የሁለት አምባዎች ወግ… ወግ አንድ – ናፍቆቴን መልስልኝ

ያሬድ ጥበቡ (የቀድሞ ኢህዴን / ብአዴን ሊቀመንበር ነበሩ)

የዘንድሮ የልደት በአል ከወትሮው ለየት ያለ ነበር። ገፀ በረከትም ነበረው፣ ያውም ሁለት። በረከት ስምኦንና ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ ያቀረቡልን ሰጦታ። ስጦታዎቹንም ከከፈትሁ በሁዋላ እኔም ስለሁለቱ አምባዎች ወግ ላወጋችሁ አሰብኩ። አንዱ አምባ የኢህአዴግ መሆኑ ነው ሌላው ደግሞ የደርግ። አምባ ላይ የሚሸልል ደግሞ አምባገነን ነው። እናንተዬ ይህን ቃል የፈጠረ መንዜ የኖቤል ሽልማት እንደሚገባው አትስማሙም? የመጀመሪያውን ወግ ‹‹ናፍቆቴን መልስልኝ›› አሰኝቸዋለሁ። ያለምክንያት አይደለም። ከአንድ ሁለት አመት በፊት “አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ላቀረበልኝ ቃለምልልስ ‹‹የአዲሱና በረከት ሳቃቸው ይናፍቀኛል›› ብዬ ናፍቆቴን በአደባባይ ገልጬ እንደነበር የጋዜጣዋ ታዳሚዎች ያስታውሱ ይመስለኛል።