ዘጠኝ የመድረክ አመራር አባላት በሽብር ወንጀል ተከሰሱ
(ሪፖርተር) — የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሥራ አስፈጻሚ አባልና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ በቀለ ገርባና የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦሕኮ) የፓርቲ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኦልባና ለሊሳን ጨምሮ ዘጠኝ ግለሰቦች፣ በሽብር ወንጀል ተሳትፎ ተጠርጥረው ታህሳስ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 1 ቀን 2004 ዓ.ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ ከትናንት በስቲያ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋ መምህር፣ የኦፌዴን ምክትል ሊቀመንበርና የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ የፓርቲ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ አቶ ወልቤካ ለሚ (ኩማ ቀቢ)፣ አደም ቡሳ፣ ሀዋ ዋቆ፣ መሐመድ መሉ፣ ደረጀ ከተማ፣ አዲሱ ሞክሪና ገልገሎ ጉፋ ይባላሉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) (ለ)፣ 38 እና 241ን በመተላለፍ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ውስጥ ታጣቂ አባል መሆናቸውን የክስ ቻርዱ ይገልጻል፡፡ ኬንያ ሶለሎ ጎልቦ በሚባል ቦታ ሥልጠና ወስደዋል፤ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ የኦነግን የሽብር ተልዕኮ ለማስፈጸም መንቀሳቀሳቸውን ክሱ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ዓቃቤ ሕግ አቶ በቀለ ገርባ የኦፌዴን ፓርቲን ሽፋን በማድረግ ወጣቶችን በማደራጀትና በመመልመል፣ ለኦነግ በህቡዕ እንዲሠሩ በማድረግ፣ በጥር ወር 2002 ዓ.ም በአምቦ ከተማ ኦነግ በቅርቡ አሸንፎ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ በመግለጽና ‹‹ከኦነግ ጎን ቆመን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መጣል አለብን›› በማለት መመርያ በመስጠት፣ በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም ተማሪዎችንና ሕዝቡን ለአመፅና ለብጥብጥ እንዲነሱ ቅስቀሳ እንዲደረግ መመርያ በመስጠትና መምህርነታቸውን ሽፋን በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጽሑፍ ሊሰጧቸው የሚመጡትን ተማሪዎች ‹‹በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በሰላማዊ ትግል ማውረድ አዋጭ አይደለም፤ በኃይል ከሥልጣን ማውረድ አለብን፤›› በማለት መመርያ መስጠታቸውን በክስ ቻርጁ አመልክቷል፡፡
አቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ ሕጋዊ ፓርቲን (ኦሕኮ) ሽፋን በማድረግ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በአምቦ ከተማ ወጣቶችን በመሰብሰብ ‹‹ምርጫው ስላልተሳካልን›› በማለት በመንግሥት ላይ ረብሻ እንዲያነሳ ትዕዛዝ በመስጠት፣ በህቡዕ ለኦነግ አባልነት በመመልመል፣ በአምቦ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ንብረቶች እንዲወድሙ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ አቶ ኦልባና ቀኑ ባልታወቀበት ሰኔ 2003 ዓ.ም ምርጫ 2002 ስላልተሳካ በ2004 ዓ.ም በመላው ኦሮሚያ አመፅና ብጥብጥ እንዲነሳ ለማድረግ አባላትን በማደራጀት፣ በማሳተፍ፣ አባላትን በኦሕኮ ከለላ አዲስ አበባ በመጥራት፣ ‹‹ይኼንን መንግሥት በኃይልና በትጥቅ ትግል መናድ አለብን፤›› በማለትና በኦሕኮ ስም የኦነግን ተልዕኮ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡
ቀሪዎቹም ሰባት ተከሳሾች የኦነግ አባል በመሆን በምዕራብ አርሲ ኮፈሌ ወረዳ በህቡዕ በመንቀሳቀስ ተማሪዎች እንዲረብሹ በማስተባበር፣ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና ኬንያ ሰላሎ በመሄድ በኦነግ ካድሬዎች መሠልጠናቸውን ክሱ በዝርዝር አስፍሯል፡፡
ከዘጠኙ ተጠርጣሪ ተከሳሾች መካከል አምስተኛ ተከሳሽ ሀዋ ዋቆ ሴት ስትሆን፣ እ.ኤ.አ በ2006 ኬንያ ማንዴራ የተባለ ቦታ በመሄድ የኦነግ የፖለቲካና ወታደራዊ ሥልጠና መውሰዷን፣ የኦነግ አባል መሆኗን፣ ኬንያ ሞያሌ ቡትዬ በተባለ ቦታ ሆና የኦነግ አባላትን ስትመለምልና ወደ ኬንያ ስትልክና እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ የሽብር ተልዕኮውን ለማሳካት ስትንቀሳቀስ እንደነበር፣ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ውስጥ የተሀድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ እያለች የኬንያ ስልክ መስመር አውጥታ ለሚሠለጥኑት አባላት በመስጠት ኦነግን በአዲስ ሁኔታ ለማደራጀት ስትንቀሳቀስ እንደነበረች የዓቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር ይገልጻል፡፡ ደረጀ ከተማ የተባለውም ተጠርጣሪ የኦሕኮ አባልነቱን ከለላ በማድረግ በህቡዕ ለኦነግ አባላትን ሲመለምል እንደነበር፣ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጊኒር እንዲሄዱ በማድረግና የሽብር ተልዕኮውን ለማሳካት ከኦነግ ታጣቂ ቡድን ጋር በድብቅ በመገናኘት ሲሳተፍ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በኦልባና፣ በደረጃና በገልገሎ ላይ ሁለት ሁለት ክሶችን የመሠረተ ሲሆን፣ መሣሪያዎችን ደብቆ በመገኘት፣ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የጋራ ጠላትን አብሮ መፋለም የወቅቱ ጥያቄና የታሪክ ግዴታ ነው፤ በጠመንጃ እናስወግደዋለን፤›› ብለው በመቀስቀስ፣ የሥራ ዕቅድና የወጣቶች ስምሪት ተግባራትን በማስቀመጥና በሦስት ደረጃ በመከፋፈል፣ በማዘጋጀትና ከኦነግ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት ውሳኔ በመስጠት መሳተፋቸውን ክሶቹ ያብራራሉ፡፡
ሁሉም ተጠርጣሪ ተከሳሾች የኦነግን የሽብር ተልዕኮ ለማሳካት የቅስቀሳ ጽሑፎችን በማስተላለፍ የተንቀሳቀሱ በመሆኑ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃላቸው ክሱን እንደማይቃወሙ፣ ድርጊቱን ግን እንዳልፈጸሙ አስረድተዋል፡፡ ሦስተኛና ስድስተኛ ተከሳሾች ግን ክሱንም ድርጊቱንም ተቃውመዋል፡፡
አቶ በቀለ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ የኦሮሞ ሕዝብ እየተበደለና እየተገፋ ያለ ሕዝብ ነው ብለው ስለሚያምኑ ለውጥ እንዲመጣለት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ኦልባና በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ እሳቸው የታሰሩት ለአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ልዑክ መረጃ ሰጥተዋል በሚል መሆኑንና ሌላ ምንም የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከትናንት በስቲያና በትናንትናው ዕለት ዘጠኝ፣ ዘጠኝ በድምሩ 18 የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን የሰማ ሲሆን፣ ምስክርነታቸውን የሰጡት መስካሪዎች ተጠርጣሪዎቹ ለኦነግ አባልነት እንደመለመሏቸው፣ ሥልጠና መውሰዳቸውንና ከኦነግ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት አስረድተው፣ በመጨረሻም የኦነግ ዓላማ የኦሮሞ ሕዝቦችን የሚያስጨርስ መሆኑ ስለገባቸው ከአባልነት ትተው የወጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከፊሎቹ ምስክሮች የተጠርጣሪዎቹ ቤት ሲበረበር በታዛቢነት የተገኙ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀሪ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማትና በኤግዚቢትነት የተያዙና ከክሱ ጋር ያልተያያዙ ሰነዶች ካሉ ተያይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ለጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡