ኢትዮጵያ እንደ ሩዋንዳ ? የዳዎድ ቡድን ባወጣዉ መግለጫ ላይ (ግርማ ካሳ)

መግቢያ

በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራዉ ኦነግ «ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነዉ። ቅርንጫፍ ከግንድ ይገነጠላል እንጂ ግንድ ከቅርጫፍ አይገነጠልም» በሚል፣ የኢትዮጵያን አንድነት ተቀብሎ፣ ለኦሮሞ ባህልና ቋንቋ መስፋፋት፣ ለዜጎች ሁሉ መብት መከበር፣ ከተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጎን በመቆም ትግሉን እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል። ይህ ከኦነግ ዘንድ ይፋ የተደረገዉ የፖለቲካ አቋም ለዉጥ ኦሮሞ ነን የሚሉትን ጨመሮ በበርካታ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ከፍተኛ ዉይይትን ጭሯል።

 

አንጋፋዉ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ጨምሮ፣ የበርካታ ድርጅቶች ስብሰብ የሆነዉ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ መስራችና የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የቀድሞ ሊቀመንበር፣ የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ኦነግ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ይህንን ጠቃሚና ወቅታዊ እርምጃ መዉሰዱን አድንቀዋል። «ጄኔራል ከማል ገልቹ ብቻ ሳይሆኑ ሁላቸዉም በዚህ ሃሳብ ዙሪያ ቢሰባሰቡ ጥሩ ይመስለኛል» ያሉት አቶ ቡልቻ «ኦነግ እገነጠላለሁ ሲል ነበር። ይሄን እኔ ከድሮ ጀምሮ የምቃወመዉ ነገር ነዉ። አሁን ጄኔራል ከማል የተናገሩትን እኔ በደስታ ነዉ የማዳምጠዉ። ኦሮሞው፣ አገር ዉስጥ ኖሮ፣ በኢኮኖሚ በፖለቲካ በማህበራዊ ኑሮ ሁሉ ተሳተፎ፣ በኢትዮጵያ ዉስጥ አለሁ ብሎ፣ የሚኖር ሕዝብ ነዉ። የሚሸሽ ወይንም የሚገነጠል ህዝብ አይደለም» ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

 

ሌላ አንጋፋ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አባት፣ የተከበሩ አቶ ሮቤል አባቢያ በበኩላቸው፣ የኦነግ አመራሮች የወሰዱት ድፍረት የተሞላበትን አቋም፣ «የተቀደሰ» ሲሉት፣ በታሪክ ትልቅ የጀግንነት ገድል ካላቸው፣ የኦሮሞዉ ሕዝብ አብላጫ (ማጆሪቲ) ከሆኑት፣ አገር ወዳድና ኩሩ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ወገኖቹ ጋር፣ ኦነግ መቀላቀሉ እንዳስደሰታቸዉም ገልጸዋል።


የኦነግ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል የሚቃወመዉ የዳዎድ ኢብሳ ቡድን

ምንም እንኳን በኦነግ አቋም የተደሰተዉ ሕዝብ እጅግ በጣም ቢበዛም፣ በተቃራኒዉ ይህ ታሪካዊ ክስተት ያላስደሰታቸው ጥቂቶች እንዳሉም እየታዘብን ነው። በዳዎድ ኢብሳ የሚመራዉ የኦነግ አክራሪ ቡድን፣ በሚቆጣጠረዉ ድህረ ገጽና አንዳንድ የፓላቶክ ክፍሎች፣ በጄኔራል ገልቹ በሚመራዉ ኦነግ፣ እንዲሁም ከነጄኔራል ገልቹ ጋር በቅርበት በሚሰራዉ ግንቦት 7 በተሰኘዉ ድርጅት ላይ የከፈተዉን ከፍተኛ የሆነ የፕሮፖጋንዳ ጥቃት እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

 

«ግንቦት ሰባት የተሰኘው ድርጅት የኦሮሞን ሕዝብ የነጻነት ትግል ጎራ በማናጋት ላይ አተኩሯል። ድርጅቱ ከኦሮሞ ሕዝብ የትግል ጎራ በጣት የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን በጉያዉ ሸጉጦ እንደ መሳሪያ በመጠቀም፣ የኦነግን ታላቅነት ሊያረክስና የትግሉን አላማም ለመቀልበስ ሲል ደጋፊዎቹን ደቦ ጠርቶ ወደ ዘመቻ ገብቷል» ሲል የዳዎድ ቡድን ይከሳል።

 

«የኦሮሞ ሕዝብ የሚኖርበትን ሰፊ መሬት የሚያሳየዉ፣ የኦሮሞያ ካርታም ኢትዮጵያን የሚንድ አደጋ ተብሎ በዚህ ኃይል ዘንድ በጽኑ እየተወገዘ ይገኛል። የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ ወስኖ፣ ካሻዉ የራሱን መንግስት መመስረት፣ አልያም ከጎሮቤቱ ሕዝቦች ጋር የፖለቲካ አንድነት የመፍጠር መብቱ፣ ግንቦት 7 ዘንድ እንደ ወንጀል ታይቶ፣ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ጥቃት ተከፍቶበታል። ባጭሩ ለማስቀመጥ ይህ ድርጅት በኦነግ ላይ የተያያዘዉን የጥቃት ዘመቻ አድማስ በማስፋት ሰፊዉን የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል» ሲልም የግንቦት 7 ንቅናቄ አዉግዟል።

 

ኢሳት እንደ ሚል ኮሊንስ ራዲዮ ?

የዳዎድ ኢብሳ ቡድን ጥቃቱን በግንቦት ሰባት ብቻ ላይ በማድረግ አልተቆጠበም። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን የሆነዉን ኢሳትን እንደ ጥላቻ አራማጅ፣ በኦሮሞ ላይ እንዳነጣጠረ ሜዲያ አድርጎም አቅርቦታል። «ኢሳት የተሰኘዉ ቴሌቭዝኝ እየነዛ ባለው ፀረኦሮሞ ፕሮፓጋንዳ፣ ከራዲዮ ሚል ኮሊንስ ጋር የሚቀራረብ ሚና እየተጫወተ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነዉ። ኢሳት አሁን በኦሮሞ ሕዝብ፣ በመሪ ድርጅቱ ኦነግና በኦሮሞነት ላይ አነጣጥሮ በተለያዩ ስልቶች እየነዛ ባለዉ አደገኛ ፕሮፓጋንዳ፣ ነገ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሩዋንዳ አይነት ቀዉስ እንዲቀሰቀስ መሰረት እየጣላ መሆኑን አስቀድመን መጠቆም እንወዳለን» ሲል ኢሳትን ለሩዋንዳ እልቂት ዋና ተጠያቂ ከሆነዉ ከሚል ኮሊንስ ራዲዮ ጋር አመሳስሎታል።

 

በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፣ ኢንተርሃሙዌ በሚል በሩዋንዳ ያሉ ሁቱዎች ቱትሲዎችን እንደጨፈጨፉት፣ የተቀረዉ ኢትዮጵያዊም ትግሬዎችን ሊጨርስ እንደተነሳ አድርጎ በማቅረብ፣ አሳዛኝና ኃላ ቀር የዘር ካርድ በመጫወት፣ በትግሬዎችና በተቀረዉ ኢትዮጵያዊ መካከል መፈራራት እንዲኖር ለማድረግ መሞከሩ የሚታወስ ነዉ። ከቅንጅት እንደመጣ በማስመሰል፣ ሕወሃቶች እራሳቸው «ትግሬን ግደሉ» የሚል የጥላቻ መግለጫ እየጻፉ ሲበትኑም እንደነበረ ብዙዎች ይናገራሉ።

 

እዉነቱ ግን ሌላ ነበር።፡ሕወሃቶች የአጋዚን ጦር ልከዉ፣ የተቀረዉን ኢትዮጵያዊ በጥይት አረገፉት እንጂ እነርሱ የጭካኔ የግድያ ድርጊት ፈጸሙ እንጂ፣ አንድም ሰላማዊ ዜጋ፣ ጦር አንስቶ ትግሬ ወንድሙን የገደለበት ሁኔታ አልተከሰተም። አንድም ሰዉ በትግሬ ጎሮቤቱ ላይ አልተነሳም። ሕዝቡ ትግሬ ላይ ቢነሳ ኖሮ 10 ሺህ የማይሞሉ የአጋዚ ወታደሮች ነበሩ እንዴ፣ ሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብን መክተው ትግሬዉን ሊያድኑ ይችሉ የነበረዉ? ሕውሃቶች የትግሬዉን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ብቻ፣ ትግሬዉን በዉሸት ፕሮፖጋንዳ ቢያስፈራሩትም የተቀረዉ ኢትዮጵያዊ፣ ለትግሬዉ ወገኑ ፍቅርና አክብሮት እንጂ ጥላቻ ኖሮት አያውቅም። አይኖረዉምም። የትግራይ ሕዝብ አሉላ አባ ነጋን አጼ ዮሐንስን የመሳሰሉ ጀግናዎችን ያፈራ፣ ለኢትዮጱያ አንድነትና ሉዓላዊነት አጥንቱን የከሰሰ ኩሩ ሕዝብ እንደሆነ የተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ያውቃል።

 

እንግዲህ ያኔ ሕወሃት ሲያደርግ እንደነበረዉ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከሕዉሃት ደብተር በመኮረጅ፣ የዳዎድ ኢብሳ ቡድን ስለ ሩዋንዳ እልቂት እንደገና እየነገረን ነዉ። «ኦሮሞዉ ኢትዮጵያዊ ነዉ ከተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በፍቅር በመከባበር ለአንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አብሮ ይሰራል» ማለት፣ እንዴት ተደረጎ በሩዋንዳ የታየዉን አይነት የዘር እልቂት ሊፈጥር እንደሚችል ሊገባኝ አልቻለም። እንዴት ተደርጎ «ተፋቅረን፣ ተከባበረን እንኑር» ማለት በወገንና በወገን መካከል ጥላቻን እንደመንዛት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል?

በጄኔራል ገልቹ የሚመራዉ ኦነግ፣ ከነዳዎድ ኢብሳ ቡድን ጋር ያለዉ ትልቁ ልዩነት

ጃዋር ሲራጅ መሃመድ፣ በነጄኔራል ገልቹ በሚመራዉና በዳዎድ ኢብሳ ቡድኖች መካከል ብዙ ልዩነት እንደሌለ የሚገልጽ አንድ ጽሁፍ በቅርቡ አስነብቦናል። ወንድም ጃዋር እንዴት ወደዚህ ድምዳሜ እንደመጣ ባይገባኝም፣ ከመግለጫዎቻቸው እንደተረዳሁት ግን፣ በሁለቱ መካከል ትልቅና ቁልፍ የሆነ ልዩነት እንዳለ ነዉ የሚታየኝ።


የዳዎድ ኢብሳ ቡድን «ኦሮሞው ከኢትዮጵያ ጋር ለመሆን ይወስን። ከፈለገም ኦሮምያን ይዞ መገንጠል መቻል አለበት» ባይ ነዉ። የዳዎድ ቡድን ስለ አቢሲኒያ ኢምፓየር፣ ስለ ቅኝ ግዛት ያወራል። እነ ጀነራል ገልቹ ደግሞ ከመጀመሪያ ኦነግ ሲቋቋም የነበረዉ አላማ የመብት ጥያቄ እንጂ የመገንጠል ጥያቄ እንዳልነበረ በመግልጽ «ኦሮሞዉ ኢትዮጵያዊ ነዉ ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነት ነው » የሚል ጠንካራ አቋም ወስደዋል። ድብን አድርጎ ትልቅ ልዩነት ነዉ እንጂ ያለዉ በሁለቱ መካከል!!!

የኦሮሞነት መመዘኛ ምንድን ነዉ ?

የነዳዎድ ኢብሳን ፖለቲካ እስቲ ዘርዘር አድርገን ሊያስከተል የሚችለዉን ነገር እንመርምር። በመጀመሪያ «ኦሮሞዉ ሕዝበ ዉሳኔ ይስጥ» ከተባላ፣ ሕዝበ ዉሳኔ ለመስጠት አንድ አይነት ሂደት(ፕሮሰስ) መኖር አለበት። ለምሳሌ መራጮች መመዝገብ አለባቸዉ፤ የምርጫ ካርድ ሊሰጣቸዉ ይገባል። እንግዲህ አንዱና መሰረታዊ ጥያቄ « ማን ነዉ ኦሮሞ ተብሎ የምርጫ ካርድ የሚሰጠዉ ? » የሚለዉ ነዉ። ይህ ጥያቄ ቀላል ይመስላል እንጂ እጅግ በጣም የተወሳሰበ ጥያቄ ነው።

 

ኢሕአዴግ አዲስ አበባ እንደገበ በቀበሌ ደረጃ የክልል ምርጫ ተደረጎ ነበር። ለመምረጥ ወደ ቀበሌ ሄድኩኝ። የዘር ሃረጌን ጠየቁኝ። «ኢትዮጵያዊ» ብላችሁ ጻፉ አልኩ። «አይደለም እርሱማ ዜግነትህ ነዉ። የጠየቅንህ ብሄርህን ነዉ» አሉኝ። «ኦሮሞና አማራ» አልኩ። «አንዱን ምረጥ» አሉ። «በጭራሽ ሁለቱን እፈልጋለሁ» አልኳቸው። ጭቅጭቅ ተፈጠረ። ካርድ ሊሰጡኝ ፈቃደኛ አልሆኑም። ሳልመርጥ ቀረሁ። በአገሬ፣ በተወለድኩባት መንደር በመሃይምነት ይጥፋ ዘመቻ ባስተማርኩበት ቀበሌ፣ ጭካ ባቦካሁበት፣ በባዶ እግሬ እግር ኳስ በተጫወትኩበት ሰፈር፣ እንደ ባእድ ዜጋ ተቆጠርኩ። እንግዲህ የዘር ሃረግ ሂሳብ ከተሰላ እንደ እኔ አይነቱ ሰው ምኑ ጋር ነዉ የሚመደበው ?

 

ኦሮሞዉ ከአማራዉ፣ ጉራጌዉ፣ ከሶማሌዉ ተደባልቋል። በምን መመዘኛ ኦሮሞዉን ከሌላው መለየት እንደሚቻል ግልጽ የሆነ ነገር የለም። የመጀመሪያው ቋንቋ አፋን ኦሮሞ የሆነ ነዉ ኦሮሞ የሚባለዉ ? ወይንስ አራሱን ኦሮሞ ነኝ ብሎ አንድ ሰዉ ስለቆጠረ ነዉ የኦሮሞነትን ሚዛን የሚያልፈው? እንግዲህ አስቡት፣ የዳዉድ ቡድን እንደሚፈልገው፣ «ኦሮሚያ ትገንጠል፣ አትገንጠል» የሚል ሬፌረንደም ለማድረግ ቢሞከር እንኳን፣ ምን ያህል ገና ከጅምሩ ሊያስከትል የሚችለዉን ጭቅጭቅና ዉዝግብ !!!

 

ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ብትገነጠል እነ ፊንፌኔ/ድረዳዋ/ጂም ከኦሮሚያ ቢገነጠሉስ ?

ኦሮምያ እንደምናዉቀዉ ታላላቅ የኢትዮጵያ ከተሞችን የያዘች ክልል ናት። (በነገራችን ላይ ኦሮሚያ የሚባል ክልል በታሪክ ኖሮ አያውቅም። ሕውሃት እና ኦነግ የፈጠሩት ግዛት ነዉ) ፊንፊኔ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ዋና ከተማ ናት። በኦሮምያ እምብርት ዉስጥ ትገኛለች። 99 በመቶ የፊንፊኔ ሕዝብ፣ ከተለያዩ ብሄሮች የተወጣጣ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ሕዝብ ነው። ድረደዋ አማሮች (በዚያ አካባቢ ክርስቲያኖች ናቸው አማሮች የሚባሉት) ሶማሌዎች ኦሮሞዎች ተደባልቀዉ የሚኖሩባት፣ በኦሮሚያ ዉስጥ የምትገኝ ሌላ ሕብረ ብሄር ትልቅ ከተማ ናት። የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ/ናዝሬት፣ ጂማ የመሳሰሉ ከተሞች 80 በመቶ በላይ አማርኛ ተናጋሪ፣ ዜጎች የሚኖሩባቸው ሕብረ ብሄር ከተሞች ናቸዉ። በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ፣ በሰሜን በኩል እሰከ ለገጣፎ፣ በደቡብ እስከ ናዝሬት ተለጥጣለች። ከጥቂት አመታት በኋላ አዲስ አበባ ከናዝሬትና ከደብረ ብርሃን ጋራ መግጠሟ አይቀሬ ነው።

 

እንግዲህ ኦሮሚያ የምትገነጠል ከሆነ፣ ከደብረ ብርሃን እስከ አዳማ የሚኖረዉ ሕዝብ ምን ሊደረግ ነዉ ? የጂማ የድሬደዋ እንዲሁም ያልጠቀስኳቸዉ በርካታ የኦሮሚያ ታላላቅ ከተሞች እንዴት ሊሆኑ ነው? «እኛም ደግሞ በበኩላችን ከኦሮሚያ ተገንጥለን፣ ለብቻችን እንሆናለን» የሚል ጥያቄ ቢያነሱስ ? ኦሮሞዉ ከኢትዮጵያ የመለየት መብት እንደተሰጠዉ እነርሱም ከኦሮሚያ የመለየት መብት የላቸዉም ወይ? አዲስ አበባ፣ ናዝሬትን፣ ደብረ ዘይትን፣ ጂማን ድረዳዋን፣ መቱንወዘተረፈ ጨምሮ በኦሮሚያ ያሉ ከተሞች ለብቻ ሆነዉ እንዴትስ ነዉ ኦሮሚያ ልትኖር የምትችለዉ? ገጠሩ ያለ ከተማው እንዴት ሊሆን ይችላል? ወይንስ በቀድሞ ዩጎዝላቪያ ክሮዬሻዎች ከክራዪና ሰርቦችን ሰርቦች ከባኛ ሉካ ቦስኒያዎቹን በግፍ እንዳባረሩት፣ «ኦሮሞ አይደላችሁም፣ ኦሮሞ ናችሁ» በሚል የዘር ጦርነትና በዘር ላይ የተመሰረተ የሕዝብ ፍልሰት ሊከሰት ነዉ?

 

እንግዲህ ስለ ሩዋንዳ እልቂት ከተነሳ፣ በግልጽ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በአገራችን የዘር ግጭት እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችለዉ፣ የዳዎድ ቡድን የሚያራምደዉ፣ ኦሮሚያ የሚላትን የኢትዮጵያ ግዛት ለመገንጠል የሚደረገው የጥላቻ ፖለቲካ ነዉ እንጂ፣ ኦሮሞዉ፣ አማራዉ ጉራጌዉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ተካባብሮ፣ ተቻችሎ ለመኖር መወሰኑ አይደለም።

 

ሁሉም የኢትዮጵያ ምድር ለኦሮሞዉ መሬቱ ነዉ !

ከጥቂት አመታት በፊት በመቀሌ አረና ትግራይ በጠራዉ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት፣ ሕወሃት በባደመ ጥያቄ ዙሪያ ነደፎ ያስቀመጠዉን አምስት ሰላምሃሳቦች በመቃወም በአዲስ አበበ መስቀል አደባባይ በተዘጋጀዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ንግግር ማድረጋቸዉን በማስታወስ፣ አንድ የሕወሃት ካደሬ «ጠላት ከሆኑት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተገኝተህ ለምን ንግግር አሰማህበሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። አቶ ገብሩ ሲመለሱ «ኢትዮጵያዉያንን እስከሆንን ድርስ ትግራይ መሬታችን ነዉ። ኦሮሚያ መሬታችን ነዉ። ደቡብ እና ሶማሊያ መሬታችን ነዉ። አፋርም መሬታችን ነዉ። ለነርሱም ትግራይ መሬታቸዉ ነዉ። አማራም ትግራይ መሬቱ ነዉ። ሊኖርበት ይችላል። በዚህ ማመን አለብን። ከዚህ ዉጭ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶችን እንደጠላት ለማስፈራሪያ መጠቀም የሥልጣን እድሜን ማራዘሚያ እሆኑ መታወቅ አለበት። አሁንም በሰላምዊ ትግል ካመኑትና ሕጋዊ ፈቃድ ካገኙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብረን መሥራት እንቀጥላለን።በማለት ድርጅታቸዉ ከሌሎች የተቃውሚ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንደሚሰራና በኢትዮጵያ የመከፋፈል ፖለቲካ ቦታ እንደማይኖረዉ ነበር ያስረዱት።

 

በርግጥ አቶ ገብሩ እንዳሉት ለኦሮሞዉ ሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት መሬቱ ነዉ። ባህሉና ቋንቋውን በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ክልሎች ሊከበሩለት፣ ደሴ እንደ ደንቢዶሎ፣ አዋሳ እንደ ደደር፣ መቀሌ እንደ ያቤሎ ሊሆኑለት ይገባል። በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ክልሎችም መስራት፣ መነገድ፣ መኖር መቻል አለበት። ሌላዉም ኢትዮጵያዊ እንደዚሁ።

 

ቋንቋ መግባቢያ ነዉየግጭት መንስዔ ሊሆን አይገባዉም !

አፋን ኦሮሞ ቋንቋችን ነዉ። አማርኛም ቋንቋችን ነዉ። ትግሪኛም ቋንቋችን ነዉ። ብንችል፣ ሁለት ሶስት ቋንቋ ብንናገር ጥቅም አለው እንጂ ጉዳት የለዉም። እናቴ አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ ሶማሌኛ ትችላለች። ጣሊያንኛም ትሞክራለች። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስተማሩኝ ነፍሳቸዉን መድሃኔዓለም ይማርና፣ የምወዳቸው የአማርኛ አስተማሪ ነበሩኝ። ጉራጌ ነበሩ። ጉራጌኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮሞኛን ትግሪኛ ይችሉ ነበር። ታዲያ ይሄ መታደል አይደለም? ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ እንጂ የልዩነትና የመከፋፈል ምክንያት ሊሆን አይገባም። ብዙ ቋንቋ ማወቁ ጥቅም አለዉ እንጂ ጉዳት የለዉም።

 

አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ ጋር ብሄራዊ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን በአንዳንድ ኦሮሞ አክቲቪስቶች እየተጠየቀ ነዉ። «አፋን ኦሮሞ የፌደራል ቋንቋ ከሆነ፣ ኦሮሞዉ በክልልም በፌደራልም ደረጃ ከሌላዉ ሕዝብ ይነጣል። ቢያንስ አማርኛ ፌደራል ቋንቋ መሆኑ ነዉ፣ አንድ የሚያደርገንና የሚያስተሳስረን » በሚል ተቃዉሞ የሚያነሱ አሉ። «አፋን ኦሮሞ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን ከተደረገ፣ አማርኛም ከአፋን ኦሮሞ እኩል የኦሮሚያ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት» የሚሉም ጥቂት አይደሉም። ግእዝ ብቸኛ አፍሪካዊ ፊደል ከመሆኑም ባሻገር ፣በግእዝ መጻፉ፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደመግደል የሚቆጥሩም አሉ። በአንድ ጊዜ የግእዝ ፊደልን በማወቅ፣ አፋን ኦሮሞንም አማርኛንም ማንበብ ስለሚቻል። በተቃራኒዉ ደግሞ ከግእዙ ፊደል ይልቅ «በላቲኑ ነዉ አፋን ኦሮሞ መግልጽ የሚቻለዉ» የሚሉም የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች አሉ። ነገሮችን ከተለያዩ ማእዘናት ከማየታችን የተነሳ የሃሳብ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

 

ነገር ግን፣ ከተከባበርን፣ በመሃከላችን ቅንነት ካለ፣ አንዳችን የሌላችንን ስሜት መረዳት ከቻልን፣ ለሁሉም የሚጠቅም፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ መተማመን የሞላበት ዉሳኔ ማሳለፍ እንችላለን። ለምሳሌ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል ቋንቋ እንዲሆን ቢወሰን፣ በኦሮሚያም አማርኛ ከአፋን ኦሮሞ ጋር የሥራ ቋንቋ ቢደረግ፣ በፌዴራል ወይንም በክልል ደረጃ ላቲን ወይን የሳባ ፊደል መጠቀም አለብን » የሚል ከላይ ወደ ታች የሆነ ዉሳኔ ከሚተላለፍ፣ ሁለቱም ፊደሎች ለሕዝቡ እንደ አማራጭ ቀርበዉለት፣ በወረዳና በዞን ደረጃ ሕዝቡ የሚመቸውን እንዲወስን ማድረግ ቢቻል ለሁሉም የሚቀል ሊሆን ይችላል። አማርኛ ተናጋሪዉ ከልቡ አፋን ኦሮሞን ለመማርና ለማወቅ ቅናት ካደረበት፣ ኦሮሞዉም እንደ አፋን ኦሮሞ አማርኛን ቢማረው፣ አብረን የበለጠ እናድጋለን። በጭራሽ ቋንቋ የመለያየታችን ምክንያት ሊሆን አይገባም።

 

ማጠቃለያ

እነ ዳዎድ ኢብሳ «ኦሮሚያ የኦሮሞ ብቻ ነው። ኦሮሞዉ ከፈለገ ይገነጣል» ሲሉን ለኦሮሞ የቆሙ ሊያስመስላቸዉ ይችል ይሆናል። ነገር ግን አይደለም። የኦሮሞን መብት እያስከበሩ ሳይሆን ኦሮሞዉን እየጎዱት ነው። ኦሮሞዉ በአካባቢ ካሉት ወንድሞቹ ጋር እንዲቃቃር፣ እንዲለያይ ነው እያደረጉት ያሉት።

 

ሕወሃት በስልጣን ለመቆየት ሲል በትግሬዉና በተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ዘንድ የጥላቻ ግንብ ለመገንባት እንደሞከረዉ፣ የዳዎድ ቡድንም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በኦነግ ዉስጥ ሃሳባቸው ዉድቅ ሲሆንባቸው፣ በኦነግ ዉስጥ ያላቸዉን ቦታ ለመቆናጠጥ ሲሉ በኦሮሞዉና በተቀረዉ ኢትዮጵያዊ መካከል ችግር ለመፍጠር ደፋ ቀና እያሉ ነዉ። ይህ ቡድን እያሰራጨ ያለዉ፣ የዘር ጥላቻ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ፣ የወጣት ኦሮሞዎችን እንጭጭ አይምሮ እያበላሸ ያለ ወይንም ሊያበላሽ ስለሚችል፣ በሙሉ ኃይል፣ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሊመከተና ሊሸነፍ የሚገባዉ ፀረሕዝብ፣ ፀረኢትዮጵያና ጸረኦሮሞ ፖለቲካ ነዉ።

 

እግዚአብሄር ፍቅርና አንድነቱን ይስጠን!