የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር!! ከመድረክ የተሰጠ መግለጫ

በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የባለአገርነት ስሜት እንዲኖራቸው የሚወጡ አዋጆች መመሪያዎችና ድንጋጌዎች ሁሉ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ስምምነት ያገኘ መሆን ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ሕዝቡ የሚተዳደርበትን የትኛውንም አይነት ሕግ ሲያወጣ ማዕከል ማድረግ ያለበት የዜግነት መብትን ለማስጠበቅ ለማጎናጸፍ እንጂ አንገት የሚያስደፋ የሚያሸማቅቅ የሚያስፈራራ አፋኝና ባጠቃላይ በመብት ገፈፋ ላይ የተመረኮዙ መሆን አይኖርበትም፡፡ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም በማን አለብኝነት የዜጎችን ንብረት የማፍራት የመሸጥ የመለወጥ እና የመጠቀም መሠረታዊ መብቱን በሕግ ሽፋን የገፈፈ አዋጅ ነው፡፡ በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በሥልጣን በቆየባቸው 20 ዓመታት ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የሚወጡ ህጎች ከፖለቲካና የሥልጣን ዕድሜ ከማራዘም አንፃር ብቻ ታይተው በሕዝብ ላይ የሚጫኑ ናቸው፡፡

የሊዝ አዋጅ አወጣጥ እና የአፀዳደቁን ሂደት ብንመለከት ፈፅሞ የተለመደውን አሰራር የተከተለ አይደለም፡፡ የዚህ አዋጅ አፀዳደቅ እና አቀራረብ ሁለት መሠረታዊ ግድፈቶች ይታይበታል፡-

1ኛ. በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀፅ 3 “የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ሉአላዊነታቸው የሚገለፀው በዚህ ሕገ-መንግሥት መሠረት በሚመርጣቸው ተወካዮቻቸው እና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይሆናል፡፡” ይላል ይሁን እንጂ በአዲሱ የሊዝ አዋጅ መሬትን በመሰለ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆነውና በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተው ሕዝብ ጉዳዩ ቀርቦለት በነፃነት እና በግልፅነት እንዲወያይበት አልተደረገም፡፡

2ኛ. ኢህአዴግ በፓርላማው የወጣው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ስነ-ምግባር ደምብና አሰራር እንኳን እንደሚገልፀው ከስብሰባው 48 ሰዓት በፊት የአንድ አዋጅ ረቂቅ ለም/ቤቱ አባል መድረስ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የፓርላማ አባሉ በዚህ 48 ሰዓት ውስጥ ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ባለሞያዎችን አማክሮ ይቀርባል፡፡ ረቂቅ አዋጁም ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል፡፡ ኮሚቴውም ባለሞያ ጋብዞና አማክሮ ለሕዝብና ለሚዲያው ክፍት አድርጎ ያወያያል ሃሳቡን አዳብሮ በድጋሚ ለፓርላማ ያቀርባል፡፡ ፓርላማው ሲፈልግ ያፀድቃል፡፡ ሳይፈልግ ውድቅ ያደርገዋል፡፡ ግልፅ የሆነው አሰራር ይህ ሆኖ ሳለ ለራሱ ከመሰለውና ለፖለቲካ ፍጃታ ይጠቅመኛል ካለ እንኳን የሥነ ምግባር ደምብና አሰራር ቀርቶ ሕገ-መንግሥት የሚጥሰው የኢህአዴግ መንግሥት ትልቁን የዜጎች መብት ለፓርላማ አባላት ማታ 12፡00 ታድሎ ጧት 3 ሰዓት አዋጅ ሆኖ እንዲፀድቅ አድርጓል፡፡

እዚህ ላይ አንዳንድ ጉዳዮችን ወደ ኋላ መለስ ብሎ መዳሰስ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ በብዙ ጉዳዮች በኢህአዴግ መንግሥት በወንጀለኝነት የሚጠቀሰው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እንኳን የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ንብረት ለማድረግ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 47/67 መዕራፍ ሁለት አንቀፅ 1 “አንድ ቤተሰብ ወይም ግለሰብ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ የሚያውለው እስከ 500 ካሬ ሜትር የሚደርስ የከተማ ቦታ ሚኒስትሩ በሚወጣው መመሪያ መሠረት በይዞታ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ባለይዞታ የሟች ሚስት ወይም ባል ወይም ልጆች በቦታው ተተክተው የመጠቀም መብት ይኖራቸዋል፡፡” ይላል፡፡ ለም/ቤት ወይም ድርጅት በሚቀርበው አቤቱታ መሠረት ሚኒስቴር መ/ቤት እንደሚሰጥ በዚሁ መዕራፍ አንቀፅ 2 እና 3 ይገልፃል፡፡ በዚሁ አዋጅ ምዕራፍ 3 እና 12 የከተማ ቤት ስለማስተላለፍ በሚለው ሥር “አንድ ቤተሰብ ግለሰብ ወይም ድርጅት በከተማ ቤቱ የመጠቀም ወይም ይህንኑ ቤት የማውረስ የመሸጥ ወይም የመለወጥ መብት አለው፡፡” ይላል፡፡

ይህንን አዋጅ ስንመለከት የአገሪቱን የከተማ ነዋሪዎች ከግለሰብ ጭሰኝነት ነፃ ያወጣ የከተማ ቦታን የመሸጭ የመለወጥ እና የባለቤትነት ክብር እንዲጎናፀፉ ያስቻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንድ አዋጅ ትክክለኛ አዋጅ ነው፡፡ ሕዝባዊ ነው፡፡ ሊባል የሚችለው ብዙሃን ሕዝብ ሲያስደስት ነው፡፡ ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያወጣቸው አዋጆች ግን ገዢዎችን የሚጠቅም ሕዝብና ሀገርን የሚጎዳ ዜጎችን አንገት የሚያስደፋ መብትና ጥቅምን የሚጋፋ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ሰሞኑን የወጣው አዋጅ 721/2004 ዓ.ም የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅን ብንመለከት የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ የዚሁ አዋጅ ክፍል ሁለት አንፅ 6 ነባር ይዞታዎች ወደ ሊዝ ስሪት ስለሚቀየሩበት ሁኔታ ከተራ ቁጥር 1-7 ተዘርዝሮ ተቀምጧል፡፡ የኢህአዴግ ሹመኞች የነባር ይዞታዎችን አይመለከትም፡፡ ዝርዝር መመሪያ አልወጣም፡፡ ተረጋጉ እያሉ በሕዝብ ላይ ውዥንብር ይፈጥራሉ፡፡ ነባር ይዞታዎችን አይመለከትም ቢሉም ሲሸጥ ሲለወጥ ሊዝ እንደሚገባ በግልፅ ደንግጓል፡፡ አንድ ነባር ይዞታን ሲገዛ ከባለንብረቱ ከሚከፍለው ክፍያ በተጨማሪ ለመንግሥት ያንኑ ቦታ የሊዝ ዋጋ ይከፍልበታል፡፡ ይህ አሰራር ብዙ ምርምር ማይጠይቅ ንብረት በማስተላለፍ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ለማንም ግልፅ ነው፡፡ የነባር ይዞታው ባለቤት ቦታውን ሸጦ ሌላ አነስተኛ ቦታ ገዝቼ በተረፈችኝ ገንዘብ ሕይወቴን ልምራ ቢል የሚገዛው በሊዝ ነው፡፡ ነባር ይዞታዎች ከሊዝ የሚያመልጡት እንዴት ነው ይዞታው ሳይሸጥ ሳይለወጥ የንብረት ዋጋ ሳኖረው እንደ ጉልቻ በመቀመጡ ብቻ ከሊዝ አመለጠ ማለት ነውን?

አዋጁ ሕዝብ የአገሩን ባለቤትነት የሚነካ ነው፡፡ የሊዙ ጥሩነት ነባር ይዞታዎችን ይነካል አይነካም በሚለው አይለካም፡፡ የዜጋን ሁሉ ተስፋ ያጨለመ ነው፡፡ አዋጁ የአገሪቱን ሕዝብ ከይዞታ ባለቤትነት አሽቀንጥሮ ጥሎ መንግሥትን የመሬት ባለቤት የሚያደርግ ነው፡፡ አዋጁ አምባገነኖች በማን አለብኝነት የሚያወጡት አዋጅ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ቢልም ኢህአደግ ግን በራሱ ጠቅልሎ ሕዝብን ጭሰኛ አድርጐታል፡፡ ንብረት የማፍራት ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን ነጠቆታል፡፡ በዚህም ሕዝብ አቋሙን በግልፅ አሳውቋል፡፡ ሕዝብ ከአዋጁ መውጣት በኃላ ለይስሙላ በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ በአዋጁ መውጣት ቁጣውን ገልጿል፡፡ ሕዝብ ትክክለኛ አቋም ወስዷል፡፡ ሕዝብ ሊደመጥ ይገባል፡፡ ሕዝብ መከበር አለበት የሕዝብን እምነትና ፍላጎት በጡንቻ እየጨፈለቁ የሕዝብን ጮኸት እንደ ቁራ ጮኸት እየቆጠሩ መጓዝ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ሕዝብ የማስጠንቀቂያ ደውሉን አሰምቷል፡፡ ሕዝብ የመደመጥ መብት አለው፡፡ በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በተቆጣጠራቸው የሚዲያ ተቋማት የመሰለውን የሚያስፈልገውን በሕዝብ ስም እያስተላለፈ የሚያካሂደው ፕሮፖጋንዳ ለራሱም ለሕዝቡም ለአገርም እንደማይጠቅም አውቆ ሊያስብበት ይገባል፡፡

በአዋጁ ዙሪያ በመንግሥት ባለሥልጣናትና ካድሬዎች የሚሰጠው መግለጫና ከሕዝብ ለሚቀርበው ጥያቄ የሚሰጡት መልሶች የፌዝ መሆናቸው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክን (መድረክ) ያስገረመው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ነባር ይዞታህ እስክትሸጠውና እስክትለውጠው ድረስ ሊዝ አይገባም ማለት “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” አይነት መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ አካላት አንዳብራሩት “ነባር የዞታዎች ወደ ሊዝ ስርዓት የሚቀየሩበት ሁኔታ ዝርዝር ጥናት ተደርጎ በ4 ዓመት ጊዜ ውስጥ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ነው፡፡” (አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2004 ዓ.ም) ከባለሥልጣናነቱ ማብራሪያዎች ለመረዳት እንደተቻለው አዋጁ ከጥናት በፊት ቀድሞ የመጣ እንደመሆኑ የኢህአዴግ ሥርዓት የሕዝብን መብት ቤተ ሙከራ ማድረጉ የአገዛዙን ሥርዓት የዜጎችን ጥቅምና ክብር ማዕከል ያላደረገ መሆኑን ሕዝባችን ይገነዘበዋል፡፡ በመድረክ ዕምነት ደግሞ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ተገቢው ጥናት መካሄድ ነበረበት እንላለን፡፡

ስለሆነም በገጠር ነዋሪው አርሶ አደር የይዞታው ባለቤት መሆን እንዳለበትና የከተማ ነዋሪውም የመኖሪያ ቤት የሰራበት መሬት ባለቤትነት እንዲያረጋግጥ መድረክ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ያሰፈረውን አውን ለማድረግ በተያያዘው ትግሉ እንደሚቀጥል እየገለፅን መላው ሕዝባችንም መብቱን የሚጋፉ አዋጆችንና ድርጊቶችን ለመቃወም በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ከጎናችን እንዲቆም ሀገራዊ ጥሪችንን እናቀርባለን፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)
ጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም
አዲስ አበባ