የፍኖት ጋዜጣ ርእስ አንቀጽ – መደማመጥ፣ መሰብሰብና ወደ ሕዝቡ መዉረድ የገባል !

ሀገራችን ኢትዮጵያ ረጅም የመንግስትና የፖለቲካ ታሪክ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የምትመደብ ናት፡፡ ይችው እድሜ ጠገብ ውድ ሀገራችን መንግስት በማቋቋም፣ በስልጣኔ በንግድና ሉዓላዊነቷን በመጠበቅ ፈር ቀዳጅ ከሆኑ ጥንታዊ ሀገሮች የምትመደብ ቢሆንም ቀዳሚነቷን አስጠብቃ መጓዝ ግን አልቻለችም፡፡

ኢትዮጵያችን በድህነትና በኋላቀርነት፣ እንዲሁም በበሽታና በእርዛት መታወቅ መቻሏ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በቁጭት የሚያንገበግብ፤ የእኛ ባህሪ የሆነውን አይነኬነት የሚፈትንና እልህ የሚያስይዝ ጉዳይ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ከሌሎች ሀገራት ፈጥነን ጀምረን ቀዳሚ የሆንባቸው ጉዳዮች በርካታ ቢሆኑም ፖለቲካችን በተመለከተ ግን የሚጠበቅብንን ያህል በበጎ መልኩ አልተጓዝንም፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የዓለማችን ሀገሮች በመንደር አለቃ፣ በጐሳ መሪና በሀገር ሽማግሌ በሚተዳደሩበት ጊዜ ከሦስት ሺ ዓመት በፊት ጀምሮ መንግስት መስርታ በንጉስ ወይም በንግስት የምትተዳደርና ከዚያም አልፎ የተፈሩና የተከበሩ መሪዎች የነበሯትም ሀገር ነበረች፡፡ እንዳጀማመሯ ግን አልቀጠለችም፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ አስተማሪ ሊባል የሚችል ስርዓት መፍጠር በተገባት ነበር፡፡ ነገር ግን በፖለቲካውም ከፊተኛው ረድፉ እንዳልነበርን ሁሉ ትናንት የጀመሩ ሀገሮች ወደፊት ሲገሰግሱ እኛ ግን ቁልቁል መውረዱን ተያይዘነዋል፡፡ ግን አሁንም አረፈደም፤ አቀበቱን ተሎ ወጥተን፣ ቁልቁለቱን ወርደን ከፊተኞች ተርታ መመደብ ይቻላል፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገን መደማመጥ፣ መከባበር፣መስማማት፣ መቆጨትና ቅንነት ናቸው፡፡

እንደሚታወቀው “በቁጭት ተወለድኩ” የሚለው ኢህአዴግ የንጉስነቱን በትረስልጣን ሲጨብጥ ወደ ኋላ የቀረውንና በመጯጯህ የተሞላውን፤ እንዲሁም በሴራ፣ በመጠላለፍና በፍረጃ የሚታወቀውን ፖለቲካችንን ከቁጭቱ በመነሳት ያስተካክለዋል የሚል ተስፋ ነበር፡፡ነገር ግን የባለፉትን 20 ዓመታት የገዥው ፓርቲ ጉዞ ስንገመግም አርቲስቱ እንዳለው “አዲስ ንጉስ እንጅ ለውጥ እንዳልመጣ” በግልፅ እንገነዘባለን፡፡ ከምር የሆነና ስርነቀል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡

በእርግጥም “ዴሞክራሲያዊና የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እገነባለሁ” ያለው ኢህአዴግ ራሱን ወደ አንድ ፓርቲ ስርዓት (One party system) እያሳደገና የሴራና የፍርጃ ፖለቲካውን እያሳበጠ ቢሄድም የዚችን ሀገር ቀዳሚ ዝና ለመመለስ ግን ብቃት አላገኘም፡፡ ሊያገኝም አይችልም፡፡ የዚችን ሀገር ሁለገብ ችግር ለመቅረፍ ከተፈለገ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን፡፡ በብዙ ሺ ዴሞክራሲ ናፋቂዎች ደም ወደ ስልጣን የመጣው ገዥው ፓርቲ ዓላማውን ቢዘነጋም በሀገር ጉዳይ “ምናገባኝ” አይባልምና ሀላፊነት አለብን፡፡

ሀገራችንን እንደ በፊቱ በብዙ ዘርፍ ኋላቀር መሆኗ አክትሞ ወደ ፊተኛው ረድፍ እንድትመጣና ፍትሃዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሰረት ተቃዋሚ ነን የምንል ሁሉ ሃላፊነት አለብን፡፡ ሃላፊነታችን ካልተወጣን ደግሞ ውሎ አድሮ ከተጠያቂነት አናመልጥም፡፡ እየሰራን ያለነው በሀገር ጉዳይ ላይ ነውና፡፡ ተቃዋሚ ስንል ደግሞ ዛሬ ዛሬ መልሱ ብዙ ሆኗል፡፡ የምርጫ ቦርድ ድህረ ገፅ እንደሚያመለክተው ገዥውን ፓርቲ እንቃወማለን ብለው የምስክር ወረቀት የወሰዱ ከ76 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ቢሮ ከፍተውና ተደራጅተው ወደ ህዝብ ወርደው እየሰሩ ያሉ ስንቶች እንደሆኑ ሚዛናዊ ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የምንተወው ይሆናል፡፡ አብዛኞቹ የወረቀት ላይ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ምርጫ ሲደርስ የተጨማደደ ሱፋቸውን ተኩሰው ምርጫ ለማሟሟቅ የሚሰለፉ ናቸው፡፡ ይህንን የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብም የራሱን ደረጃ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሄውም ሀቀኛ ተቃዋሚ፣ ተለጣፊ ተቃዋሚና የምርጫ ጊዜ ተቃዋሚ የሚሉ ናቸው፡፡

ከዚህ በኋላ መቀለዱ የሚበቃ ይመስለናል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ በላይ የሚገነግንበት እድል መስጠትም አይገባንም፡፡ የተጠናከረ የተቃዋሚ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ የዳበረ ክንድ ያስፈልገናል፡፡ ይሄ ኃይል የሚፈጠረው ደግሞ በሀቀኛ የተቃውሞ ረድፍ የተሰለፉ ሃይሎች ሲሰባሰቡ ነው፡፡ይሄ ማለት ምርጫ ሲደርስ መሰባሰብና ከምርጫ በኋላ መበታተን የሚቆጨን ከሆነ ተሰባስበን ቁም ነገር የምንሠራበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ የሕዝብን ሕሊና ማቁሰል መቆም አለበት ብለን እናምናለን፡፡ የህዝቡን ምክር መስማትም ጠቃሚ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ተዳክሞ በራሱ ጊዜ እስከሚወድቅ መጠበቅ የለብንም፡፡ የሀገራችን ህልውና እያንዳንዱን ዜጋ ሊያሣስበው ይገባል፡፡ በኑሮ ውድነት፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በመንደር ከድሬዎች እየታመሰ የቁም ሲቃይ ለሚያየው ወገናችን ልንደርስለት ይገባናል፡፡

ህዝቡ “ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” እያለ ነው፡፡ እውነት አለው፡፡ መተባበርና መሰባሰብ ከዚያም ወደ ህዝብ መውረድ ይገባናል፡፡ መሰባበር የሚገባውም መሰባበር አለበት፡፡ በተለይ በተቃዋሚ ስም የሚቀልዱና ምርጫ ሲደርስ ብቻ ብቅ ብለው ገዥው ፓርቲ ሲጠራቸው“አቤት? ሲልካቸው ወዴት?” የሚሉ የወረቀት ላይ ፓርቲዎች መሰባበርና መክሰም አለባቸው፡፡ በህዝብ ትግል ላይ መቀለድ ይበቃል፡፡

አሁን የምንደማመጥበት፣ የምንሰባሰብበትና ወደ ህዝብ የምንወርድበት ጊዜ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ ለዚች ደሃ ሀገርና ለዚህ ባለታሪክ ህዝብ ከምር እንታገላለን ለሚሉ ሁሉ ሁልጊዜም በሩ ክፍት ነው፡፡ አንድነት የፈረጠመ ክንድ ያለው ተቃዋሚ እንዲፈጠር አበክሮ ይሰራል፡፡ ጊዜው የመሰባሰብ ነው በማለትም ጥሪውን ያስተላልፉል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብም የሀገሩ ጉዳይ ያገባዋል፡፡ ስለዚህም በመሰባሰብ፣ በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በመስማማት የሁላችንን ኢትዮጵያ እንፍጠር፡፡ ይህ የምንጊዜም ጥሪያችን ነው፡፡

የፍኖት ነጻነት ጋዜጣ በተሳምንቱ በአንድነት ለዲሞርካሲና ለፍትህ ፓርቲ የምትታተም ጋዜጣ ናት። ጋዜጣው በብዛት እንዲታተም ፣ በስፋት በየክልሎቹ እንዲሰራጭ እርዳታዎትን የአንድነት ፓርቲ ይጠይቃል።
የፍኖት ጋዜጣ እትም 24ን በሙሉ ለማንበብ ክለዚህ ይጫኑ !