ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 እና እኛ በዮሐንስ እ ተመስገን

ጽሁፍን ለመተቸት ጸሀፊን መዝለፍና መስደብ እንደ ባህል እየሆነ መምጣቱ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል:: በውጭ የምንገኝ አብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን እኔንም ጨምሮ የሰፈረብን ዕውቀት ማነስ ካለን ባህልና ወግ ካደግንበት የፖለቲካና የማህበራዊ ደረጃ አወቃቀር ካደረሱብን ጉዳቶች ለመላቀቅ ቆም ብለን ካላሰብንበት ነገ የምንደርስበት ነገር ከዛሬው በከፋ ቁጥር ብዙዎችን የማያስማማ ሊሆን ነው::
ከቤተሰብ ተነስተን በትምህርት ቤት: በየስራ ቦታችን በየእድሩ በየቀበሌው በየሃይማኖቱ በፖለቲካው በጠቅላላው በሀገሪቱ አብዛኛዎቻችን ሲነገረንና አሜን ስንል ኖርን እንጂ ሀሳብ በእኩል አፍልቀን ስንከራከር ስንረታታ ስላላደግን ዛሬ እኛነታችን ላይ የሚንጸባረቀው ሁኔታ በጉልህ እየታየ ነው:: ከቤተ ሰብ ጋር እንኳን ልጆች ሆነን ከአዋቂ ጋር ማውራት እንደ ባለጌ በሚያስቆጥርበት ህብረተሰብ ልማድ ውስጥ አልፈን ዝምታ ወርቅ ነው እና ዝም ባለ አፍ ምን አይገባበትምን ሲያስጠኑን አድገን እንዳለ አለን::

የዚያም ውጤት የየራሳችንን የሰውነት ቦታ በራስ መተማመንና ድፍረቱን ሸርሽሮ ስነልቦናዊ ተጽዕኖው ካሳረፈብን ጠባሳ ለመውጣት የምናደርገው ትግል በትክክለኛ መስመር እየተጓዘ ስለመሆኑ መረጃዎች በበቂ አልታዩም:: ታድያ ከዚያች ካሳደገችን ሀገር ውጭ ስንወጣና ነጻ የሆን ሲመስለን ያንን ጉዳታችንን ለመሸፈን ለመፋቅና ለማካካስ የምናደርገው መውተርተር ይመስለኛል የተጻፈውን ነገር ከመተቸት ሃሳቡ ላይ ከመነጋገር ጸሀፊውን መሳደብ ስራዬ ብለን የምንያያዘው:: ማስረዳት ሲያቅተን ወደ ንዴት የምናመራው በተሻለ ሃሳብ ማሳመን ሳንችል ስንቀር የተበለጥን የተናቅን አድርገን በመቁጠር ተከራካሪአችንን ላይ ታርጋ በመለጠፍ ስለጠላሁት አገር ይጥላው ብሎ ማሳደምና ያለ የሌለውን ጨምሮ ውጉዝ ከመአርዮስ ብሎ መመደብ መሥደብና ለሰዳቢ አሳልፎ መስጠት የተለመደው::

ከዚያም ባለፈ ዛቻና ያልሆነ ስም በመለጠፍ እንደኔ ስላላሰበ ከጠላት መመደብ አለበት ተብሎና በማህበረሰቡ እንዲጠላ ለማድረግ በየስልኩ በየማህበሩና በየስራው ቦታ ለማስጠቆር መሬት ሲጭሩ የሚያድሩ በሚያሳዛን ሁኔታ ቁጥራቸው እየበዛ ነው:: እንዴትስ ነው ተስማምተን የሃሳብ ልዩነቶች እንዳሉ በማክበርና በመረዳዳት ሀሳብን በሃሳብ ለመቃወም የምንሞክረው? ስንቶቻችንስ ነን ሌላውን ላለመጉዳት ተጠንቅቀን ጥሩውን ስናመስግን ስናበረታታ ስህተቱንም ጠቁመን እንዲታረም የምናደርግ? ዛሬ ዛሬ የሚታየው ግን ሃሳብ ያመጣው ሰው ላይ ማነጣጠርና ስሜቱን ለመጉዳት ለመበቀልና ወደታች እኛ ካለንበት ወለል በታች ድረስ ጎትተን ለማዋረድና ለማሳፈር ሌት ተቀን የምናስበው? ከሰሞኑ ዲያቆን ሙሉጌታ ለአዜብ ጌታቸው የተጻፈ አሳዛኝና የዘቀጠ አሳፋሪ ነገር ቀንጨብ አድርጌ እንደማስረጃ ላቅርብ::

ይቻላል! ለዛውም በተሻለ አማርኛ፣ እንደ ቅዱስ ገብርኤል ሰይፍ በዋለ ባደረ ቁጥር የማይበርድና እያዋዛ እየቆራረጠ በሚገባ ባማረ ፍልስፍና ድህረ-ገጽ የሚሉት ነገር እርም እስክትዪ ድረስ ልክሽን ማስገባት ዕድሜ ልክሽን ጎብጠሽ፣ ተሳቀሽና በራስሽ ላይ አፍረሽ ትኖሪ ዘንድ የሚያደርግ ራስሽን የሚያስተውና የሚያስጠላ በገባሽ በወጣሽ ቁጥር የሚያሳድድሽ በዘመንሽ ሁሉ የሚጸጽትሽ ቃል ለአንዴና ለመጨረሻ የማያዳግም ምላሽ ማስታጠቅ ማሸከምና መስጠት ይቻላል! ይህ ግን ዓላማና ግብ ያለው ሰው ባህሪ አይደለም። አንቺ ስላበድሽ ዕብድን ተከትዬ ገደል አልገባምና ይህን አላደግኩም። (ማቴ. 27፥39-44 ይመልከቱ) አደራ!

እዚህ ላይ ነገሩን ያመጣሁት የዲያቆን ሙሉጌታን የአማርኛ እውቀት ወይም የተልዕኮውን አግጣጫ ለማመላከት አይደለም አዜብ ጌታቸው ሀሳቡን ተቃውማ ስለጻፈች ለምን ተደፈርኩ እኔ የምለውን የሚቃወም ወዮለት አይነት በማስፈራራት ለማጥፋትና የስነልቦናዊ ጉዳት በመፍጠር በስጋት እንድትኖር ስብዕናዋ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ መርዝ በመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስ ለውሶ ሊጎዳት እንደሚችል ነገር ግን ዓላማውና ግቡ እንዳልሆነ ዲያቆኑ ቸርነቱንና መሃሪነቱን መግለጹን ለማሳየት ነው:: ክፋትና ምቀኝነትን ያዘለው የመበቀልና የማጥፋት ዛቻ በመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስ ተሸፍኖ እግዚአብሄርን አውቃለሁ ከሚል ዳያቆን ይህን መሰል የእፉኝት መርዝ ሲረጭ ማየት አሳፋሪና አሳዛኝ ከማለት በላይ ቃልም የለኝም ለዚህ የዘመን መጨረሻ ምልክት::

ገደብ ያልተበጀለት ነጻነት ያለሃላፊነትና ተጠያቂነት ስርዓት አልበኝነት ነው:: ይህ ዲያቆን ነኝ የሚል ሰው በነጻነት ስም ወይም ጥሩ ቃላት አሳክቼ መጻፍ እችላለሁ ብሎ ወይም ከኔም በላይ ዕውቀት ላሳር ብሎ መስቀል በሚይዝበት እጁ ጦር ከሰበቀ የእግዚአብሄር ቃል በሚሰበክበት አፉ ዓጉራ ዘለል አስጸያፊ ነገር ካወራበት አንባቢው ይህን መሰል ጤና የጎደለውን አጻጻፍ ሊያወግዝ ይገባል:: ይህ ዲያቆንም ይህን ለከት የሌለው የንቀት ንግግር ለሃያ አመታት ሲሰማ ስላደገ ሰውን ማዋረድና ሰውን ማስፈራራት ትልቅ የሚያደርገው መስሎት ከሀገር መሪ ተብዬው የተማረውን ነው እያሳየን ያለው::

ሌላው ችግር ከአብዛኛው የሀገራችን ህዝብ አንስቶ ፊደል ቀመስ በተባለው ከትንሹ 12 አመት ትምህርት እስከ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው በሀገርም ውስጥ ይሁን በውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ በዓለም አቀፋዊው የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ የተጻፉትን መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ያላነበበ የሚበዛ ነው የሚመስለኝ:፡ ጥቂቱም አነበበ እንኳን ቢባል ያልተረዳው ይበዛል የተረዳውም ቢኖር ከእለት እለት ኑሮው ጋር አያይዞ በዚያ መርህ ሊጓዝ ራሱን ያስገዛ ኢትዮጵያዊ እጅግ እጅግ በጣም ትንሽ ቁጥር ያለው ሰው ነው በኔ ግምት:: በተቀረው የአለም ከፍል ከትምህርት ቤት ጀምሮ ዜጎቻቸውን እያስተማሩ ዜጎች መብታቸውንና ግዴታዎቻቸውን ለማሳወቅ መንግስታት ይጥራሉ:: እኛ ግን በዚህ ረገድ ያለን ግንዛቤ ውሱን ነው ብዙም ይቀረናል:: በየራሳችን ሀሳብ ሳንጋጭና ሳንዘላለፍ መኖር እንችላለን ለራሳችን ሳናሳንስ ልንዝቀው የምንፈልገውን መብት ለሌላው ለመከልከል ስንደፋደፍና ስንሳደብ እኛ ከልካዮቹ ያንን መብት ማን እንደሰጠን ራሳችንን ለመጠየቅ ድፍረት የሌለን ደካሞች መሆናችንን ላለማሰብ አእምሮአችንን ከርችመን ሌላውን በመሳደብና በማንኳሰስ በሌላው ሂሳብ ራሳችንን ለማግዘፍ እንደክማለን:: እንደየእምነታችን መኖር ስንችል እኔ እንደማስበው ስላላሰብክ ጠላቴ ነህ ብሎ መፈረጅና ሌላውን ለማጣጣል ትንሽነትን በሚያሳይ ስድብና እርግማንን መራቅ መሞከር ተገቢ ነው:: ለምሳሌ አስር ኢትዮጵያውያን ብንገናኝና በሃያ የተለያዩ የሀገራችን ማህበራዊ ፖለቲካና ኤኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ብንመክር አስራችንም በሙሉም ይሁን በከፊል በጉዳዮቹ ላይ መስማማት አይጠበቅንም በአንድ ወይም ከአንድ በሚበልጥ ርእሶች ላይ አስራችንም የተለያየ አመለካከት እምነትና አፈጻጸም ሀሳብ ሊኖረን ይችላል ያን ግዜ ታድያ ወያኔ የደርግ ስርአት አቀንቃኝ ነፍጠኛ ኢሰፓ ኢህአፓ ሻእቢያ ኢህአደግ ብሎ መለያ በመለጠፍ በንቀት በፉከራ በጥላቻ በስድብ በመሰነዛዘር ለመጠፋፋት በማሰብ መፍትሄ ለማምጣት ስንሞክር ነው የከረምነው:: ሌላውን ወደኛ አስተሳሰብ የምናመጣው ሀሳቡን በማክበር የተሻለና ለሀገር ለወገን የሚበጅ እንዲህ ቢሆን ነው እስኪ እንምከርበት በማለት እንጂ በጥላቻና በመናናቅ አይደለም የተለያየን ሰው ሀሳብ ወደ አንድ ማቀራረብ የሚቻለው:: ዛሬ ዛሬ እንደሚታየው በብእር ስም ጀርባ በመከለል ስልጣኔ የጎደለው ጸያፍ ንግግር በየድረ ገጹ የሚለጥፍ ድሮ በትምህርት ቤት ሽንት ቤት ግድግዳ ላይ ብልግናውን ነገር እንደሚጽፍ ጋጠወጥ ነው ራሱን ማየት የሚገባው:: በአደባባይ ለማለት የማልደፍረውን ተደብቄ የምለው ምን አይነት ሰው ተርታ ራሴን ብመድብ ነው ብሎ ሁሉም ስልጣኔ የጎደለው ነገር የሚጽፍ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል::

አንድ የቅርቤ ሰው ግሩም የተሰኙ የተለያዩ ጽሁፎች በተለያዩ ድረ ገጾች ያወጣል:: ታድያ ከሰሞኑ ለጻፋቸው የተሰጡት አስተያየቶች አበረታች ሆነው ጥቂት ዘራፍ ባዮች ጽሁፉን ትተው ወደስድቡ መግባታቸው እንዳሳዘነው ሲገልጽልኝ እነዚያን ውብ መጣጥፎቹን እንደገና እንዳይጽፍ ተጽዕኖ አሳድረውበት ይሆን? አልኩና ለማንኛውም በዚህ ጽሁፍ መልዕክት የምለው ደካማውንና ስልጣኔ የጎደለውን ተቺ እንደሌለ በመቁጠር የምናምንበትን በመጻፍና በመናገር መብታችንን መጠቀም ነው:: ለማጠቃለያም ለዚሁ ወዳጄ አንድ በቅርብ የሰማሁትንና ያስደመመኝን ወግ እነሆ:
በእድሜ ጠና ያሉ አዛውንት ከልጃቸው ጋር በቅሎአቸውን እየጎተቱ በገበያ መሃል ይሄዳሉ::

ገበያተኛው እኒህ ሁለት ሞኞች በቅሎ እየጎተቱ በእግራቸው ይሄዳሉ ሲሉአቸው አዛውንቱ ይሰማሉ ከዚያም ትንሽ እንደተጓዙ አዛውንቱ በቅሎዋ ላይ ይወጡና ልጅ ፊት ፊት ይሄዳል:: አሁንም ተመልካቹ ገበያተኛ አይ ይሄ ሽማግሌ ለራሱ በቅሎ ላይ ሆኖ ይህን አንድ ፍሬ ልጅ በእግሩ ያስኬደዋል ሲል ሽማግሌው ጆሮ ይገባል:: ትንሽ ተጉዘው አዛውንቱ ይወርዱና ልጁን በቅሎዋ ላይ እንዲወጣ አድርገው እርሳቸው ከፊት ፊት መጓዝ ጀመሩ በዚህ ሁኔታ ያዘኑ ሌሎች ገበያተኞች አይ ስምንተኛው ሺህ ምናለ ይህን የመሰለ ጎረምሳ በግሩ ቢጓዝና እኒህ አዛውንት በቅሎዋ ላይ ቢወጡ ሲሉ ተሰሙ:: በተለያየው የሰው ሀሳብ የተገረሙት አዛውንት ጉዞውና እርጅናው ገፋፍቷቸው ልጁን ከፊት በቅሎዋ ላይ አድርገው እርሳቸው ከኋላ ተቀመጡና ሁለቱም በቅሎዋ ላይ ሆነው ሲጓዙ ያዩአቸው በመማረርና ለጌታ በማሳቀል ይችን የግዜር ፍጡር እንስሳ ለሁለት ተቀምጠውባት ሊገሏት ነው ግፍ የማይፈሩ አባትና ልጅ ሲባል የሰሙት አዛውንት ለልጃቸው የሆነውን ሁሉ ካስረዱ በኋላ ሰው የሚለውን ስለማያጣ ትክክል የሚመስልህን ነገር ብቻ አድርግ ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ::

ቸር ይግጠመን