ኦነግና ኢትዮጵያዊነት – ምላሽ ለዶር ብርሃኑ ክፍል 3-ግርማ ካሳ

[email protected]

ዶር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዙሪያ ለአንባቢያ ያቀረብኳቸው ሁለት መጣጥፍት ከፍተኛ የአንባቢያን አስተያየቶችን እንደጫሩ ለማየት ችያለሁ። የድጋፍም ሆነ የተቃዉሞ ኤሜሎች በብዛት የደረሱኝ ሲሆን፣ በአቡጊዳ ድህረ ገጽ ላይ የቀረቡ አሰትያየቶች ከወትሮ እጅግ የበዙ ነበሩ ።

በጽሑፌ ቅር የተሰኙ ፣ ለምን ቅር እንደተሰኙ በአግባቡ ለመግለጽ ያልቻሉ፣ ያቀረብኳቸዉን ነጥቦች ትክክል እንዳልሆኑ ለማሳመን የራሳቸዉን መከራከሪያ ያላቀረቡ፣ ሃሳቤን በነጻ የመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብቴን እንዲሁ በደፈናዉ ተጋፍተዉ የስድብ ዉርዥብኝ ያወረዱብኝም ጥቂቶች አይደሉም።


የስድብ ፖለቲካ የትም አያደርሰንም !

ከቀረቡልኝ አስተያየቶች መካከል በአንድ በኩል ያሳቀኝን፣ በሌላ በኩል ግን ያሳዘነኝ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በአቡጊዳ የለጠፈዉን አስተያየት ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ። የሁለት ወያኔዎች ወግ በሚል ነበር አስተያየቱ የተሰጠዉ።

–ሰማህ!
..ምኑን?
–አንድ ግርማ ካሳ የተባለ ሰው በኢንተርነት ብርሃኑ ነጋን ደህና አድርጎ አገባለት
..እንዴት እባክህ?
– “ሰላማዊ ትግል አይሰራም እያለ ይዘባርቃል፤ በሶስት አመት ግንቦት7 የፈየደው ነገር የለም …ምናምን” እያለ…
..ወግ አይቀር– ”ምን ይዞ ጉዞ አለ” አማራ ሲተርት–ደርግን ለመጣል ስንት አመት እንደወሰደብን አያውቅም ማለት ነው? እንዲሁ እርስ በርስ ሲበላሉ አይደለም ሶስት አመት አይደለም ሰላሳ አመት የትም አያደርሳቸው
–ይልኩንስ እኔ የደወልኩልህ ነገሩ ወዲህ ነው
..እንዴት ማለት!
–እነዚህ ተቃዋሚ ተብዬዎች ተስፋ ሲቆርጡና ወደ እኛ ጠጋ ጠጋ ማለት ሲፈልጉ፣ የራሳቸውን ሰውና ግሩፕ በአደባባይ ድባቅ ማግባትን ይመርጣሉ–የግርማ ካሳም ጽሁፍ ይዘት ይህን ይመስላል–ሰለሞን ተካልኝን ታስታውሰው የለ?
..i understand perfectly! ይህን ካልክሰ የጌታ ክርስቶስ ልደት የሚከበርበት ቀን ደርስዋል–የገና ስቶጣ መሆኑ ነው! አሃሃሃ!!!
–ስለሆነም እንዲህ አይነቱ ወላዋይ በጣም ይጠቅመናል–በዚያ ላይ ቦታ ቢሰጠውና ትንሽ ብር ብናስታቅፈው ግንቦት ሰባትን ገትሮ ይይዝልናል ብዬ አምናለሁ
..እርግጠኛ ነህ? ይህ ሰው ለመንበርከክ ተዘጋጅቷዋል?
–እንዴታ! ፈርቶ ነዉ እንጂ ልቡ ከእኛ ጋር ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ወያኔ በሩን ከከፈተልን ለመወያየት ዝግጁ ነን ብሎ በብእሩ አሰፍርዋል።
..ታዲያ ምን ትጠብቃለሀ! አስገባዋ! በሩ ክፍት ነው በለው–እንደተለመደው የተራረፈንን እንወረወርለታለን!!”

በመጀመሪያ ላነሳ የምፈልገዉ ነጥብ ቢኖር ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ እኛ የኢትዮጵያዊያን (በተለይም በዉጭ አገር ያለን) ያሉንን ልዩነቶች አቻችለን፣ እንደ ጨዋ፣ በሰለጠነ መልኩ መነጋገር አለመቻላችን ነዉ። ከኛ የተለየ አስተያየት አንድ ሰው ስለሰጠ፣ እኛ የምንደግፈዉን ድርጅት አንድ ሰዉ ስለተቃወመ፣ ያንን ሰው እንደ ጠላት የማየት ዝንባሌ አለን። ማንም ዜጋ ሃሳቡን በነጻነት የመግልጽ መብት ያለው ይመስለኛል። ሰዎች ከፈለጉ የኢሕአዴግ ደጋፊ የመሆን ሙሉ መብት አላቸዉ። ኢሕአዴግን ስለደገፉ የሚሰደቡበት ምንም ምክንያት የለም።
ይልቅስ የሰለጠነዉ ፖለቲካ የምንቃወማቸዉን መስደብና ማዋረድ ሳይሆን የምንቃወማቸዉን አሳምነን ወደ እኛ ማምጣት ነዉ። ፈረንጆች the power of persuasion ይሉታል።

የተቃዋሚ ድህረ ገጾች ተሃድሶ ያስፈልጋቸዋል

ሌላዉ ላነሳ የምፈልገዉ ነጥብ የተቃዋሚ ድህረ ገጾችን በተመለከተ ነዉ። ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵሜዲያ «ግርማ ካሳ የወያኔ ፕሮፖጋንዲስት ነዉ» ሲል ክስ ማቅረቡ ይታወቃል። የዶር ብርሃኑ ነጋን የኢሳት ቃለ መጠይቅ ኢካዴፍ፣ አዲስ ድምጽ፣ ኢትዮሜዲያ እና ቋጠሮ ድህረ ገጾች አዉጥተዉት አይቻለሁ። ዶር ብርሃኑ በኢሳት ለሰጡት ቃለ መጠይቅ ያሉኝን አስተያየቶች፣ እነዚህን ድህረ ገጾች ጨምሮ፣ ለበርካታ ሜዲያ ግሩፖች ልኪያለሁ። ነገር ግን ከአቡጊዳና ከኢትዮጵያ ዛሬ በስተቀር እንደ ኢትዮሜዲያ ያሉ ታዋቂ ድህረ ገጾች አስተያየቴን ሊያስተናግዱ ፍቃደኛ አልሆኑም። በሌላ አባባል ነጻ የሃሳቦች መሸራሸርን እያገዱ ነዉ ማለት ነዉ። በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አቶ መለስንና ድርጅታቸዉን መቃወም እንደማይቻል፣ በነዚህ ድህረ ገጾችም እንደነዶር ብርሃኑ ነጋ ያሉ የተቃዋሚ መሪዎችን ለሚናገሩትና ለሚሰሩት ስራ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም።

ፌስቡክ፣ ትዊተር ፣ ነጻ ብሎጎች በሽ በሽ በሆነበት ዘመን፣ ሃሳብን ለሕዝብ ማሰራጨት ከመቼዉም የበለጠ ቀላል እንደሆነ ሁላችንም የምንዘነጋዉ አይመስለኝም። እንደ ኢትዮጵያዊ ሃሳባችንን በነጻ እንዳንገልጽ ፣ እነዚህ ድህረ ገጾች ፣ እገዳ ቢያደርጉም፣ ሃሳብችንን ከመግልጽ ለአገራችን ያለንን አስተዋጾ ከማድረግ የሚከለክለን ምንም ነገር እንደሌለ መቼም የሚታወቅ ይመስለኛል።

ነገር ግን ይህን የምጽፈዉ እነዚህ ለዲሞክራሲ ቆመናል የሚሉ ድህረ ገጾች እራሳቸዉን እንዲመረምሩ ነዉ። ለዲሞክራሲ መቆም የሚጀመረዉ ከራስ ነዉ። እኛ የማናደርገዉን ነገር ሌሎች እንዲያደርጉ መጠበቅ የለብንም። እኛ ሳንሱር እያደረግን ፣ ከኛ የተለያ አስተያየት ያላቸዉን ዜጎች ወያኔ ሆዳም ብለን እየሰደብን፣ እኛ መስማት የምንፈልገዉን አስተያየቶች ብቻ እያስተናገድን፣ ለዴሞክራሲ ቆመናል ማለቱ ትንሽ የሚያሰኬድ አይመስለኝም።

በጣም የሚገርመዉ ደግሞ እነዚህ ስድብና ወገዛ የሚያበዙ ወገኖች እነርሱን አገር ወዳድ ሌሎቻችን ኢትዮጵያ ለማፍረስ የተነሳን የኢትዮጵያ ጠላቶች፣ እነርሱን ታጋይ፣ ሌሎቻችንን ለሰላምና ለዴሞክራሲ የሚደረገዉን ትግል ለመጉዳት የተሰማራን አድርገዉ ማቅረባቸዉ ነዉ።

እዉነት እንነጋገር ከተባለ፣ በተቃዋሚዉ ጎራ የሚታየዉ ይህ አይነት ያለመቻቻልና የመሰዳደብ ፖለቲካ ነዉ ከምንም በላይ ትግሉን እየጎዳዉ ያለዉ። የተማሩ ዜጎች፣ ለአገራቸዉ አስተዋጾ ማድረግ የሚፈልጉ፣ በፖለቲካ አስተሳሰባቸዉ እንጭጭ በሆኑ ላላመሰድ ሲሉ፣ በራቸዉን ዘግተው ከትግሉ የሸሹ ብዙ ናቸዉ። እንግዲህ ይህ የዜጎች ከትግሉ መሸሽ ነዉ ትግሉን ክፉኛ የሚጎዳዉ። ነጻ፣ ዲሞክራሲያዊ ዉይይቶችን ማድረግ እንደዉም የበለጠ እንድንግባባ የሚያደርግ ትግሉንመ የሚጠቅም ነዉ። የሚያሳዝነዉ በርካታ የሜዲያ ወገኖቻችን ይህን መረዳት አለመቻላቸዉ ነዉ።

ሁላችንም ቆም ብለን በረጋ መንፈስ ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። አቶ መለስ ላይ መጀመሪያ ከማነጣጠር በፊት እራሳችን ላይ ማነጣጠር አለብን። በተቃዋሚ ወገን ነን የምንል ሁሉ፣ ስር ነቀል የአስተሳሰብ ለዉጦች ማድርግ ይኖርብናል። ከጥላቻ፣ ከእልህ፣ ከስድብ ፖለቲካ ወጥተን ዜጎችን የማቀራረብ፣ በኢሕአዴግ ካምፕ ያሉትን ሳይቀር ወደ ዴሞክራሲዉ ካምፕ የማምጣት፣ የሚያዋጣና የሰለጠ ፖለቲካ ማራምድ መጀመር ይኖርበናል።

የኦነግ ዉሳኔ ኢትዮጵያዊነት ማሸነፉን ያሳል !

ዶር ብርሃኑ ነጋ በኢሳት ቴሌቭዥን በቀረቡበት ጊዜ ከተጠየቋቸዉ በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ከኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ጋር ድርጅታቸዉ ግንቦት ሰባት ስላለዉ ግንኙነት ነዉ። ሁሉም የተቃዋሚ ኃይሎች ኦነግን ጨምሮ፣ በአንድ ላይ መሰባሰብ እንዳለባቸዉ ዶክተሩ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ከኦነግ አንጃዎች ጋር በሙሉ እየተነጋገሩ የኦነግ አንጃዎችንም ለማስማማት እየሞከሩ እንደሆነም ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ከጥቂት ቀናት በፊት በጀኔራል ገልቺ የሚመራዉ የኦነግ ቡድን የኢትዮጵያን አንድነት ተቀብሎ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ለመታገል መወሰኑን ይፋ አድርጓል። በአንጻሩም ደግሞ በዳዎድ ኢብሳ የሚመራዉ የኦነግ ቡድን ባወጣዉ መግለጫ «የኦሮሞ ጥያቄ ከሌላው ሕዝብ ጥያቄ የተለየ ነዉ» በሚል ዘረኛና ከፋፋይ ምክንያት የነጄነራል ገልቺን ቡድን ሲያወግዝ የግንቦት 7 ድርጅትን « የኦነግን ለመድ የለበሱ ጥቂቶች » ሲል ከሷል።

አብዛኛዉ የኦነግ አባላትን ያቅፋል የሚባለዉ የጀነራል ገልቺ ቡድን በይፋ ኢትዮጵያዊነትን ማወጁ በርግጥ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ሊያስደስት የሚገባ ትልቅ ዜና ነዉ። ይህን ስል ኦነግ ትልቅ ነገር ያመጣል በሚል አይደለም። ኦነግ ኤርትራ ወይንም አሜሪካ ተቀምጦ፣ ትግሉን በአገር ቤት በሪሞት ኮንትሮል ሊመራ አይችልም። ኦነግ ምናልባት ከግንቦት ሰባትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በዉጭ አገር አንድ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ስብስብ ቢፈጥርም፣ ትግሉ አገር ቤት ነዉና፣ በአገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ጋር እስካላበረ ወይንም አገር ዉስጥ ገብቶ እስካልታገለ ድረስ ብዙም የሚያመጣዉ ለዉጥ አይኖርም።

ነገር ግን ፖለቲካዉን ነዉ ማየት ያለብን። የኦነግ ኢትዮጵያዊንትን መቀበል፣ በምርጫ ዘጠና ሰባት ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነትን በመምረጡ የተመታዉ፣ በመድረክ ምስረታ የተዘረረዉ የሕወሃት/ኢሕአዴግ የዘር ፖለቲካ፣ የበለጠ ድባቅ እንደገባ ነዉ ያሳየዉ። ኢትዮጵያዉያን በዘር በሃይማኖት እንደማይከፋፈሉ በድጋሚ እንዲረጋገጥ ነዉ ያደረገዉ። ለ19 አመታት በሕዝብ ጫና ላይ በጉልበት የተዘረጋዉ የአቶ መለስ ዜናዊ የኋላቀር ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ መሸነፉን፣ ኢትዮጵያዊነትም ማየሉን ነዉ ያወጀዉ።

በኦነግ የአቋም ለዉጥ የግንቦት ሰባት ሚና

እነጀኔራል ገልቺ ከአራት አመታት በፊት ከነዳዎድ ኢብሳ ሲለዩ ፣ በይፋ አልወጡም እንጂ፣ ዉስጥ ዉስጡን ፣ «ኢትዮጵያዊያን ነን፤ ከተቀሩት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ጋር አብረን መስራት አለብን» ይሉ እንደነበረ፣ ከነዳዎድ ኢብሳ ጋር የተለያዩበት ዋናዉ ምክንያትም ይሄ እንደነበረ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ።

ለዚህም ነዉ እነጄነራል ገልቺ ወደ ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ኦነግ እንዲመጡ ሲያደርጉ፣ ግንቦት ስባት አስተዋጽኦ አደረገ ብዬ የማላምነዉ። ነገር ግን እነጀነራል ገልቺ፣ በዉስጥ የሚያራምዱትን አቋም በይፋ እንዲያወጡ በማድረጉ አንጻር፣ ግንቦት ሰባት ጉልህ ሚና የተጫወተ ይመስለኛል። ለዚህም መመስገን አለባቸው ባይ ነኝ። ትልቅ ነገር ነዉ ያደረጉት።

ከግንቦት ሰባት አብዛኞቹ የአመራር አባላት ጋር ትውውቅ አለኝ። ዶር ብርሃኑ ነጋ ቅንጅትን ወክለዉ በቺካጎ ባደረጉት ስብሰባ፣ የስብሰባዉ ሞደሬተር ነበርኩኝ። ቃሊት እሥር ቤት ታስረዉ በነበረ ጊዜ የተሸጠዉን ትምህርት ሰጪ መጽሃፋቸዉን፣ በቺካጎ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከፋፋል ያደረኩት እኔ ነኝ። ስለሰላማዊ ትግል ይናገሩት የነበረዉ ሁሉ፣ ልብን የሚስብና የሚማርክ ነበር። ትዝ ይለኛል አንድ ቀን ያሉት፣ «እነርሱ (ኢሕአዴጎች) መሳሪያ አላቸዉ። ሊገድሉን ይችላሉ። እኛም የራሳችን ሽጉጥ አለን፤ ፍቅር የሚባል» ነበር ያሉት።

ዶር ብርሃኑ የሰላማዊ ትግል መሪ በነበሩት ጊዜ በጥቂት አመታት ዉስጥ ትልቅ አስተዋጾ ያደረጉ ሰው ናቸዉ። በብዙዎች ዘንድ ዶር ብርሃኑ አሁን ያላቸው ፍቅርና ከበሬታ፣ በግንቦት ሰባት መሪነታቸው ያገኙት ሳይሆን በቅንጅት መሪነታቸዉ፣ በሰላማዊ ትግል ባስመዘገቡት ዉጤት፣ ያገኙት ነዉ። የግንቦት ሰባት የሌለ የትጥቅ ትግል ያታረፈላቸው ነገር ቢኖር፣ እንደ እኛ ካሉ ከብዙ ደጋፊዎቻቸዉ ጋር መጋጨትን ነዉ።

ግንቦት ሰባት ከኦነግ ጋር ባደረጋቸዉ የመናገገርና የመወያየት እንቅስቃሴዎች ዉጤት ሲያመጣ፣ ያደረጋቸዉ የሰላማዊ እንቅስቃሴ መሆናቸዉን አንርሳ። የግንቦት ስባት መሪዎች የሰላማዊ ትግል መሳሪያ የሆኑትን ፣ መጻፍ፣ መናገር፣ ማግባባት የመሳሰሉትን መጠቀም ይችሉበታል። ለምሳሌ ተመልከቱ «የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ከተመሰረተ በየሳምንቱ የሚያወጣቸዉ ጋዜጣዎች ወደ ቁጥር 189 ደርሷል። ( ከ189 ሳምንታት ወይንም ሶስት አመት ከሰባት ወራት በፊት የተጀመረ)

ስለ ጦርነት የማውራት፣ እንዲሁ በባዶ የመፎከር ፖለቲካ አያምርባቸዉ። አይችሉበትም። መቼም ሁላችንም የምናስታወሰው ነዉ። ሲመሰርቱ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ወያኔ ያበቃለታል ብለዉ አምስት መቶ ብሮች ከደጋፊዎቻቸዉ ሲሰበስቡ ነበር። ያ ሳይሆን ሲቀር ደጋፊዎቻቸዉ “ምንድን ነዉ እየተሰራ ያለዉ ?” ብለው መጠይቅ ሲጀምሩ ወደ አስመራ ሄዱ። ከአርበኞች ግንባር ጋር አንዳንድ ነገር ለማድረግ አስበዉ፣ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ሻእቢያ የአርበኞች ግንባር መሪዎችን ወስዶ አሰረ። በዚያም በኩል ያለዉ ነገር ከሸበፈባቸዉ። “የትጥቅ ትግል፣ ሁለ ገብ ትግል ወዘተረፈ ” የሚሉት ነገር በጭራሽ ሳያዋጣላቸዉ ቀር። አልሰራላቸዉም። በዚያ ረድፍ ያመጡትም ሆነ ያስመዘገቡት አንዲት ውጤት የለም። አንዲት ቀበሌ አልተቆጣጠሩም ፣ አንድ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣን አልገደሉም። ዜሮ !! ባዶ !!!!

ግንቦት ሰባት ያስመዘገበዉ ትልቅ ዉጤት ቢኖር የጠመንጃን ሳይሆን የማሳመንን፣ የቃላትን ኃይል በመጠቅም ያስመዘገበዉ ዉጤት ነዉ። ወደዚህ በችሎታቸው ዉጤት ሊያመጡበት ወደ ሚችሉበት ትግል ተመልሰዉ እንዲመጡ ነዉ ጥሪ የማቀርብላቸዉ። የግንቦት ሰባቱን ዶር ብርሃኑን አንፈልግም። የቅንጅቱን ዶር ብርሃኑ ይመለሱልን ነዉ የምንለዉ።

ትብብር ስለመፍጠር

ትብብርን ለመፍጠር በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ የግንቦት ሰባት መሪዎች ይናገራሉ። ይህንን ጥረታቸው ልቃወም አልችልም። በተለይም በዉጭ አገር የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ሊያሰባስበዉ በሚችል፣ በአንድ ትልቅ ኃይል ስር መሰባሰቡ ትልቅ ጥቅም ነዉ የሚኖረዉ። በአዉሮፓ ሕብረት፣ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትና ኮንግረስ ተሰሚነት እንዲኖረንና በዲፕሎማሲው አንጻር ከፍተኛ ተጽእኖ ማድረግ እንድንችል፣ አንድ ድምጽ ሊኖረን ይገባል። ለዚህም የሁላችንም መተባበር አስፈላጊ ነው። በአሁኑ ወቅት አንድ ድምጽ የለንም። በዚህም ምክንያት በተጠናጥል የምናደርጋቸዉ የተለያዩ ጥረቶች ዉጤት ሊያመጡልን አልቻሉም።

«እንዴት እንሰባሰብ ?» የሚለዉ ጥያቄ ተከትሎ የሚመጣ አንገብጋቢ ጥያቄ ነዉ። ትብብርን ለመፍጠር ከሚያስፈልጉት አበይት ነጥቦች መካከል ዋናዉ ቅንነት ነዉ። ብዙዎች በዉጭ አገር የሚደረገዉን ፖለቲካ እንደ ኑሯችን ያደረግን አለን። በመሆኑም ጥቅማችን ከተነካ፣ ምንም ለአገር ይጠቀም፣ ትብብሩ እንዳይሳካ ችግር ከመፍጠር ወደ ኋላ አንልም፡፡

ሌሎቻችን ደግሞ ዝና እንፈልጋለን። መምራት እንጂ መመራት፣ ማዘዝ እንጂ መታዘዝ አንወድም። በየመድረኩ የአንቱታ የክብር ቦታ እንፈልጋለን። እኛ ካልመራነዉ በቀር ምንም አይነት ትብብር አንደግፍም።

ነገር ግን ሁላችንም ከጥቅማችን እና ከዝናችን ይልቅ አገራችንን ካስቀደምን ፣ በቅንነት ከተነጋገረን፣ ያሉንን ልዩነቶች ማናጠብበት ምንም ምክንያት ያለ አይመስለኝም። ቅንነት ካለ እንከባበራለን። እንቻቻላለን። አንሰዳደብም።

ሁለተኛ እንድንሰባሰብ የሚያደርገን ነገር፣ ከፊታችን የተቀመጠ፣ ልንደርስበትና ተግባራዊ ልናደርገዉ የምንችለዉ የተጨበጠ አላማ ወይንም ግብ ነዉ። ትብብር ስንፈጥር ለምን እንደምንተባበር ማወቁ አስፈላጊ ነዉ። የት እንደምንሄድ ሳናወቅ ጉዞ አንጀምርምና።

አንዳንዶቻችን ወያኔን ለማስወገድ ነዉ መጓዝ ያለብን እንላለን። በአገራችን ሰዉ መግደል፣ ሰዉ ማሰር፣ ግፍ መፈጸም እኮ የተጀመረዉ በወያኔ አይደለም። ከዚያ በፊት ነዉ። ወያኔም ብትሄድ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣዉ በሌላ መልኩ ሊቀጥል ይችላል።

በመሆኑም ወያኔን ማስወገድ የሚለዉ አላማ የሚያሰባስብ አላማ አይመስለኝም። ነገር ግን፣ «አንዲት ኢትዮጵያን ማቆየት፣ በአገራችን ሰላም፣ ዲሞክራሲ የሕግ የበላይነትን ማስፈን፣ ሕዝባችንን ከድህነት ማውጣት ..» የሚሉ የተቀደሱ አላማዎች ይዘን ብንወጣ ግን ሁላችንም በቀላሉ ልንስማማ እንችላለን።

ሶስተኛ አስፈላጊ ነጥብ፣ «ወደ ዘረጋናቸዉ ግቦች ለመድረስ የትኛዉን መንገድ ነዉ መያዝ ያለብን ? » በሚለዉ ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ መድረሱ ነዉ። እንዲሁ በደፈናዉ «ይሄ ያዋጣል፣ ያ አያዋጣም» በሚል ሳይሆን በቅንነት፣ ሁሉን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በማመዛዘን ፣ ተነጋግረን ተወያይተን፣ ከስሜት፣ ከጥላቻና ከእልህ በጸዳ መልኩ፣ የሚበጀንን መንገድ በጋራ መርጠን፣ በዚያ መሰረትም በአንድነት መሰማራት እንችላለን።

ሁለት በጋራ ልናደርጋቸዉ የምንችላቸዉን ምሳሌዎች ልጥቀስ፡

• የግንቦት ሰባት ድርጅት፣ የአንድነት ድጋፍ ማህበራት፣ ሕብረት፣ ኢሕአፓዎች፣ ሶሊዳሪቲ ንቅናቄ፣ ማርች ፎር ፍሪደም፣ በቃ ፣ አድቮከሲ ኢትዮጵያ ፣ ኦነግ …የመሳሰሉ በዉጭ አገር ያሉ ድርጅቶች፣ አንድ በተቀናጀ መልኩ፣ ዉጤት የሚያመጣ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሰራ፣ በዚያ ረገድን በዉጭ የሚደረገዉን የዲፕሎማሲ ትግል የሚመራ አካል ማቋቋም ይችላሉ።

• በአገር ቤት ያሉ በከባድና ፈታኝ ሁኔታ ዉስጥ እየታገሉ ያሉትን የሲቪክ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በገንዘብና በሞራል መደገፍ እንችላለን። በየቦታዉ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዲያደርጉ፣ ጋዜጣዎችን በስፋት እንዲያሳትሙና እንዲያሰራጩ፣በየወረዳዉ ጽ/ቤቶችን እንዲከፍቱ በማድረግ አንጻር ትቅል ሚና ልንጫወት እንችላለን።

• የታሰሩ ወገኖቻችን ቤተሰቦችን መርዳት፣ ለጠበቃዎቻቸዉና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያስፈልጉትን ወጪዎች መሸፈን የመሳሰሉ ቁልፍ ተግባራትን መፈጸም የሚከብደን አይመስለኝም።

እነዚህን እንደምሳሌ የዘረዘርኳቸዉን ተግባራት ከማድረግ ዉጭ፣ ሌላ «ሊሰሩ የሚችሉና በመላ ምት ሳይሆን በተጨባጭ ዉጤት ሊያመጡ የሚችሉ ተግባራት አሉ የሚሉ ወገ»ኖች ካሉ፣ ሃሳባቸዉን ጠረቤዛ ላይ ያስቀምጡ። እንየዉ እናጥናዉ። እስከተመካከርንበትና እስከተነጋገርበትን ድረስ፣ ካመንበት፣ አብረን የማንሰለፍበት ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም።

በአራተኛነት የማስቀምተጠዉ «ለመለያየቶቻችን ምክንያት የሚሆኑትን ኮንትሮቨርሻልና ከፋፋይ የሆኑ ነገሮችን ከኛ ማራቅ» የሚለዉን ነዉ።

ኦነግ ኢትዮጵያዊነትን በመቀበሉ ከብዙ የአንድነት ኃይሎች ጋር አብሮ የመስራት በሩን በእጅጉ ከፍቶለታል። የመገንጠል ጥያቄን እያነሳ፣ ኢትዮጵያዊነትን እያረከሰ፣ ከሕውሃት/ኢሕአዴግ የባሰ እንጂ ያልተሻለ ዘረኛ ፖለቲካን እያራመደ ከኦነግ ጋር ትብብር መፍጠር የሚቸግር ነበር ።

በአሁኑ ጊዜ ከግንቦት ሰባትም ሆነ ከኦነግ ጋር አብሮ ለመስራት ትልቅ እንቅፋት ይሆናል ብዬ የማስበዉ አንድ ትልቅ ጉዳይ አለ። እርሱም ከሻእቢያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ነዉ። ጽ/ቤቶቻቸዉ አስመራ እስከሆነ ድረስ ፣ ከኢሳያስ አፈወርቂ ተጽእኖ ነጻ ናቸዉ ማለት አይቻልም። ሻእቢያ ኢትዮጵያዉያን እንድትከፋፈል ያደረገ ቡድን ነዉ። በሻእቢያ ምክንያት መከፋፈላችንን መቀጠል የለበትም። ከሻእቢያ ጋር ሆነን የትም መግፋት በጭራሽ አንችልም። የተከበሩ አባቴ አቶ ሮቤል አባቢያ በጥሩ ሁኔታ አስቀምጥዉታል።

“Ethiopians should at least strongly suspect that Isaias Afeworqui and Meles Zenawi are still buddies ”keeping their tents apart but their hearts together” as the old adage goes. These two despotic rulers must be dethroned by their respective oppressed peoples for the sake of regional stability, tranquility, democracy and prosperity.” ነበር የጻፉት አቶ ሮቤል።

በመሆኑም ከሻእቢያ ጋር የተቃቀፉ ኃይላት እጃቸዉን እንዲሰበሰቡ፣ ለኢትዮጵያዉያን መሰባሰባና አንድነት ሲሉ ከሻእቢያ እንዲለዩ የግድ ነዉ። አፍቃሪ ሻእቢያ የሆኑ ድርጅቶች አቋማቸዉን በአስቸኳይ የማያስተካክሉ ከሆነ፣ ኢትዮጵያዉያን በአንድነት ወደ አንድ የጋራ አቋም በነዚህ ድርጅቶች ላይ መድረስ ያለብን ይመስለኛል። ይህ በኢትዮጵያ ለዉጥ ላማምጣት የሚደረገዉ ትግል ጨዋታ አይደለም።

ለሁላችንም ባለንበት ቦታ ቸር ይግጠመን !