በዳርፉር አመጽያን መሪ ግድያ ዙሪያ የወያኔ እጅ ሳይኖርበት እንደማይቀር ተዘገበ። መለስ ዜናዊ የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን የማስገደል ዕቅድ እንዳለው ተጋለጠ
የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ኢሳት በትናትና ዜናው እንደዘገበው፤ የዳርፉር አማጺ መሪ የነበሩት ዶ/ር ካሊል ኢብራሂም ግዲያ ላይ የወያኔ እጅ ያለበት መሆኑን የሚያመለክት ፍንጮች መገኘታቸውና የዘረኛው መለስ ዜናዊ አፈቀላጤ የሆነው በረከት ስሞኦን ከግዲያው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ካርቱም ውስጥ ከሱዳን ከፍተኛ የደህንነት ሰዎች ጋር ውይይት ማድረግ መታወቁ መረጃውን የበለጠ አጠናክሮታል።
እንደኢሳት መረጃ ምንጮች ዘገባ በረከት ስሞኦን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ሳይደረግ ቁጥራቸው እስከ 10 ከሚደርሱ የደህንነት አባላትና የግሉ ጥበቃ ሰዎች ጋር እንደፈረንጆች አቆጣጠር ዲሰምበር 23 ቀን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ተጎዞ ከከፍተኛ የአገሪቱ የደህንነት ሰዎች ጋር ካርቱም ላይ ምስጥራዊ የሆነ ውይይት አድርጎአል።
በረከት ስሞኦን ካርቱም ካረፈና ከአገሪቱ የደህንነት ሰዎች ጋር ውይይት ካደረገ ከሰአታት በሁዋላ የአመጽያኑ መሪ የዶ/ር ካሊል ኢብራሂም መገደል ይፋ እንደሆነ የዘገበው ኢሳት የዳርፉር አማጽያን ቃል አቀባይ የሆኑት ጂብሪል አዳም ቢላል መሪያቸው የተገደለው ከአውሮፕላን ላይ በተተኮሰ ሚሳኤል መሆኑን መግለጻቸውን ገልጾአል። የሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት አብዱል ራሂም ሙሀመድ በበኩላቸው፣ ዶ/ር ካሊል ከአየር ላይ በተተኮሰ ሚሳኤል የተገደሉ መሆኑን አምነው፣ ግድያው የተፈጸመው ግን የስልክ ጠለፋ በማካሄድ ነው ይበሉ እንጂ ግዲያውን ለመፈጸም የአካባቢና አለማቀፍ ሀይሎች እንደተባበሩዋቸው ለቢቢሲ ዜና አግልግሎት መናገራቸው የወያኔ እጅ እንዳለበት ምንጮች ለሰጡት መረጃ ማጠናከሪያ እንደሆነ ኢሳት ዘግቦአል።
የሱዳን ትሪቢውን በትናትናው ዕለት ባወጣው ዘገባ የአማጽያኑ መሪ የተገደሉት ሰው አልባ በሆነ የጦር ጀት መሆኑንና ሁለት ጎረቤት አገሮች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በርካታ የአገሪቱ ጋዜጦች እንደዘገቡ ገልጾአል። የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት ዳርፉር አካባቢ የሰፈረው የኢትዮጵያ ጦር የ ዶ/ር ካሊልን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተመለከተ የደህንነት መረጃ ለሱዳን መንግስት አሳልፎ ሰጥቷል። ይህም ወያኔ ከሱዳን መንግሥት ልኡካን ጋር በቅርቡ ባህርዳር ከተማ ላይ አድርጎት በነበረው 14ኛው የድንበር ውይይት ወቅት ሁለቱም አገሮች በድንበሮቻቸው አካባቢ የምንቀሳቀሱትን የሁለቱን አገሮች አማጽያን እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በወያኔ በኩል የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ የሚናገሩ የኢሳት ምንጮች፤ ሱዳን ሕልውናዋን የሚፈታተነውን የዳርፉር አማጽያን መሪ እንድትገድል ወያኔ ላደረገው ውለታ የሱዳን መንግስት የኤርትራውን መሪ ኢሳያስ አፈወርቅን ለማስገደል እንዲተባበር በበረከት ስሞዖን በኩል መጠየቋን ጠቁመዋል።
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ እያካሄደ ያለውን አፈናና ዘረፋ የሚያስቆም ሃይል በሱዳን መሬት በኩል እንዳይመጣበት ለመከላከል ከ1300 በላይ ርዝመት ያለው ለም የድንበር መሬታችንን በገጸ በረከትነት ለሱዳን እንዳስረከበ ሲታወቅ አሁን ደግሞ የዳርፉሩን አማጽያን መሪ በማስገደል የአልበሽሪን ወዳጅነት ለማግኘት ጎንበስ ቀና ማለቱን ቀጥሎበታል።
ተቃዋሚ ሃይሎችን ከጎረቤት አገራት ጋር በመተባበር መንቀሳቀሻና መተላለፊያ በማሳጣት አገር ውስጥ ያለውን ተቃውሞ አፍኖ የሚቀጥል እየመሰለው ያለው የወያኔ አገዛዝ ያልተረዳው ነገር ቢኖር፤ የግፍ ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ባለበት በዚህን ሰዓት ከአገረ ውስጥ ሊፈነዳ የሚችለውን እሳተ ጎሞራ ሊያስቆም ከቶ እንደማይችል የተረዳ አይመስልም የሚሉ በርካቶች ናቸው።