አቡጊዳ – እነ ርዮት አለሙ ከ14 አመት እስከ እድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው !

በሽብር ሥራ ተሰማርታቿል በሚል ክስ በታሰሩት የፍትህ እና የአዉራምባ ታይምስ ጋዜጠኞች ርዮት አለሙ፣ ሂሩት ክፍሌ፣ ዉብሸት ታዬ እንዲሁም የብሄራዊ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሄር ላይ፣ የመለስ አገዛዝ በሚቆጣጠረዉ ፍርድ ቤት በኩል የቅጣት ዉሳኔ እንዳሳለፈ፣ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ያመልክታል።

እንደ ደረሰን ዘገባ መሰረት ሂሩ ክፍሌ ለአሥራ ዘጠኝ አመታት፣ አቶ ዘሪሁን ለአሥራ ሰባት አመታት ፣ ርዮት አለሙና ዉብሸት ታዬ ለአሥራ አራት አመታት እንዲታሰሩ፣ ዳኛ ተብዬዉ ካደሬ እንዳሻዉ አዳነ የወሰነ ሲሆን፣ በጋዜጣ ላይ ጽሁፍ በመጻፋቸው ይሄን ያህል አመት መቀጣታቸውም፣ የገዢዉ ፓርቲ ደጋፊዎችን ሳይቀር እያስገረመ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል።

«ፓርላማዉን 99.6 በመቶ ስንቆጣጠር ለዲሞክራሲ ቆመናል ብለን የመናገር አቅማችን ነዉ የተጎዳዉ። አሁን ደግሞ በጋዜጠኞች ላይ ሴንስ የማይሰጥ የአሥራዎች አመታት የፍርድ እሥራት መወሰን፣ የፍርድ ሂደቱን እንዳንመክት ነው የሚያደርገን» ያሉት አንድ ስማቸዉ እንዲጠቀስ የማይፈልጉ የአገዛዙ ደጋፊ፣ ወደ ልማት እንዳናተኩር ለተቃዋሚዎችም የመታገያ ተጨማሪ ሰበብ የሚሰጥ የማይጠቅም ዉሳኔ መሆኑን ለምንጮቻችን ገልጸዋል።

ጋዜጠኞቹ ለከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚሉ የገለጹ ሲሆን፣ በፍርድ ቤትም ጥፋተኛ እንዳልሆኑ በይፋ መናገራቸዉን የደረሰን ዘገባ አክሎ ያትታል።