መለስ ሆይ ፡- ባልተመቸው ሕዝብ ላይ የተመቸው መሪ መሆን እስከ መቼ?
ተመስገን ደሳለኝ
“ክልምኖም ይስምዑኒ!!!”
“(እስኪ ልለምንዎ አንዴ ይስሙኝ)”
…እያልኩ ያለሁት ‹‹አባታችን ሆይ›› አይደለም፤ ‹‹መለስ ሆይ!›› ነው። መለስ ሆይ…(በእርግጥ አንዳንድ የድረ ገጽ ተቺዎች (Sic!) ‹‹ሁልጊዜ መለስ፣ መለስ ትላለህ? መለስ ምን ያድርግህ? ወይስ ከመለስ ወንበር ያየኸው ነገር አለ ወይ?›› ሲሉ ይወቅሱኛል። ምንም እንኳ በባሕርዬ ወቀሳ ተቀባይ እና ጥፋቴን ፈጥኜ የማምን ብሆንም በዚህ በኩል የሚመጣውን ወቀሳ ግን አልቀበልም። አዎ፣ አልቀበልም የምለው እንደወትሮዬ በትሕትና አይደለም። በቁጣ እንጂ! ያውም በታላቅ ቁጣ!! ያውም ገና ተራሮችን ያንቀጠቅጣል ብዬ በማስበው ቁጣ። እናም እደግመዋለሁ፤ እንኳንም ከስንት አንዴ ‹‹መለስ ሆይ›› ማለት ብቻ ሳይሆን እንደ ሠርክ ጸሎት አዘውትሬ ‹‹መለስ ሆይ›› ስል እጮኻለሁ።