በሽብር ወንጀል የተከሰሱት ኤልያስ ክፍሌና ጋዜጠኞች ጥፋተኛ ተባሉ
ሪፖርተር — ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብር ድርጊት ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል በሽብር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ኤልያስ ክፍሌ፣ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌና ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ ጥር 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን አራት ክሶች፣ ያቀረባቸውን የሰዎችና የሰነድ ማስረጃዎች ተከሳሾቹ ካቀረቧቸው የሰውና የሰነድ መከላከያ ማስረጃዎች ከሕጉ ድንጋጌ ጋር በመመርመር የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያስተላለፈው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረውና በአገር ውስጥ ሆነው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ባሉት የመኢዴአፓ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፣ በአውራምባ ታይምስ ምክትል አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌ፣ ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የሰጡትን የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤቱ በንባብ አስታውሷል፡፡
በሌለበት ክስ በተመሠረተበትና ጥፋተኛ በተባለው ኤልያስ ክፍሌ የፋይናንስ ድጋፍ ሰጪነት፣ አስተባባሪነት፣ በህቡዕ ተደራጅተው ጥቃት ለማድረስ የሽብር ቅስቀሳ ለማድረግ ‹‹በቃ፣ መለስ በቃ›› የሚል ጽሑፍ በቀይ ቀለም በአዲስ አበባ በተለያዩ ሥፍራዎች በተለይ አቶ ዘሪሁን በመረጣቸው ቦታዎች መጻፋቸውንና መመስከራቸውን ገልጿል፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸትና ርዕዮት ዓለሙ ፎቶግራፍ በማንሳት ለኤልያስ ክፍሌ መላካቸውን፣ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለመጻፍ ጸሐፊዎችን በመመልመልና ከኤልያስ ክፍሌ ጋር በመገናኘት የተለያዩ ትዕዛዞችን እንደተቀበሉ ምስክሮቹ መመስከራቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
አቶ ዘሪሁን ባቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ መሆናቸውን፣ ገንዘብ ከውጭ የተላከላቸው ከዘመድ መሆኑን፣ ገንዘቡንም ለፓርቲ ሥራና ለግል መጠቀሚያ ማዋላቸውን፣ በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ፈቃድ ጠይቀው መከልከላቸውን በሰውና በሰነድ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬም ገንዘብ ተልኮለት ለአባቱ የሕክምና ወጪ ማዋሉን፣ ጋዜጠኛ መሆኑንና የብተና ፖለቲካ በሚል በሚሠራበት ጋዜጣ ላይ ትችት ማቅረቡን ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡
ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና የመከላከያ ምስክሮችን የምስክርነት ቃልና የሰነድ ማስረጃዎች ከሕጉ አግባብ ጋር በመመርመር ‹‹በቃ መለስ፣ በቃ›› የሚል ጽሑፍ ለመጻፍ መስማማታቸውን፣ ፎቶ አስነስተው መላካቸውን፣ በኢንተርኔት የተለያዩ ጽሑፎችን መጻጻፋቸውን፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ያስረዱ መሆኑንና ተከሳሾች ያቀረቡት መከላከያ ምስክርና ማስረጃ የሽብር ወንጀሉን ለመፈጸም የሚያስችላቸው አለመሆኑን ባለማስረዳታቸው፣ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ የሽብር ወንጀሉን ለመፈጸም ማሴራቸውንና ማቀዳቸውን የሚያስረዳ በመሆኑ፣ በሽብርተኛ ሕጉ 652/2001 አንቀጽ 4 መሠረት ጥፋተኛ መሆናቸውን በንባብ አሰምቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ በአንደኛው፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ክስ ሁሉም ተከሳሾች ጥፋተኛ ሲባሉ፣ ኤልያስ ክፍሌ በአራተኛ ክስ ማለትም የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነው ከኤርትራ መንግሥት ጋር በማበር የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመጣል ከሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን የሰበሰበውን ገንዘብ የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈጸም ለማድረግ በስውር በመላኩ በድጋሚ ጥፋተኛ ተብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርዱን ከሰጠ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ፣ ሁሉም ተከሳሾች በሠሩት ተደራራቢ ወንጀል ቅጣቱ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2002 ዓ.ም. በወጣው የቅጣት ማንዋልና በወንጀል ሕጉ እጅግ ከብዶ እንዲቀጡ ጠይቋል፡፡
የአቶ ዘሪሁን፣ የጋዜጠኛ ውብሸትና የሂሩት ክፍሌ ተከላካይ ጠበቃ፣ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ፣ ወንጀሉ የተፈጸመው በሕግ የተፈቀዱ ተግባራትን ማለትም የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሩ፣ ጋዜጠኛ ሆነው ማኅበራዊ ለውጥን ሲፈልጉ ወሰን ስላለፉ እንጂ፣ በአፍቅሮተ ነዋይ ተጠምደው ወራዳነትን ያልፈጸሙ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪ ድርጊቱ ፍጻሜ ሳያገኝ በሙከራ የቀረ በመሆኑ፣ በተለይ ዘሪሁንና ውብሸት ከዚህ በፊት በሌላ ወንጀል ተከሰው የማያውቁ በመሆናቸውና ሪከርድም ስላልቀረበባቸው፣ ሂሩት ክፍሌ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባት ተደራራቢ የወንጀል ድርጊት ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 67 አንፃር እንዲመዘንላት አቶ ደርበው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ሁሉም ተከሳሾች የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን፣ በእስራት ቢቀጡ ቤተሰቦቻቸው የማኅበረሰቡ ሸክም እንደሚሆኑ በመጥቀስ ቅጣቱ በቅጣት ማንዋሉ የተቀመጠው በዝቅተኛ ደረጃ እንዲሆንላቸው፣ ከባድ ሆኖ የሚወሰነው ከባድ ጥፋት ላደረሱ ወንጀለኞች መሆኑን፣ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከቅጣት ማኑዋሉ ጋር በተቀራረበ ጊዜ ስለወጣ በወንጀል ሕጉ መሠረት እንዲወሰንላቸው ጠይቀዋል፡፡ እስራት ከተወሰነባቸው ደግሞ በገደብ እንዲያዝላቸው ወይም በገንዘብ እንዲለወጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው የቅጣት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡
የጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ጠበቃ፣ ጠበቃ ሞላ ዘገዬ ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ፣ ርዕዮት አስተማሪና ጋዜጠኛ መሆኗን ገልጸው፣ ተፈጸመ በተባለው ድርጊት ውስጥ የገባችው አስቀድማ አስባ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ሳይሆን፣ በጋዜጠኛነቷ የተፈጸመ መሆኑንና ከእሷ ሐሳብ ውጭ በሆነ በእግረ መንገድ የተፈጸመ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ተከሳና ተወቅሳ የማታውቅ፣ በአካባቢዋም ሆነ በመሥሪያ ቤቷ በፀባይዋ የተመሰገነች መሆኗን፣ ፍርድ ቤቱ ወጣትነቷን ከግምት ውስጥ አስገብቶ በእስር ከምትቆይ ለኅብረተሰቡ የምትሰጠውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ ቅጣቱ እጅግ በጣም ቀሎና በቅጣት ማንዋሉ ዝቅተኛው ተብሎ እንዲወሰንላቸውና ቢቻል በገንዘብ እንዲቀየርላት በመጠየቅ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የቤተሰብ ኃላፊ ናቸው የተባሉትን ጥፋተኞች ከቅጣት ውሳኔ በፊት ማስረጃ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡