በአዳማ 45 ክሊኒኮችና የመድኃኒት መደብሮች ታሸጉ
የአዳማ (ናዝሬት) ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ጉድለቶች አሉባቸው ያላቸውን 21 ክሊኒኮችና 24 የመድኃኒት መደብሮችን አሸገ፡፡ ከከተማው የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ባለፈው ሐሙስ እንዲታሸጉ ከተወሰነባቸው መድኃኒት ቤቶች መካከል ስድስቱ ምንም ዓይነት ፈቃድ ያልነበራቸው ናቸው፡፡
ለእሸጋው ምክንያት ናቸው ከተባሉት ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት የተጠቀሱት በትክክለኛ ባለሙያዎች ማሠራት አለመቻል፣ ፈቃድ ያለማደስ፣ በሌሎች ሰዎች ሥራውን ማሠራት፣ ከተፈቀደላቸው የአገልግሎት መጠን በላይ ሲሠሩ መገኘትና የመሳሰሉት እንደሚገኙበት የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበራ ፈይሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዕርምጃው አስተዳደራዊ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አበራ፣ እሸጋ የተደረገባቸው ክሊኒኮችና የመድኃኒት መደብሮች የታየባቸውን ጉድለት እንዲያስተካክሉ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የተወሰደባቸው አስተዳደራዊ ዕርምጃም ከአንድ እስከ ሁለት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ማሟላት የሚገባቸውን አሟልተው የሚቀርቡ ከሆነ አገልግሎታቸውን መልሰው የሚጀምሩበት ዕድል ያለ ሲሆን፣ ይህንን ካላደረጉ ግን ሥራውን መጀመር እንደማይችሉ ከአቶ አበራ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ማሟላት የሚገባቸውን በተደረገው ጥናት መሠረት በዝርዝር የተነገራቸው ሲሆን፣ ለምሳሌ በቂ ባለሙያ የሌላቸው ከሆነ ይህንን ማሟላት አለባቸው፡፡ የሕክምና መሣሪያ ጉድለት ከሆነም የጎደለውን መሣሪያ አሟልቶ መቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ይህ ውሳኔ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲሠሩ የቆዩትን ክሊኒኮችና መድኃኒት ቤቶች እንደማይመለከት ገልጸዋል፡፡
ጽሕፈት ቤታቸው ይህንን ዕርምጃ ቀደም ብሎ በተወሰነ ደረጃ የወሰደ መሆኑን የገለጹት አቶ አበራ፣ አሁን ግን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል የተደረገው ተጠቃሚዎችን ጉዳት ላይ የሚጥሉ ሕገወጥ ተግባራት እንዳይስፋፉና የተሻለ የጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ለመዘርጋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የታሸጉትን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 128 የሚሆኑ ክሊኒኮችና መድኃኒት መደብሮች በአዳማ ውስጥ ይገኛሉ፡፡