሁሉ ነገር የሚጀመረዉ ከቅርብ ነዉ። ለአስመራ ያዉለበለቡትን ነጭ ባንዲራ ለኛም ሊያዉለበልቡልን ይገባል። ለፍርድ ቤት ቀጥተኛ ትእዛዝ በመስጠት በግፍ ያሰሯቸዉን ንጹሃን ዜጎች በአስቸኳይ መፍታት ይኖርባቸዋል። የሰላም እጃቸዉን ለኤርትራዉያን ብቻ ሳይሆን ለተቀረዉም ኢትዮጵያዊ ሊዘረጋ ይገባል።
በአገር ዉስጥ በሰላም የሚታገሉትን ብቻ አይደለም። በዉጭ አገር የአመጽ/ትጥቅ ትግል እናደርጋለን ከሚሉ፣ ከነ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ ከመሳሰሉ ድርጅቶች ጋር፣ ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እንዳደረጉት፣ ያለ አንዳች ቅድሜ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል።
ደግሜ እናገራላሁ። አዲስን ነገር ያድርጉ አይደለም የምለዉ። ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ያላቸዉን ቅን አመለካከት ለተቃዋሚዎችም ያሳዩ ነዉ የምለዉ።
አቶ መለስ ለአቶ ኢሳያስ የከፈቱትን የሰላም በር ለተቀረዉ ኢትዮጵያዊም የየማይከፍቱ ከሆነ፣ ብሄራዊ እርቅና መግባባት እንዲፈጠር የማይሰሩ ከሆነ፣ አጉል የጸረ-ሽብርተኛ ሕግ እያሉ ዜጎችን ማሸበር የማያቆሙ ከሆነ በርግጠኝነት የምነግራቸው ነገር ቢኖር አወዳደቃቸው፣ ለርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለደጋፊዎቻቸዉ እጅግ በጣም የከፋ እንደሚሆን ነዉ።
ጆሮ ያለዉ ይስማ ፣ ልብ ያለዉ ያስተዉል