አቡጊዳ – ኦነግ ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ የጋበዘ ስብሰባ በሜኔሶታ ጠራ !

የኦሮሞ ነጻ አዉጭ ግንባር፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ የጋበዛ አገራዊ ስብሰባ በሜኔሶታ እንደጠራ የዘሐበሻ ጋዜጣ ድህረ ገጽ ገለፀ። «እሁድ ጃንዋሪ አንድ ቀን በኢን ሆቴል ሴንት ፖል በሚደረገዉ በዚሁ ስብሰባ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቹ ጋር በጽናትና በአንድነት የሚታገልበትን ሁኔታ ያበስራል ተብሎ ይጠበቃል» ሲል ያተተዉ ዘሃበሻ፣ በአካካቢዉ ካሉ በርካታ ስቴቶች ብዙዎች የሰብሰባዉ ተካፋይ ለመሆን እንደሚመጡም ይገልጻል።

ኦነግ ከዚህ በፊት «ኦሮሞዎች» የሚላቸዉን ብቻ ይጋብዝ እንደነበረ የገለጸው ዘሃበሻ ድህረ ገጽ፣ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ በዚህ በስብሰባዉ እንዲገኙ መጋበዛቸዉን ይጠቅሳል።

ኦነግ ቢያንስ ለሶስት እንደተከፋፈለ የሚገልጹ በስፋት መዘገቡ ይታወቃል። ነገር ግን ከኦነግ አንጃዎች መካከል፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የእኩልነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ከተፈታ፣ የኦሮሞ ጥያቄ ይፈታል የሚለዉና ከተቀሩት ኢትዮጳያዊ ወንድሞቹ ጋር በጋራ ለመስራት የሚፈልገዉ፣ የኦነግ አንጃ፣ የበለጠ ተቀባይነቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸዉ።

በጃንዋሪ አንድ የሚደረገዉን የኦነግ ስብሰባ የትኛዉ የኦነግ ቡድን እንደጠራዉ በግልጽ ዘሃበሻ ባይዘግብም በጄነራል ሃይሉ ጎንፋ የሚመራዉ፣ የቀድሞ የኦነግ መሪ የነበሩት የአቶ ዲማ ነጎ ድጋፍ ያለዉ የኦነግ ቡድን እንደሆነ ብዙዎች ግምት ይሰጣሉ።

የኦነግ ድህረ ገጽን የሚቆጣጠረዉ በዳዎድ ኢብሳ የሚመራዉ ቡድን ግን ትላንት ዲሴምበር 28 ቀን 2011፣ “The Illegal Use of the Name and Logos of the OLF Should be Stopped” በሚል ርእስ ፣ በኦነግ ስም የሚደረጉ ሕገ ወጥ የሚላቸው ተግባራት እንዲቆሙ፣ ኦሮሞዎች በዚህ እንዳይታለሉ የሚገልጽ መግለጫ አውጥቷል።

ይህ መግለጫ በጃኑዋሪ የሚደረገዉን ስብሰባ ጥላሻት ለመቀባትና እንዳይሳካ ለማድረግ ሆን ተብሎ የወጣ መግለጫ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።

ሁሉም የኦነግ አንጃዎች ጽ/ቤቶቻቸዉ አስመራ ሲሆን ፣ በሻእቢያ ላይ ያላቸዉን ሙሉ ጥገኝነት እንዲያቆሙ ፣ እንደነ ዶር ጌታቸው በጋሻዉ ባሉና ከኦነግ ጋር አብሮ መስራት ያስፈለጋል በሚሉ በርካታ ወገኖች፣ ግፊት እየተደረገባቸዉ እንደሆነም የሚታወቅ ነዉ።

የዘሃበሻን ዘገባ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !
የዳዎድ ኢብሳ ቡድን ያወጣዉን መግለጫ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !