በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች ደንበኞቻቸው ከ200 ሺ ወይም ከ10 ሺ ዶላር በላይ ገንዘብ ሲያስገቡም ሆነ ሲያስወጡ ለብሄራዊ የጸረ ሽብር የመረጃ ማእከል ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዙ

የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በፍርሃት ለማሸምቀቅ ተብሎ በዘረኛው መለስ ዜናዊ የተቋቋመው የጸረ ሽብር የመረጃ መእከል የተባለው መሥሪያቤት ለግልና ለመንግስት ባንኮች ባወረደው መመሪያ ማንኛውም ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ አገር ዜጋ ከ200 ሺ ብር ጀምሮ በባንኮች ለማስቀመጥ ወይም ለማውጣት በሚሄድበት ጊዜ፣ ባንኮች የግለሰቦችን ስምና ማንነት ለብሄራዊ የጸረ ሽብር የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማእከል ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የጸረ ሽብር ግብረሀይሉ ከህወሃት ቁንጮዋች በተሰጠው ልዩ መመሪያ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፈው፣ በአገር ውስጥ የሚደረግን የጸረ ሽብር እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነው በሚል ምክንያት እንደሆነና መመሪያው ከጥር 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሚመሆን ሲሆን፣ መመሪያውን በማይፈጽሙ ባንኮች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሎአል።

አገዛዙ ከዚህ ቀደም ባወጣው መመሪያ ከ10 ሺ ዶላር በላይ ለማስቀመጥ ወይም ለማውጣት ወደ ባንኮች የሚሄዱ ግለሰቦችን ማንነት ራሳቸው ባንኮች እንዲያጣሩ ያደርግ ነበር።

ይሁን እንጅ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ሹሞች በአገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ አየር አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ መግባቱ ከፍተኛ ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ስለከተታቸው ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስተባበር ተቃዋሚዎች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ የሚላክላቸውን ገንዘብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ በሚል ስጋት አንድ ዜጋ በአንድ ጊዜ ወይም በተከታታይ ቀናት ወይም ወራት በድምሩ እስከ 200 ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከባንክ ካወጣ ወይም ወደ ባንክ ካስገባ፣ ባንኮች የግለሰቡን ማንነት ለጸረ ሽብር ግብረሀይሉ መላክ አለበት በሚል መመሪያ መቆጣጠር ይቻላል ብለው ይህንን ውሳኔ እንዲተላልፍ እንዳስደረጉ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የተገኘ መረጃ አመልክቶአል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የባንክ ሰራተኛ ለኢሳት እንደገለጹት ውሳኔው በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ላሉ የፖለቲካ ሀይሎች የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ ጭምር ለመከላከል ነው ተብሎአል።

ወያኔ በቅርቡ አኬልዳማ በሚል ርእስ በሰራው ድራማ ላይ በውጭ የሚገኙ ሀይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ለማስነሳት ከ500 ሺ ብር በላይ መድበዋል በማለት መግለጡ ይታወሳል።

አዲሱ የወያኔ መመሪያ ባለሥልጣናቱ የግለሰቦችን የገንዘብ ሚስጢር ለማወቅ ከፍተኛ እድል ስለሚሰጣቸው በኢትዮጵያ ባንኮች የሚጠቀሙ ዜጎች ችግር ይገጥማቸዋል ተብሎ ተፈርቷል። የጸረሽብር መርጃ ማዕከል ማን ምን ያክል ገንዘብ በየቀኑ እንደሚያንቀሳቀስ በሚደርሰው መረጃ መሰረት የመንግስት ደጋፊ ያልሆኑ ወይም በተቃዋሚነት የተፈረጁ ግለሰቦችን ገንዘብ ለመውረስም ሆነ ጥቃት ሊፈጽምባቸው እንደሚችል ስጋታቸውን የሚገልጹ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ።

በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ በተካሄዱ ህዝባዊ አመጾች ስጋት ውስጥ የገባው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ዜጎችን በማሸበርና በፍርሃት በማሸማቀቅ የሥልጣን እድሜውን የሚይራዝም መስሎት የተለያዩ የአፈና እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ይታወቃል።