ወያኔ በሙስሊም ሃይማኖት ውስጥ እያደረገ ካለው ጣልቃ ገብነት አለመታቀቡ ምዕመናኑን ማስቆጣቱን ቀጥሎአል
ህዝብን በዘርና በሃይማኖት ከፋፍሎ መግዛት ብቸኛ የህይወት እስትንፋሱ የሆነው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ፤ ቀደም ሲል በአገራችን ሙስሉም ህብረተሰብ ዘንድ ፈጽሞ የማይታወቅ አህባሽ የተባለ የእምነት ትምህርት በሃይል ለማስፋፋት እያደረገ ያለውን ዘመቻ በተለያየ የአገራችን ክፍል የሚኖሩ ሙስሊም ወገኖቻችን እየተቃወሙት መሆኑ እየተዘገበ ነው።
በመለስ ዜናዊ የሚመራው የወያኔ አገዛዝ በሃይል ለማስፋፋት የወሰነውን ይህንን አህባሽ የተባለውን አዲሱን የሙስሊም ትምህረት በመቃወም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ 3 ቁጥር ማዞሪያ ቶታል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የአወሊያ ቁጥር 2 ት/ቤት ተማሪዎች ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ በእስላማዊ ምክር ቤት ወይም መጅሊስ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡
ተማሪዎቹ ቀኑን ሙሉ የዋለ ተቃውሞ ሊያሰሙ የቻሉበት ምክንያት፤ መጅሊሱ የአረብኛ መምህሮችን ከትምህርት ቤቱ በማባረሩና፤ በምትኩ በራሳቸው ያሰለጠኗቸውንና የአሕባህሽ ተከታይ የሆኑትን በማሰማራት ተማሪዎቹን ከእስልምና ለማስወጣት በማሰባቸው ነው ተብሎአል።
ዜናውን የዘገበው የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ተማሪዋቹ የአህባሽን አመለካከት ፈጽሞ እንደማይቀበሉት፤ የኢስልምና ጉዳይ የበላይ አካል የሆነው መጅሊስ የቅጥር ግቢውን ዘበኞች ሳይቀር ስልጠና ብሎ የት እንደወሰዳቸው እንደማይታወቅ እንደገለጹለት አስታውቆአል፡፡
የአይን እማኞች እንደሚሉት ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት ትምህር ቤት በርካታ የወያኔ ፌደራል ፖሊሶች ተገኝተው ግቢውን በማጠር አንድም ተማሪ ከግቢው እንዳይወጣ እንዳፈኑዋቸውና በአካባቢው ያለው ህብረተሰብ ተቃውሞውን እንዳይመለከት የግቢውን አጥር በጨርቅ ሳይቀር ሸፍነውት እንደነበር ይናገራሉ፡፡
የተቃውሞ ሰልፉን ለማክሸፍ በጊቢው የተገኙት የወያኔ ፈደራል ፖልሲ በርካታ ተማሪዎችን አፍሰው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከወሰዱ ቦኋላ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስፈታት በነቂስ ከመውጣት አይመለሱም የሚል ስጋት በአለቆቻቸው ላይ ስላደረ ከአሁን ቦኋላ ተመሳሳይ የሆነ ተቃውሞ እንዳይቀሰቅሱ በማስጠንቀቅ እንደፈቱዋቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል።
ኢሳት ከትናንትና ወዲያ ማክሰኞ በ3 ቁጥር ማዞሪያ ተነስቶ የነበረው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ቀደም ብሎ ሰኞ ውንጌት አካባቢ ያለው ዋናው የአወሊያ ግቢ ውስጥ ተማሪዎች አሰምተውት የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ እንደሆነ ዘግቦአል።