አቡጊዳ – አፍቃሪ ሕወሃት የትግራይ ተወላጆች በሻእቢያ ላይ ጦርነት እንዲከፈት ጠየቁ !
ገዢዉ ፓርቲ በአፋር ክልል ተፈጸመ ባለዉ የሽብር ተግባርን አስመልክቶ፣ አፍቃሪ ሕወሃት የሆነዉ የትግራይ ተወላጆች ማህበር በሰሜን አሜሪካ፣ በሰጠዉ መግለጫ የመለስ አገዛዝ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቀ።
የገዢዉ ፓርቲ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት በሻእቢያ መንግስት ላይ ተገቢዉን እርምጃ የማይወስድ ከሆነ ኢትዮጵያ እርምጃ እንድምትወስድ መግለጹን ያስታወሰዉ የማህበሩ መግለጫ፣ የተባበሩት መንግስታት ማእቀብ ቢጥልም የሻእቢያን እኩይ ተግባር የሚለዉን ለማስቆም እንዳልቻለም ይገልጻል።
“መንግስታችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስከበር መብቱን በመጠቀም ይህንን የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ስጋት የሆነዉን ኃይል ሽብራዊ ተግባርና ጥቃት ለማቆምና የሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያረጋገጥ» በመግለጫቸው የጠየቁት የማህበሩ አባላት፣ ገዢዉ ፓርቲ በሻእቢያ ላይ ለሚወስደዉ እርምጃ በሙሉ አቅማቸው እንደሚደግፉት አረጋግጠዋል።
የኢሕአዴግ ድጋፍ ማህበር በሰሜን አሜሪካ የሚባለዉ ማህበር እያለ፣ ለምን የትግራይ ተወላጆች ብቻ ይህንን መግለጫ እንዳወጡ ብዙም የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፣ በብዙ አፍቃሪ ኢሕአዴግ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ፣ በአቶ መለስ ዜናዊ ላይ ትልቅ ጥርጣሬ እንዳለም ከውስጥ አዋቂዎች የሚደርሰን ዘገባ ያለመለክታል።
ከዚህ በፊት የተለያዩ ቅሬታ ቢኖራቸዉም ዉስጥ ዉስጡን ከመናገር ዉጭ በይፋ ከገዢው ፓርቲ የተለየ አቋም አንጸባርቀዉ የማያወቁት የአገዛዙ የትግራይ ተወላጅ ደጋፊዎች ፣ አሁን ይሄን አይነት ከአቶ መለስ ፖሊሲ የተለየ፣ አቋማቸዉን ይፋ ማድረጋቸዉ፣ አቶ መለስ በኤርትራ ላይ ባላቸው አቋም፣ ከብዙ የሕወሃት ታጋዮችና ደጋፊች ጋር መሰረታዊ ልዩነቶች እንዳላቸው የሚያሳያ ነዉ።
አቶ መለስ ዜናዊ፣ በባድመ ጦርነት ወቅት፣ ሻእቢያ በመቀሌ ትምህርት ቤት ላይ ቦምብ አፈንድቶ ብዙ ሕጻናትን ሲገድል፣ ኢትዮጵያ እራሷን እንዳትከላከል፣ በኤርትራ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘር ፍላጎት እንደነበራቸውአን ሲያከላክሉ እንደነበረ ይታወቃል። ከርሳቸዉ ፍላጎት ውጭ፣ ጦርነቱ ተጀምሮ ፣ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም ፣ የአልጀርስ ስምምነትን ተሯሩጦ በመፈረም፣ በአሥር ሺሆች የኢትዮጵያን ደም የተገኘዉን ድል ማስቀልበሳቸው ይታወሳል።
«የትግራይ ተወላጆች ያወጡትን መግለጫ የሚያነብ አይኖርም» ያሉን በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲአክ ተንታኝ «አቶ መለስ ሻእቢያ ላይ ጦርነት መቼም አይከፍቱም። በየጊዜዉ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ፣ የሚያወጧቸዉ ማስፈራሪያዎች፣ የትግራይ ተወላጆችን በሻእቢያ ላይ ጠንካራ እንደሆኑ ለማሳየትና ለማታለል ሲሉ የሚያደረጉት ነዉ» ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።