የሁለት አምባዎች ወግ ወግ አንድ – ናፍቆቴን መልስልኝ

በያሬድ ጥበቡ

የዘንድሮ የልደት በአል ከወትሮው ለየት ያለ ነበር። ገፀ በረከትም ነበረው፣ ያውም ሁለት። በረከት ስምኦንና ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ ያቀረቡልን ሰጦታ። ስጦታዎቹንም ከከፈትሁ በሁዋላ እኔም ስለሁለቱ አምባዎች ወግ ላወጋችሁ አሰብኩ። አንዱ አምባ የኢህአዴግ መሆኑ ነው ሌላው ደግሞ የደርግ። አምባ ላይ የሚሸልል ደግሞ አምባገነን ነው። እናንተዬ ይህን ቃል የፈጠረ መንዜ የኖቤል ሽልማት እንደሚገባው አትስማሙም? የመጀመሪያውን ወግ ‹‹ናፍቆቴን መልስልኝ›› አሰኝቸዋለሁ። ያለምክንያት አይደለም። ከአንድ ሁለት አመት በፊት “አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ላቀረበልኝ ቃለምልልስ ‹‹የአዲሱና በረከት ሳቃቸው ይናፍቀኛል›› ብዬ ናፍቆቴን በአደባባይ ገልጬ እንደነበር የጋዜጣዋ ታዳሚዎች ያስታውሱ ይመስለኛል። ታዲያ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ባለፉት ወራት ‹‹በረከት መፅሀፍ እየፃፈ ነው›› የሚል ወሬ ስሰማ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን በጡረታ መወገድ አይቀሬ መሆኑን የተቀበልኩት ጉዳይ ስለነበር፣ የሚተካቸውም ለዐይን የሚሞላ ሰው በአካባቢያቸው ስላልተረፈ፣ ምናልባት በረከት በዕድሜውም ወጣት ስለሆነ፣ ተኪያቸው እርሱ ሊሆን ስለሚችል “ለዚህ ሽግግር የሚያመቻች የበረከትን ሰብዕና የሚገነባ መፅሀፍ ሊያወጡ እንደ ቡድን ወስነው መሆን አለበት” በሚል በናፍቆት የተጠባበቅኩት መፅሀፍ ነበር። ፖለቲካዊ ብልጠቱን የሚያንፀባርቅ መዘርዝር ሳይሆን፣ በመሟሸት ላይ ያለ ሃገር መሪ አርቆ አስተዋይነቱን ከህሊናው ማዕድ የሚያካፍልበት ልዩ አጋጣሚ ነበር ስጠብቅ የከረምኩት። ሆኖም ያ በወጣትነቱ የማውቀውን ደጉን በረከት አድጎ ተመንድጎ፣ ልምድ አካብቶ፣ በዕድሜ ጨምቶ፣ በዘመን ርቀት ለስልሶ ላገኘው አልቻልኩም። ናፍቆቴን የሚመጥን በረከት በ‹‹ሁለት ምርጫዎች ወግ›› ገጾች መሃል አፈላልጌ ላገኝ ባለመቻሌ ነው ንዑስ ርዕሱን ‹‹ናፍቆቴን መልስልኝ›› ማሰኘቴ።

የመፅሀፉ ምረቃ፣ የሪፖርተር ዘገባና መቅድም

ሪፖርተር ጋዜጣ ስለ መጽሀፉ ምረቃ ሲዘግብ፣ በረከት ሼክ አላሙዲንን ‹‹መሃመድ ወሬኛ ነው›› አላቸው የሚለውን ሳነብ፣ “በረከት ይህን ያህል አማርኛ ሊጠፋው አይችልም ፣ ያው ሪፖርተር ከተጠናወተው ጠባብ ብሄርተኝነቱ በመነሳት ዕድሉን ባገኘበት ቅፅበት ሁሉ የኢህዴንን ልጆች ከማጥቃት ስለማይመለስ እንጂ ነው” አልኩ ለራሴ። ሁሌም መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ግን ማ ከሁዋላ አይዞህ ቢለው ነው አማረ አረጋዊ ብአዴኖችን እንዲህ ሊያጠቃቸው ቀንዱን እንዳቆመ የሚኖረው የሚለው ነበር። ስለመፅሃፉ የምረቃ ስነስርአት ግራ የተጋባውን የሪፖርተር መጣጥፍ ካነበበኩ በሁዋላ መፅሃፉን ሳፈላልግ፣ ሰሞኑን በረከት ስምኦን ለስደት የዳረገው የ‹‹አውራምባ ታይምስ›› ዋና ኤዲተርና ባለቤት የሆነው ዳዊት ከበደ መፅሀፉን በዲ.ኤች.ኤል ፖስታ ማስመጣቱን ነገረኝና፣ እንደ ቀድሞ አጫሽ ጓደኞቼ ‹‹ወጋሁ›› ብዬ እስኪጨርስ በእግር ጣቶቼ ቆሜ ተጠባበቅሁ። ምስጋና ይድረሰውና ዳዊት በሁለት ቀን ፉት ብሎ ሰጠኝ።

ተስፋዬን ሰንቄ ወደቤቴ አመራሁ፣ እያነበበኩ አድሬ ከስራ ለመቅረት ውሳኔ አድርጌ። ‹‹መታሰቢያነቱ ለወንድሜ ካሳሁን ገብረ ህይወት – እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጉዋዛለሁ›› ይላል ከማውጫው በፊት ያለው ገፅ። ‹‹ጉድ ሊፈላ ነው›› አልኩ ለራሴ። ያለምክንያት አልነበረም። ካሳሁንን በኢህአፓ ሰራዊት ውስጥ አውቀው ነበር። እጅግ ተወዳጅ ሰው እንደነበር ትዝ ይለኛል። ታዲያ ተሓህት ‹‹ትግሬ ለትግሬዎች ፣ የትልቋ ኢትዮጵያ (በትግርኛ ዓባይ ኢትዮጵያ ይሉታል) ህልመኞች ከሃገራችን ውጡ›› ብሎ ድንገት በከፈተብን ጥቃት ካሳሁን ውጊያ ላይ ተማረከ። ከጠባቂዎቹ አምልጦ በአካባቢው ወደነበረችው የጀብሓ አሃዱ አስጥሉኝ ብሎ ሲሮጥ የወያኔ ዘቦች በጀርባው ባወረዱበት የመትረየስ ጥይት ተመትቶ እንደተሰዋ አሳዛኙ ዜና ደረሰን። አዎን ካሳሁን ‹‹ትግራይ የኢትዮጵያ አይደለችም፣ የአማራና የትግሬ ለማኞች አብረው መለመን እንኳ አይችሉም›› ብለው የትግራይን ህዝብ ይቀሰቅሱ በነበሩ ጠባብ ብሄርተኞች እጅ ነበር የወደቀው።

ታዲያ በ1992 ህወሃት አመራር ውስጥ ክፍፍል ሲፈጠር፣ በረከት የመለስ አዳኝ ሆኖ የቆመ በመምሰል የወንድሙን ገዳዮች በከፊል የተበቀላቸው ነበር የመሰለኝ። ሆኖም እዚህ የመጀመሪያ ገፅ ላይ ወንድሙን ካሳሁንን ‹‹እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጉዋዛለሁ›› ሲል፣ በረከት ከጠባብ ብሄርተኞች ጋር የሚያደርገው ትግል አሁንም የቀጠለ መሆኑን ነው ሹክ የሚለን።

ከ1992 ክፍፍልና የነስዬ ቡድን መወገድ በሁዋላ በአቦይ ስብሃትና በቀዳማይት እመቤቲቱ መሃል የቀጠለው ትግል ለሽማግሌው መረታትና ከጨዋታው መገለል፣ በቅርቡ ደግሞ የርሳቸው አጋሮች ናቸው የሚባሉት ሁሉ እየተነቀሱ ገሚሶቹ በአምባሳደርነት፣ ገሚሶቹ በጡረታ እየተገለሉ፣ ዛሬ ኤፈርት የተሰኘውን ‹ግብረ-ሰናይ› ድርጅት ቀዳማይት እመቤቲቱ ብቻ እንደሚቆጣጠሩት ነው ንግስተ ሳባ ቤት መብልኢ ስሄድ የትግራይ ልጆች ሲያወሩ የምሰማው። ታዲያ በረከት ‹‹እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጉዋዛለሁ›› ሲልና፣ ሪፖርተር ደግሞ ተሩዋሩጦ በመፅሃፉ ምረቃ ስም ባቀረበው ሪፖርት ሼኩንና በረከትን አዳብሎ ለማቅረብ ያደረገውን መታከት ሳይ፣ አማረ ‹‹የማንን ተልእኮ አስፈፃሚ ነው›› እንድል አስገድዶኛል። ምናልባት ቀጣዩ መድረክ ደግሞ በበረከትና በቀዳማይት እመቤቲቱ መሀል የሚደረግ ሊሆን ይችል ይሆን? በረከትን ቀረብ ብለው ያዩት ሁሉ የሚመሰክሩለት አንድ ነገር ቢኖር ‹‹ከምቀበርባት ስድስት ክንድ መሬት በቀር ሌላ ሃብት አልፈልግም›› ማለቱን ነው። የነዚህን ሁሉ አንድምታ ወደፊት የምናየው ይሆናል።

አብረው የፈሱት…

ከላይ ባነሳሁዋቸው ሃሳቦች ከራሴ ጋር እየተሙዋገትኩ ወደመጀመሪያው ምእራፍ ዘው ስል የበረከት ‹‹ማሙዋሻ ወግ›› ጥሜን ሊያረካው አልቻለም። ሙሉ ሌሊት ሳነብ አድሬ ከስራ እቀራለሁ ብዬ ያቀድኩ ሰው፣ የግዴን ወደመኝታዬ አመራሁ። የመጀመሪያው ምእራፍ በአሰልቺና ትርጉም የለሽ ‹ፅንሰ ሃሳቦች› የተሞላ ሆነብኝ። አቶ መለስ በጦርነቱ አመራራቸውና በኤርትራ ፖሊሲያቸው ሲወጠሩ፣ መውጫ ቀዳዳ ሲፈልጉ ያገኙትን ‹‹ቦናፓርቲዝም››፣ የዱሮ ጉዋደኛዬ እንደ ዕውቀት ወስዶ ሲያነበንብ ሳየው አሳፈረኝ። የአቶ መለስን ቦናፓርቲዝም በወቅቱ አዲስ አበባ በሚወጡ መፅሄቶች እንደ አቅሜ ያፌዝኩበት ስለነበር በረከት ሳያነበው እንዳልቀረ እገምታለሁ። በረከት፣ ይህንኑ ፌዝ የኢህአዴግ ተሃድሶ መሰረት አድርጎ እንዴት ከክፍፍሉ ወዲህ ለተገኘው ኢኮኖሚያዊ ‹‹ግስጋሴ›› መሠረት እንደሆነ ሊያቀርብ ሲሞክር ግን ‹‹ምነው ጓዴ›› ከማለት በቀር የምለው አልነበረኝም።

በመጀመሪያው ምእራፍ ከቦናፓርቲዝም በተጨማሪም አርማጌዶን፣ ጥገኛ ዝቅጠት፣ ናዳን የገታ ሩጫ፣ አቦ ሸማኔ ወዘተ የመሰሉ አሰልቺ ቃላት እንደ መርግ እየወረዱ ስለሚከመሩ፣ የመፅሃፉን ተነባቢነት በእጅጉ ጎድቶታል። እነዚሁ አድካሚ ቃላት ግን ስለ ደራሲውና ‹‹እድገትና ዘመናዊነት ስላመጡት የአመራር ጓዶቹ›› የሚያሳብቁት ቁምነገር አለ። ፈረንጆች ‹‹ማይንድ ሴት›› ስለሚሉት ፋይዳ። መረጋጋት የሌለበት ህይወት ውስጥ እንደሚኖሩና፣ በነርሱ እድሜ አንድ ተአምር ፈጥረው ለራሳቸው ተኪ ትውልድ አውርሰው ለመሞት ትግል ውስጥ እንዳሉ ይጠቁማል። የልብ ህመሙ እየጠና በሄደ ቁጥር፣ ራሳቸውን ላልቻሉ 10 ጨቅላ ልጆቹ ማሳደጊያ የሚሆን ንብረት ለመተው ከላይ ታች ብቻውን ይባክን የነበረው አባቴ ታወሰኝና በረከት አሳዘነኝ። አባቴ እንደዚያ የደከመበትን ንብረት ግን፣ አብዛኛውን ደርግ የተረፈውን ደግሞ በረከት ሰሞኑን ባወጣው የሊዝ አዋጅና በዘመናዊነት ስም በሚደረመሱት ታሪካዊ ሰፈሮች ተዘመተበት። የዛሬ 20 አመት የነበረከት የአቦ ሸማኔ ሩጫም ከፈሩት ናዳ እንዳያድናቸው መተንበይ ይቻል ይመስለኛል። የነበረከት የአቦ ሸማኔ ሩጫ ሁሉን አግልሎ፣ ሁሉን አዋርዶ፣ ሁሉን አሳዶ በተመረጡ ጥቂት ጀግኖች ብቻ ሊደረግ የታሰበ ለመሆኑ የመፅሃፉ ቀጣይ ምዕራፎች ይፋ ያደርጉታል። የዋህነት ነው። ምክንያቱም አበው ‹‹አብረው የፈሱት ፈስ አይገማም›› ብለዋልና ነው።

የመፅሀፉ ንኡስ ርእስ ‹‹ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ›› ይላል። ገባ ብለው ሲመረምሩት በናዳ የተመሰሉት ረሃብ፣ በሽታ፣ ጠኔ፣ ኋላ ቀርነት፣ ድህነት እና ከነዚህ ችግሮች ለመላቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢህአዴግ የተለየ አማራጭ የመፈለጋቸው ፋይዳ ናቸው። ግራ የሚያጋባው ጉዳይ ግን እነዚህ የጋራ ብሄራዊ ችግሮች በኢህአዴግ ላይ የሚወርዱ መርጎች ተደርገው መታየታቸውና፣ በአቦ ሸማኔ ፍጠነት ካልሮጠ በናዳው የሚደባየውም ኢህአዴግ ሆኖ መታየቱ ነው። አንድም ቦታ በስህተት ናዳው እንዳይነሳ ምን ማድረግ ይቻለናል ብሎ ደራሲውም ሆነ የሚመራው ፓርቲ ሲጨነቁ አይታይም። ናዳው እንዳይንከባለል በብሄራዊ ምክክር ሊፈጠር ስለሚችለው መላም ለማሰብ ፍልጎቱም ጊዜውም የላቸውም። ከአይቀሬው ናዳ እንዴት ብቻቸውን ፈጥነው እንደሚያልፉ ብቻ ነው የሚያውጠነጥኑት። ወደሃገራዊ መንግስትነት ላለማደግ የቆረጡ መሆናቸው ነው ፍንትው ብሎ የሚታየው። በ2002 ምርጫ ማግስት መስቀል አደባባይ ላይ መለስ ባደረገው ንግግር ውስጥ ‹‹የመረጠንን ህዝብ ድምፅና ውሳኔ እንደምናከብር ሁሉ ያልመረጠንን ህዝብ ድምፅም እንደምናከብር ያለአንዳች ማወላወል ለመግለፅ እወዳለሁ›› ብሎ የተናገረ ቢሆንም፣ ንግግሩ የተፃፈበት ቀለም ሳይደርቅ በከተማ ሊዝ አዋጅ አልመረጠንም ብለው የሚገምቱትን የህብረተሰብ ክፍል ለማራቆትና በረሃብ አለንጋ ለመግረፍ ጨካኝ አዋጅ ወደማወጅ ተሸጋገሩ። አዋጁ የዘርና ፖለቲካዊ ስሌት እንደሌለበት መናገር ያስቸግራል። ለኢህአዴግ ትልቁ ጥያቄ ግን መቼ ነው ብሄራዊ መንግስት ለመሆንና ያለአድልኦ ሁሉንም ዜጋ በእኩል ዐይን ለማየት የሚነሳው? የሚለው ነው። ምዕራፍ አንድ ከቻርለስ ዲክንስ ‹‹የሁለት ከተሞች ወግ›› ገፅ አንድ ላይ በተወሰደ ሰፊ ጥቅስ ይቋጫል። በረከት በራሱ አነጋገር ‹‹እረፍት በሚነሳ ህይወት ውስጥ የሚጉዋዝ›› በመሆኑ ዲክንስን ከገፅ አንድ ባሻገር ማንበቡን ተጠራጥሬአለሁ። ቢሆንማ፣ በሚቀጥሉት ምእራፎች የምናየውን ብልጠት፣ ጭካኔና፣ እልህ ባላየን ነበር። ላደለውማ ፣ እደግ ተመንደግ ተብሎ ለተመረቀማ የዲክንስ አይነት ፀሀፊዎችን ማንበብ አንዱ ጥቅም፣ የህይወት ቀለሟጥቁርና ነጭ ብቻ እንዳልሆነና፣ ዕውነትም ብቸኛ ባለቤት እንደሌላት መማር በመሆኑ፣ የበረከት ወግ ደግሞ ከነዚህ ሃብታት በእጅጉ የራቀ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ንባቡ ከገፅ አንድ አልዘለለ ይሆን ብዬ መጠርጠሬ።

ምርጫ 97ና የበረከት ወግ ሁለተኛው ምዕራፍ እንደ ቁምነገር ሳይሆን እንደ ወግ የተዋጣለት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የሚያስቁም የሚያሸማቅቁም ወሬዎችን ያካተተ ነው። በመጠኑም ቢሆን ለምእራባውያን አለመንበርከክም የታየበት፣ ለበረከትም ሃገራዊ አርበኝነት ስሜት አድናቆት እንድንቸር የሚያስገድድ አቀራረብ ነው ያለው። ከተለመደው የኢህአዴግ ‹‹ሃገሪቱ›› ከሚል የባዕድ የሚመስል አቀራረብ ራሱን አርቆ፣ በረከት የአባቶቻችንን አርበኝነት ለማወደስም ሆነ ኢትዮጵያን በስሟ ለመጥራት የደፈረ በመሆኑ፣ ደስ መሰኘቴን መደበቅ አልሻም። ምናልባትም ኢህአዴግ ወደ ጉልምስና መሸጋገሩን የሚያበስርም ከሆነ መልካም ዜናም ነው። ከአዲሱ ለገሰ በቀር ሁሉም ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ረቂቁን ያነበቡት መሆኑን ራሱ ደራሲው ስለነገረን፣ ‹‹አርበኝነት አብዝተሃልና ቀንስ፣ ቁረጥ›› አለመባሉም ለተስፋችን ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በበረከት የምርጫ 97 ትረካ ከቅንጅት ብርሀኑ ነጋ፣ ከህብረት ደግሞ ነገደ ጎበዜ ዋነኛዎቹ ተዋናይዎች ሆነው ቀርበዋል። ከብርሀኑ ጋር ከመድረክ ውጪ ስላወጉት፣ ሁለቱ ብቻ ስለሚያውቋቸው ነገሮች በብዛት ያትታል። በዚያ ላይ ብዙም ማለት ባልችልም አንድ የማውቀው ነገር ግን፣ የካቲት መጀመሪያ ላይ ፊንፊኔ በገባሁ ማግስት፣ ብርሃኑ፣ ‹‹ከፓርቲዎች ድርድር ስብሰባ ስንወጣ እዚያው ሼራተን እንገናኝ›› ብሎኝ ከምሽቱ ሁለት ሰአት አካባቢ ሶስታችንም ተገናኝተን ካወራናቸው ነገሮች ዋነኛው በግል ደረጃ የሚደረጉ ግንኙነቶች ያላቸውን ጠቀሜታና፣ ከድርጅቶች መግለጫዎች ባሻገር ውጥረትን ማርገብ ላይ ስላላቸው አስተዋፅኦ ሃሳብ መለዋወጣችንን አስታውሳለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ኢህዴን ውስጥ እያለን እኛ እየተጎዳንም ቢሆን፣ ለህወሓቶች የውስጥ ምስጢራችንን እንዴት እናካፍላቸው እንደነበር በረከት ያውቃል። ዱሮ በጦር ሜዳ የተሞሻለቅናቸው ሰዎች ስለነበሩ፣ የጠላትነት ስሜታቸውን ለማብረድና ረጅም ርቀት አብረን ለመሄድ እንድንችል ብዙ የሚያረጓጓቸው የሚመስሉንን መረጃዎች እንሰጣቸው ነበር። ሱዳን በነበርኩባቸውም አመታት ከኦነግ መሪዎች ጋር ፅህፈት ቤታቸው ከማደር ጀምሮ እስከ መረጃ ልውውጥ ድረስ እነርሱ የሚሰማቸው የጠላትነት ሰሜት የሌለን መሆኑን ለማሳየትና የወዳጅነት ስሜት ለማዳበር የምናደርገው እንደነበር በረከት ያውቃል። ለብርሀኑም ካካፈልኩት ልምዶቼ መሃል ነበሩ።

ሁሌም ከብርሀኑ ጋር ከምንጋራቸው ሃሳቦችም አንዱ፣ ኢህአዴግ በወታደራዊ ሃይል አሸንፎ የገባ ሀይል ቢሆንም ህዝቡ ለምን አልተቀበለኝም ለሚለው ጥያቄ ድርጅቱ የሚሰጠው መልስ አደገኛ በመሆኑ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ድርጅት መሆኑን ነው። በተለይ ደግሞ በህዝብ ድምፅ ለመዳኘት ፈቃደኛ ነኝ ብሎ ዘው ባለበት ምርጫ 97 ወዳልተጠበቀ ጭካኔ እንዳይረማመድ ፍርሀቱ ነበረን። ለዚህም ይመስለኛል ብርሀኑ በረከትን ‹‹አንድ ነገር ቢሆን ዘልዬ አንተ ቤት ነው የምደበቀው›› ሊለው የሚችለው። በረከት ሊያስጥለው እንደማይችል ጠፍቶት ሳይሆን፣ በተቃዋሚው በኩል የጠላትነት ስሜት እንደሌለና፣ ስልጣንን ጠብቆ ለማቆየት ኢህአዴግ በሚያደርገው ጥረት ተገቢ ያልሆነ አመፅ ውስጥ ቢገባ እንኳን፣ ‹‹ተደናብራችሁ የምታደርጉት ሊሆን ስለሚችል ዶፉ እስኪያልፍና ነገሮች እስኪጣሩ እቤትህ ብደበቅ እንኳ ትተባበረኛለህ›› በሚል የጓደኝነት ስሜት የተናገረው ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ሁኔታዎች ተለዋውጠው ዛሬ በጠላትነት ተሰልፈው በሚገኙበት ሁኔታ በረከት ይህን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋሉ ሊያስገምተው ካልሆነ በቀር፣ እንደገመተው ብርሀኑን የሚያንኳስሰው አይመስለኝም።

ሌላው የበረከት የምርጫ 97 ወግ ትኩረት ነገደ ጎበዜ በህገ መንግስቱ ላይ ስለፃፈው ትችትና፣ ቅንጅት እንዴት አድርጎ ዋናው አስፈፃሚ ሊሆን እንደቻለ የሚተነትን ነው። በዚህ ወግ ብዙ ከመራቀቁ በፊት ግን፣ የቅንጅት አመራር አባላት በወቅቱ እንዴት የነገደን ‹‹ህገ መንግስቱን በህዝባዊ አመፅ መናድ›› ጥሪ እንደማይቀበሉ ከሰጡዋቸው ህዝባዊ መግለጫዎችና ንግግሮች እንዲሁም የመድረክ ላይ ክርክሮች መመርመር ነበረበት። ሆኖም የመፅሃፉ አንዱ ዋነኛ አላማ በ1997/98 ለደረሰው የህዝብ ዕልቂት ተጠያቂው ቅንጅት እንደነበር ዋቢ መሆን ስለሆነ፣ ደራሲው የቅንጅቱን መግለጫዎች የሚገባቸውን ክብደት ሊሰጣቸው አልፈለገም። ለታሪክ ተመራማሪዎች ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችል ሰነድ ለማሰናዳት ለፈለገ ሰው ግን እንዲህ አይነት ሸፍጠኝነት አይፈቀድም። ቢበዛ በረከት ማድረግ የሚችለው፣ ‹‹ቅንጅቶች በአፋቸው ተቃዋሚ መስለው ቢቀርቡም፣ በተግባር ግን የነገደን ተልዕኮ ለማሰፈፀም ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መን አድርገዋል›› ብሎ መከራከር ነበር። ሆኖም በረከት በእጁ ያሉትን የቅንጅት ዶሴዎች ከፍቶ ሊያያቸውና ሊያካፍለንም ፈቃደኛ አልሆንም። የካቲትና መጋቢት 1997 አዲሰ አበባ በነበርኩበት ወቅት፣ ብርሀኑ በምርጫ አዝማችነቱ እጅግ በስራ ተወጥሮ ስለነበር ፣ ወደ ዲሲ ከማምራቱ በፊት ንግግር እንዳዘጋጅለት ጠይቆኝ፣ እኔ ካዘጋጀሁትና መጋቢት 4 ቀን 1997 አም ብርሀኑ በዋሽንግተን ዲሲ ለ2000 ያህል ዕድምተኞች ያቀረበው ንግግር የቅንጅቱን የወቅቱን አመለካከት የሚያንፀባርቅና፣ የበረከትን ክስ ፉርሽ የሚያደርግ በመሆኑ በረጅሙ ለመጥቀስ ተገድጃለሁ። እንዲህ ይላል፣

‹‹ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በከፍተኛ ትኩረት የሚንቀሳቀስበትን ‹‹ሕገ መንግስታዊውን ስርአት የማፍረስ ስትራተጂ አላቸው›› ለሚለው ክስ ያለንም መልስ ግልፅ ነው። ቅንጅት አብዮታዊ ድርጅት አይደለም። ለስርነቀል ለውጥ የቆምን፣ በማፍረስና በመናድ የምናምን ፖለቲከኞች አይደለንም። ስማችን እንደሚጠቁመው የአንድነትና የዲሞክራሲ ሀይል ነን። ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን ማፍረስ ሳይሆን ማሻሻል ነው አላማችን። ለማሻሻል እንኳን ህግን መሰረት አድርገን፣ ለማሻሻል የሚያስፈልገውን ድምፅ በማሰባሰብ እንጂ በአዋጅና በኣሻጥር የመለወጥ ፍላጎት የለንም። ኢህአዴግ የህዝብን ይሁንታ እስከተቀበለ ድረስ የግንቦት ምርጫ አሸናፊዎች የቅንጅቱ ዕጩዎች ብንሆንም የምንመሠርተው መንግስት የኢህአዴግን ህጋዊ መብት የሚያከብር፣ ተወዳድረው ባሸነፉበትም ወረዳዎች የተሰጣቸውን የህዝብ አደራ በተገቢው የሚወጡበትን የምክር ቤት ወኪሎቻቸውን የሚያከብር መንግስት ይሆናል። ኢትዮጵያዊዉ ዜጋ በፖለቲካ አስተያየቱም ሆነ በሚያምንበት ርዕዮቱ የማይታደንበት፣ በነፃነትና ያለፍርሃት የሚኖርበት ሃገር መገንባት ነው የቅንጅቱ ዕይታ። ይህ ደግሞ የኢህአዴግ አባላትንም መብት ያካተተ ነው›› ይላል። በስፋት በጠቀስኩት ደስ ባለኝ ነበር፣ ሆኖም በረከት የእጅ ፅሁፌን አጣጣል ስለሚያውቀውና ኦሪጅናሉም የቅንጅት ቢሮ በተወረረ ወቅት ተወስዶ በበረከት እጅ ስለሚገኝ፣ ፈልጎ እንዲያነበው አሳስቤ በዚሁ ይህን ክርክር እልባት ልስጠው። ኦሪጂናል ቪዲዮው አርቲስት ታማኝ በየነ ጋ ስለሚገኝ ‹‹ዩ ቱብ›› ላይ ቢያስቀምጠው አንባቢው ሁሉ ሊያደምጠው ይችላል።

በምርጫ 97 ወጉ በረከት፣ ቅንጅት የነገደን የአመፅ ጥሪ ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን፣ ከምዕራባውያን የቀለም አብየተኞች ጋር ተመሳጥሮ እንዴት አመፅ ለማካሄድ እየተሰናዳ እንደነበር በስፋት ያትታል። ለዚሁም ዋነኛ መረጃ አድርጎ የሚያቀርበው የጂን ሻርፕ ‹‹ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ›› የተሰኘ መፅሀፍ በምዕራባውያንና በቅንጅት እንዴት ተተርጉሞ እንደተሰራጨ በማተት ነው። የጂን ሻርፕ መፅሀፍ ለበረከት የቀለም አብዮት ክስ ማእከላዊ ዋቢ ጉዳይ ሆኖ ስለቀረበ፣ በዐይን ምስክርነት የማውቀውን ማቅረብ ተገድጃለሁ። ከምርጫ 97 በፊት ስለዚህ መፅሀፍ ዕውቀት የነበረው ብዙም ኢትዮጵያዊ የነበረ አይመስለኝም፡፡ ከምርጫው ሁለት ሳምንታት በሁዋላ የሰኔ አንድ ግድያ በተፈፀመ ማግስት እዚህ በዋሽንግተን አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ሀዘንና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። ታዲያ ለትግሉ አዲስ የሆኑ ወጣቶችና ፕሮፌሽናሎች ሁሉ ከስራ መልስ እየተሰበሰቡ ‹‹የህዝቡ ድምፅ እንዳይሰረቅ ትግሉ እንዴት ይቀጥል›› የሚል ውይይት ይጧጧፋል። በዚህ መሃል ነው የቅንጅትም የህብረትም አባል ያልነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ከጂን ሻርፕ መፅሀፍ ጋር ያስተዋወቀን። ቅንጅትና ህብረት አመራር አካባቢ ስለ ሰላማዊ የትግል መንገዶች በቂ ግንዛቤ የለም የሚል እምነት ላይ ስለደረስን፣ በመፅሀፏ ወደ አማርኛ መተረጎምና መሰራጨት ተስማማን። ከሃያ የማንበልጥ በአመዛኙ ወጣቶች ያሉበት ስብስብ፣ ሁለት ሁለት መቶ ዶላር አዋጥተን ፣ ድንቅ ተርጓሚዎች ተገኙና እዚያው አዲስ አበባ ልከን አሰራነው። ገንዘብ ያዋጣው ስብስብም ከዚህ ሌላ ተግባር ውስጥ አልቀጠለም፣ ተበተነ። ሓቁ ይህ ነው። የበረከት ወግ ግን ራሱ በፈበረከው የወዳጅ ጠላት አሰላለፍ፣ ቅንጅት እንዴት ከኢምፔሪያሊስት ሓይሎች ጋ ወግኖ የነገደን ‹‹ህገ መንግስቱን በአመፅ የመናድ›› ጥሪ ተግባራዊ ለማድረግ የጂን ሻርፕን መፅሀፍ እንደተረጎመና እንዳሰራጨ ይነግረናል። ይህ ፍፁም ሀሰት ነው። ኢህአዴግ በሀሰት መረጃ ላይ ተመርኩዞ በለኮሰው አመፅ ብዙ ወጣቶች፣ ባልቴቶችና አረጋውያን ለሞት ተዳርገዋል። ተጠያቂውም ‹‹የህብረት መንግስት እናቋቁም›› ብሎ ኢህአዴግን ይለማመጥ የነበረው ቅንጅትና አመራሩ ሳይሆኑ፣ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› የተሰማራው መንግስት በምናቡ የፈጠረውን የቀለም አብዮት ሴራ ለማክሸፍ በወሰደው አላስፈላጊ እርምጃ ነበር። የበረከት ወግ ትልቁ ክስረት በዚህ በቀለም አብዮት ዙሪያ የሚከሽነው ታሪክ በሃቅ ላይ ያልተመሠረተና፣ ለአብዮቱ ጥሪ አድርገዋል ብሎ በረከት የሚከሳቸው ጆርጅ ቡሽ በወቅቱ የካርተር ማዕከልን፣ አምባሳደር ያማሞቶንና፣ ቪኪ ሃድልስተንን በመጠቀም ለኢህአዴግ ስርአት ቀጣይነት የተረባረቡ መሆናቸውን ነው። ይህንንም ያደረጉት ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ከአውሮፓውያኑ የተለየ ፍቅር ስላላቸው ሳይሆን፣ አካባቢውን ከሽብርተኞች ለመታደግ ከኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ ስላልታያቸው ይመስለኛል።

በእኔ ግምት አቶ ሃይሉ ሻውል በመስከረም 98 ዋሽንግተን በመጡበት ወቅት ከፔንታጎንና ስቴት ዲፓርትመንት አማካሪዎች ጋር ባደረጉዋቸው ስብሰባዎች፣ የቅንጅቱ መሪ ግትርና የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ተደርገው ስለተገመገሙ ለአቶ መለስ አማራጭ ሆነው ሊታዩ አልቻሉም። በቅንጅት ላይ የመጨረሻውም የክተት አዋጅ የታወጀው ከዚህ ስብሰባ በኋላ መሆኑ የሚያሳብቀው ነገር ካለ፣ ‹‹እኛ አልታይቶም እንላለን የመሰላችሁን በአፋጣኝ አድርጉ›› የሚል አረንጓዴ መብራት ከዋሽንግተን አቅጣጫ የበራ መሆኑን ይመስለኛል። የቅንጅት መሪዎች ከታሰሩ በሁዋላ የአሜሪካዋ ሻርዤ ዳፌየር ቪኪ እንዴት ከአቶ በረከት ጋር እጅና ጓንት ሆና ትሰራ እንደነበር ደራሲው የሚያውቀውን ሊያካፍለን አለመፍቀዱ ንፉግነቱን ብቻ ሳይሆን የመፅሀፉ አላማ ፕሮፓጋንዳዊ መሆኑንም ጭምር ይጠቁማል። በመተካካቱ ሂደት ራሱን ለማግለል የበሩ ዳፋ ላይ ቆሞ፣ በረከት የኢህአዴግ ነባር አመራር ‹‹ከእንግዲህ የቀረው ያልተነገረ ታሪኩን መንገር ሊሆን ይችላል›› ቢለንም፣ ታሪክ ግን ከፕሮፓጋንዳ ካልፀዳ ፋይዳ እንደሌለው ከዚህ ካሁኑ ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› ሙከራው ይማርበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በምዕራፍ ሁለት፣ ሶስትና አራት፣ ወጉ እየተሟሟቀ ቢሄድም በረከት አንዲትም ቃል ሳይተነፍስ የሚያልፍባቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው። አንደኛው የኢህአዴግ የ‹‹ኢንተርሃምዌይ›› ክስ ሲሆን ፣ ምናልባት የጋራ ጓደኛችንን አዲሱን ከማስቀየም ዝምታን መርጦ ይሆናል። ስለ ምርጫ 97 ሶስት መቶ ገፅ መፅሀፍ ፅፎ ግን ስለ ኢህአዴግ ‹‹ኢንተርሃምዌይ›› ክስ በዝምታ ማለፍ አይቻልም። አዲሱ ብዙ በሞትና ህይወት መሃል ባሉ ጉዳዮች ላይ (በራሱም ሆነ በሌሎች) ለመወሰን የሚያስገድደው ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ሰው ነው። ሆኖም በምርጫ 97 ወቅት የ‹‹ኢተርሃምዌይ›› ክስ በምረጡኝ ክርክሩ ውስጥ በማስገባት ቀጣዩን ቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ ሂደት አላሰፈላጊ የዘር ውጥረት እንዲኖር አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል። ይህን ኩነት በረከት በዝምታ ማለፍ መርጧል። ሊታለፍ ግን የሚችል አይመስለኝም። ምክንያቱም የቅንጅቱ በድሩ አደም የሚያዚያ ሰላሳ ሰልፍ ላይ ‹‹ኢህአዴግን ወደመጣበት እንመልሰዋለን›› ሲል፣ በሰልፉ ትልቅነት ተሳክሮ የዘላበደው መሆኑ ግልፅ ሆኖ ሳለ፣ ‹‹ነፍጠኞች መጡብህ›› ለሚል ቅስቀሳ ኢህአዴግ ተጠቅሞበታል። ያውም በድሩ ኦሮሞ መሆኑ እየታወቀ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በረከት የፈፀመው ስህተት ደግሞ፣ በማግስቱ ቅንጅቱ የበድሩን መፈክር ለማስተባበል የብዙሃን መገናኛ እንዲፈቀድለት ሲጠይቅ እምቢተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው። ስለምርጫ 97 ብዙ እዚህ ግቡ የማይባሉ ጉዳዮችን የከተበው በረከት፣ እንዲህ የሰማይ ስባሪ የሚያህሉ ጥፋቶቹን፣ ይቅርታ መጠየቅ የሚችልበት ዕድል አግኝቶ እያለም ሳይጠቀምበት ማለፍን መርጧል።

ከዚሁ ከምርጫ 97 ወግ ሳንርቅ አንድ ሌላ ለፕሮፓጋንዳ ተብሎ ለመስዋዕት የቀረበ ሀቅ ላቅርብ። አቶ በረከት ስለ ቅንጅት ነፍጠኝነት ዋቢ ለማቅረብ እንዲህ ይለናል። ‹‹አዲሰ አበባ የብዙ ብሄር ተወላጆች የሚኖሩባት ከተማ ሆና እያለ፣ አንድም የኦሮሞ ተወላጅ የምክር ቤት አባል አድርገው አለማስመረጣቸው በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ በመሪነት ለተሰለፉት የብሄሩ ተወላጆች ጭምር ቁብ አልሰጣቸውም›› ይለናል። እኔ እንኳ እዚህ ከ10 ሺህ ማይልስ ርቀት ላይ የማውቀውን መረጃ፣ በረከት ስላልነበረው ነው የሚያወራው እንዳልል፣ ከእኔ የተሻለ መረጃ ሊኖረው ይገባል፣ ወይም አለው። ቢያንስ ቢያንስ በ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጠኝነቱ የሚያውቀው ታምራት ነገራ የቅንጅት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመራጭ ከመሆኑም በተጨማሪ ኦሮሞ መሆኑንም ያውቃል። ‹‹አንድም የኦሮሞ ተወላጅ የለም›› ብሎ በድፍረት ስለተናገረ ግን ለትምህርት ያህል አንድ ካቀረብኩ በቂ ነውና ሌሎች ኦሮሞዎችን ወደመጥራት አልሸጋገርም። ኦሮሞዎች ሁሉ ስማቸው ኩማ ካልሆነ በቀር እንደ ኦሮሞ አንቆጥራቸውም የሚል አዋጅ እስኪወጣ ድረስ ማለቴ ነው።

በዚህ ምዕራፍ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲል በረከት መስዋዕት ያደረጋቸውን ሀቆች ዘርዝሮ ማቅረቡ አድካሚ ስለሚሆን ራስን መወሰን የግድ ቢሆንም፣ የበረከት ወግ ፈፅሞ ዕውነት የለበትም ብዬ ለመከራከር ግን አልከጅልም። ለምሳሌ በዕጩዎች አቀራረብ ላይ በኢዴፓና መኢአድ መካከል የነበረው ፍጥጫና ራስ ወዳድነት ራሴ በየካቲት መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ሳለሁ የታዘብኩት ስለነበር የበረከት ዘገባ ትክክል ነበር እላለሁ። ስለተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችም በየምዕራቡ ኤምባሲ ደጅ መጥናትም ተገቢ ትችት ያቀረበ ይመስለኛል። እኔ እንዳውም ራቅ ብዬ ሄጄ፣ ይሄ ምዕራቡን እንደ ስልጣን መወጣጫ መሰላል የማየት ችግር፣ ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት ለከፈለው መስዋዕትነት የሚገባውን ከበሬታ ላለመስጠት ተቃዋሚዎች ‹‹አሜሪካዊው ኸርማን ኮሆን ‹አዲሰ አበባ መግባት ትችላላችሁ› ሲል፣ ኢህአዴግ በአንድ ሌሊት ጦር መስርቶ እመር ብሎ የእምዬ ምንሊክ ቤተመንግስት ውስጥ እንደገባ›› እያስመሰሉ ማቅረባቸውና፣ ይህንንም ፕሮፓጋንዳቸውን በጊዜ ርቀት እያመኑበት መሄዳቸው ለገቡበት ቅርቃር አንዱ ምክንያት ይመስለኛል። ሆኖም ተቃዋሚዎች በኩርኩም ብዛትም ሆነ፣ በአመለካከት መሸጋሸግ የተነሳ የኢህአዴግን ቀድሞ መሪዎች በድርጅቶቻቸው አመራር ውስጥ እስከማቀፍ የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገዋል። በቆሙበት የወዳጅ- ጠላት ክፋትና ጨለማ ተሰትሮ የቀረው ኢህአዴግና አመራሩ ናቸው።

ከላይ ያልኩት እንደተጠበቀ ሆኖ በምዕራብ ኤምባሲዎችና በተቃዋሚ ድርጅቶች መሃል ያለው ግንኙነት የሚከነክነውን ያህል፣ በረከትም ሆነ ኢህአዴግ ይህን ችግር ለመቅረፍ ስላደረጉት ሙከራ ምንም ወግ አያካፍለንም። ወይም በሌላ አነጋገር ‹‹ለምን ይሆን ወደ ምዕራቦች አንጋጠው የሚያዩት›› ብለው የጠየቁ አይመስሉም። አሁንም ከብዙ ሺህ ማይልስ ርቀት የምታዘበው፣ ከላይ ከምዕራቡ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጥቂት የአመራር አባላት ትቶ ከነርሱ በታች ያሉትንና ሊያደራጁ የሚችሉትን አባላቸውን ከስር ኢህአዴግ ስለሚያጭድባቸው፣ ኢምዩኒቲ (ጠለላ) ለማግኘት ማድረግ የተገደዱት ነገር ሆኖ ይሰማኛል። ኢህአዴግ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር እንደ ወዳጅና ጠላት መተራረጃ ሰንጋ ተራ አድርጎ ከማየት ይልቅ፣ በተለይ እገነባዋለሁ የሚለው ነጭ ካፒታሊዝም ዕምነቱ በብሄራዊ መንግስትና ሁሉንም ዜጎች በዕኩል በማስተናገድ በመሆኑ፣ ወዳጅ/ጠላት ከሚል አስተሳሰብ ቢላቀቅ፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችንም ከኢህአዴግ አመፅ ከለላ ፍለጋ ወደ ምዕራባውያን ኤምባሲዎች ከመንጦልጦል ያድናቸው ነበር። ባለፉት ሃያ አመታትም ለኤምባሲዎች ከሰጠናቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተሰባስበው የመምከርና ውሳኔዎች የማካሄድ ውርደትም እንላቀቅ ነበር። የለጋሾች ጉባኤ የሚባል ስድብ አጥንታችን ስር ገብቶ ሊሰማንም በተገባ ነበር። ቢሆንልንማ ከምርጫ ታዛቢነታቸውም ልንሰርዛቸው ብንችል በተገባ ነበር። አቶ በረከትም በሁለት ምርጫዎች ወግ ዳር ዳር ያለው ሃገራዊ አርበኝነት፣ እንደወጉ ተቃዋሚው ላይ መሳለቂያ መሆኑ ቀርቶ እንደአባቶቻችን የሁላችን መጎናፀፊያ በሆነ ነበር።

በምእራፍ 2፣ 3 ና 4 አንድ ግልፅ የሆነ የአገዛዙ አስተሳሰብ ኢህአዴግን መቃወም በብርሃን ፍጥነት የዘር ጉዳይ ሆኖ የሚተረጎም መሆኑ ነው። ይህን ሽግግር ለመረዳት የኢህአዴግ አመራር መሆን የግድ ይመስለኛል። በአንድ በኩል ኢህአዴግ ህብረ- ብሄራዊ ስብስብ ስለመሆኑ በአፅንኦት ይናገራል። እዚያው በዚያው ግን ቅንጅት ለጥቅምት 21 ቀን በጠራው የቤት ውስጥ ቆይታ አድማ ካወጣው ባለሰባት ነጥብ ጥሪ በቁጥር አራት የሚገኘው ስለማህበራዊ ማግለል እርምጃዎች የሚጠቅሰውን በረከት እንዲህ ሲል ጠቅሶ ‹‹በተለይም አብረውን ከጎናችን እየኖሩ ለዚህ ጥፋት መሳሪያ የሆኑ ወገኖቻችንን ለማስጠንቀቅ…ቡና አትጣጡ፣ ለቅሶ አትዳረሱ፣ አብራችሁ ቀብር አትቋቋሙ›› ብሎ ቅንጅት ጥሪ አደረገ ይለንና፣ እዚያው በዚያው፣ በአቶ በረከትና ኢህአዴግ ዐይን ይህ ጥሪ ሲተረጎም ‹‹የጋራ አገር ለመገንባት ቆርጦ የተነሳውን ህብረ ብሄር ህዝብ የሚነጣጥልና ወደመጨረሻው ጫፍ ሊወስድ የሚችል አደገኛና ከፋፋይ ጥሪ…›› ተብሎ ይተረጎማል። ኢህአዴግ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት ከሆነ፣ እንዴት ነው አንድ ጉራጌ አገር ያለ የኢህአዴግ አባል በአክስት አጎቶቹ መገለል ቢደርስበት፣ እንዴት በዘር መከፋፈል ሊሆን እንደሚችል የተለየ የሎጂክ ትምህርት ይጠይቅ ይመስለኛል። ለእኔ የታየኝ ግን ያልተረጋጋ አእምሮ የሚፈበርከው ፅልመት ነው።

ሆኖም እዚህ ላይ ከበረከት ጋር የምጋራው ፋይዳ ግን አለ። ለኢህአዴግ ጭካኔ መሳሪያ ለሆኑ ወገኖቻችን እሳት አታቀብሉ የሚለው የቅንጅት ጥሪ የተሳሳተ ነበር። እዚህ ዳያስፖራ ውስጥ እንኳ እንዳየነው የ‹‹ባላገሩ›› ዘፈን እመቤት የሆነችውን አቢቲ ‹‹ለምን አዲስ አበባ ላይ ለኢህአዴግ ሬዲዮ ቃለምልልስ ሰጠሸ›› ብለው ሲያፋጥጧት ‹‹ከቻላችሁ ወርዳችሁ ግጠሙዋቸው እኔን ተውኝ›› በማለቷ ምግብ ቤቷን የሚያዘጋ አድማ እንደተደረገባት በዐይኔ ብሌን ያየሁት በመሆኑ፣ ከበረከት የዘር ክስ ባሻገር የቅንጅቱ ውሳኔ አደገኛ እንደነበር አያጠያይቅም። ሆኖም፣ ያ ሁሉ የስሜት መደፍረስ በነበረባቸው የድህረ ምርጫ 97 ወራት ግን አንድም የትግሬ ቢዝነስ የማግለል እርምጃው ሰለባ ስላልነበር፣ የበረከት ወግ ‹‹ህብረ ብሄር ህዝብ የሚነጣጥልና ወደመጨረሻው ጫፍ ሊወስድ የሚችል›› የሚለው ትንተና መረን የለቀቀና የሃላፊነት ስሜት የጎደለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

የበድሩ አደም ‹‹ኢህአዴግን ወደመጣበት እንመልሰዋለን›› መፈክር ሚያዚያ 30 ምሽት በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ከአቦይ ስብሃት ጋር ሼራተን ውስጥ አብሮ ይጠጣ የነበረ ትውውቄ እንደነገረኝ ሽማግሌው ከመቅፅበት ተርጉመው ‹‹እኛ ወደመቀሌ ስንሄድ እናንተን መንዝ ላይ አራግፈናችሁ ነው የምናልፈው›› ሲሉ መስማቱ እንዳስደነገጠው አጫውቶኝ ነበር። የሚገርመው ግን በሳምንቱ ቅንጅት ሸገርን በዝረራ ሲያሸንፍ ይሄው የስብሃት ዛቻ መንግስታዊ ፖሊሲ ሆኖ በፊት ስንትሰ የኦሮሞ ተማሪዎች በጉዳዩ ከዩኒቨርሲቲ እንዳልተባረሩበትና እንዳልታሰሩበት ‹‹አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ናት›› ተብሎ ታወጀ። የበረከት ወግ ግን ይህንንም ጉዳይ በዝምታ ያልፈዋል። በወቅቱ የመንግስት ውሳኔ አሳፋሪ የነበረ ቢሆንም እንኳ ታሪክን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ለተነሳ ደራሲ የማይታለፍ ጨለማ ነበር።

በረከት ከምርጫው በሁዋላ ኢህአዴግ ስህተቶቹን በማረም እንዴት ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ከወጣቶችና ሴቶች ጋር እየተወያየና እያቀፋቸውም እንደሄደ በስፋት ያወጋናል። ‹‹ በኢህአዴግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርከት ያሉ ተማሪዎች የኢህአዴግ አባላት እንዲሆኑ አስቻለ›› ይለናል። ልክ ነው ኢህአዴግ የቅንጅትን አባላት ጭምር መልምሎ በምርጫ 97 ወቅት ከነበረው 700 ሺህ አባላት ዛሬ ወደ 5 ሚሊዮን ተመንደጓል። በረከት በጨዋነት የማይነግረን ግን በምርጫ 97 ማግስት በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ኢህአዴግ ምን አይነት ቅስቀሳዎችን ያደርግ እንደነበርና ‹‹ነፍጠኞች ተመልሰው መጡብህ›› የሚለው ማነሳሳቱ፣ እንዴት በወጣቱ መሃል ሊሰራለት እንደቻለ ግን ምንም ትንፍሽ አይልም ፡፡ በኢህአዴግ ‹‹ነፍጠኞች መጡብህ›› የበረገገው የኮሌጅ ተማሪና ምሩቅ ሁሉ ከኢህአዴግ ጋር ወግኖ ክልሉን ለማስተዳደር የዘመተበትን ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮለታል። በዚህም የተነሳ የክልል አስተዳደሮች ከምርጫው በሁዋላ እንዲሻሻሉ ሳይረዳ አልቀረም። የበረከት ወግ አንድም ስለዚህ ትንፍሽ የሚል ባይሆንም፣ ከተገኘው ጥቅም አኳያ ሲታይ በዜጎችና ሃገር አንድነት ላይ የደረሰው ጉዳት ያመዝን እንደሆን መገመት ከባድ አይመስለኝም። በመተካካት ሂደት ለመገለል ዝግጁ የሆነው በረከት፣ ስለዚህ ጠባሳ በዝርዝር እንኳ ሊያወራን ባይፈቅድ፣ ይህ ስልጣንን ለመከላከል ሲባል የተወሰደ እኩይ ተግባር ህሊናውን የሚከነክነው መሆኑን እንኳ ቢያጋራን በተገባ ነበር ። ምናልባት ዝምታው ከፓርቲው መስመር ጋር አለመስማማቱን ጠቋሚ ይሆን ይሆናል።

የበረከት ወግ ስለ ህብረት ድርጅት መሪዎች ክህደት ብዙ መረጃዎችን ያቀርባል። ስለዝርዝር ጉዳዩ የማውቀው ብዙ ባይኖርም፣ መረራና በየነ በዚያን ወቅት ለወሰዱት ተገቢ ያልሆነ እርምጃ (ከህብረት መሪነታቸው አኳያ ሲታይ ማለቴ ነው) መንስኤው የሚመስለው ከእነበረከት ጋር የሚጋሩት ‹‹የነፍጠኛ ፍርሃት›› ነው። የቅንጅት ጠንካራ የህዝብ ድጋፍ ያስደነገጠው ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚነት የተሰለፉትንም ብሄርተኞችም ጭምር ስለነበር፣ እነበየነ ለወሰዱት እርምጃ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። ስለሆነም ቅንጅት ከሚጠናከር የኢህአዴግ አገዛዝ ቢቀጥል የተሻለ መሆኑን አምነው የወሰዱት እርምጃ ነበር። በተመሳሳይ መንገድም እዚህ ዳያስፖራ አካባቢ ያሉ ህብረ ብሄር ድርጅቶችን ዛሬም አንዱ የሚፈትናቸው ጉዳይ ኦነግን በተቃዋሚው ህብረት ውስጥ የማሰለፍ ጥያቄ ነው። ችግሩ ግን የኦነግ መሪዎችም ሆኑ ሌሎች ብሄርተኞች ለነርሱ ሙሉ ለሙሉ የሚመቻቸው ህብረት ካላገኙ፣ የኦሮሚያ በኦህዴድ መተዳደር የሚያንገበግባቸው ጉዳይ አለመሆኑን ነው። የኦነግ መሪዎች ሌሎቹ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች አካባቢ የሚያዩት ጥድፊያ ምክንያቱ ጨርሶ አይገባቸውም። በነሱ ዕምነት እስካሁን በተገኙት ድሎች ላይ መገንባት እንጂ፣ ወደኋላ የሚመልስ ስምምነት ከሚደረግ ኢህአዴግ ዝንተ አለሙን ቢገዛ ይመርጣሉ። በድህረ ምርጫ 97ም የበየነና መረራም አስተያየት ተመሳሳይ የነበረ ይመስለኛል።

የኢህአዴግ ሟርት

በረከት ወደ 2002 ምርጫ ከመሸጋገሩ በፊት የ1997ን ምርጫ ከኬንያ ጋር በማወዳደር ‹‹ኢህአዴግና ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ የአስተዳደር ስርአቱ እስካሉ ድረስ ፣ የኬንያው አይነት የብሄር ብሄረሰብ መጨፋጨፍ ፣ እልቂትና መፈናቀል በኢትዮጵያ የሚመጣበት ዕድል በአያሌው ተዘግቷል›› ይለናል። አሜን ብለን ሃተታችንን በጨረስን በወደድን ነበር። ሆኖም ከዚሁ ‹‹ኢህአዴግ እስካለ የብሄር ብሄረሰብ መጨፋጨፍ አይኖርም›› የሚል የስልጣን መከላከያ ሟርት ምን ያህል የኢህአዴግን መሪዎች ደም ስር ሰርስሮ የገባ እንደሆን እንይ። ‹‹ከጎረቤትህ አንድ የዚህ ብሄር ሰው ግደል የሚል አደገኛ መልዕክት አልበቃ ብሎ አደገኛው ጥሪ እንደገና በሌላ ቡና አትጣጡ፣ ለቅሶ አትዳርሱ፣ አብራችሁ ቀብር አትቋቋሙ… በሚል ተጨማሪ ጥሪ ተጠናከረ ›› ብሎ ያወጋናል በረከት ቅንጅትን ሲከስ። እንግዲህ የቴክስት መልዕክቶችን መነሻ ለመለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ‹‹አክራሪዎቹ ኒዎ ሊበራሎችና የቀለም አብዮተኞች›› የሰጡት ለኢህአዴግ መንግስት ነው። መልዕክቱ የቅንጅት ቢሆን ኖሮ በረከት ላኪውን እጅ ከፍንጅ አቅርቦ እንዴት ከቅንጅት መመሪያ እንደተሰጠው ያጋልጠው ነበር። ሆኖም የ‹‹ኢንተርሃምዌ›› ክስ ጀማሪው ራሱ ኢህአዴግ በመሆኑ፣ ‹‹ከጎረቤትህ አንድ የዚህ ብሄር ሰው ግደል›› የሚል መልዕክት የላከው በሚያዚያ 30 ቀን ሰልፍ ትልቅነትና በአዲሰ አበባ ምርጫ ውጤት የተደናገጠው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ተገቢ ነው። ከሚያዚያ 30 ሰልፍ በሁዋላም ሐሙስ ማታ በተደረጉት የሻማ ማብራት ምሽቶች ኢህአዴግ ‹‹ነፍጠኞች መጡብህ›› ወደሚል ማስፈራራት መረማመዱ የሚያሳየው፣ በቴክስት መልዕክት አማካይነት የዘር ግጭት የመቀስቀስ ፍላጎት ስለነበረው ሊሆን እንደሚችል ነው። ባይሆንማ ለምን የዘረኛውን ቴክስት ስልክ ባለቤት ሳያቀርብልን ቀረ? በረከት ይህን ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሊጠቀምበት ከመፈለግ ባሻገር ከላይ ለተነሱት ጥቆማዎች መልስ ሳይሰጠን ማለፍን መርጧል።

ኢህአዴግ ‹‹እኛ ስልጣን ላይ ከሌለን ሃገሪቱ ትበታተናለች›› ብሎ ጠዋት ማታ የሚያላዝን ፓርቲ ስለሆነ፣ 17 አመታት ገደል ቧጥጦ፣ በአሜባ ተቅማጥ አምጦ፣ ጥሬ ቆርጥሞ፣ ያለመጫሚያ በባዶ እግሩ የደጀን ተራራን ዘልቆ፣ ከ60 ሺህ በላይ ታጋዮቹን መስዋዕት አድርጎ ያገኘውን መንግስታዊ ስልጣን ‹‹ሃገር ለሚበታትኑ›› ‹‹ነፍጠኞች›› አስረክቦ እንዲገለል አይጠበቅበትም። ጥያቄው ግን በማ ስሌት ነው ስልጣን ከኢህአዴግ ከወጣች ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚል ሟርት የተሰላው የሚለው ነው፡፡ የአንድ ቡድን ስልጣን ጊዜያዊ፣ ሃገርና ህዝብ ግን ቋሚ ናቸው። በተለይ ደራሲው ለልጆቹ በላከው መቅድም ‹‹ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር ተመችቷችሁና እንደ ሰው ተከብራችሁ የምትኖሩባት ሃገር እንድትኖራችሁ›› ብሎ እየተመኘ፣ የኔ ቡድን በስልጣን ላይ ከሌለ ሃገሪቷ ትበታተናለች እያለ ሲያሟርት ስንሰማው ምን አይነት የታመመ አንጎል ነው ይህን ፅልመት የሚጋርደው፣ ይህን መጸልም የሚያበቅለው ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በዚሁ የኢህአዴግ ሟርትም የተነሳ ዘወትር የሚምል የሚገዘትበት ዴሞክራሲ ባዶ ፊሽካ መሆኑም ገሃድ ይወጣል። በምርጫ ስም ስልጣኑን ለሃገር በታኞች አሳልፎ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ ስለማይኖር ለህዝቡም ድምፅ ራሱን ተገዢ ማድረግ አይቻለውም። የተሳሳተንም ህዝብ ማረቅ በኢህአዴግ የተጀመረ አዲስ ግኝት አይደለም። የኢህአዴግ አምሳያ ሲሪያ ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት የሚያደርገውም ያንኑ ነው። የተሳሳተን ህዝብ መቅጣት።

ቅንጅትን በአመፅ ካንበረከከ በኋላ በረከት በሰላም ይተኛል ብዬ ስጠብቅ እብሪቱ እየናረ መጣ ፡፡ በመፅሀፉ መጀመሪያ ላይ ‹‹ታማኝ ተቃዋሚ›› ባለመኖሩ ሃገራችን መጎዳቷን ያስተዛዘነን ደራሲ፣ በቅንጅት ላይ በወሰደው አመፅ የራዱትን ሰላማዊ ተቃዋሚዎች መሳለቂያ አደረጋቸው። ‹‹ከቅንጅት ኢዴፓ፣ ከሌላው የተቃዋሚ ድርጅት ደግሞ ህብረትና ኦፌዴን መስከረም ላይ የተሰመረው ቀይ መስመር የምር እንደሆነ ተገንዝበው አቤት ወዴት ሲሉ ሰንብተዋል›› በማለት ያንቋሽሻቸዋል። ከልደቱ የተሻለ ታማኝ ተቃዋሚ አንዲት ሃገር እንዴት ልታበቅል እንደምትችል ግር የሚል ነው። በረከት በማከታተልም ‹‹ሁለቱም ወገኖች ፀጋዬ ገብረመድህን እሳት ወይ አበባ በሚለው የግጥም መድበሉ በተሰለምላሚነት የገለፃትን ቢራቢሮ ያስንቃሉና ›› በማለት ይለቀልቃቸዋል። የልደቱን ‹‹መድሎት›› መጽሀፍ አንብቦ የ2002 ክርክሩን ላደመጠ፣ ‹‹በሁለት ምርጫዎች ወግ›› ውስጥ ልደቱ የተሳለበትን ካራ ላየ፣ በረከትና ኢህአዴግ ታማኝ ተቃዋሚ ሳይሆን የሚፈልጉት፣ ምንም አይነት የተለየ ሃሳብ ያለው ዜጋ የማይኖርበት ሃገር መሆኑን ነው። ይህ የበሽታ ነው።

የጤንነት ጉዳይ ከተነሳ አይቀር፣ ከድህረ ምርጫ 97 በሁዋላ ‹‹በረከት አእምሮውን አሞት ለህክምና ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደ›› የሚል ወሬ ስሰማ፣ ባንድ በኩል በደረሰበት ህመም ባዝንም በሌላ ወገን ግን ያመመው አእምሮውን በመሆኑ ደስተኛ ነበርኩ። ‹‹የኔ ወንድም ህሊና ስላለው ነው የታመመው – በድህረ ምርጫው ብካይ ልቦናው ስለተሰበረ›› እያልኩ ነበር ቅርበታችንን ለሚያውቁ ሁሉ የማወራው። የነሽብሬ ሞት ሰቅጥጦታል፣ የ196ቱ እልቂት እንቅልፍ ነስቶታል ብዬ በማመን። ሆኖም በሁለት ምርጫዎች ወግ ውስጥ ያንን በረከት ፈልጌ አላገኘሁትም። ምናልባት ለጊዜው ለጤናው ፋታ ለማግኘት ተበዳዩ ላይ ማላከክ የሚጠቅም ሆኖ አግኝቶት ይሆናል። ዕውነተኛው መድህን ግን ከይቅርታ መጠየቅና ከይቅርታ ማድረግ ይመነጫል። ከጡረታ ጋር ፋታ ሲገኝ በረከት እዚያ ላይ ይደርስ ይሆናል እንዳልል፣ ጡረታ ለጨዋነትና ሃቅ ራሱን እንደማያበድር የኮሎኔል መንግስቱ ወግ ተስፋ ስላስቆረጠኝ እምብዛም ብሩሃዊ ልሆን አልተቻለኝም።

በረከት ለጊዜው እንኳንስ ለማያውቃቸው ተቃዋሚዎች፣ ራሱ ኮትኩቶ ላሳደጋቸው የገበሬ ልጆች እንኳ ጭካኔን ማሳየት መርጧል። በእስር ላይ ሰለሚገኙት ስለእነ ጄኔራል ኣሳምነው ሲያወጋን ‹‹ጄኔራሎቹ የድሮ ታጋዮች ነበሩ። ከነርሱ ጋር ከታሰሩት መካከልም በርከት ያሉ የድሮ ታጋዮች ይገኙበታል። ከነዚህም የቀድሞ ታጋዮች ውስጥ አንዳንዶቹ በፀረ-ደርግ ትግል ወቅት በጥሩ ተዋጊነትና አዋጊነታቸው የሚታወቁ ነበሩ። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜም እንደዚሁ ጥሩ የአዋጊነት ሚና የተጫወቱ ናቸው…ይህም ሆኖ እንደ ጄኔራል ተፈራ ማሞ ዐይነቶቹ ከምርጫ 97 በሁዋላ የትምክህት አስተሳሰብ በማቀንቀን የተለየ አቅጣጫን መከተል መርጠው ነበር›› ይለናል። በረከትን በአካል ባገኘው፣ ለምን ጓዴ እንዲህ ዐይነት ጭካኔ ውስጥ ትዘፈቃለህ? እንዴት ለወንድምህ ለካሳሁን የገባኸውን ቃል አጥፈህ ፣ ካሳሁን ኢትዮጵያንና ህዝቧን በመውደዱ ‹‹ከትግራይ ውጣ አንተ ትምክህተኛ›› ተብሎ መረሸኑን እያወቅክ እንዴት ከተራ ታጋይነት ተነስተው ለጄኔራልነት ማዕረግ በበቁ ጀግኖች ላይ የትምክህተኝነት ውንጀላ ታካሂዳለህ? ወግህን ከመጀመርህ በፊት ለወንድም ካሳሁን የገባኸውን ቃል እንኳ ለ254 ገፆች መጠበቅ እንዴት ያቅትሃል? ልቤን ሰብረኸዋል። በእጅጉ አዝኜብሃለሁ። ጭካኔህ ወሰን አጣ። ናፍቆቴን መልስልኝ እለው ነበር። ለናፍቆቴ የሚመጥን የጥንቱን የጠዋቱን፣ ዐይኖቹ የሚስቁትን በረከትን ፈልጌ ላገኘው አልቻልኩም። በ16 አመታት የትጥቅ ትግልና በ20 አመታት ስልጣንን የመከላከል ትግል እንዳልነበር ሆኖ ተደምስሷል። እጅጉኑ አዝናለሁ።

ማሳረጊያ

ለእኔ እንደሚገባኝ የአንድ ፓርቲ ብስለት (ማቹሪቲ) ሊለካ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ ከውስጡ የወጡ መሪዎችና አባላት በተቃዋሚው ጎራ ውስጥም ተቀባይነትና ተፈላጊነት ሲኖራቸው ነው። የኢህአዴግ አመራር አባላት በሄዱበት ሁሉ ከታች መፈተንና መጣራት ሳይኖርባቸው ከላይ አመራሩ ውስጥ በቀጥታ የሚገቡበት ሁኔታ መፈጠር ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ያሳደጋቸው እሴቶች ተፈላጊነት ያላቸው ለመሆኑ የሚመሰክሩ ይመስሉኛል። ዛሬ ስዬ፣ ነጋሶ፣ አውአሎም፣ ገብሩ፣ አዳነች፣ በዳያስፖራ ደግሞ በሪሁ ወዘተ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ናቸው። መቼም የትግራይ ብሄርተኝነት ጠንሳሾቹ እነዚህ በመሆናቸው በእርግጥ ኢህአዴግን የሚያባንነው የትግሬዎች ደህንነት ከሆነ፣ ከርሱ ይበልጥ ስሱ መሆናቸውን በትግላቸው ያረጋገጡ ሰዎች ተቃዋሚ ሃይሉን ስለሚመሩ፣ ከምንጊዜም በበለጠ ኢህአዴግ ገላውን መስደድ ነበረበት። የበረከት ወግ ግን ያንን መረጋጋት አያሳየንም። በነስዬ ስለሚመራው መድረክ እንዲህ ይለናል ‹‹መድረክ ከተደራጀ በሁዋላ የድርጅቱ መሪዎች ትልቁ ስራ የቅንጅትን መፅሀፍ ማንበብና በጂን ሻርፕ ንድፈ ሃሳብ ማስታጠቅ ሆነ›› ይለናል። የጂን ሻርፕ ‹‹ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ›› ለምንና እንዴት የቅንጅት እንዳልነበረ አቅርቤአለሁ። በረከት የጂን ሻርፕን መፅሀፍ ከመድረክ ጋር የሚያስተሳሰረው አለምክንያት አይደለም። መድረክ ለህዝብ አመፅ እንደማይሰራ ምርጫ 2002 በብቃት መስክሮለታል። ሆኖም ለበረከት ያ በቂ አልሆንም። የስዬ ለትምህርት ወደ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መምጣትና የጂን ሻርፕም ሃርቫርድ መገኘት እንደከነከነው ግልፅ ነው። ‹‹አክራሪ ኒዮ ሊበራሊስቶች›› ስዬን በሰላማዊ አመጽ ንድፈ ሃሳብ አስታጥቀው ሊልኩብን ነው ብሎ እንቅልፍ አጥቷል። ስለሆነም ከአሁኑ መድረክን ማጥላለት የግድ ሆኖበታል።

ከ97 ምርጫ ጥቂት ወራት በሁዋላ የኦነጉ ዮሃንስ ለታ ኖርዌይ ላይ ለቀድሞ የኦነገ፣ ህወሃትና፣ ኢህዴን መሪዎች የሃሳብ መለዋወጫ መድረክ አዘጋጀልንና ተገናኝተን ነበር። ታዲያ ስብሰባው ላይ ላገኘሁዋቸው ለገብሩ አስራትና የማነ ጃማይካ፣ ውጪ በተናጠል ፣ መለስ በልብ ድካም ቢሞት ማን የሚተካው ይመስላችኋል ብዬ ጠየቅኳቸው። ጃማይካ በረከት ሲል፣ ገብሩ አዲሱ ብለው መለሱልኝ። ይሄ እንግዲህ ከስድት አመታት በፊት ነበር። ዛሬ አዲሱ በጡረታ ተገልሏል፣ በረከትም የመውጫው በር ዳፋ ላይ ተገትሯል። አሜሪካኖቹም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ለዐይን የሚሞላ ሰው ሊያገኙ ስላልቻሉ (የሃይለማርያም ደሳለኝ ተኪነት ስላጠራጠራቸው) አማራጭ እያዘጋጁ ሊሆን ይችላል። ሰራዊቱ ያውቀዋል፣ ጄኔራሎቹ ይቀበሉታል፣ ስለሆነም እስቲ ቀረብ አድርገን እናጥናው እርሱም የተሻለ ይወቀን ብለው ሊሆን ይችላል ስዬን ወደ ሃርቫርድ ያስመጡት። በረከት እንደገመተው ግን በጂን ሻርፕ ጠበል ለማጥመቅ አይመስለኝም።

በረከትና ፓርቲው አንድ ከምርጫ 97ሊማሩ የሚገባቸው ነገር፣ በአመጽ ሃይል አሸናፊ ሆነው መውጣታቸውንና፣ ይህም አመፅ የፈጠረላቸው የፖለቲካ ሽግሽግ በመኖሩም ጭምር፣ በተቃዋሚው መድረክና በኢህአዴግ መካከል ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ነው። ይህን ልዩ አጋጣሚ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ‹‹መድረክ የቅንጅትን የአመፅ መጽሀፍ ማንበብ ጀመረ›› ወደሚል ጥርጣሬና ክስ ከተረማመዱ ግን የሚፈሩትን የቀለም አብዮት ያቃርቡታል።