እሰከመቼ ነዉ የመጨረሻዉ አድራሻን ዉጭ አገር ወይንም ቃሊቲ የሚሆነዉ ? -ግርማ ካሳ

«ፍርድን ፈልጉ፣ የተገፋውን አድኑ፣ ለድሃ አደጉ ፍረዱለት፣ ስለመበለቲቱ ተሟገቱ» ኢሳያስ 1፡ 17

በአዲስ አበባ ከተማ ነበር የተወለዱት። ገና የሶስት አመት ሕጻን የነበሩ ጊዜ ቤተሰባቸዉ ወደ ድሬዳዋ ይዞራሉ። ፋሺስት ጣሊያን አገራችንን ሲወር፣ የስምንት አመት ልጅ ነበሩ። በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ከተወረወረ በኋላ፣ ጣሊያኖች በፈጸሙት የብዙ መቶ ሺህ ዜጎች ጭፍጨፋ፣ የእኝህ ሰው አባት ተገደሉ። እናታቸው ብዙ ሳይቆዩ አረፉ። ጣልያን ተሸንፎ. እነ በላይ ዘለቀ የኢትዮጵያን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በአዲስ አበባ ከሰቀሉ በኋላ ፣ ከድረደዋ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ።

አዲስ አበባ በሚገኘዉ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቅቃሉ። በእንግሊዝ አገር በኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ሞያ እድነ አዉሮፓዉያን አቆጣጠር በ1956 ዓ.ም ይመረቃሉ። ኑሯቸዉን በዚያዉ በውጭ አገር ከማድረግ፣ ሕዝባቸዉንና አገራቸውን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ። በልእልት ፀሐይ (ጦር ኃይሎች) ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ። ጥቂት አመታት እንደቆዩም፣ አሁንም በእንግሊዝ አገር.፣ በቀዶ ጥገና ስፔሻላይዝ ያደርጋሉ። በ1965 ዓ.ም ወደአገራቸው ተመልሰዉ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር፣ የመጀመሪያውን የሕክምና ኮሌጅ፣ በኢትዮጵያ ያቋቁማሉ።

የቀዶ ጥገና ቢላዎችና መቀሶችን እንጂ እጆቻቸው ጠመንጃና ቦምብ ጨብጠው አያውቁም። ሐኪሞች የሚለብሱት ነጭ ካፖርታ እንጂ፣ በየጫካዉና በየበረሃዉ የሚለበሱ አረንጓዴና ቡና አይነት መለዮዎች አለበሱም። ለሕክምና የሚመጡ ሰዎችን ጠረን እንጂ፣ የባሩድን ሽታ አላሸተቱም። ኪኒኖች እያዘዙ፣ ካንሰሮችንና ጠጠሮችን ከሰዉነት ዉስጥ ቆርጠዉ እያወጡ ኢትዮጵያውያንን አዳኑ እንጂ፣ ማንንም ዜጋ ተኩሰዉ አልገደሉም።

እኝህ ሰዉ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጅ፣ የምንወዳቸው፣ የምናከብራቸዉ እና መቼም የማንረሳቸዉ ታላቁ ፕሮፌሰር አሰራት ወልደየስ ነበሩ።

ፕሮፌሰር አስራት «አመጽን ቀስቅሰሃል» በሚል በ1992 ዓ.ም. ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ይታሰራሉ። በዚያኑ አመት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የ«ሕሊና እሥረኛ» ብሎ ሲሰይማቸው፣ በዋስ የመፈታት እድል ያገኛሉ። ደጋግሞ ማሰራና ማሰቃየት ልማዱ የሆነዉ የመለስ አገዛዝ፣ ከአንድ አመት በኋላ መልሶ ያስራቸዋል።

ከሁለት አመት የፍርድ ሂደት በኋላ በዲሴምበር 1995 ወንጀለኛ እንደሆኑ ዳኛ ተብዬ የአገዛዙ ካድሬዎች ይወስናሉ። በ1998 በእሥር ቤት ሳሉ በደረሰባቸው መከራ ክፉኛ ይታመማሉ። ሊሞቱ ትንሽ ሲቀር፣ ከፍተኛ የአለም አቀፍ ግፊት ስለበዛ፣ በዲሴምበር 1998 ፣ ይፈታሉ።

ወደ አሜሪካን አገር ሲመጡ ሃኪሞቹ «አስቀድሞ ሕክምና ማግኘት ነበረባቸዉ። ጊዜዉ አልፏል» ይላሉ። ብዙም አልቆየም ከዘጠና ቀናት በኋላ፣ በእሥር ቤት እያሉ ሕክምና ካለማግኘታቸዉ የተነሳ፣ ሕይወታቸው ያልፋል። አቶ መለስ ዜናዊ በዚህ መልክ ፣ እኝህን አንጋፋ ኢትዮጵያዊ አሰቃይተዉ ይገድላሉ።
የአቶ መለስ አገዛዝ እንደ አቶ አሰፋ ማሩ፣ ሽብሬ ደሳለኝ፣ ቢያንሳ ዳባ፣ አረጋዊ ገብረ ዮሀንስ የመሳሰሉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ቀጥፏል። በአስር ሺሆች የሚቆጠሩትን በእሥር ቤት እያንገላታ ነዉ።

ለሃያ አመታት ያየነዉ ነገር ቢኖር፣ አቶ መለስና አገዛዛቸዉ የፈለጉትን ሲያሰሩ፣ የፈለጉትን ሲዘርፉ፣ የፈለጉትን ሲገድሉ፣ የፈለጉትን ሲያፈርሱ ነዉ። በአገራችን.ና በምድራችን ባርያ፣ እንግዳ፣ ባይተዋር እየተደረግን ነዉ። ማንም ጉልበተኛ ተነስቶ ቤታችንን ያፈርሳል። በአንዲት ቀጭን ትእዛዝ ከስራችን ያባርረናል። አንገታችንን ደፍተን፣ ሕሊናችንን ሽጠን፣ «እሺ ጌታዬ» እያልን እንደ ባርያ ካልኖርን በስተቀር፣ በኢትዮጵያ ክብራችን ተጠብቆ፣ ስብዕናችን ተከብሮ የምንኖርበት ሁኔታ የለም።

ለዚህም ነዉ «ነጻነታችንን እንፈልጋልን» የሚሉ ወገኖች በእሥር ቤት የሚገኙት። ለዚህም ነዉ ብዙዎች፣ «በአገሬ ታፍኜና ተዋርጄ ከምኖር በባእድ አገር ትንሽ የነጻነት አየር እየተነፍስኩ መኖር ይሻለኛል» ብለው ስደትን የመረጡት።

እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ «እንደ ሕዝብ እሰከመቼ ነዉ የመጨረሻዉ አድራሻን ዉጭ አገር ወይንም ቃሊቲ የሚሆነዉ ?» የሚል ነዉ።

ትላንት እነ ፕሮፈሰር አስራትና አሰፋ ማሩ ተገደሉ። ትላንት ብርቱካን ሚደቅሳ ዘግናኝ፣ በማንም ነፈሰ ገዳይ ላይ እንኳን ያልደረሰ፣ ግፍና ቶርቸር ወያኔዎች ፈጽመዉባት፣ አሰቃይተዋት ከቃሊቲ ወጣች። ዛሬ ደግሞ የነፕሮፌሰር አስራትንና ብርቱካን ሚደቅሳን ቦታ እነ እስክንድር ነጋ፣ ርዮት አለሙ፣ አንዱዋለም አራጌ .. ተክተዉታል።

በነእስክንድር ላይ የቀረቡትን መረጃዎች ሰምተናል። አቃቢ ሕግ እራሱ ባቀረበዉ መረጃ እነ እስክንድር ለሰላም እንደቆሙ በይፋ ሲናገሩ ተደምጠዋል። እንደዚያም ሆኖ ግን ገዢዉ ፓርቲ የሚቆጠጠረዉ ፍርድ ቤት፣ መረጃ በፊቱ በግልጽ ተቀምጦለትም፣ ሰላም ወዳድ ወገኖቻችንን ሊፈታቸዉ ፈቃደኛ አልሆነም።

እነ ርዮት አለሙና ዉብሸት ታዬ ጋዜጠኞች ናቸዉ። ከመጻፍ ዉጭ ያደረጉት አንዳች ወንጀል የለም። በበቤታቸዉ ፈንጂ ወይንም የስለላ ራዲዮዎች አልገኙባቸዉም። ነገር ግን ጥፋተኛ ወንጀለኞች ተብለዉ አሥራ አራት አመት ተፈርዶባቸዋል። ሌላዋ የፍትህ ጋዜጣ ዘጋቢ ሂሩት ክፍ፤እ አሥራ ዘጠኝ አመታት ተብይኖባታል። ምን ያህል በሕግ ስም በፍርድ ቤት አሳፋሪ ድራማ እየተሰራ ፣ ሕግም መቀለጃ እንደሆነ እያየን ነዉ።

ከዚህ በኋላ ምንድን ነዉ የሚደረገዉ ? እነርዮት አለሙን እንደገና ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳእቅን ልከን በልመና ልናስፈታ ነዉን ?

ለፕሮፌሰር ኤፍሬም ትልቅ ከበሬታ አለኝ። ከዚህ በፊት ላደረጉት ጥረቶች ከምስጋና በቀር ምንም የምለዉ ነገር የለም። አገራቸዉን የሚወዱ፣ በኢትዮጵያ ባሉ እሥረ ቤቶች አንድም የፖለቲካ እስረኝ እንዲኖር የማይፈልጉ ቅን ሰው ናቸዉ።

ነገር ግን ፕሮፌሰሩ በቅን ልቦና የሚያደርጉትን ጥረቶች፣ አቶ መለስ ለፖለቲካ ጥቅም ፍጆታ እየተጠቀሙበት ነዉ። ለወራት የፕሮፌሰሩን ተማጽኖ ለመስማት ፍቃደኛ የማይሆኑትና ፕሮፌሰሩን የሚያጉላሉት አቶ መለስ፣ ትንሽ ግፊት ከዉስጥና ከዉጭ ሲበዛባቸው፣ ያኔ ያስጠሯቸዋል።

ይህ አይነቱ ጨዋታ ማብቃት ያለበት ይመስለኛል። ሰርካለም ፋሲል ባሌቤቷ እስክንድር ሲታሰር የተናገረችዉ አንድ ትልቅ አባባል ነበር። «እስክድንር ላመነበት ነገር ነዉ የታሰረዉ። ዛሬ በእስክንድር የደረሰዉ ነገ የእያንዳድንዱን ቤት ያንኳኳል»ነበር ያለቸዉ።

እንግዲህ ትግሉ መልክ መያዝ ያለበት ይመስለኛል። እሥረኞችን ለማስፈታት ከሚደረገዉ ትግል አልፈን በመሄድ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ በነአንዱዋለም ላይ የተፈጸመዉን አይነት ግፍ፣ ከአሁን በኋላ እንዳይፈጸም፣ ፍርድ ቤት፣ ጥቁር ካፓርት ለብሰዉ የሚቀመጡ ካዴሬዎች የሚፈነጥዙበት ሳይሆን ነጻና ገለተኛ በሆነ መንገድ ፍትህን የሚያሰፍን፣ ለዜጎችም የሕግ ዋስተና የሚሰጥ እንዲሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የነአቶ መለስን ቀልደና ጨዋታ ለማቆም መታገል አለብን።

እነእስክንድር አለመታሰር ይችሉ ነበር። ርዮት አለሙ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የምትጽፋቸዉን ብታቆም፣ አቶ አስክድንር እንደ ሌሎች ዜጎች አርፎ ቢቀመጥ፣ አቶ አንዱዋለም የአንድነት ፓርቲም ለቆ ቢወጣ አይታሰሩም ነበር። ነገር ግን ሕሊናቸው አልፈቀደላቸዉም። ባርያ ሆኖ ከመኖር ፣ በስጋ ነጻ ሆኖ በመንፈስ ከመታስር፣ በመንፈስ ነጻ ሆኖ በስጋ መታሰርን መርጠዋል። ለነርሱ መታሰራቸዉ ክብራቸዉ ሆኗል። «እምቢ ለአምባገነንነት፣ እምቢ ለዘረኝነት፣ እምቢ ለጭቆና፧ የሚለዉን መፈክራቸዉም» ከእሥር ቤት እያስተጋባ ነዉ። በአካል አናያቸዉም። ግን በመንፈስ እናያቸዋለን። በአካል ድምጻቸዉን አንሰማም። ግን በመንፈስ ለሕሊናችን ሲናገሩ እንሰማለን።

ጊዜዉ ፈታኝና ወሳኝ ጊዜ ነዉ። ከነእስክንድር ጎን ተሰልፈን እኛም «እምቢ» የምንልበት ጊዜ ነዉ። ሊያስሩን ይችላሉ፤ ግድ የለም ይሰሩን። ሰማኒያ ሚልዮን ህዝብ ሊያስሩ አይችሉም። አንፍራቸዉ። በአይምሯችን እራሳቸዉን እንደ ትልቅ አድርገዉ ስለሳሉ ትልቅ ይመስሉናል፤ እንጂ ምናምንቴዎች ናቸዉ። በራሳቸው የማይተማመኑ፣ ሌለት በሰላም የማይተኙ፣ እርስ በርስ የሚፈራሩ፣. ሕዝቡ እፍ ቢል እንደ አቧራ የሚበተኑ ናቸዉ።

ከንፈር መምጠት፣ በየፓልቶኪ መፎከር፣ በየአሜሪካና አዉሮፓ ከተሞች ስብሰባዎች በማድረግ ጠረቤዛ መደብደብ፣ ፣ በየቡና ቤቱ ዉስጥ ዉስጡን ማንሾካሾክ ይብቃ። በአገር ዉስጥ ያለኸው ኢትዮጵያዊ ተነሳ። ኦባማ ወይንም ኢሳያስ ነጻ ያወጡኛል ብለህ አትጠብቅ። የሌለ የትጥቅ ትግልንም ተማምነህ፣ የትጥቅ ትግል እናደርጋለን የሚሉ ቡድኖች ነጻ እንዲያወጡህ ተስፋ አታድርግ። ነጻነትህ ያለዉ በአንተዉ እጅ ነዉ።

ዛሬ አገዛዙ ጥቅም ሊያስቦጭክህ ይችላል። አትረሳ… ነገ የምትቦጨቀዉ አንተዉ እራስህ ነህ። ልብ ግዛ። ተነሳ። «አትነሳም ወይ ፣ አትነሳም ወይ ፣ የግፍ አገዛዝ አይበቃህም ወይ ?» እያልክ ከወንድምህ ጋር ተነቃቃ።

በዉጭ አገር ያለኸዉ ኢትዮጵያዊ፣ ከወያኔዎች በባሰ ሁኔታ አምባገነን በሆኑ በነሻእቢያ መተማመንህን አቁም። ኤርትራዉያን ወንድሞቻችንን እያረዳ ያለ፣ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተገለ፣ ከራሱና ከእግዚአብሄር ጋር የተጣላ ቡድን ምንም አያደርግልህም።

አገር ቤት የሚታገለዉን ኢትዮጵያዊ በምትችለዉ አቅም ደግፍ። ትግሉ አገር ቤት እንደሆነ አትርሳ። አገር ቤት የሚደረገዉ ትግል እንዲጠናከር አግዝ እንጂ ሰዉን ተስፋ የሚያስቆረጥ ፖለቲካህን ከዉጭ አታሰራጭ።

ብዙዎቻችን ገዢዉ ፓርቲ ሕሊና ገዝቶ ለአገር የሚበጀዉን እንዲያደርግ መምከራችንን እንቀጥላለን። ገዢዉ ፓርቲ ሊለወጥ ይችላል ብለን እናምናለን። የገዚዉ ፓርቲ አካላት የሆኑ ጥሩ ልብ ያላቸው ብዙዎች እንደሚኖሩ እናወቃለን።

ነገር ግን እርቅን ሰላምን፣ መግባባትን ፣ ይቅር መባባልን፣ ፍቅርን መፈለግ ማለት ፍርሃት አይደለም። ግፍን. ኢፍትሃዊነትን፣ ጭቆናን፣ አምባገነንነትን መቀበል ማለት በጭራሽ አይደለም። ድካማችንና ጥረታችን ተሳክቶ እነ አቶ መለስ የሚበጀዉን ካደረጉ እሰየዉ። አለበለዚያ ግን በሕዝብ የተባባረ ክንድ የሚገፉ እንደሆነ አወዳደቃቸዉን እጅግ በጣም ከባድ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም።

ፈረንጆች “ካሮት ኤንድ ስቲክ» (ካሮትና ዱላ) እንደሚሉት፣ በአንድ በኩል ካሮት መጨበጣችንን እየቀጠልን፣ በሌላ በኩል ዱላዉን መያዝ ያለብን የመስለኛል። አለበለዚያ እንደቀለዱብን፣ ሃያ አመታት እንደኖሩ ሌላ ሃያ አማታቶች ይጨምራሉ።