ወያኔ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የፓርቲ መዋቅሩን እያስፋፋ ነው ተባለ
ዘረኛው ገዢ ቡድን፣ መምህራን እና ተማሪዎችን የፓርቲ አባል እንዲሆኑ ማስገደዱ ሳያንስ፣ በተለይ የትምህርት ጥራትን እንደ ሽፋን በመጠቀም በትምህርት ቤቶች ውስጥ መዋቅሩን እያስፋፋ ነው ተባለ።
ለግንቦት 7 ድምጽ እና ለሌሎች መገናኛ ብዙሃን የተላከ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በየትምህርት ቤቶች ውስጥ ከተዘረጋው ዋና መዋቅር በተጨማሪ፣ መምህራን በህዋስ እንዲደራጁ እየተገደዱ ነው። በደቡብ ክልሉ የወያኔ ተለጣፊ ፓርቲ – ደኢህዴን – የተዘጋጀ እና “የአባል መምህራን ሞዴል ቅጽ” በሚል ርእስ የተዘጋጀ መመሪያ እንደሚለው፤ ድርጅቱ “በትምህርት ሴክተር የተደራጀ ሰራዊት ለመገንባት የሚያስችል መርሐ ግብር ዘርግቶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው”። ይሁን እንጂ የተቀረው የመመሪያው አካል መምህራን እንዴት አድርገው የትምህርት ጥራት ለማሻሻል መስራት እንደሚገባቸው ከማተት አልፎ፤ አባል መምህራን እና ተማሪዎች ሊፈርሙት የሚገባውን የስምምነት ቅጽ ያካትታል።
ለዝግጅት ክፍላችን መረጃውን ያቀበሉት ምንጭ፥ ይህ አገዛዝ መዋቅሩን ለማስፋፋት የሚጠቀመው ሽፋን ነው ብለዋል። ይህ ጉዳይ የወያኔ የፓርቲ ፖለቲካ ምን ያህል ትምህርት ቤቶቻችንን እና ማህበረሰባችንን እንደወረረ ያሳያል ያሉት ምንጭ፤ እነዚህ መዋቅሮች የተፈጠሩት የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ ለመከፋፈል፣ ለስለላ ስራ እና ወደፊት ሊነሳ የሚችልን ተቃውሞ ለማፈን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል። “ሂውማን ራይትስ ዋች” በኢትዮጵያ ላይ በቅርቡ ባወጣው ሰፊ ሪፖርት፣ በትምህርት ቤቶች ውስት ስለሚካሄደው የአፈና ስራ መዘርዘሩ ይታወሳል።