“እኔ ከታሰርኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይታሰራሉ!?”

አቤ ቶክቻው

“እያሱ በርሄን ያላየ ኦሞት… ይሄዳል ወደ ሞት!” (አድማጭ ተመልካቹ)

ቆይማ አንዴ…ነገሩን ላልሰማችሁት ወዳጆቼ ከስረ መሰረቱ ለማስጨበጥ ሙከራ ላድርግ! ምን ሆነ መሰልዎ…? በጋምቤላ ክልል አንድ ሹም አሉ። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው። አቶ ኦሞት ኦቦንግ ይባላሉ። ሹምየው በ1996 ዓ.ም ያኔ የፖሊስ ኮሚሽነር እያሉ የክልሉ ፖሊስ ሆዬ ከፌደራሉ ፖሊስ ጋር በመተባበር፤ በአኝዋክ ወንድሞቻችን ላይ “ዘግናኝ” የተባለ ጭፍጨፋ አካሂዶ ነበር። እንደውም፤ ምነው እንኳ የሆነ ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሱዳኑ ጋሽ አልበሽር “በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለዛውም በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊከሰሱ ነው” ተብሎ በሀገር ምድሩ ሲወራ፣ እኛም ስናንሾካሹከው አልነበር? ታድያኮ አንዱም ክስ ይሄ ነበር።

(ቆይማ እዝች ጋ አንድ ጨዋታ መጣች። በስንተኛው ግዜ እንደሆን እንጃ፤ ሼክ መሃመድ አላሙዲን ሆዬ የኢትዮጵያ ሪቪው ድህረ ገፅ አዘጋጁን ኤልያስ ክፍሌን በስም ማጥፋት ወንጀል እከሰዋለሁ ብለው “ያዙኝ ልቀቁኝ” ሲሉ አንድ ወዳጃችን ሰምቶ ምን አላቸው መሰልዎ “አረ ሼኩ “ሼም” ነው ጓደኛዎ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀሙ እርሶ በስም ማጥፋት ሰው ሲከሱ ነውር አይደለም እንዴ?” ብሏቸው ሲያበቃ “እናቱ ውሃ ልትቀዳ የሄደችበትና እናቱ የሞተችበት እኩል ያለቅሳሉ!” የሚለውን ተረትም ተርቶባቸው ነበር።) ታድያልዎ ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ጀግንነቱን በተለያየ ግዜ በምስኪኑ ህዝብ ላይ አሳይቶ አይደል? እ…! በጋምቤላም የተፈፀመው የዚሁ አካል ነበር። በወቅቱ በርካታ የአኝዋክ ህዝቦች ተገድለዋል ቆስለዋል ተሰደዋል። ይህ ከሆነ አሁን ዘጠኝ አመት ሞላው።

እንዳልኩዎት ያን ግዜ አቶ ኦሞት ሆዬ ፖሊስ ኮሚሽነር ነበሩ። ታድያልዎ አሁንለታ ከአለቆቻቸው ጋር ግምገማ ተቀምጠውልዎት ሳለ እኒህ የቀድሞው ፖሊስ ኮሚሽነር የዛሬው የክልል ፕሬዘዳንት፤ በግምገማው በርካታ ክስ መጣባቸው። “አንደኛ ብቃትህ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሁለተኛ ወደ ሰማኒያ ሚሊዮን ብር በሚደርስ ገንዘብ ሙስና ውስጥ እንደተዘፈቅህ ማስረጃዎች ያሳብቃሉ፣ (በቅንፍ፤ ልብ አድርጉልኝ ይሄ ማለት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንድ አንድ ብር መውሰድ እንደማለት ነው። አሁንም በዛው ቅንፍ፤ ልብ አድርጉ ይሄ ገንዘብ ማለት የጠቅላይ ሚኒስሩ ቤት ለመገንባት ይፈጃል ተብሎ የተገመተው ነው… እኔ የምለው ጠቅላያችን ይሄ ቤት ግንባታቸው እንዴት አድርጓቸው ይሆን? አሁንስ አሳዘኑኝ ስንቱን ነገር ገንብተው ይችሉታል? አቅማቸውን ይገነባሉ፣ መልካም ገፅታቸውን ይገነባሉ፣ ቤተመንግስታቸውን ይገነባሉ… እግዜር ይሁናቸው ልላቸው ነበር… “የቱ እግዜር!” ብለው እንዳይቆጡኝ ፈራሁ!) በሶስተኛውም ክስ አቶ ኦሞት ሆዬ የዛሬ ዘጠኝ አመት ለተገደሉት የአኝዋክ ህዝቦች ተጠያቂ ነህ? ተባሉትና እርፍ ! ታድያ እሳቸውስ ምናቸው ሞኝ ነው… ሁሉንም በሆዳቸው ቻል አድርገው፤ “ብቃቱንም ልጣ… ገንዘቡንም ልዘረፍ…” (ሳይሉ አይቀሩም) “…ነገር ግን በአኝዋክ ህዝቦች ግድያ ከተጠየቅሁ መለስም መጠየቅ አለበት መሳሪያ እና ወታደር ብቻ ሳይሆን ትዕዛዝም የሰጠኝ እርሱ ነው! ማን ገብቶ ማን ይቀራል!” ብለው ቢናገሩ የገምጋሚዎች አይን መፍጠጥ…! “እዚህ ላይ ነው ጉዱ!” አይሉልኝም?

ውይ ወዳጄ ሰላምም ሳልልዎ ቀጥታ ወደ “ገደለው” ገባሁኝ አይደል…? ለማካካሽ ይሆን ዘንድ በአዲስ መስመር ሰላምታዬን እጀምራለሁ።

እንዴት ሰነበቱልኝ… አንበሳዬ? ገናው እንዴት አለፈ? አሁን ደግሞ ጥምቀት መጥቶልዎታል። እንዴት ሊቀበሉት አቅደዋል? እሰይ ብርችንችን ማድረግ ነው እንጂ… ለማን ደስ ይበለው ብለው አመት ባልን የመሰለ ነገር አንገትዎን ዝቅ አድርገው ያሳልፉታል? የፈለገ ቢከፋዎትም የፈለገ ኑሮ ጣራ ቢነካብዎትም አመትባሉ እንዴት ነው? ሲባሉ ቢያከብሩትም ባያከብሩትም፤ ጮክ ብለው “አሸወይና ነው!” ብለው ይመልሱ። በሆድዎም “ምቀኛን ደስ አይበለው!” ይበሉ። እውነቴን ነው የምልዎ ወዳጄ ከመንግስቴ የተማርኩት ትልቁ ቁምነገር የፈለገ ችጋር ቢመጣ የፈለገ ርሃብ ቢጠናወተኝ ፊትን በቫዚልን አውዝቶ ጥጋበኛ መስሎ መታየት ነው።

ለገና አንድ ዶሮ መቶ ሰማኒያ ብር መሸጡን ወዳጆቼ ነገሩኝ። አንዳንድ አጋኖ አዳሪዎችማ “ዘንድሮ ዶሮ ዋጋው የሚቀመስ ስላልሆነ በኪራይ ነበር!” ብለውኛል። ዶሮ በኪራይ እንዴት መሰልዎ…? ልክ ፊልም ቤት ሄደው ፊልም እንደሚከራዩት ማለት ነው። ከባለ ዶሮው ዘንድ ሄደው ገንዘብ ያስይዙ እና ከቤትዎ ይወስዱታል። ታድያ ምቀኛ ጎረቤት ደስ እንዳይለው የማረድ ሙከራ ያደርጋሉ። የዘንድሮ ዶሮ ደግሞ ለጩሀት ማን ብሎት ያንቋርርልዎታል። ከዛ ጎረቤትዎም “አይ አጅሬ ዘንድሮም አረደ!” ብሎ ያደንቅዎታል። እርስዎ ታድያ ዶሮውን በበቂ ሁኔታ ካስጮሁ በዋላ ደበቅ አድርገው ለባለቤቱ መልሰው ያስያዙትን ገንዘብ ይቀበላሉ። ታድያ በአጋጣሚ ሆኖ፣ ወይም ቀኑ ደርሶ፣ ወይም ከተከራይ ብዛት ዶሮው እጅዎ ላይ ክልትው ካለ፤ ያስያዙት ገንዘብ ይወረሳል… “እና ገናን በዚህ መልኩ ያሰለፉ ብዙ አሉ” እያሉ አጋናኞች ያወራሉ። ያውሩ! ይልቅስ ብልህ የሆነ ሰው ከዚህ ግነት ውስጥ የራሱን የስራ ፈጠራ አክሎበት ወደ ተግባር ቢቀይረው በአመቱ “ሚሊኒየነር አከራይቶ አደር” ብሎ መንግስት ሊሸልመው ይችላል። እና ልብ ያለው ልብ ይበል!

ለጥምቀት ደግሞ ሎሚ ስንት ይገባ ይሆን? የሎሚ ደግሞ ክፋቱ፤ ሲወረወር ወይ ሊስት ይችላል፣ ወይ ደግሞ ልጅት ፊት ልትነሳ ትችላለች… ታድያ በዚያ ግርግር ያንኑ ሎሚ ድጋሚ አንስቶ መውርወር ይከብዳል። ስለዚህ እንደ ዘዴ አሰቢያለሁ ሎሚውን በሆነ ነገር ማሰር… እናም የገመዱን ጫፍ ይዞ መወርወር “የወረወሩላቸው ደንበኛ አይመልሱም እባክዎ ሌላ አማራጭ ይሞክሩ” የሚል ምልክት ሲመጣ ገመዷን ጎተት አድርጎ ደግሞ መሞከር… “ችግር በቅቤ ያስበላል!” አሉ የሞላላቸው።

እኔ የምለው ነጋዴ “ፍሬንዶቻችን” ግን ለምን እንዲህ ታስጨንቁናላችሁ? በየሰበባ ሰበቡ ዋጋ እየጨመራችሁ ስለምን የደም ግፊታችንን ትጨምሩታላችሁ? የሚገርመው፤ ደም እንኳ የለንም እኮ… አስቡት እስቲ ደም የሌለው ሰው ደም ግፊቱ ሲጨምር… ባዶ የደም ቧንቧችን ተነፋፍቶ ስም ያልወጣለት አዲስ በሽታ ለምን ታመጡብናላችሁ? አረ እንተዛዘን ጎበዝ!

የኔ ነገር አንድ ወሬ ከጀመርኩኝ ማቆሚያም የለኝ…! አረ በጅማሪያችን ስላነሳነው ጉዳይ እንቀጥል እስቲ…

እናልዎ የጋምቤላው ርዕሰ መስተዳድር ሆዬ “እኔ ከታሰርኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አብረውኝ ይገቧታል!” ብለው ገምጋሚዎቹን አላስደነገጧቸውም መሰልዎ…! የአቶ ኦሞት ኦቦንግን ንግግር የሰሙ አንዳንድ ወዳጆቻችን “እያሱ በርሄን ያላየ ኦሞት… ይሄዳል ወደ ሞት!” ብለው ተርተውባቸዋል አሉ።

ትዝ አይልዎትም ወዳጄ ባለፈው ሰሞን “በኢቲቪ የሚመጡ ህመሞችን ይከላከላል” የተባለው ኢሳት ቴሌቪዥን ስለ ኢያሱ በርሄ አሟሟት የዘገበውን… ምነው እንኳ ሟች በአጓጉል ወንጀል ተጠርጥሮ… (በማጨበርበር ብዬ ብናገር ሙት ወቃሽ ያስብለኛል ብዬ ነው) ታድያ ያኔ በተያዘ ግዜ “ይሄንን ወንጀል የሰራሁት ከአዜብ መስፍን ጋር ነው! እኔ ከተጠየቅሁ እርሷም መጠየቅ አለባት…” ብሎ ማለቱ ሲሰማ አይደለም እንዴ… ወይዘሮዋ “ቆይ ልቀቁልኝ እኔ እነደሚሆን አደርገዋለሁ!” ብለው ከእስር ካስለቀቁት በኋላ… በአንዱ ቀን ከደማቅ ኪነት መልስ ያለ ኑዛዜ ፀጥ ያደረጉት…? ወይ ታጋይ መሆን! ማለት ይሄኔ ነው።

ታድያ ዛሬም አቶ ኦሞት “እኔ ከታሰርኩ መለስም ይታሰራታል!” ሲሉ ተናግረዋል። በርግጥ በሀይማኖት የበቁ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ “ሰውየውን ያናገራቸው መንፈስ ቅዱስ ነው!” ባይ ናቸው። ምክንያቱም ንግግራቸው አቶ መለስንም ሆነ ራሳቸውን ለመክሰስ ጥሩ ማስረጃ ስለሚሆን ነው። የምር ግን ይህንን ንግግር አንዳች መንፈስ አናግሯቸው ይሆናል እንጂ በወቅቱ በተደረገው “ማጣራት” ጠቡ የእርስ በርስ ነው ተብሎ እኛም አምነን እየኖርን ነበርኮ!

ታድያ ዛሬ “እኔ ከተጠየቅሁ መለስም ይጠየቃል ትዕዛዝ የሰጠኝ እርሱ ነው…” ብሎ ማስፎገር ከየት የመጣ ነው? የሚገርመው አቶ ኦሞት መጀመሪያ በግምገማው ሳብያ ከክልሉ ፕሬዘደንትነታቸው እንዲነሱ ከተወሰነ በኋላ ድጋሚ ወደ በመንበረ ስልጣናቸው እንዲቆዩ ተደርጓል። ታድያ አስተያየት ሰጪ በሞላበት ሀገር ጆሯችንን ጣል ብናደርግ ይህንን ሰማን… “ቀዳማዊ እመቤታችን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ከተሞክሯቸው አካፍለዋቸዋል አሉ!”

ይሄኔ ነው “ኢያሱ በርሄን ያላያ ኦሞት… ይሄዳል ወደ ሞት” ሲሉ መተረታቸው! እንግዲህ እኛም እንፀልያላቸዋለን አቶ ኦሞት እንደስራዎ ይስጥዎት!

የጋምቤላ ነገር ሰሞኑን ጣጣዋ በዝቶ ወሬዋም ደርቶ ሰንብቷል። ሂውማን ራይት ዎችም አንድ ሪፖርቱ ላይ በስፋት ዳሷታል።

በነገራችን ላይ ሂውማን ራይትና ኢህአዴግ በቃ እንደተጣሉ ቀሩ ማለት ነው? (ቆይ ቆይ ምን ነካኝ… ሳላውቀው አሽሙር ተናገርኩ እኮ… ሂውማን ራይት ዎች እና ኢህአዴግ እንደተጣሉ ቀሩ ማለት ነው? በሚለው ይሰተካከልልኝ።) ቅንጅትን የሸመገሉት ሽማግሌዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ሽምግልና ቢጀምሩ ጥሩ ይመስለኛል? አሃ… ለካስ ሽማግሌዎቹ ሽምግልና አላዋጣ ብሏቸው ቢዝነሳቸውን ቀይረዋል ለካ… (እናንተ ሳቄ መጣ!) የኔ ነገር መረጃ እኮ ቶሎ ቶሎ ማግኘት እየተቸገርኩ ነው ይሄኔ እኮ እኔ እዚህ ያስታራቂ ያለ እያልኩ ስል መንግስት በፓርላማው ሂውማን ራይት ዎችን አሸባሪ ድርጅት ብሎት ይሆናልኮ…!

የሆነ ሆኖ ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ወደ ሰባ ሺህ የሚጠጉ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች በግዳቸው ሰፈራ ሂዱ ተብለው እየተሰቃዩ መሆኑን አትቷል። የሰፋሪዎቹ መሬት እየተቸበቸበች መሆኑንን ደግሞ ቀድሞውኑም መነጋገሪያ ሆኗል። ይህንን ዜና አብሮኝ ሲሰማ የነበረ አንድ ወዳጄ ግራ ግብት ብሎት ጠየቀኝ “ኢህአዴግ ካለፈው ስህተት የተማረ መንግስት መሆኑን በተደጋጋሚ ይነገራል? ታድያ ምነው ያለፈው ደርግ ሲሰራ የነበረውን ሁሉ ይሰራል?” አለኝ። የምርም የግዳጅ ሰፈራን እያነሳ እሳቱ መንግስታችን በተደጋጋሚ ደርግን ሲወቅስ እኔም ሰምቼ አውቃለሁ። በሆዴ እውነት ካለፈው እንዴት አንማርም? ብዬ ሳስብ፤ አንዱ “ጎበዝ… ደርግ አልፏል እንዴ?” ሲል ጠየቀን። ይቺ ጥያቄ የዶክተር ነጋሶን “አሁን አሁንስ መንግስቱ ሃይለማሪያምን መሰልከኝ!” የምተለዋን ንግግር ታስታውሳለች። እውነት ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ፍቅር ብቻ ነው የሚጎድላቸው እንጂ ከመንጌ በምን ያንሳሉ!? “ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ወደፊት!” ስላልተባለላቸው ነው? እኛ አድናቂዎቻቸው እንለዋለና! ከመንጌማ አናሳንሳቸውም (ያቺ ትምህርተ ስላቅ ለኔ ሲሏት ነው አይደል የምትጠፋው?)

በመጨረሻም
ኢቲቪ

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ በስካይ ባስ ወደ ጎንደር ሲሄድ አውቶብሱ ላይ በደረሰ አሰቃቂ አደጋ አርባ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ እርሱ በታምሩ መትረፉን ፌስ ቡክ ላይ ለጥፎልን ተደንቀናል። እውነቱን ለመናገር የደረሰው አደጋ በጣም አሳዛኝ ነው…! ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ።

አሁን ወደ ኢቲቪ ልዙር… ኢቲቪዎች ናፍቃችሁኛል… እኔ የምለው…? በኢቲቪ ፊት ሰው ሁሉ እኩል የሚሆነው መቼ ነው? አረ ሰው ይታዘባል፣ አረ ታሪክ ይወቅሳል፣ አረ ህሊና ይሞግታል… በስካይ ባስም በሰላም ባስም የሞተ እኩል የሚታይበት ግዜ እንዲመጣ ምን ይደረግ…? ተዉ ኢቲቪዎች ተዉ!!!

ወዳጄ ይበሉ እስቲ ያሰናብቱኝ…

አማን ያሰንብተን!