አቡጊዳ- ከታሰሩ ጋዜጠኖች ጎን ሕዝቡ እንዲቆም በስደት ያሉ ጋዜጠኖች ማህበር ጥሩ አቀረበ!
በአገር ቤት የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኖች ላይ አምባገነኑን የመለስ አገዛዝ እየወሰደ ያለዉን አሳፋሪ ድርጊት አስመልክቶ፣ በዉጭ አገር የሚገኘዉ የነጻዉ ፕሬስ ማህበር፣ ኢትዮጵያዉያን ከታሰሩ ጋዜጠኖች ጎን እንዲቆሙ፣ «በጠመንጃ አስገዳጅነት የእዉነት እጆች ቢታሰሩም. ህዝብ እዉነታዉን ይረዳ፣ ታሪክም ሃቅ ይፈርዳል» በሚል አርእስትብ ሥር ባወጣዉ መግለጫ፣ ጥሪ አቀረበ።
«እነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት አለሙ በሃሰት ክስ “አሸባሪ” ተብለው ለእስር ቤት ቢዳረጉም፤መላው ህዝብ እውነተኛ ማንነታቸውን ስለሚያውቀው፤ ነጻ ጋዜጠኞቻችን ከታሰሩበት የጨለማ ክፍሎች ውጪ፤በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ምን ጊዜም አብረዋቸው ይቆማሉ። ሲል የተነተነዉ ይህ በስደት የሚገኙ የጋዜጠኖች ማህበር መግለጫ፣ ወያኔ/ኢሕአዴግ ብእር ባነሱ ዜጎች ላይ ጠመንጃ ማንሳቱ የሚያሳያው ደካማነቱንና በራሱ አለመተማመኑን መሆኑ ሳይጠቁም አላለፈም።
“እነሆ ኢህአዴግበፍርሃትና በሽብር ውቅያኖስ ላይ ሲቀዝፍ፤ በነጻ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተው ህዝባዊ መነቃቃት ደግሞ፤ የማያቋርጥ የጥሪ ደወሉን ከዳር እስከዳር እያስተጋባ፤ የነጻነት ትግሉን ይቀጥላል። ለዚህም ህዝቡ ከኢትዮጵያ ነጻፕሬስ ጋዜጠኞች ጎን በመቆም፤ የአንድነት ቃል ኪዳኑን እንዲያድስ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ሲል መግለጫዉ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ በያሉበት በአንድነት እንዲሰለፉ፣ ከታሰሩ ጋዜጠኞች ጎንም እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል።
የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግስት የሽብር ተግባር ፈጽማችኋል በሚል ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ፣ጋዜጠኛ ሂሩ ክፍሌ፣ ጋዜጠኛ ዉብሸት ታዬ ላይ በአሥራዎች አመት የሚቆጠር የእሥራ ቅጣት መበየኑ ይታወሳል።