በደርግ ዘመን የተፈፀሙ በደሎች የይቅርታና የዕርቅ ጥሪ (VOA)

በደርግ ዘመን የተፈፀሙ በደሎችንና ጥፋቶችን ሃገራዊ ይቅርታና ዕርቀሠላም ባሉት መንገድ ለመጨረስ አራት የኢትዮጵያ አብያተ-ዕምነት መሪዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጥሪ አቀረቡ፡፡

በያዝነው ታኅሣስ መጨረሻ የሠላምና የዕርቅ በዐል ለማድረግም ዕቅድ ተይዟል፡፡

የኃይማኖት መሪዎቹ ዕሁድ ታኅሣስ 10 ቀን 2003 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለፁት የይቅርታና ዕርቁ ጥረት የተጀመረው ከሁለት ዓመታት ወዲህ ነው፡፡

ለዚህም ጥረት መነሻ የሆነው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በፍርድ ሥር የሚገኙ የደርግ ባለሥልጣናትና በተለያዩ ደረጃዎች ይሠሩ የነበሩ ታራሚዎች ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሠረት እንደሆነም የኃይማኖት መሪዎቹ የፅሁፍ መግለጫ ያረጋግጣል፡፡

የኃይማኖት መሪዎቹን ወክለው ጥሪውን ያሰሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትረያርክ አባ ጳውሎስ ናቸው፡፡

አቡነ ጳውሎስ በዚሁ ጥሪ “… ልጆቻችን ቂም በቀልን መውረስን አስወግደው በሠላም፣ በፍቅርና በመቻቻል እንዲኖሩ፣ ወደፊትም ተመሣሣይ አስከፊ ድርጊት በኢትዮጵያ ታሪክ ፈፅሞ እንዳይደገም የዕርቅና የይቅርታ መልዕክታችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በመተማመን ደፍረን እናቀርባለን፡፡” ብለዋል፡፡

ጥሪውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እሥልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ የሱስ ናቸው፡፡

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

1 Comment on “በደርግ ዘመን የተፈፀሙ በደሎች የይቅርታና የዕርቅ ጥሪ (VOA)”

  1. These people have ruined the lives of millions of Ethiopians,many people were killed,others were abused and were forced to flee ,their properties were confiscated without any compnestation,the childern of the victimes are still suffering beccuse of the wrong dicisions passed by derg officials .So I don’t accept the idea of forgiving them.They have to suffer forever.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*