በብአዴን-ኢሕአዴግ 30ኛ ዓመት ዝክረ በዐል ላይ በርችት ምክንያት በተነሳ እሳት በሰዎች ላይ የመጋጋጥ እና የመረጋገጥ አደጋ ደረሰ
(ሙሉ ገ.)
በአዲስ አበባ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ እሁድ ዕለት ሕዳር 19 ቀን 2003 ዓ.ም በተካሄደው የኢህዴን (ብአዴን- ኢሕአዴግ) 30ኛ ዓመት ዝክረ በዓል ማጠናቀቂያ ላይ የተተኮሱ ርችቶች የአዳራሹን ጣራ በእሳት በማያያዛቸው ምክንያት በተፈጠረ ድንገተኛ ድንጋጤ በርካታ ሰዎች የመረጋገጥ እና የመጋጋጥ አደጋ ደረሰባቸው።
ለበዐሉ ማድመቂያ ተብለው የተተኮሱ ርችቶች በአንድ ወገን ካለው የአዳራሹ ጣራ ጋራ ተላትመው ድንገተኛ የእሳት አደጋ በማስነሳታቸው፣ በታዳምያኑ ዘንድ በተፈጠረው ከፍተኛ ድንጋጤ እና ከአዳራሹ ለመውጣት ጥድፊያ ላይ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ብዙ ላይ የመውደቅ፣ የመረጋገጥ እና የመጋጋጥ አደጋ ደርሶባቸው በሥፍራው የነበሩ የቀይ መስቀል ሰዎች የመጀመሪያ ርዳታ አድርገውላቸዋል፤ የተፈጠረው የእሳት አደጋም በአዳራሽ ውስጥ በነበረው የእሳት ማጥፊያ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል፡፡
ይህ አደጋ ከመድረሱ በፊት “የኢህዴን- ብአዴን 30ኛ ዓመት ዝክረ በዐል የማጠናቀቂያ ዝግጅት” የተከፈተው በፕሬዝዳንት ግርማ፣ በፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን (የኢፌድሪ የትምህርት ሚኒስትር)፣ በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ሲኾን፣ በልዩ ልዩ ሙዚቃዎች (ያልተንበረከክነው፣ አንበረከክም የሚሉ) እና ፉከራ ታጅቦ ምሳ ሰዓት ድረስ ዘልቋል። ሸራተን ሆቴል ያዘጋጀውን የብፌ ግብዣ የሆቴሉ አስተናጋጆች እና ከዐሥሩም ክፍለ ከተሞች ሀምሳ፣ ሀምሳ የኢሕአዴግ ካድሬዎች በአስተናጋጅነት ተመድበው ከኻያ አምስት ሺሕ እስከ ሠላሳ ሺሕ የሚኾኑትን የብአዴን ካድሬዎች ሲያበሉ እና ሲያጠጡ ውለዋል።
ለአዲስ ነገር ሪፖርተር ያስረዱ አንድ በስፍራው የተገኙ ታዛቢ ከምግብ በኋላ መድረኩ በሙዚቃ ደምቆ ድራፍት እና ቢራዎች ለካድሬዎቹ በገፍ እንደቀረቡላቸው እና ለሹማምንቶቹ እና ቪአይፒ ለኾኑት ደግሞ የተለያዩ ዐይነት የአልኮሆል መጠጦች ቀርበውላቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በዝግጅቱ ላይ ከፕሬዝዳንት ግርማ፣ ከበርካታ የአማራ ክልል እና የፌዴራል መንግሥት ሹማምቶች ባሻገር 30 ሺሕ ያህል ካድሬዎች በተሰጣቸው ኮታ ከየክፍለከተማው እንደተሰባበሰቡ የፕሮግራም አስተባባሪ ከኾኑት መካከል አንደኛው ለአዲስ ነገር ሪፖርተር አስረድተዋል።