የሁለት አምባዎች ወግ ወግ አንድ – ናፍቆቴን መልስልኝ በአቶ ያሬድ ጥበቡ (የቀድሞ ኢህዴን / ብአዴን ሊቀመንበር የነበሩ)

የዘንድሮ የልደት በአል ከወትሮው ለየት ያለ ነበር ፡፡ ገፀ በረከትም ነበረው፣ ያውም ሁለት ፡፡ በረከት ስምኦንና ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ ያቀረቡልን ሰጦታ ፡፡ ስጦታዎቹንም ከከፈትሁ በሁዋላ እኔም ስለሁለቱ አምባዎች ወግ ላወጋችሁ አሰብኩ ፡፡ አንዱ አምባ የኢህአዴግ መሆኑ ነው ሌላው ደግሞ የደርግ ፡፡ አምባ ላይ የሚሸልል ደግሞ አምባገነን ነው ፡፡ እናንተዬ ይህን ቃል የፈጠረ መንዜ የኖቤል ሽልማት እንደሚገባው አትስማሙም? የመጀመሪያውን ወግ ‹‹ናፍቆቴን መልስልኝ›› አሰኝቸዋለሁ ፡፡ ያለምክንያት አይደለም ፡፡ ከአንድ ሁለት አመት በፊት “አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ላቀረበልኝ ቃለምልልስ ‹‹የአዲሱና በረከት ሳቃቸው ይናፍቀኛል›› ብዬ ናፍቆቴን በአደባባይ ገልጬ እንደነበር የጋዜጣዋ ታዳሚዎች ያስታውሱ ይመስለኛል ፡፡ ታዲያ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ባለፉት ወራት ‹‹በረከት መፅሀፍ እየፃፈ ነው›› የሚል ወሬ ስሰማ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን በጡረታ መወገድ አይቀሬ መሆኑን የተቀበልኩት ጉዳይ ስለነበር፣ የሚተካቸውም ለዐይን የሚሞላ ሰው በአካባቢያቸው ስላልተረፈ፣ ምናልባት በረከት በዕድሜውም ወጣት ስለሆነ፣ ተኪያቸው እርሱ ሊሆን ስለሚችል “ለዚህ ሽግግር የሚያመቻች የበረከትን ሰብዕና የሚገነባ መፅሀፍ ሊያወጡ እንደ ቡድን ወስነው መሆን አለበት” በሚል በናፍቆት የተጠባበቅኩት መፅሀፍ ነበር ፡፡ ፖለቲካዊ ብልጠቱን የሚያንፀባርቅ መዘርዝር ሳይሆን፣ በመሟሸት ላይ ያለ ሃገር መሪ አርቆ አስተዋይነቱን ከህሊናው ማዕድ የሚያካፍልበት ልዩ አጋጣሚ ነበር ስጠብቅ የከረምኩት ፡፡ ሆኖም ያ በወጣትነቱ የማውቀውን ደጉን በረከት አድጎ ተመንድጎ፣ ልምድ አካብቶ፣ በዕድሜ ጨምቶ፣ በዘመን ርቀት ለስልሶ ላገኘው አልቻልኩም ፡፡ ናፍቆቴን የሚመጥን በረከት በ‹‹ሁለት ምርጫዎች ወግ›› ገጾች መሃል አፈላልጌ ላገኝ ባለመቻሌ ነው ንዑስ ርዕሱን ‹‹ናፍቆቴን መልስልኝ›› ማሰኘቴ ፡፡

የመፅሀፉ ምረቃ፣ የሪፖርተር ዘገባና መቅድም

ሪፖርተር ጋዜጣ ስለ መጽሀፉ ምረቃ ሲዘግብ፣ በረከት ሼክ አላሙዲንን ‹‹መሃመድ ወሬኛ ነው›› አላቸው የሚለውን ሳነብ፣ “በረከት ይህን ያህል አማርኛ ሊጠፋው አይችልም ፣ ያው ሪፖርተር ከተጠናወተው ጠባብ ብሄርተኝነቱ በመነሳት ዕድሉን ባገኘበት ቅፅበት ሁሉ የኢህዴንን ልጆች ከማጥቃት ስለማይመለስ እንጂ ነው” አልኩ ለራሴ ፡፡ ሁሌም መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ግን ማ ከሁዋላ አይዞህ ቢለው ነው አማረ አረጋዊ ብአዴኖችን እንዲህ ሊያጠቃቸው ቀንዱን እንዳቆመ የሚኖረው የሚለው ነበር ፡፡ ስለመፅሃፉ የምረቃ ስነስርአት ግራ የተጋባውን የሪፖርተር መጣጥፍ ካነበበኩ በሁዋላ መፅሃፉን ሳፈላልግ፣ ሰሞኑን በረከት ስምኦን ለስደት የዳረገው የ‹‹አውራምባ ታይምስ›› ዋና ኤዲተርና ባለቤት የሆነው ዳዊት ከበደ መፅሀፉን በዲ.ኤች.ኤል ፖስታ ማስመጣቱን ነገረኝና፣ እንደ ቀድሞ አጫሽ ጓደኞቼ ‹‹ወጋሁ›› ብዬ እስኪጨርስ በእግር ጣቶቼ ቆሜ ተጠባበቅሁ ፡፡ ምስጋና ይድረሰውና ዳዊት በሁለት ቀን ፉት ብሎ ሰጠኝ ፡፡

ተስፋዬን ሰንቄ ወደቤቴ አመራሁ፣ እያነበበኩ አድሬ ከስራ ለመቅረት ውሳኔ አድርጌ ፡ ፡ ‹‹መታሰቢያነቱ ለወንድሜ ካሳሁን ገብረ ህይወት – እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጉዋዛለሁ›› ይላል ከማውጫው በፊት ያለው ገፅ ፡፡ ‹‹ጉድ ሊፈላ ነው›› አልኩ ለራሴ ፡፡ ያለምክንያት አልነበረም ፡፡ ካሳሁንን በኢህአፓ ሰራዊት ውስጥ አውቀው ነበር ፡፡ እጅግ ተወዳጅ ሰው እንደነበር ትዝ ይለኛል ፡፡ ታዲያ ተሓህት ‹‹ትግሬ ለትግሬዎች ፣ የትልቋ ኢትዮጵያ (በትግርኛ ዓባይ ኢትዮጵያ ይሉታል) ህልመኞች ከሃገራችን ውጡ›› ብሎ ድንገት በከፈተብን ጥቃት ካሳሁን ውጊያ ላይ ተማረከ ፡፡ ከጠባቂዎቹ አምልጦ በአካባቢው ወደነበረችው የጀብሓ አሃዱ አስጥሉኝ ብሎ ሲሮጥ የወያኔ ዘቦች በጀርባው ባወረዱበት የመትረየስ ጥይት ተመትቶ እንደተሰዋ አሳዛኙ ዜና ደረሰን ፡፡ አዎን ካሳሁን ‹‹ትግራይ የኢትዮጵያ አይደለችም፣ የአማራና የትግሬ ለማኞች አብረው መለመን እንኳ አይችሉም›› ብለው የትግራይን ህዝብ ይቀሰቅሱ በነበሩ ጠባብ ብሄርተኞች እጅ ነበር የወደቀው ፡፡
ታዲያ በ1992 ህወሃት አመራር ውስጥ ክፍፍል ሲፈጠር፣ በረከት የመለስ አዳኝ ሆኖ የቆመ በመምሰል የወንድሙን ገዳዮች በከፊል የተበቀላቸው ነበር የመሰለኝ ፡፡ ሆኖም እዚህ የመጀመሪያ ገፅ ላይ ወንድሙን ካሳሁንን ‹‹እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጉዋዛለሁ›› ሲል፣ በረከት ከጠባብ ብሄርተኞች ጋር የሚያደርገው ትግል አሁንም የቀጠለ መሆኑን ነው ሹክ የሚለን ፡፡

ከ1992 ክፍፍልና የነስዬ ቡድን መወገድ በሁዋላ በአቦይ ስብሃትና በቀዳማይት እመቤቲቱ መሃል የቀጠለው ትግል ለሽማግሌው መረታትና ከጨዋታው መገለል፣ በቅርቡ ደግሞ የርሳቸው አጋሮች ናቸው የሚባሉት ሁሉ እየተነቀሱ ገሚሶቹ በአምባሳደርነት፣ ገሚሶቹ በጡረታ እየተገለሉ፣ ዛሬ ኤፈርት የተሰኘውን ‹ግብረ-ሰናይ› ድርጅት ቀዳማይት እመቤቲቱ ብቻ እንደሚቆጣጠሩት ነው ንግስተ ሳባ ቤት መብልኢ ስሄድ የትግራይ ልጆች ሲያወሩ የምሰማው ፡፡ ታዲያ በረከት ‹‹እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጉዋዛለሁ›› ሲልና፣ ሪፖርተር ደግሞ ተሩዋሩጦ በመፅሃፉ ምረቃ ስም ባቀረበው ሪፖርት ሼኩንና በረከትን አዳብሎ ለማቅረብ ያደረገውን መታከት ሳይ፣ አማረ ‹‹የማንን ተልእኮ አስፈፃሚ ነው›› እንድል አስገድዶኛል ፡፡ ምናልባት ቀጣዩ መድረክ ደግሞ በበረከትና በቀዳማይት እመቤቲቱ መሀል የሚደረግ ሊሆን ይችል ይሆን? በረከትን ቀረብ ብለው ያዩት ሁሉ የሚመሰክሩለት አንድ ነገር ቢኖር ‹‹ከምቀበርባት ስድስት ክንድ መሬት በቀር ሌላ ሃብት አልፈልግም›› ማለቱን ነው ፡፡ የነዚህን ሁሉ አንድምታ ወደፊት የምናየው ይሆናል ፡፡

አብረው የፈሱት…

ከላይ ባነሳሁዋቸው ሃሳቦች ከራሴ ጋር እየተሙዋገትኩ ወደመጀመሪያው ምእራፍ ዘው ስል የበረከት ‹‹ማሙዋሻ ወግ›› ጥሜን ሊያረካው አልቻለም ፡፡ ሙሉ ሌሊት ሳነብ አድሬ ከስራ እቀራለሁ ብዬ ያቀድኩ ሰው፣ የግዴን ወደመኝታዬ አመራሁ ፡፡ የመጀመሪያው ምእራፍ በአሰልቺና ትርጉም የለሽ ‹ፅንሰ ሃሳቦች› የተሞላ ሆነብኝ ፡ ፡ አቶ መለስ በጦርነቱ አመራራቸውና በኤርትራ ፖሊሲያቸው ሲወጠሩ፣ መውጫ ቀዳዳ ሲፈልጉ ያገኙትን ‹‹ቦናፓርቲዝም››፣ የዱሮ ጉዋደኛዬ እንደ ዕውቀት ወስዶ ሲያነበንብ ሳየው አሳፈረኝ ፡፡ የአቶ መለስን ቦናፓርቲዝም በወቅቱ አዲስ አበባ በሚወጡ መፅሄቶች እንደ አቅሜ ያፌዝኩበት ስለነበር በረከት ሳያነበው እንዳልቀረ እገምታለሁ ፡፡ በረከት፣ ይህንኑ ፌዝ የኢህአዴግ ተሃድሶ መሰረት አድርጎ እንዴት ከክፍፍሉ ወዲህ ለተገኘው ኢኮኖሚያዊ ‹‹ግስጋሴ›› መሠረት እንደሆነ ሊያቀርብ ሲሞክር ግን ‹‹ምነው ጓዴ›› ከማለት በቀር የምለው አልነበረኝም ፡፡

በመጀመሪያው ምእራፍ ከቦናፓርቲዝም በተጨማሪም አርማጌዶን፣ ጥገኛ ዝቅጠት፣ ናዳን የገታ ሩጫ፣ አቦ ሸማኔ ወዘተ የመሰሉ አሰልቺ ቃላት እንደ መርግ እየወረዱ ስለሚከመሩ፣ የመፅሃፉን ተነባቢነት በእጅጉ ጎድቶታል ፡፡ እነዚሁ አድካሚ ቃላት ግን ስለ ደራሲውና ‹‹እድገትና ዘመናዊነት ስላመጡት የአመራር ጓዶቹ›› የሚያሳብቁት ቁምነገር አለ ፡፡ ፈረንጆች ‹‹ማይንድ ሴት›› ስለሚሉት ፋይዳ ፡ ፡ መረጋጋት የሌለበት ህይወት ውስጥ እንደሚኖሩና፣ በነርሱ እድሜ አንድ ተአምር ፈጥረው ለራሳቸው ተኪ ትውልድ አውርሰው ለመሞት ትግል ውስጥ እንዳሉ ይጠቁማል ፡፡ የልብ ህመሙ እየጠና በሄደ ቁጥር፣ ራሳቸውን ላልቻሉ 10 ጨቅላ ልጆቹ ማሳደጊያ የሚሆን ንብረት ለመተው ከላይ ታች ብቻውን ይባክን የነበረው አባቴ ታወሰኝና በረከት አሳዘነኝ ፡፡ አባቴ እንደዚያ የደከመበትን ንብረት ግን፣ አብዛኛውን ደርግ የተረፈውን ደግሞ በረከት ሰሞኑን ባወጣው የሊዝ አዋጅና በዘመናዊነት ስም በሚደረመሱት ታሪካዊ ሰፈሮች ተዘመተበት ፡፡ የዛሬ 20 አመት የነበረከት የአቦ ሸማኔ ሩጫም ከፈሩት ናዳ እንዳያድናቸው መተንበይ ይቻል ይመስለኛል ፡፡ የነበረከት የአቦ ሸማኔ ሩጫ ሁሉን አግልሎ፣ ሁሉን አዋርዶ፣ ሁሉን አሳዶ በተመረጡ ጥቂት ጀግኖች ብቻ ሊደረግ የታሰበ ለመሆኑ የመፅሃፉ ቀጣይ ምዕራፎች ይፋ ያደርጉታል ፡፡ የዋህነት ነው ፡፡ ምክንያቱም አበው ‹‹አብረው የፈሱት ፈስ አይገማም›› ብለዋልና ነው ፡፡

የመፅሀፉ ንኡስ ርእስ ‹‹ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ›› ይላል ፡፡ ገባ ብለው ሲመረምሩት በናዳ የተመሰሉት ረሃብ፣ በሽታ፣ ጠኔ፣ ኋላ ቀርነት፣ ድህነት እና ከነዚህ ችግሮች ለመላቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢህአዴግ የተለየ አማራጭ የመፈለጋቸው ፋይዳ ናቸው ፡፡ ግራ የሚያጋባው ጉዳይ ግን እነዚህ የጋራ ብሄራዊ ችግሮች በኢህአዴግ ላይ የሚወርዱ መርጎች ተደርገው መታየታቸውና፣ በአቦ ሸማኔ ፍጠነት ካልሮጠ በናዳው የሚደባየውም ኢህአዴግ ሆኖ መታየቱ ነው ፡፡ አንድም ቦታ በስህተት ናዳው እንዳይነሳ ምን ማድረግ ይቻለናል ብሎ ደራሲውም ሆነ የሚመራው ፓርቲ ሲጨነቁ አይታይም ፡፡ ናዳው እንዳይንከባለል በብሄራዊ ምክክር ሊፈጠር ስለሚችለው መላም ለማሰብ ፍልጎቱም ጊዜውም የላቸውም ፡፡ ከአይቀሬው ናዳ እንዴት ብቻቸውን ፈጥነው እንደሚያልፉ ብቻ ነው የሚያውጠነጥኑት ፡፡ ወደሃገራዊ መንግስትነት ላለማደግ የቆረጡ መሆናቸው ነው ፍንትው ብሎ የሚታየው ፡ ፡ በ2002 ምርጫ ማግስት መስቀል አደባባይ ላይ መለስ ባደረገው ንግግር ውስጥ ‹‹የመረጠንን ህዝብ ድምፅና ውሳኔ እንደምናከብር ሁሉ ያልመረጠንን ህዝብ ድምፅም እንደምናከብር ያለአንዳች ማወላወል ለመግለፅ እወዳለሁ›› ብሎ የተናገረ ቢሆንም፣ ንግግሩ የተፃፈበት ቀለም ሳይደርቅ በከተማ ሊዝ አዋጅ አልመረጠንም ብለው የሚገምቱትን የህብረተሰብ ክፍል ለማራቆትና በረሃብ አለንጋ ለመግረፍ ጨካኝ አዋጅ ወደማወጅ ተሸጋገሩ ፡፡ አዋጁ የዘርና ፖለቲካዊ ስሌት እንደሌለበት መናገር ያስቸግራል ፡፡ ለኢህአዴግ ትልቁ ጥያቄ ግን መቼ ነው ብሄራዊ መንግስት ለመሆንና ያለአድልኦ ሁሉንም ዜጋ በእኩል ዐይን ለማየት የሚነሳው? የሚለው ነው ፡፡ ምዕራፍ አንድ ከቻርለስ ዲክንስ ‹‹የሁለት ከተሞች ወግ›› ገፅ አንድ ላይ በተወሰደ ሰፊ ጥቅስ ይቋጫል ፡፡ በረከት በራሱ አነጋገር ‹‹እረፍት በሚነሳ ህይወት ውስጥ የሚጉዋዝ›› በመሆኑ ዲክንስን ከገፅ አንድ ባሻገር ማንበቡን ተጠራጥሬአለሁ ፡ ፡ ቢሆንማ፣ በሚቀጥሉት ምእራፎች የምናየውን ብልጠት፣ ጭካኔና፣ እልህ ባላየን ነበር ፡፡ ላደለውማ ፣ እደግ ተመንደግ ተብሎ ለተመረቀማ የዲክንስ አይነት ፀሀፊዎችን ማንበብ አንዱ ጥቅም፣ የህይወት ቀለሟጥቁርና ነጭ ብቻ እንዳልሆነና፣ ዕውነትም ብቸኛ ባለቤት እንደሌላት መማር በመሆኑ፣ የበረከት ወግ ደግሞ ከነዚህ ሃብታት በእጅጉ የራቀ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ንባቡ ከገፅ አንድ አልዘለለ ይሆን ብዬ መጠርጠሬ ፡፡
ምርጫ 97ና የበረከት ወግ ሁለተኛው ምዕራፍ እንደ ቁምነገር ሳይሆን እንደ ወግ የተዋጣለት ሆኖ አግኝቼዋለሁ ፡፡ የሚያስቁም የሚያሸማቅቁም ወሬዎችን ያካተተ ነው ፡፡ በመጠኑም ቢሆን ለምእራባውያን አለመንበርከክም የታየበት፣ ለበረከትም ሃገራዊ አርበኝነት ስሜት አድናቆት እንድንቸር የሚያስገድድ አቀራረብ ነው ያለው፡፡ ከተለመደው የኢህአዴግ ‹‹ሃገሪቱ›› ከሚል የባዕድ የሚመስል አቀራረብ ራሱን አርቆ፣ በረከት የአባቶቻችንን አርበኝነት ለማወደስም ሆነ ኢትዮጵያን በስሟ ለመጥራት የደፈረ በመሆኑ፣ ደስ መሰኘቴን መደበቅ አልሻም ፡፡ ምናልባትም ኢህአዴግ ወደ ጉልምስና መሸጋገሩን የሚያበስርም ከሆነ መልካም ዜናም ነው ፡፡ ከአዲሱ ለገሰ በቀር ሁሉም ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ረቂቁን ያነበቡት መሆኑን ራሱ ደራሲው ስለነገረን፣ ‹‹አርበኝነት አብዝተሃልና ቀንስ፣ ቁረጥ›› አለመባሉም ለተስፋችን ምክንያት ሊሆን ይችላል ፡፡

በበረከት የምርጫ 97 ትረካ ከቅንጅት ብርሀኑ ነጋ፣ ከህብረት ደግሞ ነገደ ጎበዜ ዋነኛዎቹ ተዋናይዎች ሆነው ቀርበዋል ፡፡ ከብርሀኑ ጋር ከመድረክ ውጪ ስላወጉት፣ ሁለቱ ብቻ ስለሚያውቋቸው ነገሮች በብዛት ያትታል ፡፡ በዚያ ላይ ብዙም ማለት ባልችልም አንድ የማውቀው ነገር ግን፣ የካቲት መጀመሪያ ላይ ፊንፊኔ በገባሁ ማግስት፣ ብርሃኑ ፣ ‹‹ከፓርቲዎች ድርድር ስብሰባ ስንወጣ እዚያው ሼራተን እንገናኝ›› ብሎኝ ከምሽቱ ሁለት ሰአት አካባቢ ሶስታችንም ተገናኝተን ካወራናቸው ነገሮች ዋነኛው በግል ደረጃ የሚደረጉ ግንኙነቶች ያላቸውን ጠቀሜታና፣ ከድርጅቶች መግለጫዎች ባሻገር ውጥረትን ማርገብ ላይ ስላላቸው አስተዋፅኦ ሃሳብ መለዋወጣችንን አስታውሳለሁ ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢህዴን ውስጥ እያለን እኛ እየተጎዳንም ቢሆን፣ ለህወሓቶች የውስጥ ምስጢራችንን እንዴት እናካፍላቸው እንደነበር በረከት ያውቃል ፡፡ ዱሮ በጦር ሜዳ የተሞሻለቅናቸው ሰዎች ስለነበሩ፣ የጠላትነት ስሜታቸውን ለማብረድና ረጅም ርቀት አብረን ለመሄድ እንድንችል ብዙ የሚያረጓጓቸው የሚመስሉንን መረጃዎች እንሰጣቸው ነበር ፡፡ ሱዳን በነበርኩባቸውም አመታት ከኦነግ መሪዎች ጋር ፅህፈት ቤታቸው ከማደር ጀምሮ እስከ መረጃ ልውውጥ ድረስ እነርሱ የሚሰማቸው የጠላትነት ሰሜት የሌለን መሆኑን ለማሳየትና የወዳጅነት ስሜት ለማዳበር የምናደርገው እንደነበር በረከት ያውቃል ፡፡ ለብርሀኑም ካካፈልኩት ልምዶቼ መሃል ነበሩ ፡፡

ሁሌም ከብርሀኑ ጋር ከምንጋራቸው ሃሳቦችም አንዱ፣ ኢህአዴግ በወታደራዊ ሃይል አሸንፎ የገባ ሀይል ቢሆንም ህዝቡ ለምን አልተቀበለኝም ለሚለው ጥያቄ ድርጅቱ የሚሰጠው መልስ አደገኛ በመሆኑ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ድርጅት መሆኑን ነው ፡፡ በተለይ ደግሞ በህዝብ ድምፅ ለመዳኘት ፈቃደኛ ነኝ ብሎ ዘው ባለበት ምርጫ 97 ወዳልተጠበቀ ጭካኔ እንዳይረማመድ ፍርሀቱ ነበረን ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ብርሀኑ በረከትን ‹‹አንድ ነገር ቢሆን ዘልዬ አንተ ቤት ነው የምደበቀው›› ሊለው የሚችለው ፡፡ በረከት ሊያስጥለው እንደማይችል ጠፍቶት ሳይሆን፣ በተቃዋሚው በኩል የጠላትነት ስሜት እንደሌለና፣ ስልጣንን ጠብቆ ለማቆየት ኢህአዴግ በሚያደርገው ጥረት ተገቢ ያልሆነ አመፅ ውስጥ ቢገባ እንኳን፣ ‹‹ተደናብራችሁ የምታደርጉት ሊሆን ስለሚችል ዶፉ እስኪያልፍና ነገሮች እስኪጣሩ እቤትህ ብደበቅ እንኳ ትተባበረኛለህ›› በሚል የጓደኝነት ስሜት የተናገረው ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው ፡፡ ሁኔታዎች ተለዋውጠው ዛሬ በጠላትነት ተሰልፈው በሚገኙበት ሁኔታ በረከት ይህን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋሉ ሊያስገምተው ካልሆነ በቀር፣ እንደገመተው ብርሀኑን የሚያንኳስሰው አይመስለኝም ፡፡
ሌላው የበረከት የምርጫ 97 ወግ ትኩረት ነገደ ጎበዜ በህገ መንግስቱ ላይ ስለፃፈው ትችትና፣ ቅንጅት እንዴት አድርጎ ዋናው አስፈፃሚ ሊሆን እንደቻለ የሚተነትን ነው ፡፡ በዚህ ወግ ብዙ ከመራቀቁ በፊት ግን፣ የቅንጅት አመራር አባላት በወቅቱ እንዴት የነገደን ‹‹ህገ መንግስቱን በህዝባዊ አመፅ መናድ›› ጥሪ እንደማይቀበሉ ከሰጡዋቸው ህዝባዊ መግለጫዎችና ንግግሮች እንዲሁም የመድረክ ላይ ክርክሮች መመርመር ነበረበት ፡፡ ሆኖም የመፅሃፉ አንዱ ዋነኛ አላማ በ1997/98 ለደረሰው የህዝብ ዕልቂት ተጠያቂው ቅንጅት እንደነበር ዋቢ መሆን ስለሆነ፣ ደራሲው የቅንጅቱን መግለጫዎች የሚገባቸውን ክብደት ሊሰጣቸው አልፈለገም ፡፡ ለታሪክ ተመራማሪዎች ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችል ሰነድ ለማሰናዳት ለፈለገ ሰው ግን እንዲህ አይነት ሸፍጠኝነት አይፈቀድም ፡፡ ቢበዛ በረከት ማድረግ የሚችለው፣ ‹‹ቅንጅቶች በአፋቸው ተቃዋሚ መስለው ቢቀርቡም፣ በተግባር ግን የነገደን ተልዕኮ ለማሰፈፀም ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መን አድርገዋል›› ብሎ መከራከር ነበር ፡፡ ሆኖም በረከት በእጁ ያሉትን የቅንጅት ዶሴዎች ከፍቶ ሊያያቸውና ሊያካፍለንም ፈቃደኛ አልሆንም ፡፡ የካቲትና መጋቢት 1997 አዲሰ አበባ በነበርኩበት ወቅት፣ ብርሀኑ በምርጫ አዝማችነቱ እጅግ በስራ ተወጥሮ ስለነበር ፣ ወደ ዲሲ ከማምራቱ በፊት ንግግር እንዳዘጋጅለት ጠይቆኝ፣ እኔ ካዘጋጀሁትና መጋቢት 4 ቀን 1997 አም ብርሀኑ በዋሽንግተን ዲሲ ለ2000 ያህል ዕድምተኞች ያቀረበው ንግግር የቅንጅቱን የወቅቱን አመለካከት የሚያንፀባርቅና፣ የበረከትን ክስ ፉርሽ የሚያደርግ በመሆኑ በረጅሙ ለመጥቀስ ተገድጃለሁ ፡፡ እንዲህ ይላል፣
‹‹ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በከፍተኛ ትኩረት የሚንቀሳቀስበትን ‹‹ሕገ መንግስታዊውን ስርአት የማፍረስ ስትራተጂ አላቸው›› ለሚለው ክስ ያለንም መልስ ግልፅ ነው ፡፡ ቅንጅት አብዮታዊ ድርጅት አይደለም ፡፡ ለስርነቀል ለውጥ የቆምን፣ በማፍረስና በመናድ የምናምን ፖለቲከኞች አይደለንም ፡፡ ስማችን እንደሚጠቁመው የአንድነትና የዲሞክራሲ ሀይል ነን ፡፡ ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን ማፍረስ ሳይሆን ማሻሻል ነው አላማችን ፡፡ ለማሻሻል እንኳን ህግን መሰረት አድርገን፣ ለማሻሻል የሚያስፈልገውን ድምፅ በማሰባሰብ እንጂ በአዋጅና በኣሻጥር የመለወጥ ፍላጎት የለንም ፡፡ ኢህአዴግ የህዝብን ይሁንታ እስከተቀበለ ድረስ የግንቦት ምርጫ አሸናፊዎች የቅንጅቱ ዕጩዎች ብንሆንም የምንመሠርተው መንግስት የኢህአዴግን ህጋዊ መብት የሚያከብር፣ ተወዳድረው ባሸነፉበትም ወረዳዎች የተሰጣቸውን የህዝብ አደራ በተገቢው የሚወጡበትን የምክር ቤት ወኪሎቻቸውን የሚያከብር መንግስት ይሆናል ፡፡ ኢትዮጵያዊዉ ዜጋ በፖለቲካ አስተያየቱም ሆነ በሚያምንበት ርዕዮቱ የማይታደንበት፣ በነፃነትና ያለፍርሃት የሚኖርበት ሃገር መገንባት ነው የቅንጅቱ ዕይታ ፡፡ ይህ ደግሞ የኢህአዴግ አባላትንም መብት ያካተተ ነው›› ይላል ፡ ፡ በስፋት በጠቀስኩት ደስ ባለኝ ነበር፣ ሆኖም በረከት የእጅ ፅሁፌን አጣጣል ስለሚያውቀውና ኦሪጅናሉም የቅንጅት ቢሮ በተወረረ ወቅት ተወስዶ በበረከት እጅ ስለሚገኝ፣ ፈልጎ እንዲያነበው አሳስቤ በዚሁ ይህን ክርክር እልባት ልስጠው ፡፡ ኦሪጂናል ቪዲዮው አርቲስት ታማኝ በየነ ጋ ስለሚገኝ ‹‹ዩ ቱብ›› ላይ ቢያስቀምጠው አንባቢው ሁሉ ሊያደምጠው ይችላል ፡፡

በምርጫ 97 ወጉ በረከት፣ ቅንጅት የነገደን የአመፅ ጥሪ ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን፣ ከምዕራባውያን የቀለም አብየተኞች ጋር ተመሳጥሮ እንዴት አመፅ ለማካሄድ እየተሰናዳ እንደነበር በስፋት ያትታል ፡ ፡ ለዚሁም ዋነኛ መረጃ አድርጎ የሚያቀርበው የጂን ሻርፕ ‹‹ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ›› የተሰኘ መፅሀፍ በምዕራባውያንና በቅንጅት እንዴት ተተርጉሞ እንደተሰራጨ በማተት ነው ፡፡ የጂን ሻርፕ መፅሀፍ ለበረከት የቀለም አብዮት ክስ ማእከላዊ ዋቢ ጉዳይ ሆኖ ስለቀረበ፣ በዐይን ምስክርነት የማውቀውን ማቅረብ ተገድጃለሁ ፡፡ ከምርጫ 97 በፊት ስለዚህ መፅሀፍ ዕውቀት የነበረው ብዙም ኢትዮጵያዊ የነበረ አይመስለኝም፡፡ ከምርጫው ሁለት ሳምንታት በሁዋላ የሰኔ አንድ ግድያ በተፈፀመ ማግስት እዚህ በዋሽንግተን አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ሀዘንና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር ፡፡ ታዲያ ለትግሉ አዲስ የሆኑ ወጣቶችና ፕሮፌሽናሎች ሁሉ ከስራ መልስ እየተሰበሰቡ ‹‹የህዝቡ ድምፅ እንዳይሰረቅ ትግሉ እንዴት ይቀጥል›› የሚል ውይይት ይጧጧፋል ፡ ፡ በዚህ መሃል ነው የቅንጅትም የህብረትም አባል ያልነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ከጂን ሻርፕ መፅሀፍ ጋር ያስተዋወቀን ፡፡ ቅንጅትና ህብረት አመራር አካባቢ ስለ ሰላማዊ የትግል መንገዶች በቂ ግንዛቤ የለም የሚል እምነት ላይ ስለደረስን፣ በመፅሀፏ ወደ አማርኛ መተረጎም%E