የወያኔ “ባለስልጣናት ሆዳቸው አይሞላም” ሲል የሰበታ ከተማ ከንቲባ አወገዘ

በአዲስ አበባ ዳርቻ ላይ የምትገኘው የሰበታ ከተማ ከንቲባ ለወያኔ ባለስልጣናት ከፍተኛ መጠን ያለው የመሬት ይዞታ ቢያከፋፍልም ሆዳቸው የማይሞላ ሆነው እንዳስቸገሩት ለቅርብ ወዳጆቹ ማውጋቱን ለግለሰቡ ቅርብ የሆኑ ሰው ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።

የሰበታ ከተማ ከመሬት ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ከሚገኙት ከተሞች ውስጥ አንዷ እንደሆነች እና በቅርቡም መሃንዲሶችን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች መታሰራቸውን፤ የመለስ ዜናዊ ሚስት አዜብ መስፍንም እራሷ በስፍራው ተገኝታ የእስሩ ዋና አቀናባሪ እንደበረች ዘግበናል። ይሁን እንጂ፥ መሃንዲሶቹም ሆኑ ሌሎቹ ሰራተኞች በሙሉ እነ አባ ዱላ ገመዳን ጨምሮ ከበርካታ የወያኔ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር እንደሚሰሩ ከተለያዩ ምንጮች የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ዘጋቢያችን አጠናቅሮ በላከው ዘገባ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮምያ ክልል ከተሞች የድለላ ተቋሞች እንጂ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አይመስሉም። አንድ ውስጥ አዋቂ ምንጭ ጉዳዩን ሲያብራሩ፥ ሁሉም ነገር የሚሰራው በመመሳጠር በመሆኑ ዛሬ አንድ ከንቲባ ቢሮ መግባት ላይ ካለ ሚኒስቴር ጋር ቀጥታ እንደመገናኘት ነው።

እኒሁ ግለሰብ እንደሚሉት፥ የመንግስት መስሪያ ቤቶች “ለአንዳንዱ እንደ እናቱ ቤት፣ ለሌላው እንደ እንጀራ እናት ቤት ሆነዋል”። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በአንድ ግለሰብ እጅ 30 የመሬት ካርታዎች መያዛቸውን የገለጹት ምንጫችን፤ በርካታ ህግ ተከትለው መሬት የጠየቁና፣ ይሰጣችኋል ተብለው ደረሰኝ የተቀበሉ ግለሰቦች ግን አንዲት ቤት መስሪያ መሬት ለመረከብ አራት አምስት አመታት ይንከራተታሉ ብለዋል።

የዘረኛው አገዛዝ ባለስልጣናት በሙስናው ውስጥ እጃቸው እያለበት ህገ-ወጥ የመሬት ንግድን በመዋጋት ስም በሰበታ ከተማ ላይ ትኩረታቸውን መጣላቸው ያልገባው ከንቲባም፤ ለባለስልጣናቱ ሁሉ የሚፈልጉትን ያህል መሬት ማደሉን ጠቅሶ፣ “ሰው ጠገብኩ አያውቅም” ሲል ተደምጧል። አዜብ መስፍን በሺሆች የሚቆጠር ካሬ ሜትር መሬት በሰበታ እንዳላት ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

የከተማይቱን ሰራተኞች መታሰር ተከትሎ ከንቲባው ከስልጣኑ እንደወረደ የታወቀ ሲሆን፤ ይህ ግን ህዝብን ለማታለል እንደሆነ እና ግለሰቡ ወደ ሌላ መስሪያ ቤት ተወስዶ ምክትል ሃላፊ ሆኖ መሾሙን ምንጫችን ገልጸዋል።