በተለያየ ዘመን ለነበሩ የሀገራችን መሪዎች የቀረበ ጥያቄና ይሰጣሉ ተብሎ የሚታሰበው መልስ

ፍየሏ !

ፍየሏ ወንዙን አቋረጠች_ _ _ _ _ _ ለምን?

በተለያየ ዘመን ለነበሩ የሀገራችን መሪዎች የቀረበ ጥያቄና ይሰጣሉ ተብሎ የሚታሰበው መልስ

አጼ ቴዎድሮስ (ቆራጥ ጀግና የአንድነት መሪ)
ይህች ዟሪ ፍየል መሄድ የለመደች:
መሄዷን ብቻ እንጅ ሀገር ያላወቀች:
ባይገባት ነው እንጂ እራቴ ነበረች:
አንድነት የማታውቅ ይህች የፍየል ዕብድ:
ነይ ተመለሽ በሏት ርቃ ሳትሄድ::

አጼ ዮሐንስ (ሃይማኖተኛ ለስላሳ መሪ)
የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቃት እንጅ ወንዝ ማቋረጧስ ደግ አልነበረም! ግን አሉ ወደ አማካሪአቸው ዞረው:: ግን ይህች ፍየል ተጠምቃለች? ማተቧንስ እንዳሰረች ነበር?

አጼ ምኒልክ (ጀግና ዲፕሎማትና ቆፍጣና መሪ)
ስማኝ ያገሬ ሰው ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን እምነት ማዛለፍ ነውና ለሀገርህ ለኢትዮጵያና ለማተብህ የምትቆረቆር ሁሉ በምትወደው ታቦት ይዤሃለሁ ፍየሏን መልሳት:: ይህን ባታደርግ ግን ወላዲት አምላክ ምስክሬ ትሁን አልምርህም::

አጼ ኃይለሥላሴ (ዲፕሎማትና ለስላሳ መሪ)
የምንወድህና የምትወደን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ፍየሏ ወንዙን ስታቋርጥ በቸልታ መመልከት የለብህም:: በአንዲት ፍየል ወንዝ ማቋረጥ ምክንያት ሀገርን ንጉሥን ዘርን ማሰደብና ታሪክን ማበላሸት የለብንም::

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም (እልኸኛ የወታደር መሪ)
ጓዶች! ተደፍረናል: ተዋርደናል:: ፍየሏ ወንዙን አቋርጣለች!! ይህ ደግሞ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተነጣጠረ የኢምፔርያሊስት ቡችሎችና አድሃሪያን አብዮቱን ለመሸርሸርና አብዮታዊ ትግላችንን ለማደናቀፍ የሸረቡት ሴራ ነው:: ፍየሏ እስክትመለስ አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀረን እንዋጋለን::

አቶ መለስ ዜናዊ (ፈሪ ራስ ወዳድ ብልጣ ብልጥና ለጥቅሙ ብቻ የሚኖር መሪ)
በመሰረቱ የአንዲት ፍየል ወንዙን ማቋረጥ በኤርትራ ሉዓላዊነት ወይም በተከዜና በአትባራ ወንዝ የግድብ ልማት እንቅስቃሴአችን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለ ወይ ነው ጥያቄው መሆን ያለበት:: የለም::
ስለዚህ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላት! አራት ነጥብ::

ተሻሽሎ የተጻፈ
ዮሐንስ እ ተመስገን
12-10-2010